ሃይማኖታዊ መጻሕፍት የፍልስፍና ሐተታዎች አይደሉም። እንዲሆኑም አይጠበቅባቸውም። ነገር ግን ከፍልስፍና ሐሳቦች አጠገብ አይደርሱም ማለት አይደለም። እንዲያውም ዝምድና አላቸው።
በአይሁድ፣ በክርስትናና በእስልምና ሃይማኖቶች ዘንድ የሚታመንባቸው የኦሪት ትረካዎች በርካታ ቢሆኑም፣ በፍልስፍናዊ ገጽታው ግን “መጽሐፈ መክብብ” ተወዳዳሪ የለውም። እንዲያውም ከሃይማኖታዊነቱ ይልቅ ፍልስፍናው ይጎላል ተብሎ ይነገርለታል።
ጽሑፉ ሲጀምር እንዲህ በማለት መክብብን ያስተዋውቃል።
“የመክብብ ቃል፣ የዳዊት ልጅ፣ በኢየሩሳሌም
የነገሠ”…
ሌላ መሸጋገሪያ ድልድይ ጣልቃ ሳያስገባ፣ በቀጥታ ወደ ዋናው ፍሬ ነገር ዘው ብሎ ይገባል።
“የከንቱ ከንቱ” አለ መክብብ፣… “የከንቱ
ከንቱ። ሁሉም ከንቱ ነው”።
“ከፀሓይ በታች፣ ሰው በሚደክምበት ድካም
ትርፉ ምንድነው?”
መጽሐፈ መክብብ፣ ትኩረትን ከሚስቡ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች መካከል አንዱ ነው። በይዘቱ ብቻ ሳይሆን በጥበባዊ አገላለጹና አቀራረቡ ይለያል።
ነገር ግን፣ አድማጮቹን ለመሳብ ነገር በማዋዛት አይጀምርም። ታሪካዊ አመጣጥ በመተረክ ወይም ገጠመኙን በመጥቀስ አይነሣም።
አንባቢዎቹ በድንጋጤ እንዳይደነብሩ ሳያስጠነቅቅና ሳያረጋጋ፣ “መርዶውን” ይነግራቸዋል። ወይም ደግሞ… “እውነታውን ይገልጥላቸዋል” ብንል ይሻላል።
“ድንገተኛ መዓት ወረደባችሁ፣ አደጋና ጉዳት ደረሰባችሁ” የሚል መርዶ ይዞ አልመጣም። የዓለም ነገር እንዲህ ነው፤ የሕይወት ነገር ይሄው ነው… በሚል መልእክት ያዘለ ነው - ንግግሩ። “ሁሉም ከንቱ ነው” የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰው በምን መመዘኛ እንደሆነም ወዲያውኑ ገልጾልናል።
በዚህች ዓለም፣ የሰው ልጆች የኑሮ ውጣውረድ ትርፉ ምንድነው? ትርፍ ከሌለው፣ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው ይላል መመዘኛው። ትርፍ የለውም ሊል ነው? አዎ በተደጋጋሚ ይላል። ነገር ግን “የጥበብን ትርፍ አውቃለሁ” በማለትም ይናገራል። የሥነምግባር መርሖች ጠቃሚ እንደሆኑም ይገልጻል። ትርፍ ቢኖራቸው ነው። እንዲያውም ጥቅማቸውን ይዘረዝራል።
ቢሆንም ግን፣ የዚህ ዓለም ነገር ከንቱ ነው ይላል። የሰዎች የሕይወት ውጣውረድም “ነፋስን እንደመከተል ነው” ሲልም ይናገራል። ምክንያቱን ለማስረዳት በርካታ ነጥቦችን ይዘረዝራል። ከዚያ በፊት ግን፣ የምልአተ ዓለም ተፈጥሮ ምን እንደሚመስል በቅድሚያ ለማሳየት ይሞክራል። ምዕራፍ 1፡ 4-8 እንዲህ ይላል።
ትውልድ ይሄዳል። ትውልድ ይመጣል።
ምድር ግን ዘላለም ጸንታ አለች።
