Saturday, 23 November 2024 20:30

ይህ አምድ “የነቢይ መኮንን አምድ” ተብሎ ተሰይሟል

Written by  ሙሉጌታ ቢያዝን
Rate this item
(0 votes)

ባለሚዛኗ እማማ

እዚያ ማዶ መናፈሻው ውስጥ ጨበሬ ወጣቶች ‘ዛፍ ካልኾንን’ ብለው የሚጀነኑ ቁጥቋጦዎችን ጠጉር ያበጥራሉ፡፡ አጥሩ ላይ “ፈገግ በይ እንጂ.. አዎ እንደ…ሱ” እየተባባሉ ፎቶ የሚነሡ ወጣት ሴቶች ይታያሉ፡፡ እዚህ ማዶ የትኛው ባለሥልጣን እንደሚመጣ አልታወቀም፣ዝግትግት ያለ መንገድ አለ፡፡ የታጠቁ ወታደሮች ‘ውር ውር’ ይላሉ፡፡ ትራፊክ ፖሊሶች እጃቸውን ጭራሮ አስመስለው ይሄን ባለመኪና “ቁም!” እያሉ ያስቆሙታል፡፡ ልብ ብሎ ላስተዋላቸው “የት አባክ ልትደርስ?” የሚሉ ይመስላሉ፡፡ “አንተ? አንተን እኮ ነው… ዳር ይዘህ ቁም! አትሰማም?”

ተለዋጭ መንገድ የተከለከሉት ባለመኪኖች ተናድደው እጃቸውን ያወናጭፋሉ፡፡ ንዴታቸውን ላስተዋለ “እንዴት በድሃ ታስበልጡናላችሁ? የሚሉ ነበር የሚመስሉት፡፡
ድሃው ምንም እንዳልተፈጠረ በእግሩ ይፈጨዋል፡፡ ድሃ ከሃብታም ከፍ ብሎ የሚታይበት ሁለት ቀን አለ፡፡ አውቶብስ ሲሳፈርና ልክ እንደዛሬው መንገድ ሲዘጋ፡፡
የምሳ ዕቃውን በጀርባው አዝሎ የሚንከላወስ የቀን ሠራተኛ፣ የልጆቹን እጆች ግጥም አድርጎ ይዞ ተማሪ ቤት ለማድረስ የሚጣደፍ አባት፣ልጇን አዝላ “የዛሬውስ ጫን ያለ ነው” ብላ የምታሽሟጥጥ እናት፣ “ብሮ (bro) ትናንት በ’ቲክ ቶክ’ የለጠፍኩትን ዐየኸው?” የሚባባሉ በዩኒፎርም የቀለሙ ወጣቶች የእግረኛ መንገዱን ሞልተውታል፡፡ በእግረኛው መንገድ ቀኝ እንደነገሩ ዳስ ጥለው “ለውዝ አለ፣ ወተት በጽዋ አለ፣ እርጎ አለ፣ እርጥብ አለ” በሚል በአምስት የተለያየ ማስታወቂያ ተከብበው “ቡና ጠጡ እንጂ” ሲሉ በዐይናቸው የሚማፀጸኑ ሴቶች ተኮልኩለዋል፡፡ አንድ በዚያ የሚያልፍ መንገደኛ “ለዚህ ሁሉ ማስታወቂያ የሚያስፈልገው ብቸኛ ነገር አንድ ወረቀትና ነጠላ ሰረዝ መኾኑ እንዴት አልታያቸውም?” ቢል ልክ ነው፡፡ እልፍ ስንል ደግሞ ጡረታ በወጣው የአንድ ብር ሳንቲም እየቆረቆሩ የልመና ይኹን የጥያቄ ባልለየ ድምፅ “ጋሸ ተመዘን፣ወንድም ተመዘን” የሚሉ ሕፃናት ይታያሉ፡፡ ሎሚ፣ ዘይቱን፣ ፓፓያ፣እንቁላል ወዘተ የሚሸጡ ሴቶችም በዚያ ተሰልፈው ተቀምጠዋል፡፡ ሁሉም የያዘውን ሸጦ የሚጮኸውን ሆዱን ዝም ለማሰኘት ይጮሃል፡፡
