Monday, 09 December 2024 21:01

የጉጂ ትውስታዎቼ

Written by  አብርሀም ገነት
Rate this item
(5 votes)

ዛሬ ክፍለ ሀገር አቋርጦ መጓዝ ብርቅ ሆኗል፡፡ ሀገራችን በታጣቂና በሸማቂ፣ በዘማችና በአጋች ተሞልታለች፡፡ ያን ጊዜ ያደረግነውን ጉዞ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው ተረት ይመስለኛል፡፡ በወለጋ ጫካዎች መሀል በሰላም አልፈናል– ያውም ከመኪና ወርደን ፎቶ እየተነሳን፡፡ በማሽላ ባጌጠው ውብ የሀረርጌ ወጣ ገባ መልክአ-ምድር እየተደመምን ሀረር ድሬዳዋና ጅግጅጋ ደጋግመን ተከስተናል፤ በጎጃም የጤፍ ባህር መሀል እያለፍን ወደ ጎንደርም ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝም ተሻግረናል፤ በደሴ መስመር ወጥተን ያለ ኮሽታ መቀሌ ገብተናል፤ ተጠራርቶ የተሰባሰበ በሚመስል የተራራ ክምችት የተሞሉ የትግራይና የላስታ ምድሮችን አቋርጠናል…፡፡ ዛሬ ይሄ አይነቱ ጉዞ ለትዝታ የተተወ ቅንጦት ሆኗል፡፡ እንደዚያን ጊዜው በሀገራችን መልክአ-ምድርና መልክአ-ባህል እየተደነቅሁ በነፃነት የምጓዝበት ጊዜ ዳግም እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡ ይመጣል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እንዲመጣ ደግሞ ለሰላም አስፈላጊ የሆነው ስራ መሰራት አለበት፡፡  

           
ያኔ በሰላሙ ዘመን ከወቅቱ የስራ ጓዶቼ ጋር ከአዲስ አበባ ወጥቼ ከዞርሁባቸው የሀገራችን አካባቢዎች አንዱ ጉጂ ነበር፡፡ ጉጂ ያኔ እንዳሁኑ ምዕራብ ጉጂ ተብሎ ሳይከፈል አንድ ዞን ነበር፡፡ እናም ይህች የጉጂ ትውስታዎች በሚል የተሠየመችው የጉዞ ማስታወሻ፣ በስራ አጋጣሚ ወደ ጉጂ ዞን በተንቀሳቀስኩባቸው ቀናት ያስተዋልኳቸውን ተፈጥሯዊ ውበቶች፣ ሠው ሠራሽ ኹነቶችና ገጠመኞቼን በአጭሩ ለማስቃኘት የተሠናዳች ናት፡፡ አልፎ አልፎ ከፅሑፍ የተገኙ መረጃዎች (እውነታዎች) ከመጨመራቸው በስተቀር በፅሑፉ ውስጥ የሚንፀባረቁ  ሀሳቦች በሙሉ የተጓዥ ምልከታዎችና እይታዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ማስታወሻው ስለዞኑና ህዝቡ ጥልቅ መረጃ ለመስጠት  የተዘጋጀ ሳይሆን፣ አንባቢው ቦታዎችን በምናቡ እያየ፣ የማህበረሰቡን ባህል እየቃኘ እየተዝናና ቢቻልም ቁም ነገር እንዲጨብጥ ታስቦ የተፃፈ ነው፡፡


