Saturday, 23 November 2024 20:24

ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ዝግጁካልሆነች ትጎዳለች ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነትን ለመተግበር ዝግጅቷን አጠናክራ ካልቀጠለች፣ ተጎጂ ከሚሆኑ አገራት አንዷ ልትሆን ትችላለች ተብሏል። የፓን አፍሪካ ንግድ ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ክቡር ገና፤ አገሪቱ ለአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ራሷን ዝግጁ ካላደረገች፣ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የመጥፋት አደጋ ሊጋረጥባቸው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።


ኢትዮጵያ የውጭ አገር የንግድ ማሕበረሰብን የሚስብ የሕዝብ ብዛት ቢኖራትም፣ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣናን ተግባራዊ ለማድረግ የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ አቶ ክቡር ገና ተናግረዋል፡፡ “አንድን ምርት ከአንድ የአፍሪካ አገር ወደ ሌላኛው ከማጓጓዝ ይልቅ ወደ ቻይና መላክ ቀላል የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል” የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ የፖለቲካ፣ የመሰረተ ልማት፣ የቢሮክራሲና የፋይናንስ ችግሮች ለንግድ የማይመቹ ስለሆኑ መስተካከል እንዳለባቸው ጠቁመዋል።


ኢትዮጵያ የነጻ ንግድ ቀጣናውን ለመተግበር ዝግጅት እያደረገች አለመሆኗን የሚገልጹት አቶ ክቡር፤ “ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር እስከዛሬ ድረስ ንግድ እካሂደናል ለማለት አይቻልም” ብለዋል። ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የሚላኩ ምርቶች ቢኖሩም፣ በመጠን ግን በጣም አነስተኛ መሆናቸውን አቶ ክቡር አልሸሸጉም።
“አምራች ድርጅቶች የምርት መጠናቸውን እንዲያሳድጉ የሚያግዝ አቅም ሊኖር ይገባል” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ኢትዮጵያ ለነጻ ንግድ ቀጣናው ስምምነት ዝግጅቷን አጠናክራ ካልቀጠለች፣ ተጎጂ ከሚሆኑ አገራት አንዷ ልትሆን እንደምትችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ስምምነት ሳቢያ አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች የመጥፋት አደጋ ሊጋረጥባቸው እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡


“የንግዱ ማሕበረሰብ እንደዚህ ዓይነት -- የነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት -- አጋጣሚ ሲፈጠር ‘እንዴት ነው የምጠቀምበት?’ ብሎ ራሱን መጠየቅ ይኖርበታል። ራሱን ማዘጋጀትም አለበት። ለመንግስት የሚያቀርባቸው ጥያቄዎችም ካሉ፣ እንዲፈጸሙለት መጠየቅ ይኖርበታል” ብለዋል። ይሁንና ጥያቄ ከማቅረብ አንጻር ከንግዱ ማሕበረሰብ ብዙም እንቅስቃሴ እንደማይታይ አመልክተዋል።
መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ በሚገኘው አጠቃላይ የኢኮኖሚ ሪፎርም መሰረት፣ “የኤክስፖርት ንግድን ማሳደግ ይገባል” ተብሎ በተደጋጋሚ እንደሚገለጽ እና የአፍሪካ አህጉር ደግሞ ለኤክስፖርት ንግድ እጅግ አመቺ መሆኑን የገለጹት አቶ ክቡር፤ በአንጻራዊነት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ስንመዘን፣ ተመሳሳይ አቅም ላይ በመሆናችን፣ ያንን አጋጣሚ በመጠቀም ኤክስፖርትን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

Read 761 times