Saturday, 23 November 2024 20:46

የከተማችንን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የመንግስት ቁርጠኝነት

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   በአንድ ሀገር ላይ የሚከሰት የገበያ አለመረጋጋት እና የዋጋ ንረት በዜጎች ላይ የኑሮ መወደድ እና የገበያ መናር በማስከተል የመሸመት አቅምን ይፈታተናል፡፡ እንደ ሀገር የተከሰተው የኑሮ ውድነትን አለማቀፋዊ የሆኑ መነሻ ጉዳዮችን ተንተርሶ በተፈጠረ የውጪ ምንዛሬ መጨመር በአንድ በኩል የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም በሌላ መልኩ እየፈተነ ስለመሆኑ ይነገራል። በአሰራርና ቁጥጥር ሊመለሱ የሚገባቸው ተግባራት በአግባቡ ባለመሰራታቸው ምክንያት የኑሮ ውድነቱ የተፈጠረ ስለመሆኑም ይገለጻል፡፡
ይሄን ችግር ከመፍታት አኳያም በመንግስት በኩል ገበያ ማረጋጋት፣ ገቢ መሰብሰብ፣ ህገ-ወጥ ንግድ ቁጥጥር እና የኢትዮጵያ-አዲስ አበባ ታምርት ንቅናቄ በመፍጠር በከፍተኛ የከተማው አመራሮች በጥበብ እንዲመራ በማድረግ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወኑ፤ የማሻሻያ እርምጃዎችም ሲወሰዱ ቆይተዋል፡፡ ለዚህም፣ በምርትና አገልግሎቶች ላይ የዋጋ ድጎማ የማድረግ፤ የቀረጥ ነጻ አገልግሎት መፍቀድ እና አቅርቦትን ማሳደግ የመሳሰሉ ርምጃዎች ተወስደዋል፡፡


ከተማችን አዲስ አበባ በሃገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ከሚካሄድባቸው ከተሞች በዋነናነት የምትጠቀስ ስትሆን የምርት ዕጥረት በመፍጠርና ፣ ዋጋ በማናር ፣ ህብረተሰቡን ለምሬት የሚዳርግ ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በንግድ ስርዓቱ ውስጥ አርቴፊሻልና ሰው ሰራሽ የሆኑ ሆን ተብል ምርትን ያለአግባብ በማከማቸት ዕጥረት መፍጠር፤ ከደረሰኝ ውጭ ግብይት ማካሄድ፤ የድጎማ ምርቶችን ስኳር፣ ዘይት፣ ነዳጅ በህገወጥ መንገድ መሸጥ፤ በመኪና ሊይ ሽያጭ ማካሄድ በእህል ምርት፣ ሲሚንቶ ምርት፣ አትክሌትና ፍራፍሬ ምርት ወዘተ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ፤ የአስገዳጅ ጥራቱ የወጣላቸው ምርት ገበያ ዋጋ፤ የሚዛን ጉድለት በመኖሩ ታይቷል፡፡
ሌላው የመሰረታዊ ፍጆታ ምርቶችን አቅርቦት ከመጨመር አኳያ፣ የግብርናውን ምርትና ማርታማነት ማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ በዚህም የግብርና ምርቶችን በስፋት ማቅረብ እና ቢያንስ የምርት እጥረት እንዳይኖር ማድረግ ተችሏል፡፡
በጅምር ላይ ያለውን የዋጋ መረጋጋት ውጤት ማስቀጠል የሚያስችል ተጨማሪ አቅም ተደርጎ የሚወሰደው ደግሞ፣ የገበያ ሰንሰለትን መቀነስና የደላሎችን ጣልቃ ገብነት መግታት የሚያስችሉ ርምጃዎችም መወሰዳቸው ሌላው የችግሩ መቃለል ምክንያት ናቸው፡፡
በከተማችን አዲስ አበባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየናረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የከተማው አስተዳደር የተለያዩ የኑሮ ውድነት ማቅለያ አማራጮች እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ ከነዚህ አማራጮች መካከል አንዱ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል የሚሰጠው አገልግሎት አንዱ ሲሆን ለከተማው ነዋሪ የፍጆታ ምርት አቅርቦት በሚፈለገው መጠን ማግኘት እንዲችልና በተሻለ ዋጋ እንዲሸምት እየተደረገ ይገኛል፡፡
