፨ ኢትዮጵያ የብዙኀን ሀገር ናት። የአንድ ጎሳ፣ የአንድ ሰው፣ የአንድ ሃይማኖት፣ የአንድ ወገን ሀገር ኾና አታውቅም፤ አትኾንምም። ኢትዮጵያ የብዙ ዘመን ታሪክ የኖራትም ኾነ አሁን ድረስ ከነ’ክብሯ’ ያለችው በተለያዩ አለላዎች የተሰፋች ስለኾነች ነው። ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ. ዴሌቦ በ1991 ‹እፎይታ› መጽሔት ላይ ‘ታሪካዊ ትንታኔ’ በሚል ርዕስ እንደጻፉት፦ ‹‹ከ330 እስከ 615 ድረስ በ285 ዓመታት ውስጥ ኦሪት፣ ክርስትናና ኢስላም ቤተ-መንግሥት ውስጥ ገቡ። ሃይማኖቶቹን ያመጧቸው ግሪኮች፣ ሮማውያን እና የአረብ ስደተኞች ናቸው።[...] ከክርስትና ከኦሪትና ከእስልምና መካከል አንዳቸውን ብንቀንስ ኢትዮጵያ የሚባል ነገር አይኖርም፤ ይላሉ። ይህ እውነታ በሀገራችን ለረዥም ዘመን የነበረ ቢሆንም አሁንም ድረስ በ’አንዳንድ’ ሰዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለው አይደለም። ‹‹መጤ ነው›› የሚል የኋላቀር አስተሳሰብ በአዕምሯቸው ያቆሩ ሰዎች አሉ። መጀመሪያ የነበረችው ኢትዮጵያ ናት፤ ከዛ አስተማሪዎች እና ስደተኞች መጡ። አስተማሩ ተመለሱ። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ሕዝቦች አምነው ተቀበሏቸው። ተቀባዮቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ስለዚህ ማንም መጤ የለም። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ቢጎድል “ኢትዮጵያ” የምንላት ሀገር አትኖረንም። ፕሮፌሰሩ ሲቀጥሉ ‹‹...ግጭት ሳይኖር ማዋሃድ የኢትዮጵያ ልዩ ባህሪ እንደኾነ ያሳያል። ክርስትናን እስልምናን እና ኦሪትን መንግሥቱና ሕዝቡ በፈቃደኝነት ነው የተቀበላቸው።››
፨ ሰው ሳይፈልገው በኾነው ነገር ማንም አይወቅሰውም፤ ማንም አይሸልመውም። “ነጭ ስለኾነ ጥቁር ስለኾነ፣ እዚህ ጎሳ ወይ እዚያ ጎሳ ስለተወለደ” ብሎ አንድ ሰው ሌላውን መውደድ ወይ መጥላት አላዋቂነት ነው። አሁንም ድረስ፤ የተዋለደ፣ አብሮ የኖረ፣ የተዋደደ፣ አብሮ ያደገን ማኅበረሰብ፤ በውስጡ ‹ወገኔ አይደለም› ብሎ የሚያስብ ሰው መኖሩ ያስገርማል። ‹‹የኢትዮጵያን ታሪክ ሲጽፉ የኖሩት ደብተራዎች ናቸው።›› ይላሉ ፕሮፌሰሩ ‹‹በጽሑፋቸው ውስጥ ሕዝቡን ጠላትና ወገን ብለው ነው የሚፈርጁት።›› ከዕውቀት ማነስ አልያም በልብ አምኖ ‹ጠላቴ ነው፣ አረመኔ ነው› ብሎ ማሰብ የሀገራችን እድገት እንቅፋት ኾኖ የኖረና በዚሁ የሚቀጥል ከኾነም ለአገራችን ጎጂ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፡፡
