ዓለም አቀፍ የልጆች ቀን ተከብሯል
በመላው ዓለም ለ35ኛ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ ነው ዓለም አቀፍ የልጆች ቀን - “ልጆች የሚሉት አላቸው፤ እናዳምጣቸው!” በሚል መሪ ቃል የተከበረው፡፡ በዓሉ በ1959 የልጆች መብቶች አዋጅ የፀደቀበት ፤ በኋላም በ1989 የልጆች መብቶች ኮንቬንሽን የፀደቀበትን ቀናት ታሳቢ ተደርጎ ይከበራል፡፡ በመሪ ቃሉ ዙርያ አንዳንድ ሃሳቦችን ላጋራችሁ ወደድኩ፡፡
ከሃርቫርድ፣ ከማሳቹሴትስ ኢንስቲቱት ኦፍ ቴክኖሎጂ እና ከፒኒስላቪያ ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ የስነልቦናና የኒውሮሳይንስ ተመራማሪዎች ባደረጉት ጥናት፤ በልጆችና በወላጆች መካከል የሚደረግ ንግግርና መደማመጥ የልጆቹን የአእምሮ እድገት ከማሳደግ በተጨማሪ የቋንቋ ችሎታቸውን ይበልጥ ያዳብራል፡፡
የጥናት ቡድኑ መሪ ዶ/ር ራሄል ሮምዮ እንዳሉት፤ በልጆችና በወላጆች መካከል የሚደረግ ንግግር የተለያዩ የአእምሮ ክፍልን በማነቃቃት፣ ለአእምሮ እድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡
“ልጄ አይሰማኝም፣ ምን ይሻለኛል?” ብለው ያውቃሉ፡፡ ይሄ በወላጆች ዘንድ የተለመደ አንዱና ዋነኛ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህም በርካታ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለመፍትሄ ከሚጠቀሱት መካከል አንዱ፣ እኔስ ልጄን እሰማዋለሁ ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ልጆች ሃሳባቸው እንዲሰማ መሰረታዊ ፍላጎት አላቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ በወላጆቻቸው የሚሰሙ ልጆች የተሻለ ሁለንተናዊ እድገት ይኖራቸዋል፡፡
የሚሰሙ ልጆች
በራስ መተማመናቸው ይጨምራል
ተፈላጊ እንደሆኑ፣ ዋጋ እንደተሰጣቸውና እንደተወደዱ ያስባሉ
የተግባቦት ክህሎታቸው ያድጋል
በትምህርታቸው ውጤታማ ይሆናሉ
የተሻለ የስሜት ብስለት ይኖራቸዋል
በአንፃሩ ጆሮ የማይሰጣቸው ልጆች ለከፍተኛ ስነልቦናዊ ጫና ይዳረጋሉ፡፡ ለአብነትም ለድባቴ፣ ለጭንቀትና ለብስጭት የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሀሳባቸው የማይከበርላቸው ልጆች በራስ የመተማመን ስሜታቸው የተሸረሸረና አለመፈለግ ስሜት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ልጆች የሚሰማቸው ካገኙ የልባቸውን ያጫውታሉ፡፡
በምን መልኩ እንስማቸው?
ልጆች ሲያወሩ በትኩረት እንስማቸው
ልጆች ሲያወሩ ለሚገልፁት ስሜት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ተናዶ እያወራ ያለን ልጅ አትናደድ አይባልም፡፡ ንዴት ስሜቱን የገለፀበት መንገድ ነው፡፡ እንደወላጅ ልጁ የተናደደበትን ምክንያት ለመረዳት መሞከር ያስፈልጋል፡፡
ዓይን ለዓይን እየተያዩ መስማት
ነገሮችን በእነርሱ ጫማ ውስጥ ሆነን ለመረዳት መጣር
በእነርሱ ቁመት ልክ ወረድ ማለት
ንግግራቸውን አለማቋረጥ
እየተደመጡ መሆናቸውን ለማረጋገጥ የሚያወሩትን መድገምና አስፈላጊ ከሆነ ማብራሪያ መጠየቅ
የልጆችን ትናንሽ ጉዳዮች የመስማት ልማድ ካለን፣ ልጆች ትላልቁን ለአብነትም ፆታዊ ጥቃት ለመናገር አቅም ይሰጣቸዋል፡፡
ልጆችን ለማዳመጥ ትልቅ እድልን የሚሰጠን ደግሞ በጋራ በሚኖረን ጊዜ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር የሚያሳልፉት የጊዜ ብዛት (Quantity time) ሳይሆን ጥራት ያለው ጊዜ (Quality time) በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ ተአምራዊ በጎ ተፅኖ ያሳድራል፡፡ (Quality time) የሚለውን ፍሬያማ ጊዜ ብዬ መግለፅን መርጫለሁ፡፡