በቀጥታ ወደ ጉዞዬ ከመግባቴ በፊት ስለ ጉጂ ዞን ጠቅለል ያለ አጭር መረጃ ልስጥ፡፡ የጉጂ ዞን በደቡብ ኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል ይገኛል፡፡ የዞኑ ርዕሰ ከተማ ነጌሌ ቦረና ከአዲስ አበባ በ595 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡ ዞኑ በ13 ወረዳዎችና በ2 የከተማ አስተዳደሮች (ነጌሌ እና አዶላ ወዩ) የተዋቀረ ነበር፡፡ ከዞኑ አጠቃላይ ክፍል ደጋ 27%፣ ወይናደጋ 33%፣ ቆላ 40% ይሸፍናሉ፡፡ ጉጂ ለም ምድር ነው፤ በተፈጥሮ ሀብት የታደለ አካባቢ ነው፡፡ ጉጂ ወርቅ የሚታፈስበት ምድር ነው፡፡ የጉጂ ምድር በደጋም በወይና ደጋም፣ በቆላም በማራኪ ሀገር በቀል ደኖች ያጌጠ ነው፡፡ ወደዚህ ድንቅ ምድር የተጓዝነው እንዲህ ነበር፡፡
ሚያዚያ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ተነስተን ሀዋሳ ገብተን አድረናል፡፡ የተንቀሳቀስነው ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ነው፡፡ የጥናት ቡድኑ አባላት ሾፌሩን ጨምሮ አምስት ነን፡፡ አቶ አብደላ፣ አቶ ቦልተና፣ አቶ ሳሙኤል፣ አቶ ተስፋዬ እና እኔ ቦርሳንዴዝ ማለት ነው፡፡  የምንሄደውም የጉጂ ኦሮሞን ባህላዊ ህግና የዳኝነት ስርዓት ለማጥናት ነው፡፡ አብደላ እድሜው አርባ የሚሆን ጎልማሳና ጠንካራ ሠራተኛ ሲሆን፤ በተለይ ባህልና ህግን የሚመለከቱ በርካታ መጽሐፍትን ፅፎ ለህትመት አብቅቷል፡፡ ቦልተና ዕድሜው (እሱ እንደሚለው) በአርባዎቹ መጨረሻ የሚገኝ፣ ብዙ አመት ስራ ላይ የቆየ ተጫዋች ሰው ነው፡፡ ሳሙኤል ዕድሜው (እንደ እኔ ግምት) ወደ ስልሳ ገደማ የሚጠጋ በጋዜጠኝነት ሙያ ለአርባ አመታት የሠራ ሰው ነው፡፡ ሳሙኤል የዕድሜውን ያህል ጎታታ ሽማግሌ እንዳይመስላችሁ፤ አጠር ቀጠን ያለ፣ ቆፍጣና፣ ተራራ ብንወጣ ቁልቁለት ብንወርድ ከወጣቶች ጋር እኩል የሚራመድ፣ እርጅና የማይሰማው  ጥሩ ወኔ ያለውና እንደ ወጣት የሚሰራው የማይከብድ ሰው ነው፡፡ ተስፋዬ የሚትሱብሺዋ መኪናችን ሾፌር ሲሆን፤ ዕድሜው እሱ በወቅቱ እንደነገረን 42 ነው፡፡ ተስፋዬ በባህልና ቱሪዝም መ/ቤት ውስጥ ለረጅም አመታት በመስራቱ የመ/ቤቱን ስራ የባለሙያዎቹን ያህል የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ በጉዟችን ወቅት በምናነሳው ሀሳብ ላይም መሪውን እያሾረ፣ ጥሩ ጥሩ ሀሳቦችን ይሰነዝራል፡፡ ከዚያም ባሻገር ተስፍሽ ተግባቢና ፀባዬ መልካም፣ በጣም ጥሩ የሹፍርና ችሎታም ያለው ጎልማሳ ነው፡፡    የጥናቱን ስራ የማስተባብረው እኔ ስሆን፣ ከሁሉም በዕድሜ (ወደ ሃያዎቹ አጋማሽ የተጠጋሁ) ትንሹ  ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ በሌሎች የጥናት ቡድኑ ጓደኞቼ እና በእኔ መካከል ያለው የዕድሜ ልዩነት በመካከላችን የፈጠረው አንዳችም አሉታዊ ነገር የለም፤ ይልቁንም ቆይታችንን የጣፈጠ አድርጎታል እንጂ፡፡ አብደላንና ተስፋዬን ቁልምጫ ጨምሬ በስማቸው ብቻ  ነው የምጠራቸው፡፡ ቦልተናን አቶ ጨምሬ የምጠራው ሲሆን፣ ሳሙኤልን ደግሞ ጋሼ ጨምሬ መጥራት ነው የሚቀናኝ፡፡ አንቱ ማለት መቼም አይሆንልኝም፤ አንድ አረፍተ ነገር እንኳን ሳልጨርስ ወደ አንተ እመለሳለሁ፡፡ እና አንቱ ብዬ ጀምሬ ወደ አንተ አውርጄ ከማስቀይም ብዬ ማንም ላይ አልጀመርኩትም፡፡


