Saturday, 30 November 2024 20:15

ኀይለኛው የደርግ አባል! (ጴጥሮስ ገብሬ)

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

“--በተለይ አርሶ አደር፤ ከባድ ወንጀል ካልፈጸመ በቀር በየትኛውም ሰበብ በፖሊስ ታሥሮ ማደር የለበትም ብለው
ያምናሉ። ይልቅስ ጉዳዩ በአስቸኳይ ታይቶለት ወደ ልማት ሥራው መመለስ አለበት።--”

የታሪክ መለኪያ ዘንጎች ቀናት አይደሉም። የቀናት መልክና ቀለም የሚሠራው፣ጥበቡ የሚያሸበርቀው በሰው ነወና ክብሩ ወይም ውርደቱ የሚያርፈው መልሶ ሰው ላይ ነው።
በየዘመኑ መልካችንን ላጠለሹት፣ውበት ብለን አደባባይ ላይ ላጌጥንባቸው ክብሩንና ውርደቱን ተቀባዩ ሰው ነው። ቅዱስ መጽሐፍ “ቀኑ በትዕዛዝህ ይኖራል”ብሎ ለባለቤቱ የሰጠውን ሥልጣን፣መልሶ ለአዳም ስለሰጠው የተቀበለውን ቀን በደም ነክሮ፣ወይም በልማት አሳምሮ፣በጦርነት በጥብጦ፣ካልሆነም በሰላም ኩሎ ሕይወትን በልጓም አቅጣጫ የሚያስይዛት ሰው ነው። ሰው ደግሞ ክፉም ሆነ ደግ ለማድረግ ከጀርባው ገፊ ምክንያቶች አሉት።
ሒትለር እንደ ዛፍ በቅሎ፣ዝም ብሎ ምድርን አላነደደም።ከጀርባው ሰበብ አለ። እንደየዐውዱ አንዳንዴ ሃይማኖት መድኀኒት ይሆናል። ለጥፋት ደግሞ አስተዳደግ፣ጭቆናና መራራ ቂም መነሻ ሆኖ ይቆጠራል።
ከሳምንታት በፊት የደጃዝማች ፀሐዩ ዕንቆሥላሴን የልማት ጉልበትና የጀግንነት ጽናት ሳቀርብ አንዱን ከሃይማኖቸኝነታቸው፣ሌላውን ከአርበኛ ቤተሰባቸው ለማሳየት ሞክሬ ነበር። አሁን ደግሞ እሳት ሆኖ በተወለደው የደርግ መንግሥት ውስጥ የደርግ አባል የነበሩት የመቶ አለቃ ጴጥሮስ ገብሬ ጥንካሬና ልልነታቸውን ማንሳት አስፈልጎኛል።
የእኒህን ሰው ታሪክ ተጠግቼ እንዳይ፣እንድሰማና እንድፈትሽ ያደረገኝ፣ባዮግራፊ የምጽፍበት አጋጣሚ ነበርና ለትውልድ ግብዐትና እርሾ ሊሆኑ ይችላሉ ያልኳቸውን ነጥቦች አጋራለሁ።
ሰውዬው፣በተደጋጋሚ በተጻፉት መጻሕፍት፣ማለትም በኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለማርያም፣በኮሎኔል ደበላ ዲንሳና “ነበር”በተሰኘው በዘነበ ፈለቀ መጽሐፍና በሌሎቹ 4ኛ ክፍለጦር ደርግ ይሰባሰብባት በነበረች አዳራሽ ፣ገና በቅጡ ያልተግባቡት አባላት ሊበተኑ በነበረ ጊዜ፣ኤም ፎርቲኑን አውጥቶ”እያንዳንድህ ተመለስና ተቀመጥ፤ወዴት ልትሄዱ ነው?ማን ያቦካውን ማን ይጋግራል?”በማለት ደርጉን ከመፍረስ አድነውታል።
ደርጉ ሊበተን የነበረው” አየር ኀይሉ በጄት፣ክብር ዘበኛ በመድፍ የስብሰባ አዳራሹን ሊመታ ነው”በሚል ሴራ ተቃዋሚዎች ሊበትኗቸው ባሴሩት ሴራ ምክንያት ነበር። ይሁንና በዚህ ሰዐት ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኀይለማርያም ከወንበራቸው ንቅንቅ አላሉም ነበር።
እንግዲህ አንዱ የጴጥሮስ ገብሬ ቆራጥነት የተወራበት ጊዜ ይህ ነበር። ከዚያ በፊት ግን ስለጴጥሮስ የማውቀው፣ኀይለኝነታቸውን ብቻ ነው። “ጫት ስትቅም መንገድ ላይ ካዩህ በሽጉጥ አፈሙዝ  ጉንጭህን ገፍተው ያስተፉሀል” ይባል ነበር። ይሁንና በኋላ እንዳገኘሁት መረጃ፤ ጴጥሮስ የሲዳሞ ክፍለ ሀገር የደርጉ ተጠሪ በነበሩበት ሰዐት፣ሚሊሽያ አሠልጥነው በንጉሡ ከሥልጣን መውረድ ያኮረፉ የፊውዳሉ ሥርዐት ሽፍቶችን ተዋግተዋል። በሶማሊያው ወረራ ታጠቅ ጦር ሰፈር ከማሠልጠን ባለፈ እስከ ግንባር ዘምተው ተዋግተው፣አዋግተዋል።
በዚህም ጊዜ በጉዞ ላይ ሳሉ ሔሊኮፕተር ብልሽት ገጥሞት በመውደቁ፣ጆሯቸውን ተጎድተው ውጭ ሀገር ድረስ ሄደው ታክመዋል። በሌላም በኩል፣ በወቅቱ የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ዐይን የነበረውን የቡና ንግድ በኮንትሮባንድ ሲያባክኑ የነበሩ ሰዎችን በመከታተል ችግሩን በከፍተኛ ደረጃ ቀንሰው የወረሱትን ቡና ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውል አድርገው ነበር።