ፀሓይ ትወጣለች። ፀሓይ ትገባለች። ወደ
ስፍራዋም አቅንታ እዚያ ትወጣለች።
ነፋስ ወደ ደቡብ ሄዶ፣ ወደ ሰሜን ዞሮ፣
እየሾረ እየተሸከረከረ፣ ነፋስ በዙረቱ እንደገና
ይመለሳል።
ጅረቶች ሁሉ ወደ ባሕር ይሄዳሉ። ባሕሩም
አልሞላም። ሁሉም ጅረቶች ወደሚሄዱበት
ስፍራ ወደዚያው መላልሰው ይሄዳሉ።
ይሄ ሁሉ ነገር ያታክታል። ሰው ተናግሮ
አይችለውም። ዓይን በማየት አይጠግብም።
ጆሮም በመስማት አይሞላም።
የተፈጥሮ ተመላላሽ ዑደቶችን በዐጭር ድግግሞሽ ከነገረን በኋላ፣ “ቃላት ያጥሩኛል” የሚል የመታከት መንፈስን ያስጎበኘናል። የዓለም ዑደት እንደወትሮው ተመላላሽ ድግግሞሽ ቢሆንም፣ ሰው ግን እንደ አዲስ ያያል፤ ይሰማል። የዓለም ዑደት ድሮም ነበረ፤ ወደፊትም ዑደቱ ይኖራል። ብዙ ሰው ግን ታሪክን ይረሳል። መታሰቢያ የለውም። እንጂማ፣ የሰው ድርጊትም “የድግግሞሽ ዑደት” ነው የሚል ሐሳብ ይናገራል መክብብ።
የሆነው ይሆናል። የተደረገው ይደረጋል።
ከፀሓይ በታች በሙሉ አዲስ ነገር የለም።
“እነሆ ይሄው አዲስ ነገር” የሚባልለት ነገር፣
እሱ ዘላለም ከኛ በፊት የነበረ ነው።
ለፊተኞች መታሰቢያ የለም። ለኋለኞችም
በኋለኞች ዘንድ መታሰቢያ አይኖራቸውም።
በምዕራፍ 1 ገና ከመነሻው እስካሁን ድረስ የተገለጸው የመክብብ ንግግር፣ “ዱብዳ ነው” ብንል አልተሳሳትንም። “ከዓቅመ ቢስ መከረኛ ሰው የሚመጣ ከልክ ያለፈ የብሶተኛ እሮሮ” ይመስላል። ወይም ደግሞ “የሰውን ሐሳብና ተግባር በደፈናው የማጣጣል አዝማሚያ” ሊሆንብን ይችላል። ነገር ግን፣ የሰውን ዕውቀትና ጥበብ ያደንቃል እንጂ አያጥላላም። ትክክለኛ ሐሳብንና የሙያ ተግባርን ያከብራል እንጂ አያጣጥልም። ዓቅመ ቢስ ብሶተኛም አይደለም። በጥበብ የከበረ በኑሮም የበለጸገ ትልቅ ሰው ነው። ራሱ ይመሰክራል።
እኔ መክብብ፣ በኢየሩሳሌም የእስራኤል
ንጉሥ ነበርኩ።
ከሰማያት በታች የተደረገውን ሁሉ በጥበብ
እመረምርና እደርስበት ዘንድም ልቤን
ሰጠሁ። ይህም የሰው ልጆች ይሸከሙት
ዘንድ እግዚሄር የሰጣቸው ክፉ ውጣውረድ
ነው።
ከፀሓይ በታች የተሰራውን ሁሉ አየሁ።
እነሆም ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስን እንደመከተል
ነው።
የጠመመው ሊቃና አይችልም። የቀረውም
ሊቆጠር አይቻለውም።
እኔም ለልቤ ነገርኩት፡ እነሆ እኔ በኢየሩሳሌም
ከኔ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይልቅ ጥበብን
አብልጬ ጨመርኩ። ልቤም ብዙ ጥበብና
ዕውቀትን አየ።
ጥበብን ለማወቅ፣ አለሌነትንም ዋዘኛነትንም
ለማወቅ ልቤን ሰጠሁ። ይህም ነፋስን
እንደመከተል መሆኑን ዐወቅሁ።
በብዙ ጥበብ ብዙ ትካዜ አለ። ዕውቀትን
የጨመረ ሕመምን ይጨምራል (መክ ምዕ 1፡