ከዚያ ሁሉ ሰው መሃል ግን ነጠል ብለው የተቀመጡ አንድ ጠና ያሉ ሴት ይታያሉ፡፡ እሳቸውን መዝዞ ለማየት የገጣሚ ዐይን ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ የጎዳናው ላይ ለፍቶ አዳሪዎች ‘ማዘር’ የሚሏቸው እኚህ ሴት ሥዕል መስለው ሚዛናቸውን ከፊታቸው አስቀምጠዋል፡፡ “ተመዘኑ” አይሉም፡፡ አንገታቸውን ደፍተው ቁጭ ብለዋል፡፡ አልፎ አልፎ በጥቂቱ ቀና ይሉና የአልፎ ሒያጁን እግር ይታዘባሉ፡፡
እኚህን ሴት አንድ ወጣት ከተመለከታቸው ቆይቷል፡፡ ለመጀመሪያ ቀን የት እንደሚያውቃቸው ተደናግሮት ነበር፡፡ አዎ እኚህን ሴት ያውቃቸዋል፡፡ ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት ዶርማቸውን ተከራይቶ ተምሯል፡፡ ገደኛ ዶርም መኾን አለባት፤በዚያች አንድ ጠባብ ክፍል ቤት አጥንቶ ኮሌጅ በጥሶባታል፡፡
እንደሚያውቃቸው ግን አልነገራቸውም፡፡ ለምን?
“አዲስ አበባ ወድቄ ብነሣ፣
የሠራ አከላቴ ወርቅ ይዞ ተነሣ፡፡”
የሚለው ዜማ በዚህ ስፍራ ስላልደበዘዘ? አጓጉል ቢጓጉስ? የኑሮ ቀዳዳቸውን በትልቁ እንድደፍንላቸው በሰፊው ቢመኙስ ብሎ? በጭራሽ አይደለም፡፡ ምክንያቱ ቢጠይቅም ስለማይመልሱለት፣ ቢነግራቸውም ስለማይረዱት ነበር፡፡ አይናገሩም ከተናገሩ ግን ከአፋቸው የማይጠፋው ቃል “ወግዱልኝ! ማንንም አልፈልግም” የሚል ብቻ ነበር፡፡ እና ትኩስ በድቁስ ያበሉኝ ነበር፣ የሚጮኸውን ሆዴን በዝምታ አስታግሰዋል፣ ለኪራይ የምከፍለው አጥቼ ዐራት ወራት ታግሰውኛል፣ ደሞ አንድዜ ስታገኝ ታመጣለህ ብለው ለት/ቤት ከፍለውልኛል፣ ወላጅ አምጣ ተብዬ እርስዎን ይዤ ሔጄ ነበር ትዝ ይልዎታል? እ… ደግሞ ጓደኞቼ በሙሉ ብር አዋጥተው ሲዝናኑ አንተስ ለምን ትቀራለህ? ብለው ከመቀነትዎ ፈትተው…” ወዘተ ብሎ ንግግር ውለታን ይመልሳል?
ንግግር የሚያምረው ቃላት ስላሳመርን ነው? ንግግር የሚያምረው በየማሰሪያ አንቀጹ ‘ያለበት ሁኔታ ነው ያለው’ ብሎ በመደንጎር ነው? ንግግር የሚያምረው አለባበስ ስላሳመርን ወይም How to make an effective presentation የሚል ቪዲዮ አውርደን ስለተለማመድን አይመስለኝም፡፡ ንግግር የሚያምረው እንግሊዝኛ ቀልቀል በማድረግም አይደለም፤ መልካችን፣ ድምፃችን ስላማረም አይመስለኝም፡፡ ተናጋሪ ቢስት ጥሩ ጆሮ ካለ አሳክቶ ይሰማዋልና ንግግር የሚያምረው ሰሚ ሲኖር ነው፡፡ ሰሚ ብቻ ሳይኾን ጥሩ አድማጭ ሲኖር ነው፡፡
ውለታ ራሱ ምንድር ነው? ውለታ የሚመለሰው እንዴት ነው? በራዲዮ ዘፈን ምርጫ ፕሮግራምን ጠብቆ ‘ባለውለታየ’ የሚለውን የተፈራ ነጋሽን ዜማ በመጋበዝ? መጽሐፍ ካሳተሙ መታሰቢያነቱ ለ…ብሎ ቁራጭ ዓረፍተ ነገር በመጻፍ? ወይስ ሰው የሚኾን ሰው የጠፋ ዕለት ሰው ኾኖ መገኘት?
