Monday, 09 December 2024 21:06

“አንድም ከቀበሮ፤ አንድም ከአንበሳ ተማር” አንበሳ ከወጥመድ ለማምለጥ አይችልም። ቀበሮ ደግሞ ከተኩላ ለማምለጥ አትችልም። ወጥመዱን ለማየት ቀበሮ ሁን። ተኩላ እንዳይጠጋህ አንበሳ ሁን።

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ማኪያቬሊ (ጣሊያናዊ የታሪክ ባለሙያ፣ የሀገር መሪ፣ እና የፖለቲካ ፍልስፍና አዋቂ)



አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ።
የዱር አራዊት ንጉሥ አንበሳ ታሞ አልጋ ላይ ዋለ። ጠያቂና አስታማሚ አጣ።  ከህመሙም በላይ ጠያቂ ማጣቱ በጠናበት ጊዜ፣ ለአሣማና ለዶሮ በደብዳቤ መልዕክት ላከ። እንዲህ ብሎ፡-
“ውድ አሳማ!
ውዲት ዶሮ!
እነሆ ካመመኝና አልጋ ከዋልኩ አያሌ ወራት ሆኑኝ። እህል ከቀመስኩ ደግሞ ሣምንት አለፈኝ። ዞር ዞር ብዬ የሚበላ ፈልጌ እንኳ አፌ እንዳላረግ ህመምተኛ ሆንኩ። አቅሜም ደከመ። የሰው ልጆች አንበሳ ሲያረጅ የዝምብ መጫወቻ ይሆናል፤ የሚሉት የዋዛ አነጋገር አይደለም። ዱሮ የሚሰግዱልኝ፣ የሚሽቆጠቆጡልኝና ከሥሬም የማይጠፉ ብዙ አውሬዎች ዛሬ አንዳቸውም አጠገቤ ያሉ አይመስሉም። አንዳንዱ ያለወትሮው ዝምተኛ ሆኗል። በአንፃሩ አንዳንዱ፣ ምንም ፍሬ ጠብ አይለውም እንጂ፤ አፍ ለቆበታል። አንዳንዱ እኔ ካልኖርኩ የማይኖር ይመስል በፍርሃት ተውጦ ተደብቆ ይተኛል። ሌላ ቀርቶ፣  አይምሬውን ክርኔን የቀመሱት፣ ሳገሣ ድራሻቸው ይጠፋ የነበሩት እነ አያ ጅቦ፣ እነ አያ ከርከሮ፣ እነ ብልጢት ጦጣ፣ ዛሬ አልጋዬ ድረስ መጥተው እንኳ ለመጠየቅ ንቀት አደረባቸው። እንዲያውም “አንበሳ ከታመመ፣ የልብ ወዳጅ ከጠመመ፣ መመለሻ የለውም” እያሉ እየረገጡ አላገጡብኝ አሉ። በዙሪያዬ የነበሩት ሁሉ “አምላክ አንተንም  እኛንም እኩል ነው የፈጠረን” ማለት ጀምረዋል። ይሄ ቀን የማያልፍና፣ ከታመምኩት በሽታ ድኜ፣ ካልጋ ቀና የማልል መስሏቸው ነው። እንግዲህ የቀራችሁኝ ውድ ወዳጆች እናንተና ይህን ደብዳቤ ይዞላችሁ የመጣው ዝንጀሮ ብቻ ናችሁ። ስለዚህ አደራ ሳልሞትባችሁ ድረሱልኝ።”
ፊርማ የማይነበብ
የናንተው አንበሳ፣
የጥንቱ የጠዋቱ የዱር አራዊት ንጉሥ