12-18)።
ጥበበኛ በእርግጥም ብዙ ፈተና ይገጥመዋል። መልካም ዕድሎች ሲባክኑ፣ የወደፊት አደጋዎች ሲቃረቡ አብዛኛው ሰው ላያውቅ ይችላል። ጥበበኛው ግን ያውቃል። ያዝናል። ይጨነቃል። ሕመም ይሰማዋል። ይሄ አይገርምም።
ነገር ግን፣ ከጥበብ ይልቅ አላዋቂነት ይሻላል? አለማወቅ ግልግል ነው ያስብላል? ከቀሽም ይልቅ ጥበበኛ እንደሚበልጥ ቅንጣት አይጠራጠርም። ታዲያ ቅሬታው ምን ላይ ነው? የነፋስ እረኛ እንደመሆን ነው የሚለውስ ለምንድነው? የዓለም ኑሮና የሰዎች ሕይወት ከንቱ መስሎ የታየው ለምንድነው? በርካታ ችግሮችን ይዘረዝራል - መክብብ።
ከዋናው ችግር በፊት፣ ሌሎቹን እናስቀድም።
የልፋት ብዛት፣ አግኝቶ ማጣት፣ ለማይረባ ሰው ማውረስ
የመክብብ ሐሳቦችና ድምዳሜዎች፣ በራዕይ የተገለጡ ወይም ከአምላክ የተነገሩ አይደሉም። አየሁ፤ አስተዋልሁ፤ አሰብኩ… በማለት ነው ማስረጃ የሚያቀርብልን።
እናም፣ የሰዎችን ጥረትና ግረት፣ የኑሯቸውን ወጣውረድ ተመለከተ። የሚያገኙትን ውጤትና ፍሬ አየ። የልፋታቸው ያህል አይደለም ብሎ አሰበ። የድካማቸው ያህል አያከርማቸውም። የአፍታ ሽውታ ያህል ነው ብሎ ደመደመ መክብብ። ይህም ብቻ አይደለም ችግሩ።
“አግኝቶ ማጣት” የሚሉት መከራ እንዳለ ይገልጻል መክብብ። ወደ ላቀ ከፍታ ለመጓዝ ወደ ሸለቆ መውረድ ይኖራል። ወደተሻለ ኑሮ ለመሸጋገር የፈለገ ሰው ሀብቱን በሙሉ ስራ ለማዋል ይገደዳል። ግን ሁሌ ይሳካል እንዴ? እዚያው ሸለቆ ውስጥ ተደናቅፎ መውደቅ አለ። በኪሳራ ባዶ ኪስ መቅረት ይኖራል።
ታዲያ እንዲህ ዓይነት ውድቀትና ኪሳራ፣ ለሙያተኛና ለትጉህ ሰው ተገቢ ነው? ድካማቸውን ማን ይቆጥርላቸዋል? ማንም አይቆጥርላቸውም። እናም፣ ሁሉም ከንቱ ነውይላል መክብብ።
በዚያ ላይ፣ ሰዎች ሌት ተቀን ዕድሜ ልካቸውን ቢጥሩና ቢሳካላቸው እንኳ፣ የሥራ ፍሬያቸውን ላያጣጥሙ ይችላሉ። ሕመም ያጋጥማል። አደጋ ይደርሳል። ብዙ ጣጣ አለው። እናም፣ ድካማቸው ከንቱ ነው ይላል - መክብብ።
ይባስ ብሎም፣ የጥበበኛና የትጉህ ሰው የሥራ ፍሬ፣ ሌላ አላዋቂና ሰነፍ ሰው ምንም ሳይደክምበት ሊወርሰውና ሊፈነጭበት ይችላል። ይህም ክፉ ከንቱነት ነው።
ምልአተ ዓለሙ ሁሉ፣ ምድርና ፀሓይ፣ ነፍስና ጅረት፣…. ለሰው ህይወት ደንታ የላቸውም፡፡ በክፉም አያዩትም።
ሰው በጥበብ ቢራቀቅ ወይም በጭፍንነት ቢራቆት፣ ትጉህ ሙያተኛ ቢሆን ወይም በስንፍና ቢንዘላዘል፣ በልኩ ቢዝናና ወይም “አለሌ ዘለሌ” ቢሆን… ሰማይ ምድሩ ደንታ የላቸውም፡፡ ለአንደኛው የወጣች ፀሐይ ለሌላኛው ብርሃን አትነፍግም፡፡
ጥበበኛ ስራውን እስኪጨርስ ድረስ እንዳይልምበት ብላ ጀምበር ከመጥለቅ አታመነታም፡፡ ግዑዝ ነገሮች የተፈጥሮ ዑደታቸው ይቀጥላሉ፣ በምህዋራቸው ይጓዛሉ፡፡ ሰው ቢኖር ባይኖር ደንታ የላቸውም።
