Monday, 25 November 2024 07:36

የአብርሃም አስመላሽ ግጥም ቀመስ መነባንቦች!

Written by  ዮናስ ታምሩ ገብሬ
Rate this item
(1 Vote)

‹‹ተገና ጨዋታ፣ ተውሃ ዋና በቀር፤
ቦስክ የሚሉት ግጥሚያ፣ አያውቅም የእኛ አገር፤
እኔ ግን ዲያኛቸው፣ በቆፍጣናው ልቢዬ፤
ከታይሰን ጋራ፣ ለመግጠም አስቢዬ፤
ማለዳ እነሳና፣ ጂምናስቲክ ሥሰራ፤
ጣቴ እንዲጠነክር፣ ስሰብር እንስራ፤
አንድ ወር ሞላኝና፣ መዳፌ ዳበረ፤
ደረቴም ሰፋና፣ ጣቴ ጠነከረ፤
በጣም እንዳልወፍር፣ ወይም እንዳልቀጥን፤
ምግቤን አዘጋጀሁ፣ በመጠን፣ በመጠን፤
ድሮ ተምበላው፣ በግማሽ ቀንሼ፤
ሦስት አነባብሮ፣ ለቁርሴ ቀምሼ፤
በስድስት ኩባያ፣ አሬራ ከልሼ፤
መዋሉን ዠመርኩኝ፤…..››

(የአብርሃም አስመላሽ መነባንብ ነው፤ ቃላቶቹ ቀጥታ ከእሱ አንደበት የተቀዱ ስለሆኑ ገጠሪኛ ዜማውን/አወራረዱን ላለመሽረፍ ሲባል እንደወረደ ተቀምጠዋል፤)
አብርሃም አስመላሽ፣ በዘመናችን መነባንብን ከፍ አድርጎ ያኖረ ከያኒ ነው፤ የገጠሪቱን የአገራችንን ክፍል ዘይቤ ተውሶ፣ በገጠር ሰው አንደበት አድሮ፣ የተለያዩ ጉዳዮችን በመነባንብ መልክ አስቃኝቶናል፤ መነባንቦቹ ከፍ ሲሉ የግጥም ያህል ጥንካሬ ያላቸው ናቸው፤ የግጥምን አላባዊያን የተላበሱ እና በሚያነሱት ርዕሰ-ጉዳይ ደግሞ ጠንከር፣ ጠንከር ያሉ ናቸው።
አብርሃም አስመላሽ በአዲስ አበበ ከተማ፣ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ተወልዶ እንዳደገ ዕሙን ነው፤ ነገር ግን ከመሃል ከተማ ወጣ ባለ ለዛ ነበር መነባንቦቹን የሚያቀርበው፤ በኢትዮጵያ ራዲዮ በኩል ብቅ እያለ በዚያች ሰላላ ድምጹ ክቡድ ሀሳብ ያቋድሰን ነበር፤ የገጠሩን ሥነ-ቃል፣ የገጠሩን አባባል ቀምሞ ወደራሱ መንገድ ከርክሞ ይሰገስግና፣ በስላቅና በቁምነገር የታጀቡ ሀሳቦችን ያጋባል፤ መነባንብ ያዥጎደጉዳል፤ አማርኛውን ከበግ ነጋዴ ገበሬዎች እንደለመደ በአንድ ቃለ መጠይቅ ሲናገር ተደምጧል፤ ከመራቤቴ እና ከወሎ በግ አግተልትለው ከሚመጡ ነጋዴዎች ኋላ እየተከተልኩ በጋቸውን ሳይሆን አማርኛቸውን እሰርቅ ነበር ይላል።
