አንድ ዛፍ የሚቆርጥ ጅል ሰው ነበረ፡፡
የሚቆርጠው ቅርንጫፍ ላይ ሆኖ ነው ዛፉን የሚቆርፈጠው፡፡፡ ይህን ያዩ አንድ አዛውንት፤
“አንተ ሰው ምን እያደረግህ ነው?”
“ለቤት መስሪያ እንጨት አንሶኝ ዛፍ እየቆረጥኩ ነው፡፡”
“አያ ያንተስ ቤት አልተሰራም ተወው” ብለውት መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡
ሰውዬው ከነከነውና ከዛፉ ወርዶ እየሮጠ ተከተላቸውና፤
“ለምንድነው ያንተ ቤት አይሰራም ያሉኝ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
“እየቆረጥክ የነበረውን እንጨትኮ የተቀመጥክበትን ነው፡፡ አብረህ ስለምትወድቅ ቤትህን ማን ይሰራዋል ብዬ ነው፡፡”
ሰውየው እኚህ ሰው ሞኝ ናቸው ብሎ መጥረቢያውን ወደተወበት ዛፍ ተመለሰና መቁረጡን ቀጠለ፡፡
ብዙም ሳይቆይ ከነእንጨቱ መሬት ወድቆ ተሰበረ፡፡
አዛውንቱ ሲመለሱ መሬት ላይ ወድቆ አገኙት፡፡
“እንዳልኩት መሬት ወድቀህ አገኘሁህ፡፡ የሰው ምክር አልሰማ ብለህኮ ነው” አሉት፡፡
ሰውዬውም፤
“አልተጎዳሁም፡፡ ትንሽ ግራ እግሬ ላይ ስብራት ነው የደረሰብኝ፡፡ ይልቁንም አንድ እርዳታ ቢያደርጉልኝ ጥሩ ነበር፡፡”
“ምን ልርዳህ?”
“እባክዎ የወደፊት እጣ ፈንታዬን ይንገሩኝ” አለና እግራቸውን ላይ ወደቀ፡፡
አዛውንቱም፤
“አህያ ሦስት ጊዜ ካስነጠሰ ትሞታለህ” አሉት፡፡ ስለትንበያቸው አመሰግኗቸው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ቤቱ ደርሶ እከብት ጋጣ ጋ እንደቆመ አህያው አንድ ጊዜ አስነጠሰ፡፡
“ሰውዬው ያሉኝ ነገር ሊደርስብኝ ይሆን እንዴ?” ብሎ ስጋት ገባውና፣ አህያውን ሊያስነጥሰው ይችላል ያለውን የሚሸት ነገር ሁሉ ከአህያው አካባቢ ለማራቅ ሲያጓጉዝ አመሸ፡፡
ወደ እኩለ ሌሊት ላይ ግን አህያው ለሁለተኛ ጊዜ አስነጠሰ፡፡
ሰውዬው በጣም ተጨነቀ፡፡ ስለዚህ አህያ በሦስተኛ ጊዜ እንዳያስነጥስ ዘዴ መፈለግ ጀመረ፡፡ አንድ ዘዴ መጣለት፡፡ የአህያውን አፍንጫ በድንጋይ መድፈን፡፡
ድንጋይ አመጣና ምንም ቦታ ሳያስተርፍ የአህያውን አፍንጫ ደፈነው፡፡
በሰራው ስራ ተኩራርቶ አህያው ፊት ቆሞ ሳለ፣ አህያው ለመተንፈስ በመቸገር ጭምር አንዴ አምጦ ክፉኛ አስነጠሰ፡፡ ባፍንጫው የተጠቀጠቀው ድንጋይ ተፈናጥሮ ወጣና የሰውዬውን ደረት አጎነው፡፡ ሰውዬው ወደ ኋላው ተፈነቸረና ሞተ፡፡
***
በገዛ እጅ የገዛ ራስን መጥፊያ ማመቻቸት የሞኝነት ሁሉ ሞኝነት ነው፡፡ የሚነገረንን ምክር ልብ ብሎ መስማት ዋና ቁም ነገር ነው፡፡ ይደርሳል ተብሎ የሚታሰብን ችግር ለመፍታት ሌላ ችግር በራስ ላይ መጋበዝ የጥፋት ሁሉ ጥፋት ነው፡፡ ችግሮችን የባሰ ያወሳስባልና፡፡ አህያዋ እንዳታስነጥስ ብሎ ማስነጠሸዋን ለመዝጋት መሞከር የዋህነት ነው፡፡
በሀገራችን ካየነው የረዥም ጊዜ የትግል ጉዞ ሦስት ባህርያት ጎልተው ይታያሉ፡፡ አንደኛው ትግል የተመሰረተበትንና የቆመበትን መርህ እንደ ዛፍ ቆራጩ ላይ ላይ ተቀምጦ ገዝግዞ መቁረጥና አብሮ መንኮታኮት ነው፡፡ አደርገዋለሁ ያሉትን ሳያደርጉ በአጭር መቀጨት፡፡ ሩቅ አስቦ ቅርብ ማደር፡፡ ቶሎ ተስፋ መቁረጥ፡፡ ጨለማ ጨለማውን ብቻ ማየት፡፡ ሁለተኛው ዘላቂ ጎዳና ላይ ከወጡ በኋላ ከተለዋዋጩ የዓለም ሁኔታና ነፀብራቁ ከሆነው የሀገር ሁኔታ ጋር በአዲስ መልክ ራስን ለመለወጥና ለመጠንከር ዘዝግጁ አለመሆን ነው፡፡ ሦስተኛው ሌላውን በልጠው ካልታዩ ለመጠንከር ዝግጁ አለመሆን ነው፡፡፡ የራስ ማደግ አልታይ ማለት ነው፡፡ ይህ እውን ይሆን ዘንድ ሌላውን እስከመጥለፍ አልፎም እስከ ማጥፋት መሄድ ነው፡፡ ክፉ አባዜ፡፡