ይሄ እውነት፡፡ መክብብ አልተሳሳተም፡፡
ነገር ግን ምድርና ፀሓይ፣ የሰውን ድካም ባይቆጥሩትም፣ በጎ ባያስቡለትም፣ በክፉ አያዩትም፡፡
በጥላቻ አይጠምዱትም፡፡
እንሸውደው፣ ጠልፈን እንጣለው፤ ዓይኑን እናጥፋው፣ እግሩን እንስበረው ብለው በተንኮል አያሤሩበትም፡፡ ይሄ ጥሩ አይደለም? የተፈጥሮ ባህርያቸውን ለተገነዘበና ለሰራባቸው ሰው፣ ፍሬና ውጤቱን አይነፍጉትም፡፡
ይሄ ጥሩ ነው፡፡ “የተፈጥሮ ፍትህ” ልንለው እንችላለን በምሳሌያዊ ዘይቤ፡፡
ቢሆንም ግን መክብብ ያነሳውን ቁም ነገር መረሳት የለበትም፡፡ ያለ ዕውቀት፣ ያለ መላ እንዲሁ ሲደክምና ሲለፋ የዋለ ሰው፣ “ድካሜን ይቆጥሩልኛል” ብሎ አንዳች ውጤት ቢጠብቅ፤ ጠብ የሚል ነገር አያገኝም፡፡
እንኳንና ስንፍ ተጨምሮበት ይቅርና፣ ጎበዝ ባለሙያም ቀኑን ሙሉ ሰርቶም ችግር ይገጥመዋል። የሰራው ምርጥ ጥበብ፣ ባለቀ ሰዓት በቅንጣት ስህተት ከእጅ አምልጦ እንክትክቱ ሊወጣ ይችላል፡፡ አለታማው ወለል፣ የሰውየውን ድካም አይቶ፣ እንደ እንቁ የከበረውን የእጅ ጥበብ እንዳይሰበርበት አስቦ… “ፍራሽ ልሁንልህ” አይለውም፡፡ ይህን እውነት መገንዘብና በጸጋ መቀበል የግድ ነው፡፡
መክብብ ግን ሌላ ቅሬታ አለው፡፡ የራሱን ሕይወት በምሳሌነት በማቅረብም ምሬቱን ይገልጻል።
በጥበብና በእውቀት ለማደግ በብዙ ጥረት ተሳክቶለታል፡፡ ቤት ንብረት አፍርቷል፡፡ የነገሥታትና የገዢዎች እጅት የከበሩ እቃዎችን አከማችቷል፡፡ መኖሪያ ግቢውን አሳምሮ አስውቧል፡፡ ገነት ፈጥሯል፡፡ ይህን በዝርዝር ይገልፅልናል (መክ ምዕ 2፤ 3-14)፡፡
በእርግጥ የጥበብ ትርፍ እንደምታስገኝለት በእውን እንዳየ ይነግረናል። ብርሃን ከጨለማ እንደሚበልጥ ጥበብም ከዋዘኝነት ይበልጣል ብሎ ይመሰክርልናል፡፡
ቢሆንም ግን የጥበበኛውና የዋዘኛው መጨረሻ አንድ ዐይነት እንደሆነም ተመለከትኩ በማለት ይገልጽልናል፡፡ እንደዋዘኛው፣ ጥበበኛውም ይሞታል፡፡ ታዲያ ለምን እጅግ ጥበበኛ ሆንሁ? ይሄም ከንቱ ነው በማለት ያማርራል፡፡
ጥበበኛውም ሞኙም፣ የተጋም የተኛም፣ የለፋም የተንከረፈፈም… በዕድሜ ብዙ አይለያዩም። ፀሓይ የምትወጣው ለሁሉም ነው። የምትጠልቀውም ለሁሉም ነው። መወለድና መሞት ለሁሉም ነው። ታዲያ የድካሙ ትርፍ ምንድነው? ለዕውቀት፣ ለጥበብ፣ ለሙያና ለሥራ መትጋቱ ምን እላፊ ያስገኝለታል? እንደ ትንፋሽ ጤዛ፣ ሁሉም ነገር ከንቱ ሆኖ ይታየዋል - ለመክብብ። ነፋስን ለመንዳት እንደመሞከር፣ ከንቱ ልፋት ይሆንበታል።
ዐውቆና መርጦ፣ ተግቶና ጸንቶ ሕይወትን ማሳመር ካልተቻለ፣ ሌላ ምን አማራጭ አለ? የቻለውን ያህል ይችላላ። የማይችለውን ደግሞ በጸጋ መቀበል?