ይኹንና እንዴት ከዚያ የሀብት ማማ ተሽንቀንጠረው እዚህ የድህነት ጋጣ እንደተገኙ አለመጠየቅ ግን ኅሊናው ‘እምቢ’ አለው፡፡ በምን ተአምር ከሞቀ ቤት ወጥተው ጎዳና ላይ ተሰጡ?
በፎቅ ጫካ ካልተወረሩ ባንድ የጥንት ግሮሰሪ ቁጭ ብሎ ፉት እያለ ከወሬ ወሬ ተነሥቶ ይሄን ነገሩት፡፡
ወንድ ልጃቸው ትዳር ይይዛል፡፡ እናት በዚህ እጅግ ደስ ተሰኙ፡፡ አንድ ልጃቸው ነውና ደስታቸው ልክ አልነበረውም፡፡ እጅግ የወደዳት በኋላም ያገባት ይች ሴት ግን በማናውቀው ምክንያት መኖሪያ ቤቱን በስሟ አድርጋ ከባንክ ትበደራለች፤ ያ ብድር በወቅቱ ባለመመለሱ ቤቱን በሐራጅ ትሸጥና እምጥ ይኹን ስምጥ መግባቷ አልታወቅ አለ፡፡ እሷን ዐየናት የሚል ሰው ጠፋ፡፡
ባሏን ለእብደት ዳርጋ የውኃ ሽታ ኾነች፡፡ ጨርቁን ጥሎ የወደዳት ሴት ጨርቁን ጥሎ ብቻውን እንዲያወራ ምክንያት ኾነች፡፡ እናት በዚህ ዕድሜያቸው ቤታቸው ቁጭ ብለው በረከቦት ፈንታ ጎዳና ላይ ሚዛን ታቅፈው የሚውሉ ኾኑ፡፡ ለስንቱ ቤት እንዳላከራዩ ዛሬ ተከራይተው የሚኖሩ ኾኑ፡፡ ያውም ለውሻ ቤትነት ለማትመጥን ክፍል በቀን 10 ብር እየከፈሉ፡፡
ከፈላስፎች አነጋገር አንዱ እንዲህ ያለ ነው፡፡
ብረት ጽኑነቱ እሳት እስኪነካው ድረስ ነው፤ እሳትም ብርቱነቱ ውኃ እስኪያገኘው ነው፡፡ ውኃም ብርቱ ቢኾን ደመና ይሸከመዋል፤የደመና ኃያልነቱ ነፋስ እስኪበትነው ድረስ ነው፡፡ የነፋስ ጉልበቱ በመሬት ይገደባል፤ የመሬት ጽናት በአዳም ልጅ ይሸነፋል፡፡ የአዳም ልጅ ብርቱ መኾን ኃዘን እስኪያገኘው ድረስ ነው፤ኃዘን ምን ጽኑ ቢኾን ለወይን ጠጅ እጅ ይሰጣል፡፡ ወይን ጠጅም ጉልበቱ እስከ ዕንቅልፍ ነው፤ እንቅልፍም በሞት ይሸነፋል፡፡ ሁሉንም ግን ሴት ታሸንፋቸዋለች!!
“ልጃቸው እንዴት በሴት ተታለለ?” ብሎ የሚወቅስ ካለ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውር፡፡ እሱን ለመውቀስ “እንዴት ሰለሞን ጠቢብ ሳለ በሴት ተታለለ? እንደ ዳዊት ያለስ እውነተኛ እንዴት በሴት ተፈተነ? እንዴት እንደ ሳምሶን ያለ ጠንካራ ሰው በሴት ወደቀ? እንዴትስ እንደ አውኖን ያለ መልከ መልካም ሰው በሴት ተሸወደ? የመጀመሪያው ሰው፣ በሰው ማኅፀን ያላለፈው ብቸኛው ፍጡር አዳም ከእግዚአብሔር ይልቅ እንደምን ሔዋንን አመነ?” የሚለውን መመለስ አለብን፡፡
የመታለል ውርስ!
