ኪነ-ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች አንዱ ተግባራቸው ያልታየውን የህይወት ገጻችንን ገልጦ ማሳየት ነው፡፡ ሰርካዊው የኑሮ ሩጫ ወደ ራሳችን እንዳናይ፤ እኛነታችንን በጥልቀት እንዳንመረምረውና እንዳናስተውለው ያዘናጋናል፡፡ በሁነኛ ከያኒ የተከኑ የፈጠራ ሥራዎች ታዲያ ከተፋታነውና ከዘነጋነው የገዛ እኛነታችን ጋር ዳግም እንድንገናኝ ድልድይ ይሆናሉ፡፡ በትናንትና እና በዛሬ መካከል በመመላለስ አዲስ ዕይታን፤ አዲስ የህይወት ፍኖትን ለማነጽ ይታትራሉ፡፡ ተደራሲውም ህይወት አምሳለ-ብዙ ገጽታዎች እንዳሏት እንዲረዳ፤ ስለሚኖርበት ማህበረሰብ በቂ መረዳት እንዲኖረው፤ የገዛ ራሱንም ጠልቆ እንዲመለከት ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ጽሁፍ አጭር ዳሰሳ ላደርግበት የመረጥኩት ‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ የተሰኘው የወጣቱ ደራሲ ፍቃዱ አየልኝ መጽሐፍም በዚህ አውድ ውስጥ ተፀንሶ የተወለደ የፈጠራ ስራ ይመስላል፡፡
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ሊሞግተን የመጣ መምህር ነው፡፡ ሃሳብ ባጠጠበት፤ ወዴት መሄድ እንዳለብን በተደናገርንበት በዚህ ጊዜ ሌላም የሕይወት መንገድ እንዳለ አቅጣጭ ሊያሳየን የመጣ የሕይወት መምህር፡፡
እንዳናስተውል የጋረድንን አቡጀዴ ቀዳዶ ዙርያችንን በአትኩሮት እንድናስተውል ከዕንቅልፋችን ሊቀሰቅሰን የመጣ መምህር፡፡ ትኩረት የነፈግነውን፣ ጩኸቱን ጭምር የቀማነውን ማህበረሰባችን በገዛ አንደበቱ እንዲናገር ለማስቻል የመጣ አስተዋይ መምህር ነው፡፡ ያ ደግ ሰው ራሱን ግን እንደ መምህር አይቆጥርም፡፡ ‘መምህር ነኝና ላስተምራችሁ’ አይነት ግብዝነት ከቶም ከእርሱ ዘንድ የለም፡፡ ያ ደግ ሰው ካገኘው ሰው ሁሉ ለመማር፣ ከተለያዩ የህይወት መንገዶች አንዳች ቁም ነገር ለመገብየት ነው ልፋትና ጥረቱ፡፡ በብያኔና በፍረጃ ያልተቃኘ ነው፤ መምህርነቱ፡፡ ያወቀውንና ያነበበውን በሌሎች ላይ ለመጫን የማይከጅል መምህር፡፡
ታያያ ደራሲው የድርሰቱ አብይ ገጸ-ባህሪ አድርጎ ያጨው ያ ደግ ሰው፣ የህይወት ቀለም አንድ ወይም ሁለት ብቻ ሳይሆን ህብራዊ መሆኑን በመኖር ውስጥ ገልጦ ያሳየናል፡፡ ያስተምረናል፡፡ ያ ደግ ሰው ማህበረሰባዊና ፖለቲካዊ ተዋረዶችን (hierarchies) ወደ ጎን በማድረግ ሁሉም’ጋ ትምህርት መኖሩን በግብሩ ገልጦ ይነግረናል፡፡