ከሀዋሳ እስከ ቦሬ ያደረግነውን ጉዞ “ጉማሙ ጉዞ” ስል ሰይሜዋለሁ፡፡ ጉማሙን ጉዞ የጀመርነው ሚያዚያ 4 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ በ12 ሰዓት ከሀዋሳ ነበር፡፡ መቼም የዚያን ጊዜው ጉም በብሔራዊ ደረጃ የታወጀ ሳይሆን አይቀርም! ለረጅም ሰዓታት በዝናብ የተጓዝኩት በዚህ የመስክ ስራ ነው፡፡ ገና ከንጋት ጀምሮ መጣል የጀመረው ሀይለኛ ዝናብ፣ በከባድ ጉም የታጀበ ነበር፡፡ በተለይም ስምጥ ሸለቆን ጨርሰን ወደ ደጋው ክፍል እስክንወጣ ድረስ፣ በሚርከፈከፈው ዝናብ ውስጥ የተጠቀጠቀው ጉም ጉዟችንን በጣም አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፡፡ በመኪናችን ማጫወቻ እየተለዋወጡ የሚሰሙት የሙሉቀን መለሰ ጥዑም ዜማዎች ከዝናቡ፣ ከጉሙና ከብርዱ ጋር አብረው የተሸመኑ ይመስላሉ፡፡ ሀዋሳ— ቱላ— አቤላ እያልን አለታ ጩኮ ከደረስን በኋላ ዋናውን የዲላ— ሞያሌ መንገድ ትተን ወደ ግራ– ወደ ደቡብ ምስራቅ የሚሄደውን ኮረኮንች መንገድ ያዝን፡፡ ከአለታ ጩኮ ልንወጣ ስንል ትኩስ በዘይት የተጠበሱ ብስኩቶችን ገዛን፡፡ አብደላና ጋሽ ሳሙኤል ብስኩት አንበላም ስላሉ ትኩሶቹን ብስኩቶች ሦስታችን በጠዋቱ አፋችንን አሟሸንባቸው፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ ከቆፈኑ እየተነቃቃን ወሬ ጀመርን፡፡     
“ሾፌራችን ሙዚቃ መምረጥም ይችላል” አለ አብዱ፤ የሙሉቀንን ዜማ ሁላችንም ስለወደድነው፡፡
“በጣም! ከዝናቡ ጋር የሚስማማ!” አልን ሁላችንም፡፡ ትንሽም ስለ ሙሉቀን መለሠ እና ስለድሮዎቹ ሙዚቃዎች ዘመን ተሻጋሪ ጣዕምና ስለ አሁኖቹ ግልብነት ስንነጋገር ቆየን፡፡
አለታ ወንዶ ደርሰን፣ ወደ ሲዳማዎቹ በንሳና አርቤጎና ወረዳዎች የሚወስደውን መንገድ ወደ ግራ ትተን ቀጥተኛውን መንገድ ስንቀጥል፣ ዝናቡና ጉሙ ይበልጥ ተባብሮ ጨፍኖ፣ መንገዳችንን ለእይታ በጣም አስቸጋሪ አደረገው፡፡ ከአለታ ወንዶ ከተማ ጀምሮ ያለው መንገድ አዲስ የተሰራ አንደኛ ደረጃ አስፋልት ነው፡፡ በዚያ ላይ ስፋቱ እንደ ልብ መኪኖችን  ያስተላልፋል፡፡ የምንጓዘው ሽቅብ እየወጣን በመሆኑ፣ ከጎናችን እየወደቀ የሚቀረውን ሰርባዳ የሸለቆ ምድር ከውብ ጫካዎቹ፣ ከዝናቡና ጉሙ ጋር ባሻገር ስንመለከተው አስደማሚ ውበት አለው፡፡ ጠዋቱ ወደ 2 ሰዓት የሚጠጋ ቢሆንም በዝናቡና ጉሙ ምክንያት ይመስላል እምብዛም የሚላወስ ሰው አላየሁም፡፡ አብዛኞቹ የገጠርና የከተማ ቤቶችም ገና እንደተዘጉ ናቸው፡፡ ባጭሩ ህይወት የተለመደ እንቅስቃሴዋን ገና በደንብ አላሟሟቀችም ነበር፡፡    
