Saturday, 23 November 2024 20:48

ማህበራዊ ሚዲያ - ለበጎም ለክፉም

Written by  ሙሉእመቤት ጌታቸው
Rate this item
(1 Vote)

      ሶፊያ የኮሌጅ ትምህርቷን አጠናቅቃ በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ በአነስተኛ ደሞዝ ተቀጥራ ትሠራለች፡፡ ከተወለደችበት አካባቢ እርቃ ስለምትኖር ቤተሰቦቿንና አብሮ አደግ ጓደኞቿን የምታገኘው በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ነው፡፡
ሶፊያ ገና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ከነበረችበት ጊዜ አንስቶ የማህበራዊ ሚዲያ አፍቃሪ ነበረች፡፡ ለዚህም የዳረጓት ከሚዲያው የምታገኛቸው ጠቃሚ፣ አዝናኝና አስደሳች መረጃዎች ነበሩ፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው፣ ለሷ በትውልድ መንደሯ የሚፈጠሩ አዳዲስ ነገሮችን ለማሳወቅና ለማዝናናት፤ ለእርሷ ብቻ የተፈጠረ መስሎ ይሰማታል፡፡ ብቸኛ አጋሯ አድርጋ ትመለከተዋለች፡፡ ከእውነታው ዓለም እርቃ፤ በሰፊው የሚዲያ ባህር ውስጥ ሰጥማ ስትዋኝ ትውላለች፤ታመሻለች፤ታድራለችም፡፡ ነገር ግን ቀስ በቀስ በሥራዋ፤ በጊዜዋና በጤናዋ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እየፈጠረባት እንደሆነ መረዳቷ አልቀረም፡፡


ከዕለታት በአንዱ ቅዳሜ ከሥራ ስትመለስ ቦርሳዋን ሶፋው ላይ ወርወር አድርጋ ትንሽ ካረፈች በኋላ ምሳ ለመብላት አስባ ነበር፡፡ ግና ስልኳ እጇ ላይ ስለነበር ጣቶችዋን በፍጥነት ማንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ የተለጠፉ ፎቶዎችን፣ፋሽኖችን፣ ማስታወቂያዎችን፣ ዜናዎችንንና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መረጃ የሚሰጡ መልእክቶችን እያየች፤በሚፈለገው መልክ መልስ እየሰጠች (ላይክ፣ሼር፣ኮሜንት እያደረገች) ሳለ አንድ የአብሮ አደግ ጓደኛዋ የሰርግ ፎቶግራፍ ገባ፡፡ ወዲያው እጅግ ውብ እንደሆነ በመግለጽ መልስ ሰጠች፡፡ በጣም አመሰግናለሁ የሚል ምላሽ መጣላት፤ ሞቅ ያለ የአብሮነት ስሜት ተሰማት፡፡ ፈገግ አለች፡፡ ወዲያው አንድ ማስታወቂያ ደረሳት፤ የኮሌጅ ባልደረባዋ የሊያ የንግድ ማስታወቂያ ነበር፡፡ ሊያ የራሷን ንግድ ጀምራለች፤ በጣም ቆንጆና ትልቅ የኦንላይን ሱቅ ከፍታ ከሃብታሞቹ ጎራ ተቀላቅላለች፡፡ አፍታም ሳይቆይ የሌላኛዋ የኮሌጅ ባልንጀራዋ መልእክት ገባ፡፡ ይህም አትሌቲክስ ማሰልጠን እንደ ጀመረችና ደረጃዋንም እያሻሻለች እንደሆነ የሚያሳይ መልእክት ነበር፡፡ ሶፍያ ግን እዛው ነበረች፡፡ ቀለል ያለ ኑሮዋን ተቀብላ ስኬታማ እንደሆነች ነበር የምታምነው፡፡ አሁን ግን ምንም እንዳልሰራችና ከሰው ሁሉ በታች እንደቀረች መልእክቶቹ አስገነዘቧት፡፡ በዚህ ጊዜ ሰዓቷን ተመለከተች፡፡ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ ከተጣደች ሦስት ሰዓት አልፏታል፡፡ እርቧታል፤ ደክሟታል፤ እራሷን አሟታል፤ ደንዝዛለች፡፡ ተጨነቀች፤ የሕመም ስሜት ተሰማት፡፡ መብላት ፈለገች ግን አልቻለችም፡፡ መተኛት ፈለገች ግን አልቻለችም፡፡ ምን አየሰራሁ ነው? ወዴት እየሄድኩ ነው? እራሷን ጠየቀች፡፡ ስልኳን አስቀመጠች፡፡


