Saturday, 30 November 2024 20:03

ካልታገልነው የሚጥለን ሙስና

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ሙስናን በመከላከል ተግባራት በአጠቃላይ 3,483,959,491.78 ብር ማዳን ተችሏል


ሙስና የሀገርን ህልውና በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል ትውልድን የሚያመክን የዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት የመገዳደር አቅም ያለው እየሰፋ ሲመጣ ሀገር የሚያጠፋ በግልጽ የማይታይ፣ እንደ ካንሰር ውስጥ ለውስጥ እያጠቃ የሚሄድ የሀገር እድገት ጠንቅ ነው፡፡ ሙስናና ብልሹ አሰራር ልማትን በማዳከም የሀገር ኢኮኖሚ እንዲገታ፣ የሞራልና የሥነ-ምግባር ቀውስ እንዲባባስ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዳይኖር፣ ህዝብ በመንግስትና በህግ የበላይነት ላይ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርግ አደገኛና ድንበር ዘለል ባህሪም ያለው አለም አቀፋዊ ወንጀል ነው፡፡
ሙስና ደረጃው ይለያይ እንጂ በሁሉም የዓለማችን ሀገራት የሚገኝና የሁሉም ሀገራት ተግዳሮት ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ አደገኛ ወንጀል ተጠቂ ነች፡፡
ሙስና በተስፋፋ ቁጥር የዜጎች የመኖር ህልውና አደጋ ላይ ከመውደቁም ሌላ ስርአት አልበኝነትና ህገ-ወጥነት እየተስፋፋ ይመጣል፡፡ ሙስና በጣም ጥቂት በሆኑ በከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በሚገኙ ግለሰቦች በህገ-ወጥ ደላሎችና በመንግስት መዋቅር ውስጥ በሚገኙ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የስልጣን እርከን ላይ በሚገኙና ሙያቸውን አለአግባብ በሚጠቀሙ የተማሩም ያልተማሩም ሰዎች የሚፈጸም የስርቆት ወንጀል ነው፡፡
ድርጊቱ ሲፈጸም በማይታወቅ፣ በረቀቀና በቡድን በመደራጀት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሙስና ከየትኛውም የስርቆት ወንጀል ድርጊት በተለየ ውስብስብና በቀላሉ ሊፈታ የማይችል፣ ጊዜን የሚጠይቅ ክትትል የሚያስፈልገው፡፡
ሙስና በእድሜ ከተወሰደ ማንኛውም እድሜው ከ18 አመት በላይ የሆነ ሰው ሊፈጽመው የሚችል በዘር በጾታ የማይገደብ ወንጀል ነው፡፡ ችግሩን ከስር መሰረቱ መከላከል ካልተቻለ፣ ውንብድናና ስርአት-አልበኝነት የትውልድ ተጠያቂነት ማጣትና ግዴለሽነት፣ እንዲሁም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያስከትል ችግር ይሆናል፡፡
ሙስናና ብልሹ አሠራርን ለመከላከል ሀገራት በተናጠል ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ በተጨማሪ በጋራ ለመታገል የሚያስችላቸውን ዓለም አቀፍ ስምምነት እንዲኖር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኩል ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
የሀገራችን የእድገት ማነቆ ሆኖ የሚጠቀሰውን ይህንን ወንጀል ለመከላከል መንግስት የተለያዩ የመከላከል ስራዎችን ሊሰሩ የሚችሉ መዋቅሮችን ዘርግቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሙስና እና ብልሹ አሰራር የከተማዋን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እድገት የሚጎዳ ተግባር መሆኑን በመገንዘብ፤ ከተማዋ የተያያዘችውን የእድገት ጎዳና እና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እንዲፋጠንና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እንዲቻል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ ፡፡
በተለይም የቅድመ መከላከል ስራዎችን ታሳቢ በማድረግ ውጤታማ ሊባሉ የሚችሉ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከቅድመ መከላከል ስራዎች ውስጥ አንዱ የዜጎችን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት ነው፡፡ በመሆኑም በ2017 ዓመተ ምህረት በሚከበረው አለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በተለይም ወጣቶች ሙስናና ብልሹ አሰራር በከተማዋ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት በመቀነስ ረገድ ድርሻቸውን እንዲወጡና የጸረ ሙስና ትግሉ ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻል አላማ ያለው ንቅናቄም ተጀምሯል፡፡ ንቅናቄው እንደ ሀገር አቀፍ የሚተገበርም ነው፡፡
ሙስናን መከላከል የሚቻለው የህብረተሰቡን የግንዛቤ አቅም በማሳደግ ነው፡፡ በመሆኑም በንቅናቄው በሚፈጠሩት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ሁሉም አካላት በሙስናና ብልሹ አሰራር ላይ በቂ የሆነ ግንዛቤ በማግኘት በተለይም ተቋማትን ከሙስናና ብልሹ አሰራር የጸዱ እንዲሆኑ በንቃት መከታተል፤ ዜጎች በጸረ ሙስና ትግል እራሳቸውን ዝግጁ በማድረግ ሚናቸውን መወጣት የሚያስችሉ ተግባራትን በጋራ መስራት እንዲችሉ፣ ቀጣይነት ያለው ሙስናን የመከላከል ሚና መጫወት አስፈላጊ በመሆኑ፣ ንቅናቄው በከተማ ደረጃ ተጀምሯል፡፡
የሙስና ወንጀሎች የሚባሉት ምንድናቸው?