አንድ የሀገራችን ፖለቲከኛና ምሁር በፃፈው አንድ መጽሐፍ ላይ እንደጠቀሰው፤ “ጊዜው የጨለመ ይመስላል እንጂ የረጅሙ ጊዜ የኢትዮጵያ ተስፋ ብሩህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድ ድምጽ ሆኖ በነፃነት ብቻ ነው መኖር የምንፈልገው፤ በፍርሃት ማህበረሰብ ውስጥ መኖር በቅቶኛ ብሏል፡፡ አንዴ ይህን የወሰነ ህዝብ በጉልበት ተመልሶ የፍርሃት ጨለማ ውስጥ አይኖርም፡፡ ትልቁ የአሁን ጊዜ የፖለቲካ ሃይሎች ፈተና፣ ይህንን የረጅም ጊዜ ብሩህ ተስፋ የሚጎዱ እንዳይሆን መጠንቀቅ ነው፡ ለዚህ ነው የተቃውሞ ሀይሎ በአጭር ጊዜ በተወሰደባቸው የሀይል ርምጃ በመገፋት የቂምና የጥላቻ ጨለማ ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ያለባቸው፡፡ ይህ ማለት ጨቋኞችን ማባበል አለባቸው ማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም ማንዴላ እንዳሉት፤ በጉልበት የሌላውን ነፃነት ለመውሰድ የሚፈልጉ እነዚህ ሰዎች ራሳቸው በጥላቻና በትእቢት እስር ቤት ውስጥ የሚገኙ ናቸውና፣ ከጥላቻ ይልቅ ሀዘኔታችንን ነው ልንሰጣቸው የሚገባው፡፡ የሌሎቻችን ነፃ መውጣት እነሱንም ነፃ የሚያወጣቸው መሆኑን ሁልጊዜ ልንነግራቸው ይገባል፡፡ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ጠንካራ መንፈስ ሲኖረን እኛም ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተዘጋጀን መሆናችንን እናስመሰክራን” ይላል፡፡
ተስፋን ከጨለማ ውስጥም ቢሆን ማውጣት ይቻላል፡፡ ሆኖም ተስፋ በመጀመሪያ ከየራሳችን የልብ ብሩህነት የሚመነጭ መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ ከየራሳችን የእለት የሰርክ የህይወት ሂደት ውስጥም ጨላማና ብርሃን መኖሩን ማስተዋል ነው፡፡ እያንዳንዱ የመስተዋት ጡብ የፀሀይ ብርሃን በሌለበት ወገን ጨለማ አለው፡፡ ጡቡን ወደ ፀሀዩ ወገን ለማዞር መሞከር ነው ዋናው፡፡ ይህም ቢሆን ዋጋ ይጠይቃል፡፡ አልፎ ተርፎ መስዋዕትነትም ይጠይቃል፡፡ ይህንን እሳቤ በፖለቲካ መልኩ ስናጤነው፣ በትግል ውስጥ መቼም ቢሆን መቼ አቀበትና ቁልቁለት፣ ማሸነፍና መሸነፍ፣ መውደቅና መነሳት ሁሌም አለ፡፡ ካያያዝ ይቀደዳል፤ ካነጋገር ይፈረዳል፡፡ ትግል የስልትና የስትራቴጂ የማሕበራዊ መስተጋብርና የልምድ አጠቃቀም ግብዓት ውጤት ነው፡፡ ግትርነት፣ እልህ ቂምና አለሁ - አለሁ ባይነት ተስፋ ሳይሆን፣ ግንፍል ስሜትን፤ ፍሬያማነትን ሳይሆን መጨንገፍን ነው የሚወልደው፡፡ ሌላው ትኩረት የሚሻው ነገር የጊዜ አጠቃቀም ነው፡፡ የረዥም ጊዜ ትግል ጽናት መያዝን ይጠይቃል፡፡ ሳይታክቱ መጓዝን ይጠይቃል፡፡ የነዚህ ሁሉ መጠቅለያ የሰው ነገር መስማት ነው፡፡ የሰሙት ጥሩ ሆኖ ሲገኝ ስራ ላይ ለማዋል መድፈር ነው፡፡ ለመለወጥም ለመለወጥም (ለ ትጠብቃለች) ዝግጁ መሆን ነው፡፡ አዳዲስ ሀሳብን መቀበል ከችግር መውጣት ነው፡፡ ከህመም መፈወስ ነው፡፡ አላዋቂ ከሚስምህ አዋቂ ያስታምህ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