Saturday, 23 November 2024 20:27

በሚቀጥሉት 3 ሳምንታት በኦሮሚያ የሚያከናውነውን ሥራ እንደሚያጠናቅቅ ኮሚሽኑ አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሚቀጥሉት ሦስት ሳምንታት በኦሮሚያ የሚያከናውነውን ሥራ እንደሚያጠናቅቅ አስታውቋል። ኮሚሽኑ የቀረው የሥራ ዘመን ሦስት ወር ቢሆንም የተቋሙ የቆይታ ጊዜ እንዲራዘም መጠየቅ እንደማይፈልጉ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል፡፡
የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ባለፈው ማክሰኞ ሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባቀረቡት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት፤ በአገሪቱ ካሉ 1 ሺህ 400 ወረዳዎች ውስጥ በ615 ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ወደ 360 ገደማ ወረዳዎች፣ በአማራ ወደ 264 ወረዳዎች፣ እንዲሁም በትግራይ ሙሉ በሙሉ ሥራው በቀጣይ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በኦሮሚያ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው በሦስት ሳምንት ውስጥ ይጠናቀቃል ብለው እንደሚጠብቁ የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በአማራ ክልል አስቻይ ሁኔታ እስከተፈጠረ ድረስ ሥራው ይቀጥላል ብለዋል፡፡ በክልሉ ግጭት ከመነሳቱ በፊት በርካታ መሰረታዊ ሥራዎች ተሰርተው እንደነበር በማውሳት፣ ከግጭቱ መቀስቀስ በኋላም ሥራዎችን ለመስራት ኮሚሽኑ እንዳልከበደው አስረድተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ፣ የፌደራል ተቋማት በተለይም የመንግሥት ሕግ አውጪ፣ አስፈጻሚ፣ ተርጓሚ፣ እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሃይማኖት ተቋማትና የዳያስፖራ አባላትን አጀንዳ የማሰባሰብ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
አጀንዳው ተሰብስቦ እንደተጠናቀቀ በሚከናወነው የአገራዊ ምክክር ጉባዔ የሚሳተፉ 4 ሺህ ተወካዮች እንደሚኖሩ ዋና ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ ወደ መቐለ ተጉዞ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጋር መወያየቱን ያነሱት ፕሮፌሰር መስፍን፤ ፕሬዚዳንቱ የኮሚሽኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በመርህ ደረጃ እንደሚቀበሉ መናገራቸውን አብራርተዋል። ነገር ግን ኮሚሽነሩ ለመግለጽ ባልፈለጓቸው ምክንያቶች የተነሳ ኮሚሽኑ ሙሉ በሙሉ ወደ ትግራይ ገብቶ ሥራውን እስካሁን አልጀመረም።
እስካሁን በተከናወነው የአጀንዳ ማሰብሰብ ስራ በርካታ አጀንዳዎች እየመጡላቸው መሆኑን የገለጹት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥራውን እያከናወነ ያለው ከ100 ባልበለጡ የተቋሙ ሰራተኞች መሆኑን አመልክተዋል፡፡ መንግሥት ከመደበው በጀት በተጨማሪ ከውጭ ድጋፍ አድራጊዎች 13 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ዶ/ር አበባው ደሳለው፤ “ኮሚሽኑ የታጠቁ ሃይሎችን እንዴት ለማሳተፍ አቅዷል? በሰላማዊ መንገድ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ ፓርቲዎች አመራሮቻቸውና አባሎቻቸው በመንግስት እየታሰሩ የምክክር ሒደቱ እንዴት ውጤታማ ይሆናል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
በተጨማሪም በርካታ የምክር ቤቱ አባላት፤ በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች ያሉ ሥራዎች ባልተጠናቀቁበት ሁኔታ የምክክሩ ውጤታማነት ምን ሊመስል ይችላል? ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የኮሚሽኑን ገለልተኝነት በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከታዋቂ ሰዎች፣ እንዲሁም ከሌሎች አካላት ጥያቄ የሚነሳ መሆኑን በመጥቀስ፣ የፓርላማ አባላት ኮሚሽኑን ማብራሪያ ጠይቀዋል፡፡
ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው፤ “የውክልና ጉዳይን በሕዝብ ቁጥር ‘እናምጣ’ ካልን፣ አሁንም እንደሚነሳው የአንድ አካል የበላይነት እንዲኖር ሊያደርግ የሚችል በመሆኑ፣ ይህ የምክክር ሂደት በእጅ ማውጣት የሚሰራ ሳይሆን የተመረጡ ሰዎች የሕዝቡን ጥያቄ አምጥተው በአጀንዳ መልክ የሚያቀርቡበት ሂደት ነው›› ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኮሚሽኑ የቀረው የሥራ ዘመን ሦስት ወር ቢኾንም የቆይታ ጊዜው እንዲራዘም መጠየቅ እንደማይፈልጉ አስታውቀዋል፡፡ ከታጠቁ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ምክክር መኖሩን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ወደ ኮሚሽኑ ለውይይት የመጣ የታጠቀ ሃይል አለመኖሩን ያመለከቱ ሲሆን፤ ከኮሚሽኑ ጋር አብሮ ለመስራት በተፈራረሙ ማግስት አባሎቻቸው የሚታሰሩባቸው ፓርቲዎች አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

Read 805 times