በአደራ የተሰጠን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል፣ እምነትን ማጉደል ወይም አለመታመን፣ በጉቦ፣ በምልጃና በአድሎ ሃቅን፣ ውሳኔን ወይም ፍትህን ማዛባት ነው (Transparency International 2008)፡፡
ሙስና የመንግስትን ሥራ ሥነ-ምግባራዊ እና ህጋዊ መሠረት ባለው መመሪያና ደንብ ላይ ተመርኩዞ ማከናወን አለመቻል ነው ይለዋል፤ /የሙስና ቅኝት በኢትዮጵያ 1993/፡፡
ሙስና ለግል ወይም ለቡድን ጥቅም ሲባል ሥርዓቶችን፣ ህጎችን፣ ደንቦችን፣ አሰራሮችን፣ መርሆዎችን የመጣስ ማንኛውም ተግባር ነው (Kato, 1995)፡፡
ሙስና በግል ወይም በቡድን፣ በፖለቲካ መሪዎች ወይም በቢሮክራቶች ሥልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ፣ የህዝብን ጥቅምና ፍላጐት ለግል ጥቅም ማዋል፤ በመንግስትና በህዝብ ሃብትና ንብረት ላይ ስርቆት መፈጸም፣ ዝርፊያ ማካሄድ፣ ማጭበርበር፣ ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በፖለቲካ ወገንተኝነት፣ በጐሰኝነት፣ በኃይማኖት ትስስር ላይ ተመርኩዞ በመሥራት አድሎ መፈፀም፣ ፍትህን ማጓደልና ሥልጣንና ኃላፊነትን በህገወጥ መንገድ የጥቅም ማግኛ የማድረግ እኩይ ተግባር ነው /ኬምፔሮናልድና ሰርቦርዌል 2000/፡፡
በህዝብ የተሰጠ ሥልጣንና ኃላፊነትን አላግባብ በመጠቀም ህግና ደንብ የመጣስ እኩይ ተግባራትን ያካትታል / ቻርለስ ሳን ፎርድ 1998/፡፡
ሙስና ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ ስልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ፣ ህግና ሥርዓትን በመጣስ የግል ጥቅምን ማካበትና ሌላን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም ወይም መጉዳት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡
ሙስና መገለጫ የሆኑ ልዩ ባህሪያት አሉት፤ እነሱም፡-
በተለያዩ ዘርፎች እና በተለያየ ደረጃ ከታችኛው እርከን ጀምሮ እስከ ከፍተኛው እርከን ድረስ የሚከሰት መሆኑ ነው፡፡
የአፈጻጸሙ ሂደትና ስልት ውስብስብ መሆኑ፤
ለጉዳዩ ባለቤት ነኝ ባይ አለመኖር፤
ከፍተኛ የሙስና ተግባር የሚፈፀመው በኑሮ ደረጃቸው የተሻሉ፣ ከፍተኛ እውቀት፣ ሥልጣንና ገንዘብ ባላቸው ሰዎች መሆኑ፤
የሙስና ወንጀል በአብዛኛው ሰው ዘንድ እንደ ነውር አለመታየቱ፤
በሀገር አቀፍ ደረጃ
ብዙም የተደራጀ ዝርፊያ ያለባቸውም ተብለው በጥናት ከተለዩት 10 የአለም ሀገራት ያልተካተተችው ሀገራችን፣ ከአፍሪካ አስር የተሻለ ከሚባሉት ሀገራት አለመኖሯ ሊያሳፍረን እንደሚገባ የጠቀሱት ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ በ4ኛው የአገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በሀገራችን አሉ ብለው ከጠቀሷቸው በርካታ የብልሹ አሰራርና የሙስና ተግባራት መካከል “የተደራጀ ሙስና ማለት የገንዘብ ከአንዱ ኪስ ወደ ሌላው መግባት ብቻ ሳይሆን ከህግ ውጪ ሌሎች እንዲጠቀሙ እንዲያድጉ ማድረግም እምነትና እውነትን መዝረፍ ነው፡፡ በገበያ አለም ውስጥ የዋጋ ርካሽነት ውዱና ጥራት ያለው እቃ ተገፍቶ መናኛው እቃ ገበያውን ይቆጣጠራል፡፡ ኮንትሮባድ ይስፋፋል፤ታክስ ስወራ ይስፋፋል፤ ገቢ ይቀንሳል መሰረተ ልማት ይቆማል፤ ኢኮኖሚው ይቀየዳል፤ የድህነትና የጥፋት አዙሪቱ ይቀጥላል፡፡” በማለት ነበር