Monday, 25 November 2024 08:24

‘ግራው ከያኒ’

Written by  የአብሥራ አድነው
Rate this item
(3 votes)

ማዕረግ ልኩ. . . . . ያ እንኳን በፊደል ጥርሱን ‘ሚፍቀው. . . . . . ሲያስነጥስ የፍልስፍና ፍንጥርጣሪዎች ከአፉ የሚፈናጠሩት. . . . እሱ ልጅ ወለደ አሉ። አሁን ለ’ርሱ ልጅ ምን ያደርግለታል? ራሱ እንኳን መኖር አለመኖሩን እርግጠኛ ያልኾነ ባተሌ፤ መኖርን የሚከትብበት ሌጣ ጨቅላ ተጎታች አድርጎ ማምጣት ነበረበት? ወይ ማዕረግ! ‘ርሱ ግራ፥ ምርጫው ግራ፥ ንግግሩ ግራ፥ ነገረ ስራው ኹሉ ግራ። የማን ግራ ነው ግን? የእግዜር ግራ? የሰው ግራ? እንጃ ግን ‘ግራ’ ነው።
አርብ።
የሚኖርበት ጎጆ ቀዝቃዛ ነው። ሚስቱ እንደ ዕንቁ አታበራም። ቅንጡ የቤት ዕቃዎች የሏቸውም። ዘናጭ አይደለም። ብዙ ጊዜ ድምጻቸው አይሰማም። አንዴ ለመጻፍ ከተቀመጠ ቀና አይልም፤ እንዳቀረቀረ ውሎ ያድራል፡፡ ሚስቱ የሚበላውንና የሚጠጣውን በተቀመጠበት ታመጣለታለች፤ እጆቿን እየሳመ ተቀብሎ በሩን ዘግታለት እስክትወጣ በስስት ዓይን ይሸኛታል። የጽሑፎቹ የመጀመሪያ አንባቢ እሷው ነች። እይታዋን ልክ እንደ ስዕሎቿ ኹሉ ይወደዋል፤ አንድ ኹለቴ ጽፎ የጨረሰው ላይ ቀጥላ ጽፋ አስደምማዋለች። ቤታቸው ላይ የተሰቀለ የሰርግ ፎቶ የላቸውም። ነፍሱ እስክትወጣ ይወዳታል። በአደባባይ ቀለበት ይዞ አልተንበረከከም፤ እሷም አፏን ይዛ አልተደነቀችም። ትወደዋለች። በተሽቀረቅረ አለባበስ ልቡን አላጠፋችውም። ያፈቅራታል። እንደ ሐር ወደሚለሰልስ ሕይወት አልወሰዳትም። ታፈቅረዋለች። ለመውለድ አብረው አመንትተዋል፤ ደጅ የሚያድረውን ወላጅ አልባ ልጅ፣ ከነርሱ ከሚወለደው ምንድነው የሚለየው ብለው ተብሰልስለዋል። በተጋቡ በሰባተኛ ዓመታቸው ወለዱ።
ልጅ ከተወለደ ከስምንት ወር በኋላ ደግሞ ብዕሩን አነሳ። ሲሞነጭር ዋለ። አመሻሽ ላይ ሚስቱ የሚወደውን ሻይ ይዛለት ወደ ማንበቢያ ክፍሉ ገባች፤ እየጻፈ የነበረበት ወንበር ላይ ለጠጥ ብሎ ዕንቅልፍ አሸልቦታል። ብዙ አዲስ የተጻፉ ገጾች ጠረጴዛው ላይ ተበታትኗል፥ የመጨረሻው ገጽ ላይ ዓይኗ አረፈ፤ ቀ. . .ስ ብላ አንስታው ወደ መኝታ ቤቷ ሄደች። ያስተኛችው ልጅ አጠገብ ተንጋላ ማንበብ ጀመረች።
“ልቅሶ ቤት ነጭ ጸአዳ ለብሶ እንደታደመ ሰው በኑረቴ ውስጥ ስስቅ አልያም ስደሰት ነውረኝነት ይወረኝ ጀምሯል። ጠኔያም መሀል ኩርማን ለብቻው እንደሚጎርስ ትክሻዬን ለእስክስታ መስበቅ እሳቀቃለኹ። ግን መቼ ይሆን የምንድነው? አጀብ አንዳንዱን ለፈንጠዝያ ፈጠረው! ዓይኖቹን ከተድላ ሰፈር መንቀል ያልቻለ ምንኛ ታድሏል! ሕይወት ከድግስ ቤት አልፋ የማትታየው አዱኛ ታርቆታል! ምን ሲል ዓይኔ አበሳ ማየት ቀለለው? ለምን ከሳቀ ይልቅ ያለቀሰ ሳበኝ? ማን ረግሞኝ ነው ከበላኹት እንጀራ ጀርባ ያለውን ምስጢር የማነፈንፈው? ለምን ዝም ብዬ አልኖርም? ያልበላኝን ለምን አካለኹ? ብዕሬ የዓለምን ተድላ ለመጻፍ ለምን ይለግምብኛል? ደስተኞች አሸን ናቸው፤ ጨዋታቸው ለምን አይጠራኝም?