ያ ደግ ሰው በሰርካዊው የህይወት ሩጫችን ችላ ያልናቸውና የናቅናቸው ግለሰቦች ዘንድ ተጉዞ ነው ሥለ ህይወት የሚጠይቀው፡፡ እረኛ፣ ድንጋይ ጠራቢ፣ የአሞሌ ጨው ነጋዴ፣ ዕጣን ሰፍራ የምትሸጥ ሴት፣ አዝራር ሰሪ… ተጠይቀው የህይወት አተያያቸውን ይመልሳሉ፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ እንስሳትና ነፍሳትም ቦታ አግኝተው ስለ ራሳቸው፣ ስለ አካባቢያቸውና ሥለ ህይወታቸው ይተርካሉ፡፡ እንስሳትን በገጸ-ባህሪነት መልምሎ እንዲተርኩ፤ ሰውና ህይወትን እንዲሄሱ በደራሲው ታጭተዋል፡፡ ታዲያ ደራሲው እንስሳቱ ሳይጫናቸውና ሳይፈርጃቸው ነው በነጻነት እንዲተርኩ፤ ህይወትን እንዲሄሱ ያደረገው፡፡
“ያ ደግ ሰው ወደ ዕጣን መሸጫ፣ ሉባንጃ፣ ቡክቡካ ወዳለበት፣ አሪቲ፣ ጠጅ ሳር ወደ ተጎዘጎዘበት ሱቅ አመራ፡፡ ዕጣን የምትሰፍረውንም ሴት፡ ‘ሰላም ላንቺ ይኹን መዐዛን የምትሰሪ!’ ኑሮ እንዴት ይዞሻል?” አላት
ያቺ ሴትም፡ “ይኸው ነው ጋሼ፣ ኑሯችን ጥሩ ዕጣን ይመስላል፡፡ ሲቃጠል ጥሩ ይሸታል” አለችው፡፡ “ኑሮዬ በቁመቱ ምሬት ከአፉ ንዴት ከፊቱ አይታይበትም፡፡ እየተቸገርኹ ከመሳቅ በቀር ዐመል የለኝም” አለችው፡፡
ያ ደግ ሰው፡ “በሣቅ ውስጥ ስላለ ኩርፊያ፣ በብርሃን ውስጥ ስላለ ጨለማ ትንሽ ንገሪኝ” አላት፡፡… (ገጽ፣38)
እንዲህ እንዲህ እያለ ነው ያ ደግ ሰው የተለያየ ሥራ የሚሰሩ ሰዎችን የሚጠይቀው፡፡ በ’ያ ደግ ሰው የሚጠየቁ እነዚህን ሰዎች ህይወትን ከሌላ አውታር ያሳዩናል፡፡ ከኑረታቸውና ከስራቸው ሁኔታ ጋር ተነስተው ስለ ህይወት ብዙ ያወጉናል፡፡ ‘ለካስ እንዲህም አለ?!’፤ ‘ለካስ በዚህም በኩል መንገድ አለ?!’ እንድንል የሚያደርጉ ሃሳቦችን ያንሸራሽራሉ፡፡ በዚህም ደራሲው፣ በመምህሩና እንደ ማህበረሰብ ትኩረት በተነፈጋቸው ሰዎች መካከል በመመላለስ ጥቃቅን የሚመስሉ ጉዳዮችን አግዝፎ፤ የዘነጋናቸውን እኔነቶች ፊተኛው መስመር ላይ አምጥቶ፤ በተለያዩ ተረኮች የተጋረዱ ሃቆችን ግርዶሻቸውን ገላልጦ ያስነብበናል፡፡ የአንድ ደራሲና ድርሰት ኹነኛ ጉልበት ይህም አይደል፤ ያልታየውን በማሳየት፤ ከዕርጅና ውስጥ ወጣትነትን፣ ከመልከ ጥፉነት ውስጥ ውበትን፣ ከእንባ ሥር ሳቅን ፈልቅቆ ማውጣት፡፡