“ለሁሉም ጊዜ አለው” በማለት ይናገራል።
ሌላኛው ትልቁ ችግር ምንድነው? “ለሁሉም ጊዜ አለው”
ይሄ አባባል፣ ከመነሻ ወደ መድረሻ፣ ከምኞት ወደ ስኬት በአንድ ጊዜ አይደረስም የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ልንጠቀምበት እንችላለን። “ለሁሉም ነገር ትክክለኛ ጊዜ አለው” የሚል ሐሳብ የያዘም ይመስላል። መክብብ ይህን አይክድም። ነገር ግን… ችግር አለው።
ብዙ ሰዎች የየራሳቸውን ኀላፊነት ቢያሟሉ፣ በዕውቀትና በጠበብ፣ በሙያና በትጋት ቢሠሩ እንኳ፣… ነገ በአገር ምድሩ ምን እንደሚፈጠር ማን ያውቃል? ሁሉም ነገር በራሱ ጊዜ ይመጣል። ጊዜን ደግሞ “ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም” ይባላል። የነገን የሚያውቅ ሰው ከሌለም፣ ነገሩ ሁሉ የዕድል ጉዳይ ይሆናል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ስለ ነገ ብዙ አያውቁም። ነገር ግን…
ብዙ ሰዎች ስለ ነገ ብዙ ስለሚያውቁም ነው የሚሠሩት። የተፈጥሮ ዑደትን ጠብቀው ያርሳሉ፤ ይዘራሉ። የማዕድናትን ባሕርይ በማስተዋል በድንጋይና በብረት ይገነባሉ።
የሌሎች ሰዎችን ዝንባሌና ፍላጎት በማገናዘብም ነው የሚሰሩት። የነገ ገበያ አስበው ያመርታሉ። የተፈጥሮ አደጋና የወንጀለኛ ጥቃት እንደሚኖር አውቀውም፣ ለቤት ንብረታቸው፣ ለሕይወት ለጤናቸው ይጠነቀቃሉ።
ጫማ ያደርጋሉ፤ ምግብ ያበስላሉ።
ዐጥር ይሰራሉ፤ ውል ይፈራረማሉ።
ሸምጋይ ይመርጣሉ። ዳኛ ፊት ይቀርባሉ።
ፖሊስና ወታደር ይቀጥራሉ።
ይሄ ቀላል ነገር አይደለም። የሕይወት ምስጢር ነው። ዕውቀትም ጥበብም ነው። ነገን በማሰብ መሥራትና መኖር ይቻላል። “የነገን ማን ያውቃል?” ብሎ ነገር ምንድነው! ሰዎች ያውቃሉ።
እንዲያም ሆኖ፣ ሰዎች የቱንም ያህል በጥበብ ቢመጥቁ፣ ሁሉንም ነገር ያውቃሉ ማለት አይደለም። አገር ምድሩ ሰፊ ነው። የሰዎች ቁጥር ብቻ ሳይሆን፣ የሰዎች ባሕርይና ዝንባሌ ብዙ ነው። ምልአተ ዓለሙን ሁሉ አጠቃልለው ማወቅ፣ የሕዝበ አዳምን ሐሳብና ስሜት፣ ምኞትና ተግባር አብጠርጥረው መተንተን የሚችሉ ተአምረኛ ጥበበኞች የሉም። ቢኖሩስ ምን ማድረግ ይችላሉ?
የሚሊዮን ሰዎችን ኑሮ የሚመራ፣ የአገር ውሎና አዳርን የሚቆጣጠር “እረኛ” ለመሆን የሚችል ሰው የለም። ቢችል እንኳ፣ ሰዎችን የሚነዳ እረኛ መሆን ተገቢ አይደለም። የሰዎች እረኛ ለመሆን ማሰብና መመኘትም የለበትም። እና ታዲያ ምን ተሻለው? የነገን እንዴት ማወቅና ማስተካከል ይችላል?