“ሰርክ አጉረምራሚ ዓረፍተ ነገር መሰደር፤ አልቃሻ ቃላት መቀመር ይታክታል። ብርሃንን ማንቆላጳጰስ ይታሰበኛል፤ ግን የት ያየኹትን? ተስፋን ከታቢ መኾን ጠልቼ አይደለም፤ ከየት አባቴ ላምጣው ጃል? ፈጣሪ ሰውን በወራት መስሎ የሚፈጥር ከኾነ እንግዲህ እኔ ሐምሌ ነኝ- እኝኝ ዘላለም። ጭጋግ የወረሰኝ ወድጄ ሳይኾን እውነት ጨለምተኛ ያደረገኝ የሰው ሐምሌ ነኝ። እንዴት? ባለፈው ለጎረቤታችን ትዕግስት ምዕራብ አፍሪካ ለንግድ የሚመላለሰው እጮኛዋ ቀለበት አጠለቀላት - አበጀ። ማታውኑ ስትክለፈለፍ መጥታ ቀለበቱን አሳየችን። እጅግ የሚያምር ነጭ ወርቅ ነው፤ አደነቅኹላት። “ከኮንጎ ይዞልኝ መጥቶ ነው።” አለችን. . . . ምላሽ ለመስጠት ዘገየኹ. . . . . እ’ሷን እና ሚስቴን እዛው አስቀምጬ ዐሳቤ ነጎደ። ወርቋ እንዲህ ሳይሽሞነሞን በፊት የኾነ የኮንጎ ጫካ ውስጥ፤ ትንንሽ እጆቹ ያልጠና ልጅ መሬት እየቆፈረ፤ አፈር እያንጓለለ፤ በትንንሽ ጣቶቹ አንኳር እየፈለገ በአግባብ እህል ሳይበላ ዋለ። ቆፍሮ ሲያወጣ የዋለውን በአፈር የተለወሰ ወርቅ ተቀብለው ሆድ ዕቃውን ገልብጠው መፈተሽ የሚያምራቸው ካቦዎች፤ መለመላውን አቁመው ከፈተሹት በኋላ ጥቂት ሳንቲሞች እጁ ላይ አፍስሰው ሸኙት። ቀለበቱ ላይ ‘ርሷ የእጮኛዋ አሻራ ይታያታል፤ እኔ የማላውቀው የኮንጎ ሕጻን አሻራ ይከሰትልኛል - ላይኾንም ይችላል’ኮ፤ ግን ግን ሊኾንም ይችላል ደግሞ።
መቼ እንፈወሳለን? 160 ሚሊዮን ሕጻናት በዓለም አቀፍ ዙርያ ጉልበታቸው ይበዘበዛል፥ ማለትም ዓለም ላይ ካለ አስር ሕጻን አንዱ በሕገ ወጥ መንገድ ለጉልበት ብዝበዛ ይዳረጋል። አዋቂ ግን እንዴት ያስጠላል? ‘ሰው’ ግን መቼ ነው ሰው የሚኾነው? ቁመታቸው አሰሪዎቹ ታፋ ጋር የማይደርስን አቅም አልባ ነፍስ ምን ጋኔን ቢያገኛቸው ለጥጥ እርሻ ተመኙት? ትንንሽ እጆቻቸው አያሳዝኑም? የዓይናቸው ፍጹም ንጣት፥ የሚነበብበት ረዳት አልባነት አንጀታቸውን አያላውሰውም? ከጉልበታቸው እስከ ተረከዛቸው አጭር መኾኑ አያንሰፈስፋቸውም? ምንድነው የኾንነው? ሐይማኖትና ፍልስፍና ያልጠገነው ስብራታችን ተስፋው ከወዴት ነው? ሰው ራሱን ሌላኛው ሰው ውስጥ ማየት ከተሳነው የትኛው ብትርስ ወደ ቀናው መንገድ ይመራዋል?