፨ በ2008፣ በሁለተኛ እትም ተሻሽሎ የታተመው፣ በአለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ የተጻፈውን ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› መጽሐፍ አንድ ምዕራፍን እንቃኛለን፡፡ መጽሐፉ በዶክተር ሥርግው ገላው ተዘጋጅቶና ተስተካክሎ (አርትዖት ተደርጎ) የታተመ ነው። የምናየው ምዕራፍ ፯(7) ‹‹ከዐፄ ገብረመስቀል በኋላ በኢትዮጵያ ስለ ነገሡት ነገሥታት፣ ስለ እስልምና ሃይማኖት›› የሚለውን ነው።
፨ ያለ አንዱ ጎሣ፣ ያለ አንዱ ሃይማኖት ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም። የብዙኀን ደሴት እንጂ ለይቶ ‹‹የእንቶኔ›› ደሴት ናት ማለት ጭፍንነት ነው። አለቃ ተክለኢየሱስ ዋቅጅራ በዚህ መጽሐፋቸው (ከላይ በጠቀስነው ርዕስ) የተለየ ወገንተኝነት አንጸባርቀዋል። መነሻ መረጃ በሌለው ትርክት ‘ታሪክ’ ብለው ጽፈዋል። የራሳቸው ‘ሃይማኖት’ ላይ የሚያተኩር መጽሐፍ ጽፈው ቢኾንና እንዲህ ዓይነት ነገር ቢጽፉ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፤ ግን ‹የኢትዮጵያ ታሪክ› ብለው ራሳቸውን አሞግሰው ሌላውን አኮስሰው ማቅረብ ስህተት ነው። ምክንያቱም ሀገሪቷ ኢትዮጵያ ራሷ አስማምታ ያኖረችውን እሳቸው ሊሽሩ አይችሉም። በመረጃ እጦት ወይ በዕውቀት ማነስ ከኾነ እልፎች ታሪኩን የሚያውቁ በአቅራቢያቸው ማግኘት ይችሉ ነበር። ስህተቱ ደግሞ በጸሐፊው ብቻ ሳይኾን በአርታዒውም ጭምር ነው፤ ‹‹አለቃ ተክሌ እንዲህ ብለው ጽፈዋል ግን ታሪኩ እንዲህ ነው›› ብለው በኅዳግ ማስታወሻም ቢኾን ማቅረብ ይችሉ ነበር። ሁለቱም ለፍተው ለሕዝቡ ትክክለኛ ‘ታሪክ’ን ለማድረስ ጥረዋል፤ በዚህ ይመሰገናሉ። ኾኖም እንደው ሰዎችን ባያገኙ ቢባል እንኳ በሚፈልጉት ቋንቋ የተጻፉ በርካታ መጻሕፍት ነበሩ። በ’ሀገራችን ታሪክ’ ሥም ጥላቻ እና ወገንተኝነት ማንጸባረቅ የ ‘አዋቂ’ ሰው ተግባር አይደለም። የጸሐፊውን ስህተት በዘመናቸው የነበረውን የ’አግላይነት ፖሊሲ’ ተከትለው ነው በሚል ማስተባበያ ብናቀርብ አርታዒው ግን ቢያንስ ትክክለኛውን መረጃ ማቅረብ ነበረባቸው።