ማህበራዊ ሚዲያውን አሁንም ትወደዋለች፤ ስልታዊ አጠቃቀም ስላልነበራት እንጂ ሚዲያው ፈጠራን ለማሳደግ፣ ለመማር፣ መረጃ ለማግኘት፣ ግንኙነትን ለማጎልበት፣ የሩቁን ለማቅረብ፣ አለምን ለማወቅና ለመዝናናት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠንቅቃ ታውቃለች፡፡ ከማህበራዊ ሚዲያው መራቅ አልፈልግም ግን ደግሞ አጠቃቀሜ መስተካከል አለበት፤ አለች ለራሷ፡፡ በማግስቱ ፈቃድ ወስዳ እቤቷ ለማረፍ ወሰነች፤ ስልኳን መሳቢያ ውስጥ ከረቸመች፡፡
የምትፈልገውን መጽሐፍ መርጣ በማንበብ ቀኑን አሳለፈች፡፡ ጸጥታና ሰላም ሰፈነ፤ ማታም ሰላማዊ እንቅልፍ ተኛች፡፡ በማግስቱ ጠዋት ስልኳን ስታነሳ ቀለል ያለ ስሜት ተሰማት፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ቢኖሩትም፣ እንደ አጠቃቀሙ ወደ ፈለጉበት አቅጣጫ የሚወስድ ምቹ ጎዳና እንደሆነ ተገነዘበች፡፡ በሚዛናዊነት በመጠቀም እራሷን ለመለወጥ ወሰነች፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ፡- በአለም ዙሪያ ያሉ ሕዝቦች እንዲገናኙበት፡ በጋራ ፍላጎታቸው ላይ ሃሳባቸውን፤ እውቀታቸውንና ፍላጎታቸውን እንዲጋሩበትና መረጃ እንዲቀባበሉበት፤ እንዲማማሩበት፤ በሌላው አለም ስለሚከናወኑ እንቅስቃሴዎች መረጃ እንዲሰበስቡበት፤ እውቀታቸውን፤ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩበትና እንዲጋሩበት የተዘረጋ የመስመር ላይ የጋራ መድረክ ነው፡፡
ማህበራዊ ሚዲያ፡- በአግባቡ ጥቅም ላይ ሲውል ግለሰቦችና ድርጅቶች ሃሳባቸውን የሚገልጹበት፤ በአለም አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ በሌሎች ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩበት ወይም በሌሎች ተጽዕኖ ስር የሚወድቁበት፤የግል ግንኙነትን፤መማማርን፣ እውቀትን፤ ክህሎትን፤ የመረጃ ስርጭትን፡ ግብይትንና የመዝናኛ አቅርቦትን የሚያሳልጡበት ቁልፍ የግንኙነት መሳሪያ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአግባቡ ጥቅም ላይ ካልዋለና ሰዎች በሚዛናዊነት ካልተጠቀሙበት፣ ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ አዎንታዊ ገጽታዎች፡-
ማህበራዊ ሚዲያ ከግላዊ ግንኙነት እስከ ዓለማቀፋዊው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ባለው የሰው ልጆች የሕይወት ጉዞ ውስጥ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያ በትክክል ጥቅም ላይ ሲውል በሁሉም የሕይወት ዘርፍ፡-(ማህበራዊ ፤ ምጣኔ ሃብታዊ፤ ባህላዊና ፖለቲካዊ.) እድገትን ጨምሮ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ቢኖሩትም ለዚህ ጽሑፍ የሚከተሉት ተመርጠዋል፡፡
የማህበራዊ ምጣኔ ሃብት እድገትን ያሳልጣል፡- ማህበራዊ ሚዲያ በትክክል ሲተገበር፡- በትምህርት፤ በሥራ አጥነት፡ በኢ-ፍትሃዊ የገንዘብ ፍሰትና በማህበራዊ ተሳትፎ ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን በመዝጋት፤ ለመረጃ ፍሰት፣ለግንኙነት፣ ለትምህርት እድገትና ለአዳዲስ እድሎች መንገድ በመክፈት፤ ለማህበራዊ ለውጥ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፤ የንግድ ሥራ እንቅስቃሴን በማሳደግ፤ የሥራ ፈጠራን በማበረታታት፤ እውቀቶችን፤ ክህሎቶችን በማጋራትና አቅም በማጎልበት የማህበራዊ ምጣኔ ሃብት እድገትን ያፋጥናል፡፡
ብቁ ዜጋ መፍጠር ያስችላል፡- ማህበራዊ ሚዲያ፡- የመረጃ አቅርቦትን በማሳለጥ፤ ወጣቶች/ታዳጊዎች መረጃ እንዲያገኙ፤ ጥልቅ አስተሳሰብንና የፈጠራ ችሎታን እንዲያዳብሩ፤ የግንኙነት ክህሎትንና ማህበራዊ ኃላፊነትን እንዲያጎለብቱ፤ ብሩህ ነገን መምራት የሚያስችሉ ዕሴቶችን እንዲገነዘቡ በማገዝና አለምን እንዴት እንደሚቀላቀሉ በማስተማር፤ በመረጃ የበለጸገ፤ ያወቀ፤ የበቃ፡ ተሳታፊና ችግር ፈቺ፤ ለግል፤ ለማህበረሰብ ብሎም ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት የሚጠቅም፤ ተምሳሌት የሆነ ትውልድ ከመፍጠር አኳያ ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡


ለሰላም ግንባታ በር ይከፍታል፡- ማህበራዊ ሚዲያ፡- አንዳንድ ጊዜ ግጭቶችን ሊያሰፋ ወይም የተሳሳተ መረጃ ሊያሰራጭ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ስልታዊና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል የግጭት አፈታትና የሰላም ግንባታ መድረኮችን በማዘጋጀት፣የግንዛቤ ማስጨበጫ ዘዴዎችን በመፍጠር፣ ውይይቶችን በማጎልበትና የጋራ ዕርምጃዎችን በማንቀሳቀስ፡- ሰላማዊና ፍትሃዊ ዓለም መገንባት ፤ የጋራ መግባባትን መፍጠር፣ የተገለሉ ድምፆችን ማጉላት፤ ዓለም አቀፍ ትብብርን መፍጠር ያስችላል፡፡ ስለዚህም ግጭቶችን ለመፍታትና ሰላምን ለማስፈን የጎላ አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
ማህበራዊ ትስስርን ያጎለብታል፡- ማህበራዊ ሚዲያ በኃላፊነት ጥቅም ላይ ሲውል፡- ግንኙነትን በማጠናከር፤ የተለያየ ልምድ፤እምነት፤ ባህል፤ የአስተዳደግ ስርአት ያላቸውንና በተለያየ አካባቢ ያደጉ ሰዎችን በማገናኘት የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትና በማወያየት የጋራ መግባባትን፤ መቻቻልን፤ መተባበርን የእኔነትና የአብሮነት ስሜትን ያጎለብታል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ቡድኖች መሃል የሚፈጠሩ ክፍተቶችን በመዝጋት፤ መተሳሰብን፤ መከባበርን፤ የጋራ ችግር በጋር መፍታትን፤ የጋራ ኃላፊነት በጋራ መወጣትን በማበረታታት የተቀናጀና የተዋሃደ ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፡፡ ከጥላቻ፤ ከግጭት ቀስቃሽነት፤ ልዩነትን ከማጉላት የጸዳና በአክብሮት የተሞላ ንግግርን በማስተዋወቅ፤ የተገለሉ ድምጾች እንዲጎለብቱ በማድረግ አብሮ የመኖር፤ አብሮ የመስራት፤ አብሮ የማደግ ባህልን ያጎለበተ፤ ጠንካራ ትስስር ያለው ማህበረሰብ መፍጠር ያስችላል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ገጽታዎች፡-
ማህበራዊ ሚዲያ በተመጣጠነና ኃላፊነት ባለው መንገድ ሥራ ላይ ካልዋለ፡- የተሳሳተ መረጃ (የሃሰት ዜናዎችን፣ ተራ አሉባልታዎችን፣ ግጭት ቀስቃሽና ጥላቻን የሚዘሩ ንግግሮችን፣ ስሜት ጎጂ ሃሳቦችን) በማሰራጨት፣ የኢኮኖሚ አለመመጣጠንንና የማህበራዊ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆልን ያስከትላል፤ እድገትን ያዳክማል፡፡ ማህበረሰብን ወደ ተሳሳተ መንገድ በመምራት ግራ መጋባትን፤ እምነት ማጣትንና ማህበራዊ መለያየትን ያስከትላል፡፡ ማህበረሰብን ለቀውስ ይዳርጋል፤ ግጭትን በማስፋፋት ለሰላም ማጣት መንስኤ ይሆናል፡፡ ግላዊ የመብት ጥሰትን ያስፋፋል፡፡