ታዲያ፣ ሥራዎቹ ለኮሜዲ ያደሉ፣ የግጥም ለዛ እና ውበት ያላቸው፣ እንደ አንድ ሰው ቲያትር (Monologue) መድረክ ላይ ከመናገር ባለፈ በትወና በመግለጽ የሚከወኑ ናቸው፡፡ አብርሃም መነባንብ ሲያነብብ ግጥም የሚወርድ ባለስንኝ ይመስላል፤ እንዲያውም መነባንብ ሊያቀርብ ብቻ መድረክ የወጣ አይመስልም፤ መድረክ ሲይዝ ይወበራል፤ ከአንደበቱ ዕኩል በድርጊት ይገልጻል…
…ቲያትርን ከሚያስወድዱ ጠባያት አንዱና ዋንኛው ከመናገር ባለፈ መግለጽ ስለሚቻል ነው፡፡ በቲያትር፤ አብርሃም አስመላሽ እነ‹‹ጋሽ ታከለ››ን ሲያቀርብ መነባንብ የሚወርድ ብቻ ሳይሆን በድርጊቱ እዚያ ውስጥ ያለቺውን የአያ ፈንቴን ልጅ ይኩልልናል፣ የአያ ፈንቴን ጅናም ዱላ ይስልልናል፤ በሽመላቸው ሲያበራዩት እንደመወብራት ይሠራራዋል፤ በተላላፊ ያወበራናል፤ አብርሃም ሀሳቡን ለፍፎ ብቻ ሳይሆን በድርጊት ገልጾ ነበር ከመድረክ የሚወርደው፤ አጀማመሩ ላይ ፊቱን ኮሶ እንደተጋተ ሰው ይጨብጣል፤ ኩርምት ይላል፤ መሃል ላይ ደግሞ የገጸ-ባሕሪያቱን ግብረ-መልስ፣ ቁጣቸውን፣ ንዝረታቸውን ያጋባል፤ ሀሳብና ውበትን፣ ጭብጥና ድርጊትን ነው አስደምጦና አስመልክቶ የሚሰናበተን።
አንድ እናጣጥም፡-
‹‹ውሃ ተወረደ፣ ይኼ የእኔ ቦንባ፤
የፊታችን ሰንበት፣ ድፍን ወሩ ገባ፤
ታዲያ ቦንባው ደርቆ፣ ጠብታ ሳንጠጣ፤
ፈረንካ ሰብሳቢው፣ ወሩን ቆጥሮ መጣ፤
መቼስ ምን ይኮናል፣ ወር አልሰራም ብለው፣ አያልፉት በቀሪ፤
እኔው ግብር ከፋይ፣ ለእነሱ ቆጣሪ፤
ብዬ ግብሩን ልከፍል፣ አውጥቼ ብሰጠው፤
ዘጠና ብር አለ፣ አወይ ያላየ ሰው!
ጠብታ ታሕል ውሃ፣ ለአመል አልወረደ፤
ሰውን በቦንባው ውስጥ፣ ያሳፈረው የለ፣ አጓጉዞት የሄደ፤
አስመርምር አሉኝ - እንደዘላበደ፤
ለእኔ አይደል ለእነሱ፣ ግቢዬ መገተሩ፤
ይኼን ያህል ቀርቷል፣ ሲል ለመናገሩ፤
ለምን ይሆን ይሆን፣ የእኔ ማስመርመሩ?
ሊከፍሉኝ ሲገባ፣ ግቢዬ ቆሞ ውሎ ለማደሩ፤
ተምገብርበት - ለቤቱም ለአፈሩ፤
የደላው አሉ፣ አሉ፤
እንደሚያወጣ ሁሉ፣ የባላንጣውን ተዝካር፤
ያጠብኩ፣ የጠጣሁትን ለእነሱ ለሚነግር፤
ሳተ ቀባዠረ፣ ደግሞ እኔ ላስመርምር?
ለምንስ አይስት፣ ለምን አይቀባዥር?
እንኳን ሰው የሰራው፣ ቆጣሪ ይቅርና፤
ሰውስ ያለ ውሃ፣ አንድ ወር ይቆይ ነበር?