ሙስናን በጽኑ ካልታገልንና በዚሁ ከቀጠልን አስሩ አስጊ ሀገራት ተርታ እንደምንሰለፍ ያለው ሁኔታ እንደሚያመላክት የገለጹት፡፡ የተቀናጀ ዘመቻና ትግል ማድረግ የሚጠይቅ ጊዜ መሆኑን ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በመግለጽ፣ በሀገራችን የጸረ-ሙስና ተቋማትን የማቋቋም አስፈላጊነትን በማመን፣ ከላይ እስከ ታች ባለ መዋቅር ሙስናና ብልሹ አሰራርን መዋጋት የሚያስችል ተቋም እንዲቋቋም እውቅና ሰጥተው ተቋማቱ ተቋቁመው ወደ ስራ መገባቱን በ4ኛው የአገር አቀፍ የጸረ ሙስና ጥምረት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ አብስረው ወደ ስራ መግባትም ተችሏል፡፡
የጸረ-ሙስና ትግል በከተማችን፡-
ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተቋማት ላይ የሚስተዋለው ብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከስራቸው ነቅሎ መቀረፍ የሚችልበትን መንገድ በጠቆሙበት የ2017 በጀት አመት የመጀመሪያ ሩብ አመት የተተገበሩ የጸረ-ሙስና ትግሎችና ወደ ፊትም እያንዳንዱ ተቋም የብልሹ አሰራርና የመልካም አስተዳደር ተግዳሮቶችን ታግሎ ለማስቀረት የጸረ ሙስና ትግሉን የማሳካትና ውጤት የማስመዝገብ ተግባራትን እንደ ጅምር ጥሩ በሚባል ደረጃ መተግበሩ፣ ለቀጣይ በጋራ ለሚተገበሩ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የመታገል ተግባራት ፈር ቀዳጅ መሆኑን፣ በአዲስ አበባ ምክር ቤት በቀረበ 1ኛ ሩብ አመት የተቋማት አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ላይ ተናግረዋል፡፡ ከ86 እጅ በላይ ከ2017 እቅድ ክንውን መነሻ ተቋማት ብልሹ አሰራርን ከመከላከል አንጻር ጥሩ በሚባል ቁመና ላይ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ ክብርት ከንቲባዋ በከተማዋ ከመሬትና መሬት ነክ ተቋማት ቴክኖሎጂን በመጠቀም፣ በሰው ሀይልና በአሰራር ያሳየነውን እድገትና በተለይ ከመልካም አስተዳደር አገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሰራርን ከማስቀረት አንጻር ተቋማት ምን አቅደው ተገበሩ የሚለው ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባና ያመጣነውን ውጤትም የሚያመላክት፣ በተቋማት አቅም የተተገበረ መሆን እንዳለበት አሳስበው ነበር፡፡ “ሁሉም፣ አካላት ተቋማቸውን ከብልሹ አሰራር ማጽዳትና ሙስና የመከላከል ስራን መስራት ይገባል” ሲሉ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሙስናንና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል እየተደረገ ያለውን የተለያየ ጥረት ተቋማዊ፣ ቀጣይነት ያለውና ውጤታማ እንዲሆነ በሚያዝያ ወር/2015 ዓ.ም የከተማዋን ስነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽንን በአዋጅ ቁጥር 75/2014 በማቋቋም ስራ እንዲጀምር ማድረግ ተችሏል፡፡
ለጸረ-ሙስና ትግሉ አጋዥ የሆኑ፣ ከ325,860 በላይ ስልጠናዎች በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ተዘጋጅተው መስጠት የተቻለ ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ በ376 ተቋማት የሥነ-ምግባርና የፀረ-ሙስና መከታተያ ክፍሎች በማቋቋም 737 አስፈፃሚዎች እንዲመደቡ ተደርጓል፡፡