- ሰዎች ከምናባዊው ዓለም ጋር እራሳቸውን በማወዳደር በቂ ነገር እንደሌላቸውና ብቁ እንዳልሆኑ በማሰብ፣ እራሳቸውን እንዳያከብሩና እርካታ አንዳይኖራቸው ያደርጋል፡፡ ጭንቀትንና ድብርትን ያስከትላል፡፡ በራስ መተማመንን ያሳጣል፤ ምርታማነትን ይቀንሳል፤ እራስን ለማጥፋት አደጋ ያጋልጣል፡፡ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖን ያሳድራል፡፡
- ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያን ለረጅም ጊዜ ሲጠቀሙ ለሱስ ይጋለጣሉ፡፡ ተጨባጩን ዓለምና ኃላፊነታቸውን ይዘነጋሉ፤ ግለኝነት ያጠቃቸዋል፡፡ የገጽ ለገጽ ግንኙነትን በመቀነስ ማህበራዊ ክህሎታቸውንና ጥልቅ ግንኙነታቸውን ያዳክማል፡፡ ይህም በግላዊና ማህበራዊ የሕይወት ለውጥ፤ በአገር እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይፈጥራል፡፡ ጥራት ያለው ትውልድ እንደይፈጠር ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
በአጠቃላይ ማህበራዊ ሚዲያ ለግል፤ ለማህበረሰብና ለሃገር ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው ቢታመንም፣ አጠቃቀሙን በትኩረት መገምገም ካልተቻለ አደጋው የከፋ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዲጂታል እውቀትን በማሳደግ፣ የድረ-ገጽ አጠቃቀም ስነምግባርን በመተግበር፣ የስርጭትና የአጠቃቀም መመሪያዎችንና ደንቦችን በማውጣት፣ ተጠያቂነትን በማስፈን አዎንታዊ ጎኑን ማጎልበት እንደሚቻልና ይህም የተጠቃሚውና የአሰራጩ ማህበረሰብ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ድርጅቶችና የመንግሥት የጋራ ኃላፊነት እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ፡፡.

 

Read 456 times