ያለ ውሃ መቆም፣ እንደው ቢሰለቸው፤
የሐምሌን ወር ዝናብ፣ መዝግቦት ይሆናል፣ ተቀድቷል ያላቸው፤››
(ከላይ የተጠቀሱ የተሳሳቱ የሚመስሉ፣ ነገር ግን ቀዬኛ አባባል የታከለባቸው ቃላትና ሐረጋቶች የራሱ የአብርሃም ሥራዎች ናቸው፤ በአጠቃላይ በስህተት ሳይሆን የገጠሩን የአገራችንን ክፍል አወራር/አነጋገር እንዲመስሉ የታለሙ ናቸው፤)
ለኮሜዲ ያደላ መነባንብ ነው ይኼ፤ ያኔ የተባለ፤ አሁን ላይ እየሆነ ያለ፤ በቀልድ የተለወሰ መረር ያለ ሀሳብ ነው፡፡ በዚህ መነባንብ አብርሃም ማኅበረሰባዊ ችግርን ነው የሚያስተላልፈው፤ በቸልተኝነት የሚሠራውን/ የሚደርሰውን አገልግሎት ያብጠለጥላል፤ ጨዋታ መሳይ ገላጭ ሐረጋትን፣ አስቂኝ ቃላትን፣ ፌዝ የሚመስሉ ስንኞችን አካትቶ ቢያቀርብም መረር ያለ ሐቅ በውስጡ የያዘ ሀሳብ መሆኑን መካድ ዘበት ነው፡፡ የአብርሃም አቀራረብ ግን በቀዬኛ፣ በገጠር ቋንቋ፣ በቀልድ መልክ ስለቀረበ ነገሩን አለዘበው እንጂ ጉዳዩስ መዝማዥ ነው።
በኮሜዲ በኩል ደግሞ የሠራቸው ሥራዎች ማኅበረሰባዊ ትችትና ቁጠባ ላይ ያተኮሩ ናቸው፤ በከንቱ የሚባክን ነገር ሲያንገፈግፈው እናስተውላለን፤ በሥመ ከተምቼነት፣ በመዋብና በመጌጥ ሰበብ፣ በዘመናዊነት…ወዘተ. የምናባክናቸውን ይነቅፋል፤ የሕዝብ አገልግሎቶች መጓተትና ያለመዘመን፣ ከዚያም አልፎ አገልግሎቱን ያላማከለ ክፍያ መጠየቁ ያበሽቀዋል፤ ይኼንንና ሌሎች የሕዝብ እና የመንግሥት እንከኖችን ይተቻል። በመሽቀርቀር ሰበብ ስንኮሰምን ያሳያል፤ በመዘመን ፍጆታ ስንንከረፈፍ ያትታል፤ የሚተችበት ቋንቋ ደግሞ የከተማው መሠረት የሆነው የባላገሩ ቋንቋና ዘይቤ ነው፤ ሀሳቦቹን ከሚኖርበት ማኅበረሰብ እና ከገጠሩ ክፍል ያነሳና በገጠሪኛ አባባል ያቀርባል።
ኮሜዲን በተመለከተ፣ Peter (2006) የተባለ ጥናት አቅራቢ ‹‹On the Problem of the Comic: A Philosophical Study on the Origins of Laughter›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ዳሰሳዊ መጣጥፍ፣ ኮሜዲ ማኅበረ-ባሕልን ሳይለቅቅ ለአድማጭ ተመልካች የሚደርስ ጉዳይ መሆኑን አውስቷል፤ አንድ የሚገዛ አባባል ከመጣጥፉ ያክላል ይኼ ጸሐፊ፡- ‹‹The physical object must never appear more credible than, or even distinct from, the mental one.›› በማለት የኮሜዲን ማረፊያ አስቀምጧል።
ኮሜዲ መረን መንካት አይጠበቅበትም ከሚሉ ወገኖች ነኝ፤ ቀልድ፣ ጨዋታ፣ ማሳሳቅ፣ ማዝናናት ወግ አላቸው፤ ቅጥ አላቸው፤ የሰውን ልጅ ሰብዕና የሚነኩ ቀልዶች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ያመዝናል፡፡ በአሁን ወቅት በአብዛኛው ብሔር ተኮር፣ ደረቅ ፖለቲካ፣ ወሲብ ነክ እና ሌሎች የሚያሸማቅቁ ጉዳዮች ናቸው በኮሜዲ መልክ እየቀረቡ ያሉት፤ የማይነካ ነገር በመንካት ግርምት መፍጠር፣ በሃፍረት ማስሳቅ ብቻ አይደለም መኮመክ ማለት…