እንደ ከተማ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ የኑሮ ውድነትን ለማቅለልና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል በ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ ተግባራት እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን በተለይም ከመስከረም 2017ዓ.ም ጀምሮ በከተማች ከደረሰኝ ግብይት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም የዋጋ ማረጋጋትን የሚፈጥሩ 164 መሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ዩኒዬን እንደ ከተማ፤ በ800 የመቸርቸሪያ ሱቆች የሸማቹን አቅም ባመጣጠነ ዋጋ የገበያ ማረጋጋት ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኙ ሲሆን 19 ፋብሪካዎች ፣ 63 የክልል አርሶ አደሮች ፣ 282 ኢንተር ፕራይዞች እንዲሁም በ3 ግብርና ምርት ማዕከላት 195 ቸርቻሪና አከፋፋዮች የኑሮ ውድነትን በማቃለል ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ፡፡
የምርት አቅርቦትን በማሳደግ የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትን ለማቃለል በመንግስት በኩል ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሰብል ምርት በገበያ ማዕከላት 108,481ኩንታል፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት 486,765፤ በገበያ ማዕከላት የገበያ ትስስር መፍጠር የተቻለ ሲሆን በእንስሳት ግብይት ዘርፍ 120,879 የዳልጋ ከብት አቅርቦት ትስስር መፍጠር ተችሏል፡፡ 635,722 በግና ፍየሎችን በገበያ ማዕከላት ማቅረብም ተችሏል፡፡
ሌላው የነዋሪውን አቅም ባገናዘበ መልኩ መንግስት በተለያዩ ቦታዎች የእሁድ ገበያዎችን ተደራሽነትን በማስፋትና ጥራትን በማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን የእሁድ ገበያ መዳረሻዎች ላይ 969 የሰንበትና የእሁድ ገበያዎችን ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡
በተጨማሪም 106,261 ኩንታ በእሁድ ገበያ የሰብል ምርት ትስስር የተፈጠረ ሲሆን በአትክልትና ፍራፍሬ ምርትም እንደዚሁ 488,255 ትስስር መፍጠር ተችሏል፡
መንግስት ለህረተሰቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ ድጎማ በማድረግ የኑሮ ውድነቱን የማቃለል ተግባራትን በፍትሃዊነት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም 90,663 ኩንታል ስኳር የምግብ ዘይት 1,009,404 በሌትር በድጎማ በትስስሩ መሰረት ማሰራጨት ተችሏል፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም እንዲሁ በተለየ ሁኔታ 98,869,238 የሸገር ዳቦ ማሰራጨት የኑሮ ጫናን ማቃለል ተችሏል፡፡
ህጋዊ የንግድ ስርአት ተዘርግቶ በሚገኝባት ከተማችን ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት 1200 የክትትልና ቁጥጥር ባለሞያዎችን በማሰማራት አመራሩን በመጨመር ህገ-ወጥ ንግድን የመከታተልና የመቆጣጠር ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በ147‚334 የንግድ ድርጅቶች የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የንግድ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል ተችሏል፡
በተጨማሪም የከተማችን አስተዳደር ዜጎች የተሻለ ተጠቃሚ ይሆኑ ዘንድ በተለያዩ መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮቹም በተመለከተ በከተማው ሁሉም አከባቢዎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ እና ሌሎች የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ ሃላፊዎች በከተማው የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ከመከላከል እና አጠቃላይ የንግድ ህገ ስርአት ላይ ከነጋዴው ህብረተሰቡ ጋር ውይይት እየተደረገ ሲሆን የንግዱ ማህበረሰብ እና ያለ ህጋዊ ግብይት የሚገነባ ከተማም ሆነ ሃገር የሌለ በመሆኑ የነጋዴውን ህይወት ለማሻሻል እና የታክስ አሰባሰቡን ዘመናዊ እንዲሆን ሁሉም ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገባ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል ነጋዴዎች የሚያነሳው ህጋዊ ጥያቄ መስማትና ማዳመጥ የከተማዋን እድገት ማፋጠን በመሆኑ መንግስት ጥያቄዎችን ለማዳመጥ ዝግጁ ሲሆን ፍትሃዊ የንግድ ስርአት ለመፍጠር እየተሰራ ነው ፡፡ ነጋዴዎችንም ወደ ህጋዊ መረቡ መግባት እንዳለባቸው ተግባብተን ወደ ተግባር ስንገባ ያልተገቡ ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው ተገቢ እንዳልሆነም በውይይቶቹ የጋራ ተደርገዋል፡