በእርግጥ፣ የነገን ካላወቀ በሕይወት የመቆየት ተስፋ የለውም። የእውኑን ዓለምና የራሱን ተፈጥሮ እየተገነዘበ፣ የተፈጥሮ ክስተቶችንና የታሪክ ጅረትን መዘወር አለበት። ሌላ ዘዴ የለውም።
ቢሆንም ግን፣ ሁሉንም ነገር እንዳሻው ባሰኘው ጊዜና አቅጣጫ መዘወር አይችልም። የዓለም ይቅርና አገራዊ የታሪክ ጅረትን ከጫፍ እስከ ጫፍ እንዳሻው ግራና ቀኝ ማሽከርከር የሚችል ሰው የለም። ዛሬ ስላሰኘው ወደ ከፍታ፣ ነገ ስለፈቀደ ወደ ዝቅታ መዘወር አይችልም።
ገሚሶቹ ሰዎች የታሪክን ጅረት ጥዋት ማታ መቀየር ቢችሉ እንኳ፣ ገሚሶቹ ሰዎች የታሪክን ጅረት መለወጥ አይችሉም ማለት ነው።
የጎረቤታሞች የሰላምና የጦርነት ጊዜ
የጎረቤት አገር መንግሥታት ሲታረቁ፣ በተከፈተው የታሪክ ጅረት ውስጥ ገብቶ ይጎርፋል። አዳሜ ለሰላም ይዘምራል።
ዕቃዎችን ተሸክሞ፣ ሸቀጥ አስጭኖ፣ ለንግድ ድንበር ተሻግሮ ይገሰግሳል፤ ይገበያያል።
መንግሥታት ወይም መሪዎች ሲጣሉ፣ የጎረቤት አገር ሰዎች በተቆፈረላቸው የታሪክ ቦይ ውስጥ ገብተው ይጎርፋሉ። ለጦርነት ይዘምታሉ። ጠመንጃ ተሸክመው፣ መድፍ አስጭነው፣ ለወረራ ድንበር ጥሰው ይገዳደላሉ።
የሰላምና የጦርነት አመጣጥ ለብዙ ሰዎች የምርጫ ጉዳይ አይደለም ለማለት ነው። በቃ፣ ይመጣላቸዋል። ወይም ይመጣባቸዋል።
ሰዎች፣ ዐውቀውና መርጠው አይወለዱም። በሰላም ጊዜና በአዝመራ ወቅት የሚወለድ አለ፤ በጦርነት ጊዜና በድርቅ ዘመን የሚወለድ አለ።
በድሀ አገር ወይም በሀብታም አገር መወለድም የምርጫ ጉዳይ አይደለም።
እምቢ፣ “ዘንድሮ አልወለድም፤ እዚህ ሳይሆን እዚያ ከተማ ይሻለኛል” ማለት አይቻልም። ለክፉም ለደጉም፣ የሆነው ነገር ሆኗል። የቀድሞ ታሪክን ወደ ኋላ ተመልሰን መቀየር አንችልም። በጥቅሉ፣ ከምርጫችን ውጭ የሆኑ ነገሮች አሉ።
“ነባራዊ ሁኔታ” ብለው የሚፈላሰፉበት አሉ።
“የዕድል ነገር” ብለው የሚተክዙበት አሉ።
በጸጋ ለመቀበል ያህል፣ “የአምላክ ፈቃድ ነው” ብለው የሚስቡትም አሉ። “እንዳንተ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን” ይባል ይለ!
መክብብ ይህንንም እንዳሰበበት ይገልጻል። ዐውቆና መርጦ ያላመጣቸው ነገሮች፣ ዐውቆና ፈቅዶ የማይፈጥራቸው ነገሮች እንዳሉ ይዘረዝራል።
ለሁሉም ነገር ዘመን አለው። ከሰማይ በታችም ላለው ነገር ሁሉ ጊዜ አለው… ይላል መክብብ።
ለመወለድ ጊዜ አለው። ለሞትም ጊዜ
አለው። ለመትከል ጊዜ አለው፤ ለምንቀልም
ጊዜ አለው… (የተተከለውን)።
ለመግደል ጊዜ አለው። ለማዳንም ጊዜ
አለው። ለማፍረስ ጊዜ አለው። ለመገንባትም
ጊዜ አለው።
ለሐዘን ጊዜ አለው። ለሳቅም ጊዜ አለው።
ለማልቀስም ጊዜ አለው። ለዘፈንም ጊዜ
አለው።
ድንጋይ ለመወርወርም ጊዜ አለው። ድንጋይ
ለመሰብሰብም ጊዜ አለው። ለመተቃቀፍ ጊዜ
አለው። ከመተቃቀፍ ለመለያየትም ጊዜ
አለው።
ለመፈለግም ጊዜ አለው፤ ለማጥፋትም ጊዜ
አለው። ለመያዝም ጊዜ አለው። ለመልቀቅም
ጊዜ አለው።
ለመቅደድም ለመስፋትም፣ ዝም ለማለትም
ለመናገርም ጊዜ አለው።
ለፍቅርም ለጥላቻም፣ ለጦርነትም ለሰላምም
ጊዜ አለው።
ለሠራተኛ ሰው የድካሙ ትርፍ ምንድነው?