“እማማን ሊረዳቸው የፈለጉ ሰዎች ነበሩ” አሉ፡፡ ይህ ግን በሽታቸውን ይቀሰቅስባቸዋል፡፡ “ ‘ጎዳና ላይ ብታየኝ ለማኝ መሰልኩህ? ወግዱልኝ! ማንንም አልፈልግም’ ብለው ያስደነግጧቸዋል” አሉ፡፡
ዓለም እንዲህ ናት፡፡ “ወለፈንዲ” አለ አልበርት ካሙ፡፡ እውነት ብሏል፡፡
“ዓለም ሦስት ወገን ናት፡፡ ቀን ላንተ፣ቀን ባንተ፣ ቀን ለሌላ፡፡”
በወር 300 ብር በከፈሉት የኪራይ ቤት እንደሚኖሩ ያወቀው ይህ ወጣት አንድ ውሳኔ ላይ ደረሰ፡፡ በየቀኑ መመዘን! ‘ወግ ይድረሰኝ’ ብሎ ሕይወታቸውን በሰፊው ለመለወጥ አልዳዳም፤ አልተግደረደረም፡፡ ዐቅሙ የሚችለው ይህን ማድረግ ብቻ ነበርና፡፡
“እንደምን ዋሉ እማማ?”
“ዛሬ ደግሞ ስንት ኾኜ ይኾን?” ሚዛን ላይ ይወጣል፡፡
“ትናንት ተመዝነህ አልነበር? በአንድ ቀን ምን ለውጥ ይመጣል ብለህ?” እያወቁት መጥተዋል ማለት ነው፡፡
እንደ ሥራ ቢያዩት ይሄን ማለት ይገባቸው ነበር? ዓለምን ካስማ ኾነው ያቆሟት እንዲህ ያሉት ይመስለኛል፡፡ እራስ ወዳድነት ባፈነው አየር ውስጥ በተገኘችው ቀዳዳ ሾልከው ለሌላው በሚያስቡ! ያ ቢል ቡላርድ ምን አለ? “Empathy is the highest form of intelligence” ድንቅ! ድንቅ!
ዐሥር ብር አውጥቶ ሰጣቸው፡፡ መልስ ሊሰጡት ሲሉ “ግዴለም ይቀመጥ” ብሎ ሔደ፡፡
መሸ ነጋም ሌላ ቀን፡-
“እንደምን አመሹ እማማ?”
“አዬዬ ትናንት ተመዝነህ አልነበር? ምን ለውጥ ይመጣል ብለህ?”
“ግዴለም የዛሬ ጊዜ እህል …መች ሰውነት ይጠጋል ? ሐኪም ቢያዘኝ እንጂ ወድጄ ብለው?”
“በየቀኑ እንድትመዘን?”
“አዎ እማማ”
“ወይ ጉድ!”
ንግግራቸው ለስድስት ወራት ያህል ይሄ ነበር፡፡
ከዕለታት ባንዱ ቀን እንዲህ ኾነ ፡-
“ደኅና አደሩ እማማ?”
ዝም፡፡
“እማማ ለመኾኑ ቂም መቋጠር ክብደት ይጨምር ይኾን? የቂም ስፍራ ሆድም ይኹን ጭንቅላት መቼም ከትናንት ዛሬ ክብደቴ መጨመር አለበት፡፡”
ቀና ብለው ዐዩትና ለመጀመሪያ ጊዜ ፈገግ አሉ፡፡
“ቀልደኛ ነህና!”
“የምሬን እኮ ነው፡፡ የሥጋ ሚዛን እንዳለ የኅሊናም ሚዛን በየጎዳናው በኖረ፡፡ ዛሬ ስንት ሰው በደልኩ? ስንትስ ሰው አሳዘንኩ? ስንት ሰው በስውር ገደልኩ? ስንት ሰውስ አዳንኩ? ለስንት ሰው ደረስኩ? ስንት ሰው ቀማሁ? ስንት ሰው አስለቀስኩ? የስንት ሰው እምባስ አበስኩ?” የሚለውን የሚመዝን መሳሪያ በኖረ!