፨ ገጽ 10 ላይ መጽሐፉን የጻፉበትን ምክንያት ‹‹ታሪክ ጸሐፊዎች በአድርባይነት ሚዛናዊነት የጎደለው ታሪክ ጽፈው በማንበቡ ይህንን ስህተት ለማረምና ሚዛናዊ የሆነ ታሪክ ለመጻፍ ነው።›› ብለው የጠቀሱትን ተቃርነዋል። (የማተኩረው በሌሎች ታሪኮች ሳይኾን ከላይ በተጠቀሰው ርዕስ ላይ ብቻ ነው፡፡)
፨ እንቀጥል፤ ገጽ 116 ላይ እንዲህ ይላሉ፦ ‹‹... ክርስቶስ በተወለደ በ፮፻፳፪(622) ዘመን መሐመድ ተወለደ።›› ብለው ያስቀምጣሉ። በየትኛውም የታሪክ መዝገብ ብናይ፣ የትኛውንም የ‹ሲራ› (የነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) ታሪክ) መጻሕፍት ብናነብ፣ የነብዩ ሙሐመድ ውልደት በ570 ወይ 571 እ.ኤ.አ እንደኾነ እናረጋግጣለን። ለምሳሌ አንድ መጽሐፍ ልጥቀስ፦
‹‹ነብዩ ሙሐመድ(ሰ.ዐ.ወ) በመካ ከተማ በ570(ድ.ል) ተወለዱ።››(የተረሳው ኢስላማዊ ታሪካችን፣ 13)
አለቃ ተክለኢየሱስ ስለ ነብዩ ሙሐመድ (ሰላም በርሳቸው ላይ ይሁን) መወለድ ከነገሩን በኋላ ‹‹የመሐመድ ታሪክ እንዲህ ነው።›› ብለው ቀጥታ ስለ ፋርስ ንጉሥ፣ እሳቸው ከስርይ ወይም ከስሪ ስለሚሉት ወደ ኪስራ ታሪክ ይገባሉ፤ ከውልደታቸው ወዲያው ዘለው ወደ ሥድስተኛው አመተ ሂጅራ ወይም ወደ 628 (እ.ኤ.አ)። ምክንያቱም በነብዩ ሙሐመድ መልዕክተኛ አብደላህ ቢን ሁዘይፋ ሳህሚ የኢስላም ጥሪ የኪሥራ ቤተ-መንግሥት የገባው በዚህ ዓመት መኾኑን የታሪክ መጻሕፍት ያስረዳሉ። ቀጥለው ‹‹እስላም ገባበት። ሥሙም እስጥንቡል[እስታንቡል] ይባላል።›› ይላሉ። የቱርክ ከተማ የኾነችው ኢስታንቡል ወይም ቆስጠንጢኒያ የተከፈተችው ከነብዩ ሙሐመድ ኅልፈት ከ850 ዓመት በኋላ ነው። በ21 ዓመቱ ወጣት ሙሐመድ አል-ፋቲህ በሜይ 29, 1453(ጁማደል ዑላ፣ 15፣ 857 አመተ ሂጅራ) ነው - የተከፈተችው። ኢስታንቡል የሚለው ሥሟም የተሰየመው ያን ጊዜ መኾኑን ታሪክ ዘግቧል። እኛ አማን አሰፋን እንጥቀስ፦ ‹‹የከተማዋን ሥምም ቀየረ። አዲስ ሥም አወጣላት። ኢስላም ቡል አላት። የኢስላም ከተማ (መዲነቱል ኢስላም) ማለት ነው።›› (በሠይፎች ጥላ ሥር፣ 104)
፨ ቀጥሎ ‹‹ከክርስቶስ ልደት በኋላ ፮፻፴ ዘመን ነው። በዚያም እስላሞች ዓለሙን ሁሉ አሰለሙት። እጅግ በረቱ። በኢየሩሳሌም በጌታ መቃብር መስጊድ ሠርተዋል።