ብዙ ነገር የሚከሰተውና የሚከናወነው ከሱ ፈቃድና ምርጫ ውጭ ከሆነ፣ ከውጣውረድ ጋር እየታገለ ሲተጋ የነበረው ሰው፣ ምን እላፊ ያገኛል? ለንጋትም ጊዜ አለው፤ ለምሽትም ጊዜ አለው… ያው ፀሓይ የምትወጣውና የምትጠልቀው፣ ለሁሉም ነው። በምርጫ አይደለም።
በሌሎች ሰዎች ምርጫ የሚፈጠር ጸብና ጦርነት ሲመጣ ደግሞ አስቡት። ጸበኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ሰፈርተኞችም ናቸው ሰለባ የሚሆኑት። በእርግጥ ክስና ዳኝነት፣ ፍርድና ቅጣት ይኖራል። ነፍስ ያጠፋ ወንጀለኛ የሞት ቅጣት ቢፈረድበት፣ “የእጁን አገኘ” ያስብላል። ትክክል ነው። ነገር ግን፣ የጠፋው ሕይወት አይመለስም።
በቃ፣ በጎ ዘመን ይመጣላቸዋል። ወይም ክፉ ዘመን ይመጣባቸዋል።
ለሁሉም ጊዜ አለውና ነው።
ሁሉም ነገር በጊዜው በበጎ ተሰራ? የማፍረስ ጊዜ ሲመጣስ?
“ለሁሉም ጊዜ አለው” በተሰኘው አባባል፣ እንዲህ ዐይነት ጣጣ ያመጣል ለካ። እንዲህ ዐይነት ቅሬታ ያመጣል ብሎ ማን አሰበ?
የፀሓይ ብርሃን ወደ ምድር ለመድረስ 8 ደቂቃ ይፈጅበታል ይላሉ፡፡ የተዘራው እስኪበቅል፣ ጥሬው እስኪበስል፣ ህፃናት ለዓቅመ አዳም እስኪደርሱ፣ ከዩኒቨርስቲ እስኪመረቁ….
ሁሉም ነገር ትክክለኛ ጊዜ አለው።
ሁሉም ነገር የሆነ ያህል ጊዜ ይፈጃ፡፡
አለ-ጊዜው አይሆንም፡፡
አሁን ይሄ ምን እንከን ይወጣለታል?
መክብብ ይህን አይክድም፡፡
“እግዚሄር…. ሁሉን ነገር በጊዜው በጎ አድርጎ ሰራው” ይባል የለ? ወይም ደግሞ “ዓለማት ከዑደታቸው አይዛነፉም”፣ “ነገሮች ተፈጥሯቸውን አይስቱም” ተብሎም ሊገለጽ ይችላል፡፡
መክብብ ይሄን ይቀበላል፡፡ እንዲያውም፣ ምልአተ ዓለም፣ “የሚጨመርበትም የሚቀነስበትም የለውም” ይላል፡፡ ነገር ግን፣ “አገር ሰላም ነው” ብለው የሚንቀሳቀሱ ሰዎች፣ ያጠራቀሟትን ሀብት ተጠቅመው ቤት የሚገነቡ ነዋሪዎች፣…
እጃቸው ሳይኖርበት የጦርነት ጊዜ ቢመጣባቸውስ?
የግንባታ ጊዜ ሳይሆን የማፍረስ ጊዜ ቢታወጅባቸውስ?
ለማን አቤት ይላሉ? “ይሄም ከንቱ፣ ነፋስ እንደመከተል ነው” ብሎ ቢያማርር ይፈረድበታል? “ለሁሉም ጊዜ አለው” ሲባል፣ እንዲህ አይነት ትርጉምም አለው።
Saturday, 23 November 2024 20:36
Published in
ነፃ አስተያየት