ደራሲው የዕውቁ የትምህርት ፈላስፋ የፓውሎ ፌሬሬን ሥራዎች ያንብባቸው አያንብባቸው አላውቅም፡፡ ነገር ግን በ’ያ ደግ ሰው እና በሌሎች የህይወት መምህራን (ገጸ-ባህሪያት) መካከል የሚደረጉ ምልልሶች ፓውሎ ፌሬሬ አጥብቆ ከሚከራከርለት የትምህርት ፍልስፍና ጋር ቅርበት አላቸው፡፡ ፌሬሬ ‘Pedagogy of the Oppressed’ በተሰኘው ዝነኛ መጽሐፉ፣ የዘመናዊ ትምህርት አካሄድን አጥብቆ ይተቻል፡፡ ፌሬሬ በዚህ መጽሐፉ የተቸው አንዱ ጉዳይ የአስተማሪና ተማሪ መስተጋብር ነው፡፡ በዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት ሞዴል ውስጥ “የአስተማሪና ተማሪ ግንኙነት የተሰራው የተራኪና ተተራኪ፣ የተናጋሪና አድማጭ፣ የአካሚና ታካሚ፣ የአዋቂና አላዋቂ፣ እንዲሁም የ-subject-object ግንኙነት ተደርጎ ነው የተቀረጸው” ይላል፡፡ በዚህ ምክንያት “ተማሪዎች አካባቢያቸውና ሕይወትን በራሳቸው የሕይወት ልምድና መረዳት ላይ ተመስርተው እንዳይመረምሩ አድርጓል፡፡ ተማሪዎቹ በአስተማሪ ፊት ቁጭ ብለው ራሳቸውን እንደ አላዋቂ እንዲያዩ ይደረጋል፡፡ ዕውቀት የሚገኘው ከመምህሩ አፍ ብቻ እንደሆነና መምህሩ የሚናገረውና የሚያስበውን ነገር የግድ እየሸመደዱ ማስታወስ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ የተማሪው ንቃተ ሕሊና ሂደት በሌሎች ቁጥጥር ሥርዓት ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ እሳቤው፣ ድርጊቱና መሻቱ ሳይቀር በቁጥጥር ስር ይወድቃል” ሲል የዘመናዊ ትምህርት ሞዴል ህፀጽን ተችቷል፡፡
የዘመናዊ ትምህርት ሞዴል ‘ህማም ያክማል’ ሲል ፈሬሬ አማራጭ አድርጎ ባቀረበው የ-”Problem-Posing education” የትምህርት ሞዴል ውስጥ፣ በአስተማሪና ተማሪ መካከል ያለው ተቃርኖ እርቅ የሚፈጥር ነው፡፡ አስተማሪና ተማሪዎች በትምህርት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ በሁለቱ መካከል የተዘረጋ ተዋረዳዊ ሃይል አይኖርም፡፡ አስተማሪው ከተማሪ፤ ተማሪው ካስተማሪው እርስ በእርስ ይማማራሉ፡፡ ተግባቦቱ ሁለትዮሻዊ ይሆናል፡፡ በዚህም ሁሉም በራሱ አኳኋን ሥለ ሕይወትና አካባቢው የሚያሰላስልበትና ጥልቅ ሂሳዊ ትንተና የሚያደርግበት መድረክ ይሆናል፤ ፌሬሬ ባስተዋወቀው አማራጭ የትምህርት ሞዴል መሰረት፡፡