 ስምጥ ሸለቆን ወጥተን የደጋውን ክፍል ስንገባ ዝናብ የለም፤ የመሬቱ ደረቅነት ሌሊትም እንዳልዘነበ ይመሰክራል፡፡ በአንፃሩ እጅግ ጥቅጥቅ ያለ፣ ደረቅ ነጭ ጉም አካባቢውን ሙሉ ለሙሉ ሸፍኖታል፡፡ በተለይ በሲዳማ ዞን ሁላ ወረዳ ዋና ከተማ ከሆነችው ሀገረ ሰላም ጀምሮ፣ በሚትጎለጎለው ጉም የተነሳ ከፊት ለፊታችን ከጥቂት ሜትሮች በኋላ ምንም ነገር ማየት ስለማይቻል፣ የመኪናችንን ፍጥነት ቀንሰን መጓዝ ግድ ነበር፡፡ እኔ የተቀመጥኩት ጋቢና ስለነበር ከአሁን አሁን ከፊታችን ከሚመጣ መኪና ጋር የምንጋጭ እየመሰለኝ ተስፍሽን በተደጋጋሚ “ኧረ ቀስ እንበል” እለዋለሁ፡፡ እሱ ግን የጉሙ ግርዶሽ ብዙም ያሰጋው አይመስልም፤ ፍጥነቱን ጨመር ቀነስ እያደረገ በልበ ሙሉነት ነበር የሚያሽከረክረው፡፡ የልምድን ያህል በራስ መተማመን የሚሰጥ ጥሩ ነገር የለም፡፡ በጉሙ ጥቅጥቅነት የተነሳ የመንገዱ ጠመዝማዛነት እንኳን የሚገለጠው ለመጠምዘዝ ጥቂት ሜትሮች ሲቀሩ ብቻ ነው፡፡ በዚያ ላይ መልክአ-ምድሩ አደገኛ ወጣ ገባ ነው፡፡ ሾፌራችን ተስፍሽ በዚህ አስቸጋሪ አየር ፀባይ፣ በዚያ ጠመዝማዛ የዳገት መንገድ፣ በልበ ሙሉነትና በደህንነት ይነዳል፡፡ ብቃቱን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡
ዝናብና ጉም እየተፈራረቁብን፣ እየተጫወትን፣ የሙሉቀንን ሙዚቃ እየሠማን ቦሬ ከተማ ደረስን፡፡
ብርዳሟ ቦሬ
በጉጂ ዞን ስር የቦሬ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው ቦሬ ከተማ ስንደርስ መኪናችንን በሚመች ቦታ አቁመን ቁርስ ለመብላት ወረድን፡፡ ዝናቡ አልፈነው እንደመጣነው ጠንካራ ባይሆንም፣ ማካፋቱን አላቆመም ነበር፡፡ ጉም ግን አልነበረም፡፡ ጋሽ ሳሙኤል ድሮ ወጣት በነበረበት ጊዜ እዚሁ ቦሬ በመምህርነት ሰርቶ ስለነበር ስለቦሬ ብዙ ነገር ያውቃል፡፡ ጋሽ ሳሚ እጁን አፉ ላይ እየጫነ፤ “ምንም እኮ አልነበራትም! ይሄ ሁሉ እንዴት ተለወጠ ባክህ!” እያለ ቦሬን ድሮ እሱ ከሚያውቃት ገፅታዋ ጋር እያነፃፀረ ይገረማል፡፡ እኔ ቦሬን ድሮም ስለማላውቃት ትለወጥ አትለወጥ ምንም የፈጠረብኝ ስሜት የለም፣ ይሰማኝ የነበረው ብርዷ ነው፡፡ ቦሬ ብርዳም ደጋማ ከተማ      ናት፡፡    ቦሬ ስንደርስ ሰዓቱ ረፈድፈድ ብሎ ስለነበር ሰው ሁሉ ከቤቱ ወጥቷል፣ ምግብ ቤቶችም ቁርስ ማዘጋጀት ጀምረዋል፡፡ አብዱ ስጋ መብላት ስለፈለገ ወደ ሙስሊም ምግብ ቤት ሔደ፡፡ የተቀረነው አራታችን አንዲት ምግብ ቤት ገባንና እንጀራ ፍርፍርና ሽሮ ፈሰስ አዘዝን፡፡ የዚያች ምግብ ቤት ቁርስ ግሩም ነበር! ከሁሉም የማይረሳኝ በርበሬና ጨው የበዛበት እንጀራ ፍርፍሩ ነው፡፡ ያልሟሟ ጨው ሳይቀር ምግቡ ውስጥ አግኝተን በጥርሳችን ጎርድመናል፡፡ ግን ለብርዱ ጥሩ ነበር፡፡ ከብርዱ የተነሳ እዚያች ከተማ የሚሰራው ምግብ ሆን ተብሎ በርበሬና ጨዉ የሚበዛበት እየመሰለኝ ምግቡን ተመችቶኝ በላሁ፡፡    

     