በሌላ በኩል፣ በጉጂና በጌዴኦ ማኅረሰብ መካከል ግጭት ያስነሳ የነበረን ቦታ በመከለል፣ ለሁለቱም ጥቅም የሚውል ሆስፒታል አሠርተው ለአገልግሎት ከመብቃቱ ባሻገር ችግሩ ከሥሩ እንዲነቀል አድርገዋል። በኋላ እኒህ ሰው ሊፈቱትና ሊያስተካክሉት ይችላሉ ተብሎ የተገመተውንና የትውልድ አካባቢያቸው የነበረውን የከምባታና ሃዲያ አውራጃ አስተዳደር እንዲያስተዳድሩ ተመድበዋል።
ከእርሳቸው ቀድመው የሄዱት አስተዳዳሪዎች፣ ስድስት ወራት ባልሞላ ጊዜ ሦስትና ከዚያ በላይ ተፈራርቀው ችግሩን መፍታት አቅቷቸው ነበር። ለምሳሌ፣ኮሎኔል ደሠቀ ተሰማ ለስድስት ወራት፤ የመቶ አለቃ ገብረኢየሱስ በቀለ ለአንድ ዓመት፤ሻለቃ አሰፋ በርሔ ለአንድ ዓመት፤አቶ ደሳለኝ ሽርካ ለአንድ ዓመት፤አቶ አለማየሁ ታቦር ለስድስት ወራት፤ሻምበል ሰለሞን ቦጋለ ለሦስት ወራት ተፈራርቀው ስላልቻሉ፣ በፕሬዚደንት መንግሥቱ ትዕዛዝ የመቶ አለቃ ጴጥሮስ ተመድበው ሄደዋል።