ይሄን ብሎ ዐሥር ብር አውጥቶ ሲሰጣቸው ፊታቸውን አዞሩ፡፡ “እማማ ደኅናም አይደሉ?” ብሎ ቁጢጥ አለ፡፡ እምባቸው እንዳይታይ እየታገሉ ነበር፡፡ ከነተበ ሻሻቸው ያመለጠውን ሽበት የወረረውን ጠጉራቸውን ዐየ፡፡ “ወግዱልኝ! ማንንም አልፈለግም” የሚለው ዛቻቸው ትዝ አላለውም፡፡ ተጠጋቸው፡፡ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ እንደተጋባ በግራ እጁ የሚርገፈገፍ ትክሻቸውን ይዞ እምባቸውን ለማበስ ቀኝ እጁን ወደ ዐይናቸው ሰደደ፡፡ ትክ ብሎ ዐያቸው፡፡ እምባ በሚረጨው ዐይናቸው ቃላት የማይገልጠው ጥልቅ ሐዘን አድፍጦ ነበር፡፡ “ደግሞ ነጭ ነገር አጥልቶበታል ወይስ ዐይኔ ነው?” አለ፡፡ እነዚህ ዐይኖች ስንት ደስታ፣ ስንት ሐዘን ዐይተው ይኾን? ስንት ነውር፣ ስንት ቅድስና ተመልክተው ይኾን? ስንት ክፋት፣ ስንት ደግነትስ ታዝበው ይኾን? ስንት ጫማ፣ ስንት እግርስ ቆጥረው ይኾን?
እምባውን እየጨቆነ “እማ…ማ ደኅናም አይደሉ?”
“የለም ወዲህ ነው ልጄ”
“እማማ ሳላውቅ አስቀየምኩዎ?”
“እረ ምን በወጣህ ልጄ!”
ከረዥም ጸጥታ በኋላ፡-
“እማማ የሚለኝ አንድ ልጄ ነበር፡፡ እሱ ትዝ ቢለኝ ነው…”
ይሄን በተነጋገሩ ማግስት እማማ በስፍራቸው አልነበሩም፡፡ በሌላ ቀንም ሔደ፡፡ የሉም፡፡ መሸ ነጋም ሁለተኛ ቀን፡፡ እሳቸው በዚያ የሉም፡፡ “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ?” የሚለው ጥቅስ ሽው አለው፡፡ “ስፍራ ቀይረው ይኾን?” በሚል ለዐራት ቀናት ዝም ካለ በኋላ ግን አላስቻለውም፡፡ ወዲያ ወዲህ እያለ በዓይኑ አሸተታቸው፡፡ ከዚህ ቀደም ስለሳቸው ወደነገሩት ሴቶች አቅጣጫ አጨንቁሮ ተመለከተ፡፡ እነሱም የሉም፡፡ ወዴት ገቡ? ምን ጅብ በላቸው? ተመካክረው ወዴትና ማን ላይ ዘመቱ? ድህነት ላይ?
ያለው አማራጭ ከማዶ ያሉትን ጫማ አሳማሪዎች መጠየቅ ነው፡፡ ፈራ ተባ እያለ ቀረባቸው፡፡
“እህህ…” ሲል ጉሮሮውን ካፀዳ በኋላ ሰላምታ አቀረበ፡፡ ለሰላምታው መልስ ከመስጠት ከእግር እስከ እራሱ አስተዋሉት፡፡ “አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁ ነበር?”
“ ጠይቃ! ምን ይንተባተባል?” በሚል አስተያየት በዐይናቸው ላጡት፡፡
“እዛ ጋ ያሉት ሚዛን የሚይዙት ሴትዮ የ..ት ሔዱ? ሰሞኑን አላያቸውምሳ፡፡”
አንደኛው ጫማ ከሚያሳምርበት እግር ቀና ብሎ ለአፍታ ዐየውና “ምናቸው ነህ?” ሲል በግዴለሽነት ጠየቀው፡፡ ወዲያው ግን ምላሽ ሳይጠብቅ ሌላ ጥያቄ አስከተለ፡፡ “ አልሰማህም?”