ነገሩን ማን እንዳነሳው በትክክል ባላስታውስም፣ ቁርስ እየበላን እያለ እኔ፣ ጋሽ ሳሚና አቶ ቦልተና ስለ እብድ አንስተን እየተከራከርን ነበር፡፡ አቶ ቦልተና፤
“….ሰው የሚያብደው በሙቀት ምክንያት ነው፣ ሙቀት ሲበዛ ጭንቅላትን አዛብቶ ያሳብዳል” ሲል ሰዎች የሚያብዱበትን ምክንያት አብራራ፡፡
ጋሽ ሳሚም የቦልቴን ሀሳብ ደግፎ “አዎ፣ ሙቀት አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለምሳሌ፡- ብዙ እብድ የሚታየው ቆላ ላይ ነው፤ ደጋ ግን እብድ የለም” ሲል አከለ፡፡
እኔ የሁለቱ ሀሳብ አላሳመነኝም፡፡ “ሰው የሚያብደው በማህበራዊና ስነ ልቦናዊ ቀውሶች የተነሳ ነው እንጂ በሙቀት አይደለም፡፡ እንዲያውም ሙቀትና ቅዝቃዜ ከማበድ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም” አልኳቸው፡፡
እነሱ ግን አሁንም በሀሳባቸው ፀንተው ሞገቱኝ፡፡ መከራከሩን ትቼ ዝም ብዬ ሳስብ ጋሽ ሳሚ ትክ ብሎ አየኝና፤ “አልተዋጠልህም አይደል?” አለኝ፡፡
“አዎ” አልኩት፡፡ የቅሬታ ስሜቴን እኔ ብደብቀውም ፊቴ አሳብቆብኛል፡፡
በልተን ጨርሰን እጃችንን ለመታጠብ ስንወጣ ወሳኝ ነገር አየሁና ለሁለቱም አሳየኋቸው፡፡ ከምግብ ቤቱ አጠገብ አንድ እብድ ራቁቱን ሆኖ ወዲያ ወዲህ እያለ ነበር፡፡
“ደጋ ላይ እብድ የለም ብላችሁ አልነበረም? ይኸው!” አልኋቸው፣ ወደ እብዱ እያመለከትኩ፡፡ ጋሽ ሳሚና አቶ ቦልቴ፤
“…..የለም እኮ አላልንም፣ እሱ የተለየ ነው ምናምን” እያሉ ማስረጃውን አድበስብሰው አለፉ፡፡ ቡና ከጠጣን በኋላ እስከ ክብረ መንግስት እንድንወስዳት ትብብር የጠየቀችንን አንዲት ወጣት ሴት ጨምረን፣ ብርዳሟን ቦሬን ለቀናት ወጣን፡፡    
የጀምጀም አምባ
የአሁኑ ጉጂ ዞን፣ በድሮው የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ስር ይተዳደር ነበር፡፡ በርካታ ህዝቦች ተሰባጥረው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ተብለው በሚጠሩበት በዚሁ ክፍለ ሀገር ስድስት ሰፋፊ አውራጃዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም ጀምጀም አውራጃ፣ አራሮ አውራጃ፣ ቦረና አውራጃ፣ ሲዳማ አውራጃ፣ ጌዲኦ አውራጃና ወላይታ አውራጃ ናቸው፡፡ ከተጠቀሱት አውራጃዎች የአሁኑ ጉጂ ከሞላ ጎደል በጀምጀም አውራጃ ውስጥ ያሉ ቦታዎችን ያካትታል፡፡ የጉጂ ህዝብ በዋነኝነት ጀምጀም ይባል በነበረው