ይሁን እንጂ ይህን የችግር ቀጣና የሆነ አውራጃ ወደ ልማት ማዕከል በመቀየር በርካታ ሥራዎችን ሠርተዋል። ከሁሉም በጉልህ የሚታወቀው  250 አልጋዎች ያሉት የቀድሞው መንግሥቱ ኀይለማርያም፣አሁን ንግሥት ኤሌኒ ሆስፒታልን ማስገንባታቸው ነው።
የሚገርመው፣ሆስፒታሉን ማስገንባታቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሆስፒታሉን ለመገንባት ገንዘብ ያሰባሰቡበት መንገድም ጭምር ነው። ሰውዬው በወቅቱ የነበረውን የሀገሪቱን የገንዘብ ችግር ስለሚያውቁ ትኩረታቸውን ሕዝብ ላይ በማድረግ፣በሕዝቡ ዘንድ በድምቀት የሚከበረውን የመስቀል በዐል ዒላማ አድርገው፣በዕለቱ የሚታረደውን የበሬ ቆዳ በማሰባሱብ በሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ማግኘት ችለዋል፡፡ ይህም ለሆስፒታሉ ግንባታ ግብዐት ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪ ደረጃውን የጠበቀ ስቴዲየም፣የከተማው ሕዝብና ስፖርተኞች የሚጠቀሙበት ዘመናዊ የመዋኛ ገንዳ፣ደረጃውን የጠበቀ ስፖርት ሆቴል፣የእንግዶች መቀበያ፣ (አሥራ አንዱን አውራጃዎች የሚወክል አሥራ አንድ ባሕላዊ ቤቶች) እንዲሁም አንድ ለከፍተኛ ባለሥልጣን የሚሆን እንግዳ ቤት አሠርተዋል።
ከዚህም ባሻገር የልማት ተቋማትንና መንግሥታዊ ቢሮዎች ሥራቸውን በአግባቡ በመቆጣጠር፣የሕዝብን ብሶት በመስማት የተመሠገኑ ነበሩ። ለምሳሌ ራሳቸውን ለውጠው አርሶ አደሩ መንደር በመግባት ችግሩን ይጠይቁታል። ከዚያም የሚመለከተውን ክፍል አነጋግረው መፍትሔ እንዲሰጥ ያደርጋሉ። በተለይ አርሶ አደር ፤ከባድ ወንጀል ካልፈጸመ በቀር በየትኛውም ሰበብ በፖሊስ ታሥሮ ማደር የለበትም ብለው ያምናሉ። ይልቅስ ጉዳዩ በአስቸኳይ ታይቶለት ወደ ልማት ሥራው መመለስ አለበት።


በአንድ ወቀት ሆሳዕና ሆስፒታል ሕዝብ ያጉላላል ስለተባለው ዶክተር በተደጋጋሚ ከሰሙ በኋላ፣ በቃሬዛ ተሸክመው እንዲወስዷቸውና በጽኑ መታመማቸው ተነግሮ፣ዶክተሩ እንዲለመን ያደርጋሉ። ይህንኑ ሲያደርጉ አማጺው ዶክተር ቢለመን ዞር ብሎ ሊያያቸው ፈቃደኛ አልነበረም። ከቃሬዛው ተወርውረው እስኪይዙት ድረስ አልነቃም።
ድንጋጤውን ማሰብ ይከብዳል። በዘመኑ “የደርግ አባል”የሚለው ስም ብቻውን መብረቅ ነው። በዚያ ላይ ጴጥሮስ ኀይለኛ ናቸው።በዚህ ላይ ኮማንዶነታቸው ይጨመራል። ቁመታቸውም ሰማይ ይደርሳል፡፡ ታች ቃሬዛ ላይ ሆነው ያያቸውን እላይ እንደ ሰማይ ሲሰቀሉበት ምን ይዋጠው?...የገረመኝ ግን አልመቱትም። “ሕዝብ ያስተማረህ ልታገለግለው አይደለም?”ብለው ተቆጡት። ሁለተኛ እንዳይለምደው አስጠንቅቀውት ተመለሱ። ከዚያ በኋላ ሁልጊዜ ጴጥሮስ አጠገቡ የሚከሰቱ እየመሰለው ሥራውን በወጉ መሥራት ቀጠለ።
የመቶ አለቃ ጴጥሮስ ሌላው የተሰጣቸው ተልዕኮ፣ በከምባታና ሃዲያ አውራጃ ተዳክሞ የነበረውን የኢማሌድኅ አባል ድርጅት፣ ሰደድን ከተዳከመበት ማነቃቃትና ማጠናከር ነበር፤ያንን ፈጽመዋል።
በትይዩ በወቅቱ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጠፉ በግልጽና በኅቡዕ ይሠራባቸው የነበሩትን የሃይማኖት ድርጅቶች፣”አብዮቱን እስካልተቃወሙ መነካት የለባቸውም!” ብለው መሟገታቸው፣በደርጉና በኋላሞ በፓርቲው ውስጥ ብዙ አስነቅፏቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን የሃይማኖት ድርጅቶች ከማሳደድ ይልቅ፣ለልማት ብንጠቀምባቸው እናተርፋለን”በሚለው ገፍተውበታል።

Read 993 times