ያ ደግ ሰውም የፌሬሬ አይነት የትምህርት መረዳት ያለው መምህር ነው፡፡ ባለፈበትና ባገደመበት ሥፍራ ሁሉ ሰዎችን ሳይፈርጅና ደረጃ ሳያወጣ ሥለ ሕይወት ይጠይቃቸዋል፡፡ እነሱም ሥለ ህይወት በተረዱትና በኖሩት መንገድ በጨዋታ መልክ ያወጉታል፡፡ አልፎ አልፎ ያ ደግ ሰውም የራሱን የህይወት መረዳት ይገልጣል፡፡ የግርባብ ዳናዎችም ይህንን ፈለግ የተከተሉ ናቸው፡፡ ሁሉም መምህር፤ ሁሉም ተማሪ ሆኖ ሥለ ሕይወት የሚያወጉበት መድረክ ነው፡፡ ፌሬሬን እዚህ የጠቀስኩትም የእሱ የትምህርት ፍልስፍና እና የዚያ ደግ ሰው የህይወት አረዳድ ቅርርቦሽ ስላላቸው ነው፡፡
ያ ደግ ሰው የሚያነሳቸው አንዳንድ ሃሳቦች፤ የሚጠይቃቸው አንዳንድ ጥያቄዎች በጣም ጥልቅ ናቸው፡፡ ህይወትን ጠልቆ በመረዳት ሂደት ውስጥ ተፈልቅቀው የወጡ ሃሳቦችን በየተጓዘበት ያንፀባርቃል፡፡ “ያ ደግ ሰው፣ ወደ ልቡ ገብተው ያልተመለሱ የሰው ዐሳቦች የሱ እየመሰሉት ‘እኔ’ በማለት መደናገሩን ልብ አለ፡፡ ብዙ በመሰብሰቡ ሳቢያ ከልቡ ላይ ለራሱ የሚሆን ስፍራ አልነበረውም”…(ገጽ፣57)
…የሰው ልጅ ግን ከማህበረሰቡ ከሚማራቸውና ከማህበረሰቡ ወስዶ የራሱ ከሚያደርጋቸው ‘እውነቶች’ የተሻገረ እኔነት አለው ይሆን?! ግለሰቡ ገና ሲወለድ በማህበረሰቡ ዕቅፍ ውስጥ ነው የሚወድቀው፡፡ ከመወለዳችን በፊት ደግሞ ማህበረሰቡ አስቀድሞ የዘረጋቸው መዋቅሮችና የአስተሳሰብ አውታሮች አሉት፡፡ ጥቅም ይኑራቸውም አይኑራቸው ግለሰቡ ለዓመታት እነዚህን ማህበረሰባዊ ዕውነቶች እንደ ተፈጥሮኣዊ ዕውነታ አድርጎ ነው የሚረዳቸው፡፡ እኔነቱን ጭምር የሚሰራው በዚህ ማህበረሰባዊ እሴቶችና አስተሳሰቦች ላይ በመመስረት ነው፡፡ ታዲያ ያ ደግ ሰው “ወደ ልቡ ገብተው ያልተመለሱ የሰው ዐሳቦች የሱ እየመሰሉት ‘እኔ’ በማለት መደናገሩን…”የዚሁ ተቀጥላ ይመስላል፡፡ ገጣሚ ሰሎሞን ዴሬሳ “ዘበት እልፊቱ ወለሎታት” በተሰኘው የግጥም መድበሉ፤
“ነኝ እንዳልል
የት ቆሜ መሆኔን አየሁኝ?” ሲል ትልቁን የህይወት ጥያቄ የጠየቀው፡፡ ልክ እንደ ገጣሚ ሰሎሞን ሁሉ፣ ያ ደግ ሰው በእኔነትና በእኛነት መካከል ያለው ድንበር ተቀያይጦ ቢያደናግረው ነው ትልቁን የሕይወት ጥያቄ የጠየቀው፡፡ በጥያቄው ተደናግሮም አልቀረ፡፡ ያ ደግ ሰው፣ “ባዶ መኾኔ ነጻ ያወጣኛል! እያለ በልቡ ይዟቸው የነበሩትን ዐሳቦች ኹሉ እንደተከፈተ ጄሪካን እያንዶቀዶቀ…”መድፋቱን ያጫውተናል፡፡