በመንግስት፤ በግል ትምህርት ቤቶችና በኮሌጆች 1039 ክበባትን ማደራጃት ተችሏል፤ ለ1,826,500 ባለድርሻ አካላት በሥነ-ምግባርና ሙስና መከላከል ላይ የግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም ተሰርቷል፡፡ እንዲሁም ለ28,939 አመራሮችና፣ አስፈፃሚ አካላት ዳይሬክተሮች እና ቡድን መሪዎች የሃብት ምዝገባ ማከናወን ተችሏል፡፡
ሙስናን በመከላከል ተግባራት በአጠቃላይ 3,483,959,491.78 ብር፤ ቁሳቁሶች 403 በአይነት ጠቅላላ ንብረቶች ማዳንም ተችሏል፣ ከተጠያቂነት ጋር በተያያዘ በቀላልና ከባድ ዲሲፕሊን 2ሺህ 368፣ በህግ 830፤ ጠቅላላ ድምር 3,198 አመራርና ፈፃሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በ40 ተቋማት የሙስና ተጋላጭነት ጥናት ተሰርቶ፣ በጥናቱ የተሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው በሁለት ዙር የጥናት ትግበራ ክትትልና ግምገማን በ40ውም ተቋማት ማድረግ ተችሏል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ቀጣይነት ባለው መልኩ የጸረ-ሙስና ትግሉን ለማስቀጠል በ21ኛው አለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ንቅናቄ መነሻነት እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ከተማ በመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚስተዋለው የህዝብ እርካታ ችግር ዋነኛ መንስኤ ከሙስና ጋር የተያያዘ ነው የሚል እንድምታ አለው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2025 ሙስና ለከተማ አስተዳደሩ ልማትና መልካም አስተዳደር እንቅፋት የማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሶ ማየት የሚል ራእይ ይዞ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል፡፡ ራእይዩ እውን እንዲሆን ደግሞ የከተማችን ወጣቶች ተሳትፎ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡
ወጣቶች በሙስና መስፋፋት ዋነኛ ተጎጂዎች እንጂ ተጠቃሚዎች ባለመሆናቸው ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ ሙስና በእጅጉ የቀነሰባትና ለብልሹ አሰራር ያልተመቸች አዲስ አበባን መፍጠር አስፈላጊ ነው፡፡ ለዚህም ባለድርሻ ተቋማትንና ህብረተሰቡን ያሳተፈ የጸረ-ሙስና ትግልን አጠናክሮ ማስቀጠልና አሳታፊ የጸረ ሙስና ትግል በማካሄድ አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ ለውጥ ማምጣት ተቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
የዲሞክራሲ ተቋማት፤የፍትህ አካላት፤የመንግስት ተቋማት ኃላፊዎች፤ የልማትና ህዝባዊ ተቋማት አመራሮች፤ የሲቪክ ማህበራት፤ የሃይማኖት ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን፤ የቤተሰብ፤ የትምህርት ተቋማት፤ የማህበራዊ ተቋማትና የወጣቶችና ሴቶች ተሳትፎ ለጸረ-ሙስና ትግሉ ከፍተኛ ድርሻ ስለሚኖራቸው በጸረ-ሙስና ትግሉ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

Read 670 times