አሳማና ዶሮ ደብዳቤው እንደደረሳቸው በጣም አዘኑ።
“ምን ብናደርግለት ይሻላል?” አለ አሳማ።
ዶሮም፤ “መቼም ነግ በእኔ ማለት ደግ ነው። አንድ ነገር ማድረግ አለብን”
አሳማ፤ “ግን አያ አንበሶን እንዲህ እስኪማረር ድረስ ያደረሱት እነማን ይሆኑ?”
ዶሮ፤ “ዛሬ ማን ይታመናል ብለህ ነው አሳምዬ? የልብ ወዳጅ የታለና? ያው እሱ ራሱ የጠቃቀሳቸው በጣም ቅርብ ቅርብ ያሉ ባለሟሎች እነ አያ ጅቦ፣ እነ እመት አህያ፣ እነ አቶ በቀቀን፣ እነ ጆሮ-ትላልቄ ይሆናሏ።”
አሳማ፤ “አትይኝም? ጆሮ.. ትላልቄም ጨከነበት?”
ዶሮ፤ “እየነገርኩህ! ባለንበት ዘመን፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ማንም አይተኛም”
አሣማ፤ “ዕውነትሽን ነው። በይ እኛም ሳይረፍድ የምንይዘውን ይዘን ሄደን እንጠይቀውና ይውጣልን”
ዶሮ፤ “እንዲህ እናድርግ። እኔ እንቁላል ላዋጣ። አንተ ደግሞ ስጋ አዋጣና ሃምበርገር ይዘንለት እንሂድ”
አሣማ፤ “በጣም ድንቅ ሃሳብ አመጣሽ። በቃ ሀምበርገር እንውሰድለት”
በዚሁ ተግባቡና ጠዋት ወደ አንበሳው ሊሄዱ ተስማምተው ተለያዩ።
ጥቂት እልፍ እንዳሉ ግን፤ አሣማ አንድ ነገር ትዝ አለውና ዶሮዋን ጠራት። ከዚያም “ስሚ አንቺ ዶሮ፤ አሁን እናዋጣ የተባባልነው፤ ሚዛናዊ መዋጮ አይደለም። እኔ ተበድያለሁ!”
ዶሮም ነገሩ ስላልገባት፤ “ለምን? እንዴት ነው ሚዛናዊ ያልሆነው?”
አሳማም፤ “አየሽ፤ አንቺ ዕንቁላሉን የምታዋጪው ወልደሽው ነው። እኔ ግን ሥጋ እምሰጠው ከገዛ አካሌ ቆርጬ ነው። ያንቺ ተሳትፎ ብቻ ነው (Participation እንዲሉ)። የእኔ ግን ጉዳዩ ውስጥ በአካል መግባት ነው (Involvment እንዲሉ)” አላት።
***
ህመም፣ ችግርና ሣንካ ሲያጋጥመን ወዳጅ አይክዳ። እንደ አረጀ አንበሳም የዝምብ መጫወቻ ከመሆን ይሰውረን። ከፍሬ-ቢስ ልፈፋ ያውጣን። በእኩልነት የማያምን “ዲሞክራት መሪ” አያጋጥመን።
በአገራችን ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች ሚና፣ ጉዳዩ ውስጥ የመግባት እንጂ ዕንቁላል የመጣል ተሳትፎ ብቻ እንዳይሆን የሁሉም ወገን ጥረትና ትግል ሊኖርበት ይገባል። በሀገራችን የፖለቲካ ውጣ - ውረድ ውስጥ አያሌ አንበሶች ታይተዋል። ሆኖም የአንበሳነታቸው መጠንም ሆነ አንበሳዊ ባህሪያቸው፤ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። አንዳንዱ በጭራሽ ሌላ ፍጡር አያስጠጋም። ንፁህ ነው እንኳ ቢባል። ዲ.ኤች.ሎረንስ እንዳለው ነው፡- “አንበሳን ማንም ኃይል፤ ከበግ ግልገል ጋር ሊያስተኛው አይችልም። ግልገሏ ሆዱ ውስጥ ካልገባች በስተቀር።”  አንዳንዱ ደግሞ ቀን ሲጨልምበት ወይም እክል ገጥሞት ከአልጋ ሲውል በቀላሉ የሚደፈር ይሆናል። ሆራስ የተባለው የዜማና ምፀታዊ ግጥም ፀሀፊና ታዋቂ ሮማዊ (ከክርስቶስ ልደት በፊት በ65-ዓመት)፤
ታሞ ልትጠይቀው፣ ሄዳ ወደ አንበሳ
ቀን- አይታ ቀበሮ፣ ነገር ልታነሳ
እንደዚህ አለችው፣ በሰላ ወቀሳ
“ጌታው አቶ አንበሶ፤
የእግር-ጥፍር አሻራህ፣ ያስፈራኛል በጣም፤
ግን ምስሉ ይገርማል፤ መሬት ላይ ሲታተም
ወደ ራስህ ዞሮ፣ አንተኑ ሲጠቁም።
ከያዘው አቅጣጫ እንደማይመለስ፣ አሳምሬ ባቅም
የእግር- ጥፍር አሻራህ፣ ያስፈራኛል በጣም።
ከሄደበት መንገድ፣ ወደኔ ባይመጣም።”
ብሎ እንደፃፈው ነው።
አንዳንዶቹ፤ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የነበሩት የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት “በአሁኑ ሰዓት ሰላማዊ አብዮተኛ (Pacifist Revolutionary ማለት)  አትክልት-በል አንበሳ Vegetarian Lion ማለት ነው” ብለው እንደገለጹት ዓይነት ናቸው።
በአገሬው ዐይን ሌላ፣ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዐይን ሌላ፣ የሆኑም አሉ።  ሩሲያዊው ደራሲ ሶልዘንስቲን እንደሚለው፤ “ለእኛ ሩሲያ ውስጥ ላለነው፤ ኮሙኒዝም የሞተ ውሻ እንደማለት ነው። ለብዙ ምዕራባውያን ግን በህይወት ያለ አንበሳ ይመስላቸዋል” ማለት መሆኑ ነው።
ሌሎች አንበሶች ደግሞ፤ ዊንስተን ቸርችል 80ኛውን የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ለሁለቱም ምክር ቤቶች እንደተናገሩት፤ “አገሬ የአንበሳ ልብ አላት። እኔ ደግሞ እንደዳልጋ አንበሳ መጮህን ታድያለሁ”፤ የሚሉ ናቸው።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ ያየናቸው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የብዙኃን ንቅናቄ መሪዎች አንድ የጋራ ጠባይ አላቸው። ይህንን ፀባይ አፍሪካዊው የስዋሂሊኛ ተረት በደንብ ይገልጠዋል፡- “የተቆለመመ ጥፍር ያላቸው ሁሉ አንበሳ አይደሉም”።
ትላንት በተካሄደውም ሆነ ዛሬ በአገራችን እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ የሚጓዙ ኃይሎች ሁሉ መማርና ማወቅ ያለባቸው አንድ ቁም ነገር አለ፡-
“አንድም ከቀበሮ፤ አንድ ከአንበሳ ተማር”
አንበሳ ከወጥመድ ለማምለጥ አይችልም።
ቀበሮ ደግሞ ከተኩላ ለማምለጥ አትችልም።
ወጥመዱን ለማየት ቀበሮ ሁን።
ተኩላ እንዳይጠጋህ አንበሳ ሁን።

Read 1036 times