ያው ምን ማድረግ ይቻላል መተው እንጂ! መተው ማለት? የትኛው? የኛ ልጆች ሲኾኑ መዝገበ ቃላችን ላይ የሌለው መተው? አንድንም ወይ? የማናውቀውን ብላቴና ተሟግተንለት አንድንም? ለጋ እጅ የሰራውን ለመብላት ተጠይፈን አንድንም? የዘመድ ልጅ ከገጠር አምጥተን መበደል አቁመን አንድንም? ንጹሑን በሐሰት ዘብጥያ ጥለን ልጆቹን ከመበተን ተቆጥበን አንድንም ወይ? የአስራ ስድስት ዓመት ድንግል ታዳጊ ጭፈራ ቤት ማጫረት አቁመን ከሰብዓዊነት አንታረቅም ወይ? ስካራችን መቼ ይለቀናል? ድንጋይ ልባችን መቼ በሰው ፍቅር ይሸነፋል? ሰው ለመኾን አይነጋም?”
አንብባው ስትጨርስ ዓይኖቿ በዕንባ ተሞሉ።
“ሌቦ አምጪ ወረቀቴን!” መቼ መጥቶ ጎኗ እንደተገተረ አላየችውም ነበር።
“የኔ ማዕረግ?”
“ወዬ”
“የኔ ሰው”
“ወይዬ”
“ እስክሞት እቀፈኝ?”
አጠገቧ መጥቶ በቀስታ ተቀመጠ፤ ተጠመጠመችበት። ዕንባዋ ደረቱን ሲያርሰው ይሰማዋል። ‘ርሱ ይጽፋል፤ ብዕሩ ነፍሷን ይነካል። ብሩሿን ታነሳለች፤ የጋራ እውነታቸውን ትስላለች፤ ረዥም ሰዓት ስዕሎቿ ላይ ፈዝዞ ይቆያል። ሕይወትን በዝምታ የሚያርሱ ጥማድ ነፍሶች።
ቅዳሜ።
የሚካኤል ዝክር አያ አካሉ ልጅ ልከው አስጠሩት። ቤቱ ተጋድሞ እያነበበ ከነበረበት እየተወናገረ ወጣ። የሰፈሩ አድባር የሚባሉ ሰዎች ኹሉ አያ አካሉ ቤት ተኮልኩለው ጠላ እየተጎነጩ የሞቀ ጨዋታ ይዘዋል። ማዕረግ “ስብስቦች ደህና ዋላችኹ?” ብሎ ተቀላቀለ፤ ስለ ባድመ ጦርነት የጦፈ ክርከር ይዘው ነበር፤ ማንም ከቁብ ቆጥሮ ሰላምታውን አልመለሰለትም። ቤቱ ደስስስስ የሚል ድባብ አድብቶበታል፥ ቄጤማ ተጎዝጉዞ በዕጣን ታፍኖ ቡና እየተፈላ ነው። የአያ አካሉ ሚስት ላሎ የጎደለ ብርጭቆ እያየች ትሞላለች፥ ዳቦና ቆሎ ሰዎቹ ፊት “በሞቴ” እያለች በፈገግታ ተሞልታ ታስቀምጣለች። መስኮቱ ጥግ የቅዱስ ሚካኤል ስዕል በትልቁ ስስ ነጭ ጨርቅ ተሸፍኖ ተቀምጧል። ለአፍታ በዝምታ ካስተዋላቸው በኋላ ማዕረግ ዓይኖቹን ስዕሉ ላይ እንደተከለ ጉሮሮውን ጠራርጎ “እኔ ‘ምለው” ብሎ ንግግር ጀመረ። ቤቱ ኹሉ ዓይኑን ወደ ‘ርሱ ወረወረ።
“ሰይፍ የሌለው ሚካኤል የለም እንዴ? ወይ ለምን አይጥለውም?” የአያ አካሉ ሚስት ቆሎ የያዘችበት ወስኮባይ ከእጇ ወደቀ፤ ማሕበርተኛው ሚካኤል ሰይፉን እነርሱ ላይ እንዳይጥለው ሰጋ - ነፍሱ በውስጡ ሟሸሸ። አባ በዕደ ማርያም በተቀመጡበት ሦስት ጊዜ አማተቡ። እንደምንም አፋቸውን አላቅቀው ንግግር ጀመሩ።
“አበስኩ ገበርኩ! ልጅ ማዕረግ ምን ነካህ? እኩዮችህ አለቁ?”
