ላይሰናስል ሳዳውር፤
ላይጠረቃ ሳጋብስ፤
አለሁ እንዳጋሰስ።
ላይከትም ከአቦል ጀምሬ፣
በረካ አልባ ቡን ሳንቃርር፣
የማይፈፀም ሩጫ ገጥሜ፣
በባእዳን ውርጭ ጠይሜ፣
ስኳትን ቅስሜን ቀልጥሜ፣
“ቃል” ላይወጣኝ ተለጉሜ፣
“ኖሯል” ካልሽው ፥ ይኸው አለሁ።
የቅኔ ቆሌዬ በኖ፤
ዲዳነት ቋንቋዬ ሆኖ፤
ደስታ ጣእሙ ጠፍቶ፤
በአልጫ ኑሮ ተተክቶ፤
ከተማ ሳለሁ ድብርት፤
ከአሸን መሃል ብቸኝነት፤
አየሽ ጉዴን የኔ እናት!
ነጠላ ነብሴ ጤዛሽን ሲሻ፣
ሐሞቴ በጥምሽ ሲደብን፥
አለመጣራትሽ ይነደኛል፤
ዝምታሽ ያበሳጨኛል፤
ለምን ፥ ግን ለምን ይለኛል፤
ልቀጣሽ ፥ ልቆጣሽ ወጥናለሁ፣
ቀን ያማይወልድ ፥ ቃል አሰናዳለሁ፤
ኩርማን ምናቤን አዋክቤ፣
ቃል ከሃሳብ አናብቤ፣
የምትጎጂበትን ባልጩት ጠርቤ፣
የምወግርበት ደንግያ ፡ ለስድቤ፣
አጫለሁ ፥ እሰደራለሁ፤
አፌን ከፍቼ አንቺን ልቆጣ፣
የብሶትን ትንፋግ ፡ ጮኬ ላስወጣ፣
የቃላት ሳማ ቀነጥባለሁ፤
ጭካኔሽን ልዘረዝር፥
ስንክሳሬን አዘጋጃለሁ፤
ንጋት ጠብቅና ቀና እላለሁ፤
ማልጄ ወደ ምስራቅ አያለሁ፤
ከማትጠፊበት አማትራለሁ፤
ያኔ ትወጫለሽ፤
ጨለማን ገሰሽ ትፈነጥቂያለሽ፤
ባየሁሽ ፥ ባየሽኝ ግዜ. . . .
የወጠንኩትን ፥ ቃል ጥያቄዬን ዘነጋዋለሁ፤
ሁሉ ይጠፋና ትሁት ሆናለሁ፤
ሳይሽ ፥ ሳይሽ... ውላለሁ፤
በምትሄጂበት እከተላለሁ።
(ያሬድ ይልማ)
Published in
የግጥም ጥግ