አንድ ጥናት እንዳመለከተው፤ አሜሪካዊያን ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በአንድ ቀን ውስጥ ለ37 ደቂቃዎች ፍሬያማ የአብሮነት ጊዜን ያሳልፋሉ፡፡ ልጆች ከወላጆቻቸው በየእለቱ የሚፈልጉት ይህ ትንሽ ደቂቃ በልጆች ሁለንተናዊ እድገት ላይ በርካታ አዎንታዊ አበርክቶ አለው፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በቀን አስርም ሆነ አስራ አምስት ደቂቃ በእቅድና በአላማ ሃሳባችንን ከሚበታትኑ ነገሮች ሁሉ ሰብስበን ከልጆች ጋር የማሳለፍ ልማድ ማዳበር ልጆችን ለማዳመጥ ትልቅ በርን ይከፍትልናል፡፡ ምናልባትም ሁሌ አብረን አንድ ቤት አይደለም እንዴ የምናሳልፈው? ብለን ቀለል ልናደርገው እንችላለን፡፡ ነገር ግን የወላጅ እና የልጅ ፍሬያማ ጊዜ የሚባለው ፣ ወላጅ ከማንኛውም ሥራ ራሱን አግልሎ፣ ከኤሌክትሮኒክስ መገልገያ በመራቅ በሙሉ ሃይሉ እና በሙሉ ስሜት ትኩረት በመስጠት ከልጅ ጋር ማሳለፍ ሲችል ነው፡፡
ይህ ጊዜ በአጋጣሚ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብሎ ታስቦበት ከልጄ ጋር ማሳለፍ እፈልጋለሁ ተብሎ የታቀደበት ሊሆን ይገባል፡፡ ለልጆች የምንሰጠው ትልቁ ስጦታ ጊዜን ነው፡፡ “ከልጅ ጋር አትጫወት ይወጋሃል በእንጨት” አመለካከትን መስበር ይጠበቅብናል፡፡
የፍሬያማ ጊዜ ዋነኛ ማዕከል ልጆች ናቸው፡፡ በልጆች ምርጫ እና ፍላጎት የሚከናወን የጋራ ጫወታ ነው፡፡ ለአብነትም ድብብቆሽ፣ ጌም፣ መፅሐፍ ማንበብ፣ እንቆቅልሽ፣ ተረት ተረት፣ የልጅ እድሜን ያገናዘበ የቤት ውስጥ የጋራ ስራ ማከናወን፣ በጋራ ወደ ውጭ አየር መቀበል ወዘተ ሊሆን ይችላል፡፡
ለልጆች ፍሬያማ ጊዜ ለየት ያለ ትርጉም አለው፡፡ ተፈላጊነታቸውን፣ በወላጆች ዘንድ ያላቸውን ዋጋ፣ እና መወደዳቸውን ያረጋግጥላቸዋል፡፡ ሌላው ጥናቶች ያረጋገጡት፤ በፍሬያማ ጊዜ ተጠቃሚዎች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ወላጆችም ጭምር መሆናቸው ነው፡፡ ወላጆች ውጥረት ከተሞላበት የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ወጥተው በግንኙነቱ መንፈሳቸው ይታደሳል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የስሜት ትስስራቸው ይጠናከራል፡፡ በወላጅ እና በልጅ መካከል ያለው መተሳሰብ ይጎለብታል፡፡ የልጆች የስሜት ብስለት ክህሎትም እንዲዳብር ይረዳል፡፡ በተለይም የወላጅ እና የልጅ ግንኙነትን ይበልጥ ያጠናክራል፡፡ ይህ ምቹ ሁኔታ ደግሞ የልጆችን የመሰማት እድል ያሰፋል፡፡
በአሪዞና ዩኒቨርስቲ በተደረገ አንድ ጥናት መሰረት፤ ከቤተሰብ ጋር የጋራ ጊዜ የሌላቸው ልጆች ለአልኮልና ለሱስ የመጋለጣቸው እድል እጥፍ ነው፡፡ ፍሬያማ ጊዜ ግን ደስተኛ ቤተሰብን ይፈጥራል፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፤ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያሳልፉ ልጆች ለጭንቀት እና ለብቸኝነት የመጋለጥ እድላቸው ጠባብ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ እነዚህ ልጆች ችግር እንኳን ቢገጥማቸው ከቤተሰባቸው ጋር በገነቡት መልካም ግንኙነት ከችግሩ ጠንክረው ለመውጣት (Resilience) አቅም አላቸው፡፡
ለልጆቻችን አቅም በፈቀደ መጠን የተሻለ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እንደምንጥር ሁሉ ልጆቻችንን ለማድመጥም እንዲሁ እንትጋ፤ መልእክቴ ነው፡፡