››(116-117) ይላሉ። በእሳቸው አጻጻፍ ካየን ነብዩ ሙሐመድ በ622 ተወልደው በ630 ደግሞ ዓለሙን ካሰለሙት፤ በሥንት ዓመታቸው ነብይ ኾኑ? በሥንት ዓመታቸው አስተማሩ? በ8 ዓመታቸው ዓለምን መቆጣጠር የሚያስችል ጉልበት አገኙ? ስለዚህ ራሳቸው በጻፉት ስህተት መኾናቸውን ገለጹ። በ630 ነብዩ በመዲና ነበሩ። ያኔ ዓለምን ሙሉ የተቆጣጠሩበት ጊዜ አልነበረም። ወደ መላው ዓለም በስፋት ‹ኢስላምን ለማስተማር› የተሄደው በአራቱ ኸሊፋዎች ማለትም በአቡበከር፣ ዑመር፣ ዑስማን እና ዐሊይ ዘመን ነበር። ‹‹በኢየሩሳሌም በጌታ መቃብር መስጊድ ሠርተዋል።›› የሚለውም በ630 በነብዩ ዘመን ሳይኾን በዑመር ዘመን በ637(638) ነው(17 ወይም 16 አመተ ሂጅራ) ነው። ታሪክ ስናነብ እንደምናየው ዑመር ያን ጊዜ ኢየሩሳሌምን እየጎበኙ የሰላት ወቅት ደርሶ ቄሶች ‹‹ግባ እና ቤተ-ክርስቲያን ስገድ›› ቢሏቸው ‹‹ወደፊት የሚመጡት ህዝቦች ‘ዑመር ሰግዶበታል’ ብለው እንዳይወስዱባችሁ እፈራለሁ›› ብለው ሌላ ቦታ ሰገዱ፤ እንጂ አስገድደው ወሰዱ የሚል የለም።
፨ የአንድ ሐገር ሰው ኾነው ‹ይኸው የሐገራችንን ታሪክ ነው የጻፍኩት› እያሉ ግን በአግላይነት፣ በ‹አላውቅህም› ባይነት ‹‹ያንተ ሃይማኖት እኮ የጌታዬ እርግማን ነው።›› ዓይነት ማለት ጭፍን ወገንተኝነት ነው። እንዲህ ዓይነት “አሻሚ” ሃሳቦችን የሃይማኖት መጽሐፍ አዘጋጅተው በተዓማኒ ማስረጃ ላይ ማስተማር እንጂ በ‹ኢትዮጵያ ታሪክ› ሥም ማስፈር ስህተት ነው።
ይቀጥሉና፤ ‹‹የመሐመድ ታሪክ እንዲህ ነው። መሐመድ በመዲና በዓረብ ሀገር ተወለደ።››(117) ይላሉ፤ ይሄ ፍጹም ስህተት ነው። ከመረጃ እጦት አይመስለኝም፤ ምክንያቱም ዝቅ ብለው አባታቸው ገና ነብዩ ሳይወለዱ(ተረግዘው ሳሉ) እንደሞተ ይናገራሉ። ይህን ታሪክ የሰሙበት ወይ ያነበቡበት ቦታ ላይ ነብዩ በመካ እንደተወለዱ ያሳያቸዋል። እናታቸው የሞተችው 7 ዓመታቸው እያሉ(117) ሳይኾን 6 በሚል ይስተካከል። ቀጥሎ ‹‹በተወለደ በ፲፭(15) ዓመቱ ከመካ ታላቅ ሴት ባለጸጋ አገባ።›› ብለው ኸዲጃን፤ ህድጅ፣ ከዲቻ ብለው ይጠቅሳሉ። ይህም ትልቅ ስህተት ነው፤ ይህም ካነበቡበት ወይ ከሰሙበት ቦታ 25 እንጂ 15 የሚል አይኖርም።
፨ ትልቁ እና ዋነኛው ስህተታቸው የሀገራቸውን ሰው ከድተው ወገንተኝነታቸውን ያሳዩበት ‹ነብዩ ሙሐመድ በረኃ ለበረኃ ሲንከራተት ቆይቶ ራሱን ነብይ አደረገ፤› ብለው ከዕውነታው የራቀ እርሳቸውንም የሚያስገምት ጽሑፍ መጻፋቸው ነው፡፡ በጉዳዩ አለማመን መብታቸው ነው፤ ግን ‹የሀገር ታሪክ› ብለው እስከጻፉ ድረስ የሀገራቸው ሰው የኾነው የሚያምንበትን ጠይቆ እና ተረድቶ መጻፍ አዋቂነት ነው። ዘመዶቹ ስለሆኑ አመኑለት ለማለትም ‹‹ምሽቱና አሽከሮቹ፣ ሰይድ ባሪያው በርሱ አመኑ። የቅርብ ዘመዶቹ ዓሊና መሐመድ ያቡበከርን ልጅ አግብቶ ነበርና...