አውራጃ ውስጥ ይኖራል፡፡ ጀምጀም የሚለው ስም ሲጠራ እኔን ቀድሞ ትዝ የሚለኝ ሁለተኛ ደረጃ ጂኦግራፊ ትምህርት ላይ the Jemjem Plateau (የጀምጀም አምባ) የሚለው ነው፡፡ የጀምጀም አምባ ሠፊ ቦታ የሚሸፍን ከፍተኛ አምባ እንደሆነ በትምህርቴ አስታውሰዋለሁ፡፡ አሁን ዕድለኛ ሆኜ በስራ አጋጣሚ ያኔ በምናብ የተማርኩትን ቦታ በገሃድ እያየሁት ስለሆነ አካባቢውን የምቃኘው በንቃትና በተመስጦ ነው፡፡
ቦሬ ከተማን ከወጣን አንስቶ፣ የጀምጀም አምባ በትላልቅ  ሀገር በቀል ዛፎችና በለምለም ሳሮች ተሞልቶ ድንቅ ውበቱን ማሳየት ጀመረ፡፡ በነዚያ ግዙፍ ጥንታዊ ዛፎችና የቀርቀሃ ጫካዎች መሀል አልፎ አልፎ ግልጥ የሚለው ሜዳ፤ ለምለም መስክ ላይ የፈሰሱ ከብቶችን፣ በጎችንና ፈረሶችን ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ከቀርከሃ የተሠሩት ትናንሽ የገጠር ቤቶችም ቢሆኑ፣ በዚያ ድንቅ ተፈጥሮ መካከል ጉብ ጉብ ማለታቸው የራሳቸውን የውበት አውድ እንዲፈጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ አካባቢ በከፍተኛ አምባ ላይ የሚገኝ ደጋማ ስፍራ እንደመሆኑ መጠን፣ ከዕፅዋት ኮሶና ቀርከሀ ሲበዙ፤ ከቤት እንስሳት ደግሞ ከብት፣ ፈረስና  በግ መስኩ ላይ በብዛት ይታያሉ፡፡ በየመስኩ ላይ ከሚንፎለፎሉት ምንጮች በተጨማሪ በእርሻ ማሳዎች ላይ በቅርብ የተዘሩ ትናንሽ የበቆሎ አዝዕርቶች ይታያሉ፡፡ የአፈሩ ለምነት መቼም ለጉድ ነው! ሾፌራችን ተስፍሽ የጉጂን አፈር እየዞረ አይቶ ሲያበቃ፣ “መሬቱ ኬክ ነው!” ሲል ነበር  የገለፀው፡፡ 

       
የመኪና ውስጥ ወሬያችንን ቀንሠን በየራሳችን የህሊና አለም ውስጥ ተሠማርተናል፡፡ ከአምባው ጥቂት ወርደን ኢርባ ሙዳ የምትባል ከተማ ደረስን፡፡ ኢርባ ሙዳ በጉጂ ዞን የአናሶራ ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ የጀምጀምን የተፈጥሮ ውበት እያደነቅን ከተጓዝን በኋላ፣ ከኢርባ ሙዳ በመቀጠል ያገኘናት ትንሽዬ ከተማ ቧንቧኃ የምትባለውን ነው፡፡ ቧንቧኃን እንደወጣን ያ ቦሬ ላይ ጥለነው የመጣነው ዝናብ ከፊታችን ተቀበለን፡፡
በጉጂ ዞን እስከ ነጌሌ ድረስ፣ ኋላም በየወረዳዎች በተዘዋወርኩበት ጊዜ ሁለት ነገሮችን ታዝቤያለሁ፡፡ የመጀመሪያው ትዝብቴ እንዲያ ያለው ግመጡኝ ግመጡኝ የሚለው ለም መሬት በሚገባ አለመታረሱ ነው፡፡ ብዙዎቹ መሬቶች ምንም ያልታረሱ ሲሆን፤ ታርሰዋል የሚባሉትም ቢሆኑ በሚገባ መሬቱ ስላልለሰለሰ ማሳዎቹ ሠርዶና አረም ከእህሉ ጋር ተደባልቆ የበቀለባቸው ናቸው፡፡ በኋላ ያገኘናቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም፤ “ለዕለት ፍጆታ የሚበቃ ነገር ከተዘራ ሌላ ትርፍ ነገር