በዚህ ድርሰት ውስጥ ጎልቶ የሚደመጠው አንዱ ድምጽ፣ የህይወት አብዝሃነትና አምሳለ-ብዙ ገጽታዎችን ነው፡፡ ለዚህ አስረጅ ይሆነኝ ዘንድ ያ ደግ ሰው ጠይቆ፣ ወንድም ጋሼ ከመለሰው የሀሳብ ፍሬ እነሆ፤ “ከሙሉ ጎዳና መንገዶች ይልቅ መጋቢ መንገዶች ደስ ይላሉ፡ ምክንያቱም፣ ወደ ሜዳ ሆድ ውስጥ ይገባሉ፤ ወደ ተራራ ይወጣሉ፤ ወደ ሸለቆ ይዘምታሉ፡፡”… እዚህ’ጋ አንድ ማስተዋል ያለብን ጉዳይ፣ ሄዶ ሄዶ አንድ ቦታ ላይ የሚሰባሰብና የሚቆም ነገር የህይወት ጣዕምን ወደ መበየንና መፈረጅ ያመራል፡፡ ‘ህይወት መንገዷም፣ ጣዕሟም አንድ አይነት፤ ዓላማዋና ግቧም የታወቀ ነው’ ብለን ወደ መፈረጅ የሚወስደን አንዱ ምክንያት ከሆነ ብያኔ ተነስተን ማጠቃለል ስለሚቀናን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ልክ እንደ ወንድም ጋሼ፣ ህይወት አምሳለ-ብዙ ገጾች እንዳሏትና ይህን ገጾቿን ገልጦ ማሳየት ለአንድ ከያኒ ዋነኛ ተግባሩ ሊሆን ይገባል፡፡ ብያኔና ፍረጃ የህይወትን ጣዕም እንደሚበክሉ አጉልቶ የማሳየት ጣጣ በከያኒው ትከሻ የወደቀ ነው፡፡
በዚህ ድርሰት ውስጥ ያስተዋልኩት አንድ ጉዳይ የደራሲው ጥልቅ አስተዋይነት ነው፡፡ ደራሲው በነገሮች ላይ ጥልቅ መረዳትና አስተውሎት አለው፡፡ አብረውን የሚኖሩ ደቃቃ ፍጥረታትን በባህርያቸው ውስጥ ሰርጾ በመግባት ሲያብራራ በጣም ያስደንቃል፡፡ ሥለ ራሳችን፣ ስለ አካላችን…እንኳን መረዳት ምን ያህል ነው? በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያችን የምናልፍ የምናገድምባቸው ሥፍራዎች ምን ያህል አስተውለናቸው ይሆን?...እስኪ ራሳችንን እንጠይቅ፡፡ ደራሲው ግን ከሰዎችም አልፎ የደቃቃ ነፍሳትና እንስሳት መገለጫ ባህርያቸውን ሲተነትን ያስገርማል፡፡ ይህን ለማድረግ ትልቅ አስተዋይነት ይጠይቃል፡፡
ግርባብ አንዳንድ የተስማማንባቸው ‘እውነቶች’ን ጭምር ይቀናቀናል፡፡ አሳማኝ ምክንያቶችን በማምጣት ያልታየውን ገጽታ ያሳየናል፡፡ ያ ደግ ሰው በመንገዱ እየሄደ ሳለ ሽፍታ አገኘ፡፡…”ያ ደግ ሰው ‘ለምን ሠርተህ አትበላም? ሰው የደከመበት ገንዘብ ላንተ ምን ያደርግልሃል?’”አለው፡
“ያ ሽፍታ እያሳየ፡ ‘ስማ! ማር በልተህ ታውቃለህ?’” አለው፡፡
“ያ ደግ ሰው፡ ‘እንዴታ! በደንብ አድርጌ ነዋ የምበላው!’’” አለው፡፡
“ያ ሽፍታ፡ ‘ሰርተህ ነው ወይስ ከንብ ቀምተህ ነው? በጭስ እያስፈራራህ፣ እንዳትታይ በጭንብል እየተከለልህ ነው ንብ ለፍታ የሰራችውን የምትቀማት’”አለው፡፡…(ገጽ፣140)
