የክሪስታል ፓላስ አምባል ማርክ ጉዬ ባለፈው ቅዳሜ ከኒውካስል ጋር በነረበው ግጥሚያ የአምበልነት መለያው ላይ ‘አይ ላቭ ጂሰስ’ (እየሱስን እወደዋለሁ) ብሎ መፃፉ አነጋጋሪ ሆኗል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አስተዳዳሪ የሆነው ኤፍኤ አምበሉ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ቢቆጠብም ለክለቡ እና ተጫዋቹ መለያ ላይ ኃይማኖታዊ ፅሑፎችን መፃፍ ክልክል ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።
ማክሰኞ ምሽት ፓላስ ከኢፕስዊች ታውን ጋር በነበረው ጨዋታ ማርክ ጉዬ የኤፍኤውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ ‘ጂሰስ ላቭስ ዩ’ አሊያም ‘እየሱስ ይወዳችኋል’ የሚል መልዕክት ፅፎበት ገብቷል።
የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች ለኤልጂቢቲኪው+ ማኅበረሰብ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት አምበሎቻቸው የቀስተ ደመና ኅብረ ቀለማት ያሉትን መለያ ክንዳቸው ላይ አጥልቀው እንዲገቡ ያደርጋሉ።
ፉትቦል አሶሲዬሽን የተባለው የሊጉ አስተዳዳሪ ኃይማኖታዊ ምልክቶች የእግር ኳስ ማሊያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ መፃፍ ክልክል ነው ሲል ለክለቡ እና ለአምበሉ ማስጠንቀቂያ የላከው ባለፈው ቅዳሜ ነበር።
በተመሳሳይ የኢፕስዊች አምበል የሆነው ግብፃዊው አማካይ ሳም ሞርሲ ባለፈው ቅዳሜም ሆነ ማክሰኞ ምሽት በነበረው ጨዋታ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን የአምበሎች መለያ ሳያጠልቅ ነው የገባው።
ኢፕስዊች ታውን በለቀቀው መግለጫ ሞርሲ “በኃይማኖቱ ምክንያት” መለያውን ማድረግ እንደማይፈቅድ ማሳወቁ ይታወሳል።
ማክሰኞ ምሽት ከነበረው ጨዋታ በኋላ የፓላስ አሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ስለጉዳዩ ተጠይቀው “ማርክ የራሱ አተያይ አለው። የሁሉን ሰው አመለካከት እንቀበላለን፤ እናከብራለንም” ብለዋል።
ጉዬ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ጉዳዩን በመድገሙ ኤፍኤው ሊቀጣው እንደሚችል ይጠበቃል።
ይህ ዘመቻ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 29 እስከ ረቡዕ ታኅሣሥ 5 የሚዘልቅ ነው። የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ስቶንዎል ከተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ጋር በመጣመር ነው አምበሎች ይህን ባንዲራ እንዲያጠልቁ የሚያደርገው።
የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የኢፕስዊቹ አምበል ግብፃዊው ሳም ሞርሲ ይህን ባንዲራ አላጠልቅም ያለ የመጀመሪያው ተጫዋች አይደለም።
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የሼፊልድ ዩናይትዱ ተከላካይ አኔል አህመድሆድዚች ባንዲራውን አላጠልቅም ማለቱ ይታወሳል።
አሁን ለኤቨርተን የሚጫወተው ሴኔጋላዊው አማካይ ኢድሪሳ ጋና ጉየ ለፓሪ ሳን ዠርማ በሚጫወትበት ወቅት በተመሳሳይ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን ማሊያ አልለብስም ማለቱ አይዘነጋም።