…በርካቶቹ ኮሜዲዎች እየሳቅን ማሰብ እንድንችል፣ እንድናሰላስል የሚጋብዙን አይመስለኝም። ኮሜዲ ለሳቅ ፍጆታ ብቻ ሳይደርስ፣ የኖርከውን መልሶ ሳይደግምልህ ትምህርት ሊሰጥህ ይችላል። ኮሜዲ ለመመራመር የሚጋብዝ መሆን አለበት፤ ኮሜዲያን የወሲብ ፍላጎቱን፣ የፖለቲካ ጥማቱን፣ የብሄር ነክ ፌዙን ብቻ አጋብቶብን መሄድ የለበትም፤ ኮሜዲ በሀሳብ መኮርኮር መቻል ነው፤ ኮሜዲ የንባብ፣ የትዝብት፣ የውይይት እና የማሰላሰል ውጤት መሆን አለበት።
አብርሃም በአንድ ንግግሩ ውስጥ ሥነ-ቃል ሕመምን አካሚ፣ አገርን አስወዳጅ፣ ሰውን አስፈቃሪ ነው፤ ይለናል፡፡ ሀሳቦቹን የሚገልጽበት መንገድ ሥነ-ቃል መር ነው፤ ከውበትም ከሀሳብም ያልጎደሉ መነባንቦችን፣ ኮሜዲዎችን፣ ግጥሞችን ሰጥቶናል፤ አብርሃም ተራ ቧልት ላይ ሙጥኝ ያለ አይደለም፤ የሚያነሳው ሀሳብ አሁን ተሰምቶ ወዲያው የሚረሳ አይደለም፤ ከሃያ ዓመት በፊት ያቀረባቸው መነባንቦችና ኮሜዲዎች ዛሬ ድረስ ተወዳጅ ሆነው ይኖራሉ፤ አሁን ላይ እየሆኑ የሚገኙ በአብርሃም የተባሉ ጉዳዮችም አሉ…
…ምነው ታዲያ አብርሃምን የመሰለ ባለ ብዙ ተሰጥኦና ችሎታ ማፍራት ተሳነን? ኮሜዲያችን፣ ግጥማችን፣ መነባንባችን ውሉን የጠበቀ ነው? ኮሜዲያችን ከማሰላሰል ይልቅ ስድነታችንን የሚገልጥ አይደለምን? የሚቀርብልን ኮሜዲ አንድም ከኮሚከኛው የችሎታ ማጣትና ግብረ-ገብ ሊቀሽም ሲችል፣ በአድማጮቹ በኩል ደግሞ ያለንበትን የማጣጣም ደረጃ፣ የልኬት እና የብየና ይትባሃል ቅልብጭ አድርጎ ያሳያል…
…መረን የሚነኩ ኮሚከኞችን ባሽሞነሞንኗቸው ቁጥር ችሎታ ያላቸው ገሸሽ እያሉ ሄዱ ማለት ነው፡፡ ሀሳብ ያለው ኮሜዲያን ማፍራት ስንችል ሀሳባችንን ነጥቆ ለራሳችን የሚያቀርበውን፣ በቁስላችን የሚሳለቀውን፣ የገላ ጥማቱን የሚነግረንን ነው የምንሾም፣ የምንሸልመው፡፡ አብርሃምን አድንቀን ስናበቃ ለእሱ የምትሆን ኩርማን ስፍራ አኑረናል? ምን ብለንለት እናውቃለን? ከዓይናችን ስለ አብርሃም የፈነጠቅናት ጥርኝ ታህል እንባ አለች ይሆን? ታዲያ የነበረ፣ የለፋ ካልተከበረ አዳዲሱን እንዴት እናወጣለን?
ከአዘጋጁ
ዮናስ ታምሩ ገብሬ በእንግልዚኛ ቋንቋ ማስተማር /ELT/ የፒ.ኤች.ዲ. ተማሪ ሲሆን፣ በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የእንግልዚኛ ቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህር ነው፤ ሁለት ሥነ-ጽሑፋዊ መጻሕፍትን በግል፣ አንድ ደግሞ በጋራ ለማሳተም በቅቷል፤ ከዚህ በተጨማሪ የአንደኛና የስምንተኛ ክፍል የእንግልዚኛ ቋንቋ አጋዥ መጻሕፍትን አዘጋጅቷል፡፡ እነዚህን መጻሕፍት የምትፈልጉ በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. በኩል ማግኘት ትችላላችሁ።

 

Read 161 times