አይታሰብም” ብለውናል፡፡ ይህንን ስሰማ ቆጨኝ፡፡ ይህንን  የመሠለ ለም መሬት በደንብ አርሶ ትርፍ ማምረትና ኑሮን መለወጥ ሲገባ፣ ወርቅ ላይ ተቀምጠው እንዴት ድህነትን ታቅፈው ይኖራሉ? ሁለተኛውና ከዚሁ ጋር የተያያዘው በሰሜን ኢትዮጵያ፣ በተለይም በጎጃም አካባቢ እንዳስተዋልኩት አይነት ጉጂ ውስጥ ብዙ የገጠር ቆርቆሮ ቤቶች የሉም፡፡ ኧረ እንዲያውም በጣት የሚቆጠሩ ሳይሆኑ አይቀሩም! ቤቶቹ በቅርብ ከሚገኘው ቀርከሀ በስፋትና በውበት የሚሠሩ ቢሆን፣ ቆርቆሮም የግድ ባላስፈለገ ነበር፡፡ ውስጣቸውን አላየሁም እንጂ የገጠሮቹ ቤቶች ውጫዊ ሁኔታ የተጎሳቆለ ነው፡፡ የጉጂዎችን የተፈጥሮ አካባቢ አጠባበቅ (በተለይም ዛፎችን አለመቁረጣቸውን) ግን እጅግ አደንቃለሁ፡፡


ደጋማውን የጀምጀም ክፍል ጨርሰን ወደ ወይናደጋው መሸጋገሪያ የሆነውን የአንፈራራን ቁልቁለት ተያይዘነዋል፡፡ የአንፈራራ ቁልቁለት በዚህ መስመር ካየኋቸው ዳገትና ቁልቁለቶች ሁሉ ሀይለኛው ነው፡፡ በቁልቁለቱ ግራና ቀኝ ጥቅጥቅ ብሎ የበቀለው የተፈጥሮ ደን የአንፈራራ ጫካ ይሠኛል፡፡ ይህ ደን እንዲሁ ሲመለከቱት ዝም ብሎ ጫካ ቢመስልም፣ በውስጡ አረንጓዴው ወርቅ እየተባለ የሚጠራውን የቡና ችግኞች አስጠልሏል፡፡ በአንፈራራ ደን ላይ ከተራራው ራስ እስከ ታች እስከ ሸለቆው ድረስ ይትጎለጎል የነበረው ጉም በአእምሮዬ ተቀርፆ ቀርቷል፡፡ አንፈራራ የቁልቁለቱ (እና የዳገቱ) እንዲሁም የጫካው ስያሜ ብቻ አይደለም፤ ከተራራው ግርጌ አንፈራራ የምትባል አነስተኛ ከተማ መጠሪያም ጭምር እንጂ፡፡ አንፈራራ በእንሰት ተክል የተሞላች አነስተኛ የገጠር ከተማ ናት፡፡ ከአንፈራራ ቀጥሎ በማራኪ የተፈጥሮ ውበትና ዛፎች ተሞልታ የምትገኘው ከተማ ክብረ መንግስት ናት፡፡ ክብረ መንግስት የድሮው የጀምጀም አውራጃ ማዕከል የነበረች ናት፡፡ አሁን ስሟ ወደ አዶላ ወዩ   ተቀይሯል፡፡


እኛ አዶላ ወዩ ስንደርስ ዝናብ አስቀድሞ ዘንቦ ኖሮ ከተማው ጭቃ በጭቃ ሆኖ ነበር፡፡ ፀሐይ ደመናው ሲገላለጥላት ጊዜ ብርጭው ብላለች፡፡ ክብረ መንግስት የመኪናችንን ጎማ ለማሠራት ቆመን ስለነበር፣ ከመኪና ወርደን በእግር የመጓዝና ቡና የመጠጣት ዕድል ነበረን፡፡ ጎማችንን አሠርተን ስንጨርስ፣ ከቦሬ የጫንናትን ልጅ አሠናብተን፣ ክብረ መንግስትን ወጥተን ቁልቁል መውረድ ጀመርን– ወደ መዳረሻችን ወደ ኔጌሌ፡፡
ችግኝ በመትከል ረገድ ደርግ ጥሩ ነገር ሠርቶ አልፏል፡፡ በመንገዳችን ላይ ያስተዋልኩትን ጥቅጥቅ ያለ ሰፊ የፅድ ደን ደርግ የተባለው ነው ሲሉኝ፣ ለካ እንዲህ አይነት ሠው ሠራሽ ጫካም መፍጠር ይቻላል እያልኩ ነበር በሀሳቤ፡፡ አስቸጋሪውን የኮረኮንች መንገድ ጨርሰን አስፋልት ገባን፡፡ የመሬቱ ከፍታ በአንዴም ባይሆን ቀስ በቀስ እየወረደ ነው፤ ሙቀቱም ጨመርመር ማለት ጀምሯል፡፡ በዚያም ላይ የግራር ዛፎችን