ደራሲው ለዘመናት አብረውን ሲኖሩ ልብ ያላልናቸውን ጉዳዮች ሃሳቡን ለመፍተል የሚጠቀምበት መንገድ ያስገርማል፡፡ ተምሳሌትነታቸውም ልክክ ያለ ነው፡፡ “ሰሌዳ በማጥፊያ አይደለም የሚጠፋው ቀጥሎ በሚመጣ ዐሳብ ነው፡፡ ቀጥሎ የሚመጣው ዐሳብ ደግሞ የነበረውን ተነስ፣ እኔ በተራዬ ልስፈር? ይለዋል”…(ገጽ፣182)
ግርባብን ሳነበው ከኪናዊ ሥነጽሁፍነቱ ይልቅ ፍልስፍናዊ እሳቤዎቹ ናቸው ጎልተው የታዩኝ፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የ ያ ደግ ሰው እና የሽፍታው ምልልስ ጥሩ አስረጅ ነው፡፡ እዚህ ጋ ፍልስፍና ስል የእያንዳንዱ ገጸ-ባህሪያት የህይወት አተያይ፣ አስተውሎት ከስራቸው ሁኔታ በመነሳት ህይወትን እንዴት እንደሚገነዘቧት ለማመልከት ነው፡፡
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ እንደ አንድ ኪናዊ የፈጠራ ድርሰት ጥቂት ህፀጾች አያጡትም፡፡ ከያኒው እንደ ማናችንም ሰው በመሆኑ ከድርሰቱ ምሉዕነት መጠበቅ አግባብ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የማነሳቸው ጥቂት ህፀጾች ድርሰቱን በተወሰነ መልኩ እንዳደበዘዙትና ኪናዊ ለዛውም ትንሽ እንዲለዝዝ አድርገዋል በሚል መነሻ ነው፡፡
ምንም እንኳን ያ ደግ ሰው ትኩረት የነፈግናቸውን ግለሰቦችና እሴቶች አጉልቶ ቢያሳየንም፤ በሌላ በኩል ደግሞ የማህበረሰቡን ዕሳቤዎች፣ እምነቶችና እሴቶች መልሶ መላልሶ የሚያስተጋባ ወይም የሚያፀና አይነት ገጸ-ባህሪ ነው፡፡ ለዘመናት በውስብስብ ቀውሶች ውስጥ እየታመሰ እዚህ ከደረሰ ማህበረሰብ ውስጥ የተነሳው ያ ደግ ሰው፣ ግልጥልጥ አድርጎ ሲሄስ ብዙም አናየውም፡፡ ማህበራዊ እውነቶችን ለማጽናት የሚተጋውን ያህል ማህበረሰባዊ ህጸጾችን ለመተቸት ፈራ ተባ ይላል፡፡ ሌሎች ገጸ-ባህርያትም በአንድም ሆነ በሌላ የዚህን የህይወት እሳቤ የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡ እውቁ የስነጽሁፍ መምህር ዶ/ር ዮናስ አድማሱ፤ “ሀዲስ አለማየሁና የማህበራዊ ሂስ ስልታቸው” በተሰኘው ጥናታቸው፣ “የከያኒው ክሂልና ብቃት የሚመጠነው በግለሰቦች ውስጣዊ ሁኔታ ዘልቆ የማህበሩን ስነልቦናዊ አሻራ እንደ ካርታ ሊያስነብበን በመቻሉ ልክ ነው” በማለት፤ የከያኒውን የሃሳብ አድማስ ከየት ወዴት ድረስ እንደሚዘረጋ ነው የሚያስገነዝቡን፡፡ ደራሲው ከየትኛውም አይነት ወገንተኝነት ተላቅቆ የማህበረሰቡን ህጸጽ እንደ ካርታ ሊያስነብበን ይገባል ነው፤ የመምህሩ መልዕክት፡፡ በዚህ አኳኋን በ’ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ድርሰት ውስጥ ማህበራዊ ህጸጾችን በሚታይና በሚጨበጥ መልኩ ሊያሳየን አለመድፈሩ የድርሰቱ ህፀጽ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡
በእኔ መረዳት ግርባብ ውስጥ ማህበራዊ ህጸጾችን ጎልተው እንዳይታዩ ያደረገው ምክንያት የሚመስለኝ፣ ደራሲው በአንደበታቸው ሥለ ህይወት የሚተርኩልን ሰዎችና ፍጥረታት ደግ፣ የዋህና አዋቂ…ብቻ አድርጎ ስለቀረጻቸው ነው፡፡ ሥነ-ጽሁፍ ደግሞ እንደ ህይወት ነች፡፡ ህይወት ውስጥ ደግሞ ደግነትና ክፋት፣ ሳቅና ዕንባ፣ ውልደትና ሞት አስተዋይና ፍዝ…ተጎራብተው የሚኖሩባት አውድማ ነች፡፡ ግርባብ ውስጥ ግን ያለው ዓለም ተምኔታዊነት ያይልበታል፡፡ ይኼ ተምኔታዊነት ደግሞ ከሰርካዊ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻችን ትንሽ የተነጠለ ይመስላል፡፡ በአጭሩ መጽሐፉ የህይወትን ተቃርኖአዊ ሰበዞችን እየመዘዘ የሚተርክ ቢሆን ኖሮ ኪናዊ ለዛውን ትንሽ ማግዘፍ እንደሚቻል ይሰማኛል፡፡
ግርባብ ላይ ያየሁት ሌላኛው ህፀጽ ለድርሰቱ ኪናዊ ለዛ የተሰጠው ትኩረት አንሶ መታየቱ ነው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የድርሰቱ የሃሳብ ትባትና ሃሳቡን ለማንሸራሸር የመረጠው ስልት የሚደንቅ ነው፡፡ ቋንቋውም ያልቸከና በጣም ውብ የሚባል ነው፡፡ ነገር ግን የማዋዛት፣ ምናብ ላይ ምስሎችን የመከሰት፣ ከገጽ ገጽ ስንሸጋገር የገጸ-ባህሪያቱ ተረኮች በቀላሉ ተገማች መሆን፣…የድርሰቱን ኪናዊ ለዛ አሳንሶታል፡፡ ግርባብ ከኪናዊ ሥነጽሁፍነቱ ይልቅ ወደ ፍልስፍና ይበልጥ ያጋደለ ነው የምለው አንድም ለዚህ ነው፡፡ ምክንያቴን ልጥቀስ፤ ሥነጽሁፍ ከአመክንዮ ይልቅ ለስሜት ትቀርባለች፡፡ የሰዎችን ሃዘን ፈልቅቃ የምታወጣ፣ የሰዎችን ደስታ አጉልታ የምታሳይ ነች፡፡ ካፈቀራት ጋር አብሮ መኖርን ብቻ ሳይሆን፣ ካፈቀሩት ጋር መለያየትንም ትተርካለች፡፡ ግርባብ ውስጥ ግን ይሄን አይነቱ ተቃርኖኣዊ ስሜቶች ብዙም ቦታ አለማግኘታቸው ኪነ-ጥበባዊ ንፍገት መስሎ ተሰምቶኛል፡፡
‘ያ ደግ ሰው ግርባብ’ ግን ሊነበብ የሚገባ ድርሰት ነው፡፡ ራሳችንን መልሰን እንድናይ፤ ማህበረሰባችንን ዘልቀን እንድረዳ የሚያስችል ጥሩ ድርሰት ነው፡፡ ደግሞም እንደ ግርባብ ያሉ በይዘታቸውና በአቀራረባቸው ለየት ያሉ የፈጠራ ሥራዎች ለዚህ ለእኛው ዘመን ያስፈልጋሉ፡፡