የገቢ ዘርፍ ተቋማት ዘመኑን የሚመጥን የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በመከተል የግብር ስወራና ማጭበርበርን የመግታት ኃላፊነት የሁሉም ዜጋ በመሆኑ የገቢ መጠንን ለማሳደግ ከተለምዷዊ አሰራር የተላቀቀና በቴክኖሎጂ የሚመራ ዘመኑን የሚመጥን የገቢ አሰባሰብ ስርአት መከተል አስፈላጊ ነው።
በመሆኑም መንግስት የገቢ አሰባሰብ ሰርአትን ለማዘመንና ተገቢውን የገቢ አሰባሰብ ስርአት ለማስጠበቅ የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ገቢ እያደገ መጥቷለ። የሚሰበሰበው ገቢ እያደገ ቢመጣም ከከተማችን የመልማት አቅም እና ከሀገራዊ ምርት አንጻር ያለው ድርሻ ሲታይ ውስን መሆኑ ታምኖበት በቴክኖሎጂ የታገዘ የታክስ አሰባሰብን በማጠናከርና የታክስ አስተዳደርን በማጠናከር እንዲሁም የታክስ መሰረትን የማብዛትና የማስፋት ስራ ተከናወኗል፡፡
ግብር በአግባቡ ካልተሰበሰበ በተገቢው መንገድ ለህብረተሰቡ የመልማት ጥያቄ ምላሽ መስጠት አይቻልም የታክስ አሰባሰብና አስተዳደር ስርዓትን በማዘመን ያሉትን ፀጋዎች በመለየት ገቢ የመሰብሰብ አቅምን ማሳደግ ይገባል፡፡
ግብር የሚሰበሰበው ከማሕበረሰቡ ስለሆነ የሻጭም ሆነ የሸማቹ ደረሰኝ የመስጠትና የመጠየቅ ባህሉ ደካማ መሆን እና ነጋዴው ደግሞ የራሱ ጥቅም ከማግኘት አኳያ ደረሰኝ የመስጠት ችግሮች የሚስተዋል ችግር ነው፡፡ ችግሮቹን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው ደረሰኝ በትክክል ባልተቆረጠበት ቦታ ፍትሐዊ የግብር አከፋፈል አይኖርም፡፡ ፍትሐዊነት ግብር ከፋዩ መክፈል ያለበትን እንዲከፍል የሚያስችል ሲሆን ሁለተኛው ለመንግሥት መግባት ያለበትን ታክስና ግብር በአግባቡ ገቢ አለመደረጉ ፍትሐዊነትን ከሚያጎድል ጉዳይ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡
ያለደረስኝ በሚደረግ ግብይት ከሸማቹ አንጻር ቢታይ የሚጠቀመው ነገር የለም፤ ሸማቹ በደረሰኝም ሆነ ያለደረሰኝ ቢገዛ መክፈል ያለበትን ሒሳብ ይከፍላል፡፡ ነጋዴው የሚቀበለው ቫትንም ጨምሮ ሲሆን በሀገር ልማት ላይ የሚፈጠረው ጫና ደግሞ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ደረሰኝ በመስጠትና በመቀበል መካከል የሚኖር ክፍተት ሻጭም ገዢም ሊጠቀሙባቸው የሚገባቸውን የመሰረተ ልማት ጥያቄዎች በፍጥነት ለመመለስ እንዳይቻል አዳጋች ይሆናል፡፡ ስለዚህ የማሕበረሰቡ ንቃተ ህሊና እየጨመረና ግንዛቤ እያደገ ሲሄድ ደረሰኝ የመስጠትና የመጠየቅ ባህል እያደገ ይሄዳል፡፡ የሚሰበሰበውም ግብር ከፍ እንደሚል አጠያያቂ አይደለም፡፡
በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ በከተማችን ዘመናዊ፣ ፍትሃዊና ተደራሽ የገቢ አሰባሰብ ስርዓት በመዘርጋትና ከተማዋ የምታመነጨውን ገቢ በላቀ ደረጃ በማሰባሰብ የከተማዋን የወጪ ፍላጎት ለማሟላት በደረሰኝ ግብይትና በብልሹ አሰራሮችና በሌብነት ድርጊቶች ላይ የተጀመሩ ተግባራት እንዲሳኩና የህብረተቡ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ ጥረት እያደረገ ነው፡፡
በአጠቃላይ የከተማ አስተዳደሩ በቀጣይ የነዋሪውን ሸክም የሚያቃልሉና ጫና የሚቀንሱ ተግባራትን አጠናክሮ የሚያስቀጥል ሲሆን ምርት ደብቀው የምርት እጥረት እንዲፈጠር የሚያደርጉ የገበያ ተዋናዮችም እድል እንዳያገኙ እና ተፅእኖ እንዳይፈጥሩ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን በመሆን ህገ-ወጦችን በማጋለጥ በመሰረታዊ የድጎማ ምርቶች ላይ የሚፈጠሩ አሻጥሮችን በመከታተልና በማጋለጥ ያለ አግባብ እያሻቀበ የመጣውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የከተማ አስተዳደሩ፣ ነጋዴው፣ አቅራቢውና ነዋሪው በጋራ ተቀራርበው ሊሰሩ ይገባል፡፡

Read 277 times