›› ብለው ‘ያመኑለት ለዝምድናው ነው’ን ያስተላልፋሉ። አንደኛ ነገር ሰይድ የሚባል ባሪያ አልነበረም። አቡበከርም የሰለመው ልጁን ስላገባለት የሚለውም ልክ አይደለም። ዓዒሻ የአቡበከር ልጅ እና ነብዩ ሙሐመድ የተጋቡት እርሷ 18(ወይም 20) ዓመት ሲሆናት በ2ኛው አመተ ሂጅራ፣ ነብይ ከኾኑ በ15ኛው ዓመት ማለት ነው።
፨ ‹‹ከዚያ በኋላ የመካ ሰዎች ከነደቀ መዛሙርቱ አባረሩት። መዲና ተመለሰ። በሐምሌ ፲፭(15) ቀን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ፮፻፴፬(634) ዘመን ነው። ነገር ግን ኤድስከሬ የሚባል የመዲና ሰው በክብር ተቀብሎት ነበረ። በነዚያ ኃይል መካን ወግቶ ተመለሰ። ከዚያ ወዲያ ወደ ዕስጥንቡል ንጉሥና ወደ ፋርስ ንጉሥ ይልክ ጀመረ። ነብይነቱን እንዲያውቁለት።›› እዚህ ላይ ብዙ ልክ ያልኾኑ ነገሮችን መልቀም እንችላለን። የመጀመሪያው፦ “የመካ ሰዎች ከነደቀመዛሙርቱ አባረሩት። መዲና ተመለሰ።” ይላሉ፤ እዚህ ጋ የ‹ኢትዮጵያን ታሪክ› የሚጽፉ ከኾነ ተሰደው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ስለነበሩት ሰሀቦች ታሪክ አልጻፉም። የሀገራቸውን ትልቅ ታሪክ ዘለዋል። ሁለት፦ ቅድሚያ መዲና ይኖሩ እንደነበር አርገው ‹ተመለሱ።› ይላሉ። ሦስት፦ ‘በ634 ነው’ ይላሉ፤ ይህም በሳቸው ሂሳብ በ622 ተወልደው፣ ነብይ ሆነው፣ አሳዳጅ ተሳዳጅ የኾኑት በ12 ዓመታቸው ነው። ኸዲጃን ደግሞ ያገቡት በ15 ዓመታቸው፤ በየትኛው የሂሳብ ህግ እንዲህ እንደሚመጣ አላውቅም። አራት፦ ‘ኤድስከሬ የሚባል ሰው’ ይላሉ። ይህን ከየትኛው መዝገብ አግኝተው እንደጻፉት እኔ አላውቅም፤ የነብዩን ዝርዝር የሕይወት ታሪክ የጻፉ(ሁሉም) እንዲህ የሚባል ግለሰብ አልጠቀሱም። ‘መካን ወግቶ ተመለሰ’ ብለውም፤ ነብዩ ሙሐመድ መዲና ከተሰደዱ ከ8 ዓመት በኋላ(ማለትም በDecember 629 ወይም በJanuary 630) የተከናወነን ጉዳይ ይጠቅሳሉ፤ ደግሞም በጦርነት እንደተከፈተ ነገር ‘ወግቶ ተመለሰ።’ ይላሉ፤ ‹ረሒቀል መኽቱም› የሚለው የነብዩ ሙሐመድን ሕይወት የያዘው መጽሐፍ ስለዚያን ጊዜ ገጽ 316 ላይ እንዲህ ይላል፦ ‹‹በተለምዶ በጉዞ ወቅት ከሚያዘው የነፍስ ወከፍ መሳሪያ፣ ማለትም ሰይፍ ከነአፎቱ ካልሆነ በቀር የጦር መሳሪያ አልያዙም። ምክንያቱም የመዋጋት ሐሳብ አልነበራቸውምና።›› እናም ወግተው ገቡ የሚለው መሰረት የሌለው ተረክ ነው። አምስት፦ ከላይ እንደተገለጸው የኢስታንቡል ጉዳይ ነው።