“ምኑን?
“አርፈዋል”
“ም…ን?
“መቼ ነው አንተ ‘ማዘር’ የሞቱት?” ሲል ከጎን ያለውን ጠየቀ፡፡
“ከትናንት ወዲያ መሰለኝ፡፡”
ጎኑን የተማታ ያህል አቃሰተ፡፡ ነፍሳቸውን የነጠቀ ያህል ነፍሱ ተጨነቀች፡፡ ጸጸት ልቡን አነከተው፡፡ እራሱን እንዲህ ጠየቀ፤ “የኔ ኮሌጅ መበጠስ አንጀታቸውን ለመበጠስ ኖሯል? እሳቸውን ለማሳከም ስለምን አልቻልኩም? የድህነት ክፋቱ እጅን አጣጥፎ ወዳጅ ሲሞት ማየቱ! የሚሹትን ለማድረግ ካለመቻል በላይ ምን የሳር ኑሮ አለ? እናስ በአሳር የተማርኩት እንዲህ የሳር ኑሮ ለመኖር ኖሯል? የሕይወት ግቤ ሕይወት ከመቀጠል ሕይወት ወደ መንጠቅ ከመቼው ተመነደገ?! በዚያ ያሉት ለፍቶ አዳሪዎች ‘ማዘር’ ብሎ ከመጥራት ባለፈ ስለ ማንነታቸው የሚያውቁት ነገር ነበር? ታሪክ እንዳላቸው አያውቁም፡፡ ቢያውቁስ ምን ሊፈይዱ ይችላሉ? ከተማ ሲስፋፋ ዝግባዎችን እንዲህ ይገነድሳል፡፡ እንደ አሮጌ ቁና ከመወርወር ባለፈ ያለመታወቃቸው ሕመም ምን ያህል ጥልቅ ነው? የሰፈሩ አድባር እንዳልነበሩ እንደ ባይተዋር ኖረው ዐለፉ፡፡ እማማ ከነታሪካቸው ዐለፉ፡፡ እነዚያ ለፍቶ አዳሪዎች በዚያ ስፍራ እስካሉ ድረስ “ማዘር የሚባሉ እዛ ሚዛን ይዘው ይቀመጡ ነበር” ይሉናል፡፡ ግን ትውስታም መደብዘዙ አይቀርምና ከዕለታት ባንዱ ቀን ቃላቸውን አጥፈው ‘እኔ እንጃ’ ቢሉ ይሰቀሉ አንልም፡፡ እንረሳቸዋለን፡፡ እማማ በነበሩበት ስፍራ ሌላ ተረኛ ይተካል፡፡ ሌላ ባለሚዛን እማማ!
እንዲህ ነን እኛ! Life goes on.
…ለማጣትም ለማግኘትም፣ለመሥራትም ለማረፍም፣ ለማዘንም ለመደሰትም፣ለመታከምም ለማሳከምም፣ ለማበድም ለማሳበድም፣ ለመመዝንም ለማስመዘንም፣ለመሳቅም ለማልቀስም፣ ለመናገርም ለማድመጥም፣ ለማፍቀርም ለመጥላትም፣ ለመከራየትም ለማከራየትም፣ በ’አሳር ዋ’ ብሎ ለመማርም፣ የሳር ኑሮ ለመኖርም ለመሞትም … ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡
አና ፍራንክ “Dead people receive more flowers than the living ones because regret is stronger than gratitude” ብላለች፡፡ ንግግሯ ከጨበጠ ለዚህ ሁሉ የዳረገቻት ያቺ ሴት ጸጸት አኝኳት መቃብሯ ላይ ተገኝታ ጥቂት ዘለላ እምባ ባታዋጣ አበባ ታኖር ይኾናል፡፡ በዚያን ጊዜ የባለ ሚዛኗ እማማ ምላሽ ይህ መኾኑ አይቀርም፡- “ወግዱልኝ! ማንንም አልፈልግም!”

 

Read 310 times