“አባ ጥያቄ ነው እኮ፤ ሰላማዊው ሚካኤል የለም ወይ ማለት ምን ክፋት አለው?”
“አንተ ሰይጣን አይደለህ ምን አሰጋህ ሰይፍ ቢይዝ ባይዝ?”
“አሃ ሊጠብቀኝ ነው እንዴ የያዘው?”
“ሊቀ መልዓኩ ድረስ! ኧረ ማዕረግ ተው!”
“ምን አጠፋኹ? እኔ ፈሪ ነኝ፤ የጦር መሳርያ አልወድም፤ ፈራኹ እንዴት አድርጌ ልቅረበው? በዛ ላይ አሁን ወልጃለኹ፤ ልጄን ከፍ ሲል የት ልላከው? ጎረቤት አስፈሪ ስዕለ አድኅኖዎች ይመለከታል፤ ትምህርት ቤት አድዋን ያስተምሩብኛል፤ በየመንገዱ ጋሻና ጦር የተሳለበት አጥር ሲያይ ያድጋል፤ ‘ወንጌል ሰባኪዎች’ ጋር ብልከው ካራቴ ያሳዩብኛል፤ እኔ የት ልሒድ?”
አባ ትካዜ ገብቷቸው ትኩር ብለው እያዩት፤
“ልጄ ልብህ እውነትና ሰላምን ከፈለገ በጠበቅህበት መንገድ አይኹን እንጂ አታጣውም። ለአንዳንዱ ነገር ጊዜ መስጠት መልካም ነው፤ ባለ ሰይፉን ሚካኤል ያስነበበህ መጽሐፍ፣ በግፍ የተሰቀለውን መድኃኒታችንን ክርስቶስንም አስነብቦሃል። ተግተህ ካልመረመርኸው፥ ከፊትህ ያሉትን ጠይቀህ ለማወቅ ጉጉት ከሌለኽ ዕዳው ገብስ ነው። ልጄ መጠየቅ፥ መመርመር ጥሩ ነው።”
“እርሶ አሉ!” ለአፍታ ቤቱ ረጭ አለ። አዲስ ፊቶች ማሕበር ቤቱን ሲቀላቀሉ የቀድሞ ጨዋታ ዳግም ተጀመረ። ማዕረግ ተሰናብቶ ወጣ። እጆቹን ወደ ኋላ አጣምሮ በቀስታ ወደ ቤቱ አዘገመ። ያን ምሽት የጽሑፍ ቆሌ ራቀው፤ገብቶ ልጁን ሲያጫውት አመሸ፤ ሚስቱን አቅፎ ተኛ።
እሑድ
ጎሕ ሳይቀድድ እንቅልፉን ጨርሶ ነቃ፤ በቀስታ ከአልጋው ወርዶ ወደ ማንበቢያ ክፍሉ አመራ። ጽሑፉን ካቆመበት ሊቀጥል ብዕሩን አነሳ። ከመጨረሻው ዓረፍተ ነገር በኋላ የሚስቱን እጅ ጽሑፍ አስተዋለ።
“ስካራችን መቼ ይለቀናል? ድንጋይ ልባችን መቼ በሰው ፍቅር ይሸነፋል? ሰው ለመኾን አይነጋም? በውጫሌ ስምምነት መታለላችንን እንደ አሳፋሪ ታሪክ መቁጠራችንን መለስ ብለን ለማየት ድፍረቱ ሳይኖረን ለሰብዓዊነት ትንሳዔ ከወዴት ይገኛል? ንሕጽና እና ቅንነት ከመታለል በላይ ካሳፈሩን ደዌያችን እየጠና ወይስ እየተሻለን ይሄዳል? ጥርጣሬ አልባ እምነት ነበረን - ሌላኛው ቂልነት ቢለውም። አቡነ ጴጥሮስ ከሐውልት በላይ ካልኾኑ ሰው የመኾን ስብራቱ መቼ ጠገግ ይላል? ትንሳዔ ያለው ያታለለንን ዓይን በርሕራሔ መመልከት መጀመር ውስጥ ነው፥ ፈውሳችን ያለው ገዳያችን ያበሰለውን እያወቁ አብሮ በመብላት ውስጥ ነው። ሰንበት- ዕረፍት- ትንሳዔ ማለት ያኔ ነው፥ አልያም ኹሌም አርብ ላይ እንቆያለን፤ ስቅለት ላይ።” ሚስቱ በነዚህ ቃላት ጽሑፉን ዘግታው ነበር።

 

 

Read 241 times