በአደራ ከቆመበት የመኪና መሸጫ ግቢ ውስጥ በጥበቃ ሰራተኛው አማካኝነት የተሰረቀው መኪና ከአንድ አመት በኋላ ተገኘ።
ጥበቃው መኪናውን ለመስረቅ አስቦና አልሞ፣ ሥራ ፈላጊ መስሎ በመኪና መሸጫው መቀጠሩንም አምኗል።
ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም፣ ለሰኔ 16 አጥቢያ፣ በአዲስ አበባ ቡልጋሪያ አካባቢ ከሚገኘው ታዋቂ የመኪና መሸጫ ግቢ ውስጥ ተሰርቆ የነበረው፣ 2022 Rava 4 መኪና ህዳር 18 ቀን 2017 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ ተገኝቷል።
በተለያዩ ስሞች የሚንቀሳቀሰውና በመኪና መሸጫው ጌታነህ ብርሃን በሚል ስም የተመዘገበው ተጠርጣሪው ቀደም ብሎ ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ ወደ መኪና መሸጫው በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጥሮ የገባው መኪናውን ለመስረቅ በማሰብ መሆኑን የእምነት ክህደት ቃሉን በሰጠበት ወቅት ተናግሯል።
ተጠርጣሪው እስካሁን በዚህ አይነት ከባድ የስርቆት ወንጀል ከ80 በላይ መኪኖችን የሰረቀ ሲሆን፤ በተመሳሳይ ቡልጋሪያ አካባቢ በሚገኘው መኪና መሸጫ ውስጥ አብረውት ይሰሩ የነበሩ የጥበቃ ሰራተኞችን በጠላ ውስጥ አደንዛዥ መድሃኒት በመጨመርና እንዲጠጡ በማድረግ መኪናውን እንደሰረቀ ታውቋል።
በዚህም ከአንድ አመት ከስድስት ወር የፀጥታ አካላት ፍለጋና ርብርብ በኋላ፣ የተሰረቀው መኪና ሻንሲ ቁጥሩ ተቀይሮ ተገኝቷል።
መኪና ሻጮቹ በጓደኝነት ለመተባበር በቅን ልቦና በማሰብ ግቢያቸው ውስጥ ያስቀመጡት መኪና ጣጣ ይዞባቸው መምጣቱ ቢያሳዝናቸውም፣ በፖሊስ አባላትና በመኪና ሻጮቹ ጥረት በስተመጨረሻ የመኪናው መገኘት እንዳስደሰታቸው ገልጸው፣ ፖሊስን አመስግነዋል።