፨ ቀጥሎ እስከ መጨረሻው(ገጽ 118) ድረስ ያለው በጥቂት መነሻ ላይ ራሳቸው ጨምረው የጻፉበት፣ ለ‹ኢትዮጵያ ታሪክ›ነት የማይበቃ ወገንተኝነት ያንጸባረቁበት ጽሑፍ ነው። በአርታዒው(?) የኅዳግ ማስታወሻ ላይ ቢስተካከልም ‹‹በትንሣኤ ሙታን ግን አያምንም።›› ብለው የዕምነቱ መሠረት የኾነውን ክደው፤ የሃይማኖቱ ትዕዛዛትንም እንደ ማናናቅ አድርገው (‹‹የመሐመድ ሃይማኖት ትዕዛዙ ይህ ነው።[...] አካልን ሁል ጊዜ መታጠብ።››) ሲሉ ጽፈዋል። ‹‹ክፉ የሠራ በገሃነም መልካም የሠራ በገነት እንዲኖር ያውቃል።›› እያሉ “ትንሣኤን አያውቁም” ማለት ከ’አዋቂ’ ሰው የማይጠበቅ ነው።
፨ በመጨረሻ፣ ‹‹መሐመድ ማስተማር በጀመረ በ፲፰(18) ዘመኑ ሞተ። በሞተ በ፳፫(23) ዘመኑ የሕግ መጽሐፋቸው መጽሐፈ ቁራናቸው ተጻፈ።[...] ከርሱ በኋላ የመሐመድ ሃይማኖት በዓለሙ ሁሉ ደርሶ አሁን መካ መዲና ተመለሰ።›› (118) ይላሉ። ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ እንደመሰከረለት እንዲህ ሲል ከኔ በኋላ መንፈሴን ጵራቅሊጦስን እልክላችኋለሁ። እርሱም ሁሉን ያስተምራችኋል። ያለው ቃል እርሱን መስሎት ነበረ።›› በማለት ታሪካዊ ስህተት ፈጽመዋል። ነብዩ ሙሐመድ ማንበብም ኾነ መጻፍ አይችሉም፣ ስለዚህ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አላነበቡትም። ሰው አነበበላቸው ቢባል እንኳ የብሉይ ኪዳን በአረብኛ ቋንቋ የተተረጎመው አርሳዲያስ በሚባል ግለሰብ እ.ኤ.አ በ900 ነው። እሳቸው ከሞቱ ከ300 ዓመታት በኋላ፤ ሐዲስ ኪዳን ደግሞ አርፔኒየስ በተባለ ግለሰብ እ.ኤ.አ በ1616 ነው። ስለዚህ መጽሐፉን አግኝተው የማንበብም ኾነ የመስማት እድል እንዳልነበራቸው ይህ ማሳያ ነው።
“በ18 ዓመታቸው ሞቱ” የሚለው ማስረጃም ከባድ ስህተታቸው ነው፤ ሁሉም ታሪክ ላይ የተዘገበው በ63 ዓመታቸው እንደሞቱ ነው። “በሞተ በ23 ዘመኑ ቁርዓን ተጻፈ።” የሚለውም ታሪኩን ሲሰሙ ወይ ሲያነቡ በሥርዓት አለመስማታቸውን የሚያረጋግጥ ነው። ቁርዓን በ23 ዓመት ከሰማይ ወርዶ አለቀ እንጂ በሞቱ በ23 ዓመቱ ተጻፈ የሚለው መሠረት የለሽ ነው። ከዚያም ወገናቸውን ክደው “በዓለም ደርሶ መካ መዲና ተመለሰ” ማለት፤ የሀገራቸውን ህዝብ ‘ወገኔ አይደለህም’ ማለት ነው።
፨ አርታዒውም ኾነ ጸሐፊው እንዲህ ዓይነት ወገንተኝነት ያረበበበት ጽሑፍ መጻፍና ማስተላለፋቸው ከባድ ስህተት ነው።