ተሻሽሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቀረበው የመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ አዋጅ ላይ በተደረገው ውይይት፣ በመገናኛ ብዙኃን የሚተላለፉ የቀጥታ ስርጭቶች አርትዖት ሊደረግባቸው እንደሚገባ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ገልጿል።
የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ሌሎች ሕዝባዊ ተቋማት አመራሮቻቸውን ከሕዝብ በተቀበሉት ጥቆማ መሰረት በግልጽ ሂደት እንደሚመርጡ ሁሉ፣ የመገናኛ ብዙኃን ቦርድ አባላትም በዚሁ መልክ እንዲመረጡ በዚሁ ውይይት ላይ ተጠይቋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ኅዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም. ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን፤ በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና ሌሎች የሲቪል ማሕበራት የተለያዩ ሃሳቦችን አንጸባርቀዋል፡፡
የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፤ የመገናኛ ብዙኃን የቦርድ አባላት ባለው አዋጅ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ አባል ያልሆኑ ወይም ተቀጣሪ ያልሆኑ ተብሎ የተደነገገ ቢሆንም፣ በተሻሻለው አዋጅ ይህ ድንጋጌ መሰረዙንና የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር በቦርዱ ተመልምሎ በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ይሰየማል” የሚለው ተቀይሮ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል መባሉ “ለምን አስፈለገ?” ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በተጨማሪም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ ክፍል ባለሙያዋ ወ/ሪት ሃይማኖት ደበበ፤ መገናኛ ብዙኃን ለዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና ለሰብዓዊ መብት መከበር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው መደንገጉን በማውሳት፣ ይህ የማሻሻያ ረቂቅ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ እንዳይኖረው “ምን ያህል ግምገማ ተደርጓል?” የሚል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
በቂ የውይይት ጊዜ ሊሰጠን ይገባል” ያለው የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፤ የአዋጁ ማሻሻያ በጥድፊያ የቀረበ መሆኑን በመጥቀስ፣ የሚዲያው ማሕበረሰብ አስቀድሞ በማሻሻያው ላይ መወያየት ይገባው ነበር ብሏል።
የምክር ቤቱ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ታምራት ሃይሉ፣ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የሚወስዳቸው እርምጃዎችና የሚያስተላልፋቸው ትዕዛዞች እንደመንግስት እርምጃ እንደሚቆጠሩ አብራርተው፣ “በመገናኛ ብዙኃን ቦርድ ውስጥ የሕዝብ ተሳትፎ ካለ፣ ሕዝቡ የወከላቸው የቦርድ አባላትና አመራሮች ካሉበት የሕዝቡ ውሳኔ ተደርጎ ይወሰዳል። አለበለዚያ ወደ ቀድሞው የፕሬስ ሕግ ሊወስደን ነው”ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዕለት ተዕለት ተግባራት -- ለሚዲያ ፈቃድ መስጠት፣ ማደስና ማገድ የመሳሰሉ ስራዎችን -- ከቦርዱ ወደ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መሰጠት እንዳለበት በማሻሻያ አዋጁ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤የውይይቱ ተሳታፊዎች የሚዲያ ፈቃድ መሰረዝ ለቦርዱ መሰጠት እንዳለበት ሞግተዋል።
የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ በሰጡት ምላሽ፤ በሥራ ላይ ባለው አዋጅ የዕለት ተዕለት ተግባራት ለቦርድ የተሰጡ በመሆናቸው፣ ባለሥልጣኑ መቆጣጠር የማይችል ተቋም እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡ ቅሬታ ሲቀርብ “ለበላይ አካል አሳውቄያለሁ እያልን ስንጠይቅ ቆይተናል” ሲሉም አክለዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አሿሿምን በተመለከተ ሲያብራሩ፣ በሥራ ላይ ያለው በመንግሥት አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሰየማል እንደሚል፣ አሁን በተሻሻለው ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል ሲል እንደሚገልጸው፣ መንግሥት ሲያቀርብ ምንጊዜም በዚህ ዓይነት መንገድ ስለሆነ የአገላለጽ ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ሌላ አዲስ ነገር የለውም ብለዋል፡፡
አቶ መሐመድ ቦርዱን የማመንና ባለሥልጣኑን ያለማመን አዝማሚያ መኖሩን ጠቅሰው፣ በዚህ መንገድ ባለሥልጣኑ ካልታመነ ማፍረስና ቦርዱ የመፈጸም አቅም እንዲኖረው ማድረግ ቀላሉ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን ባለሥልጣኑ “ይፈጽም” ከተባለ በተቀመጠለት ሕግና ሥርዓት እንዲፈጽም ሥልጣን “ይሰጠው” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
“በአዋጅ ያቋቋምነውን ባለሥልጣን መጠርጠር ከየት እንደመጣ አልገባኝም” ያሉት አቶ መሐመድ፤ “ሁለተኛው ጥርጣሬ፣ ፈተናና የገለልተኝነት ጉዳይ የሚነሳበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ኃላፊን መልምሎ ለፓርላማ ስላቀረበ ገለልተኛ አይሆንም ካልን፣ የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እኮ ለፓርላማው አቅርቦ የሚያሾመው መንግሥት ነው›› በማለት አስረድተዋል፡፡
“መንግሥትን እንደውጭ አካል ማየት ተገቢ አይደለም” የሚሉት አቶ መሐመድ፤ መንግሥት ሕዝብ በጋራ ወጥቶ የመረጠው አካል መሆኑ መረሳት “የለበትም” ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠው የመሰየምና የመሾም መብት እንዳለውም አክለው ተናግረዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ አነጋጋሪ የሆነው ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ የቀጥታ ስርጭትን የሚመለከት ነው። በራዲዮና በቴሌቪዥን በቀጥታ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን በጥብቅ የመቆጣጠር ግዴታ በተሻሻለው አዋጅ መሰረት በመገናኛ ብዙኃን ላይ ተጥሏል። ቁጥጥሩን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሳሪያ መጠቀም “አለባቸው” ሲል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አሳስቧል።
ይህም የመናገር ነጻነትን ሊገድብ “ይችላል” በማለት የሲቪል ማሕበራትና የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱ በጋራ በጥብቅ ነቅፈውታል።
በቅርቡ አስራ አራት በመገናኛ ብዙኃን ነጻነት እና በሰብዓዊ መብት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች፣ የማሻሻያ አዋጁ አጠቃላይ “የአካሄድ እና የይዘት ግድፈቶች” እንዳሉበት በመጠቆም፣ መግለጫ አውጥተው እንደነበር የሚታወስ ነው።