ማየት ስለጀመርኩ ወደ ቆላማው የጉጂ ክፍል እየገባን መሆኑን ተረዳሁ፡፡ ሀረቃሎ በጉጂ ዞን የጎሮደላ ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ ምሳ የበላነው እዚህች ከተማ ነበር፡፡ መኪናችንን አቁመን ምሳ የምንበላበት ጥሩ ቤት የቱ እንደሆነ ሰው ለመጠየቅ ስንጓዝ፣ መንገድ ላይ አንዲት ዕድሜዋ በ30ዎቹ የሚገመት ቀይ ረጅም ወፍራም ሴት አገኘን፡፡    
“ጥሩ ምሳ የት እናገኛለን?” ስንል በትህትና ጠየቅናት፡፡
“እዚህ ቤት ታገኛላችሁ” አለችን ከወደቀኛችን አንዲት የጭቃ ቤት እየጠቆመችን፡፡ ወቅቱ የፋሲካ ፆም ስለነበር እኔ፣ ጋሽ ሳሚና አቶ ቦልተና የፆም ምግብ ተመጋቢዎች ነን፡፡ ወርቁ መስክ ከወጣ በኋላ አለመፆምን ስለመረጠ በምግብ በኩል ከአብዱ ጋር ተጎዳኝቷል፡፡
እጃችንን ታጥበን፣ ምግብ አዝዘን እንደተቀመጥን ያቺ ከውጭ ያገኘናት ሴቲዮ ወደ ምግብ ቤቱ ጥልቅ አለች፣ ከዚያም ወደ ጓዳ ገባች፡፡ ለካስ ምግብ ቤቱ የራሷ ኖሯል፡፡ በዚያች ከውጭ ሲያዩዋት ምንም በሆነች ቤት ውስጥ የተመገብነው ሽሮ ግሩም ነበር! እርቦን ስለሆነ ይሁን አልያም ጣፍጦን (ወይም በሁለቱም ምክንያት) ጎምጅተን ነበር ምግቡን የበላነው፡፡ በዚያ ላይ ሴትዮዋ ከውጭ አግኝታ ስላስገባችን በሚገባ ነበር የተንከባከበችን፡፡ በሁለተኛው ቀን ሀረቃሎ ለነበረን ስራ ተመልሰን ስንመጣ ምሳ በድጋሚ እዛች ቤት በልተናል፤ ሴትዮዋንም አግኝተናታል፡፡


ጉዟችንን ቀጥለን፣ ሠጥ ብሎ በተዘረጋውና በግራር በተሸፈነው ቆላማ አካባቢ በሚያምረው አስፋልት ላይ እየተንፈላሠስን፣ ቢታታ የምትባለው በጣም አነስተኛ ከተማ መሰል መንደር ደረስን፡፡ በዚህ በግራር ዛፎች ተሸፍኖ በተንሰራፋው ሰፊ መሬት እስከዚያ ጊዜ  ድረስ ያላየሁትን ነገር ተመልክቼያለሁ፡፡ በጫካውና ቁጥቋጦው መሐል ከቀይና ቡላ አፈር የተሠሩ ከሰው ቁመት የሚበላልጡ ኩይሳዎች እንደ ከተማ ህንፃ በብዛት ይታያሉ፡፡ በኋላ የሚያውቁት ጓደኞቼ ሲነግሩኝ የምስጥ ኩይሳ ነው አሉኝ፡፡ ምስጦች! ያቺን የሚያካክሉ ነፍሳት፣ ያን የመሠለ ግዙፍ መኖሪያ መስራት መቻላቸው በጣም አስገርሞኛል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ለማስታወስ ስንልም፣ ከመኪና ወርደን ከምስጦች ቤተ-ኩይሳ (ቤተ ምስጥ ቢባል ሳይሻል አይቀርም) ጋር እየቆምን ፎቶ ተነሳን፡፡ ሌላው በዚያ ጊዜ ያየሁትና እስካሁን ድረስ ከአእምሮዬ የማይጠፋኝ፣ በዚያ በግራር ተሸፍኖ በተንጣለለው ሜዳ ላይ እንደ አንከባሎ የተደፋው ብሩህ ሠማይ ነው፡፡ እንደዚያ ቀን ሠማዩ ብሩህ ሆኖ ታይቶኝ አያውቅም! ብሩሁ ሠማይ፣ የተንጣለለው ሜዳ ከነቁጥቋጦዎቹና ኩይሳዎቹ፣ በሰሜንና ምዕራብ አቅጣጫ የቆሙት ተራሮች ህብር ውበት ልዩ ነበር፡፡    
(ይቀጥላል

Read 891 times