የዓለምአቀፍ የስነተዋልዶ ጤና ማእከል [world reproductive health center] መረጃ
እንደሚያሳየው በዓለም ላይ የተለያየ አይነት ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ ህግ ወይም አሰራር አለ። ሃገራት የሚከተሏቸው የአሰራር (ህግ) አይነቶች;
ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት በተገልጋዮች ጥያቄ ወይም ፍላጎት ብቻ ይከናወናል። ይህም እንደየ ሀገራቱ ቢለያይም አብዛኛዎቹ በፍላጎት ብቻ የሚሰጡት ሀገራት ያለቅድመ ሁኔታ አገልግሎቱን የሚሰጡት እስከ 12 ሳምንት[3ወር] ነው።
በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ ተመስርቶ የሚሰጥ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ13 ሀገራት ይገኛል። የእናት እና የጽንሱን የተለያዩ ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት አገልግሎትን ለማግኘት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች በህግ ተደንግገዋል።
የእናትን ህይወት ከሞት ለመታደግ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥባቸው ሀገራት 41 ናቸው። በመውለጃ እድሜ ላይ የሚገኙ 358 ሚሊዮን ሴቶች በነዚህ ሀገራት ይኖራሉ። እነዚህም የዓለምን 22 በመቶ ይሸፍናሉ።
ሙሉበሙሉ ጽንስ ማቋረጥ የሚከለክሉ ሀገራት ይገኛሉ። እነዚህም ሀገራት 24 ሲሆኑ በየትኛውም ሁኔታ ጽንስ ማቁረጥ ህጋዊ እውቅና የለውም።
በ1998 ዓ.ም በተሻሻለው የኢትዮጵያ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ መሰረት ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጠው በ4 ምክንያቶች አማካኝነት ነው።
በመደፈር ወይንም በዘመድ መካከል በተደረገ የግብረስጋ ግንኙነት ምክንያት ጽንሱ የተገኘ ከሆነ
የእርግዝናው መቀጠል በእናቲቱም ሆነ በጽንሱ ህይወት ወይንም በእናቲቱ ጤንነት ላይ አደጋ የሚያመጣ ሲሆን
ጽንሱ ሊደን የማይችል ከባድ የአካል ጉድለት ያለው[ዲፎርምድ] ሲሆን
አንዲት እርጉዝ ሴት የአካል ወይንም የአእምሮ ጉድለት ያለባት መሆንዋ ወይም ለአካለ መጠን ያልደረሰች በመሆንዋ የሚወለደውን ህጻን ለማሳደግ የህሊናም ሆነ የአካል ዝግጅት የሌላት ሲሆን
ደህንነቱ ስለተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ማሰልጠኛ ማኑዋል(መመሪያ) ማሻሻያ ላይ ጥቅምት 27፣ 28 እና 29 2017 ዓም ለ3 ቀናት በቢሾፍቱ ከተማ ውይይት ተደርጓል። የማኑዋሉ ማሻሻያ ላይ እየሰሩ የሚገኙት የፅንስ እና ማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የማህፀን ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ይርጉ ገብረህይወት ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ለመስጠት ኢትዮጵያ ባስቀመጠችው ህግ መሰረት በጤና ሚኒስቴር መመሪያ እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል። በህጉ መሰረት በህክምና ተቋም እና በህክምና ባለሙያ ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት እንዴት መስጠት እንደሚቻል እኤአ በ2006 ጤና ሚንስቴር የመጀመሪያውን ዝርዝር መመሪያ አውጥቷል። ለ2ኛ ጊዜ እኤአ በ2014 እንዲሁም ለ3ኛ ጊዜ እኤአ በ2023 መመሪያው(technical and procedura guideline) ተሻሽሏል። ለ3ኛ ጊዜ የተሻሻለው ሰነድ ከዓለም የጤና ድርጅት መመሪያ በመውሰድ መሆኑን ዶ/ር ይርጉ ተናግረዋል። በተመሳሳይ ለህክምና ባለሙያዎች የተዘጋጀው የማሰልጠኛ ማኑዋል (መመሪያ) ከዓለም ጤና ድርጅት እና ከተሻሻለው መመሪያ የተወሰደ ነው።
በጤና ሚንስቴር እናቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች መሪ ስራ አስፈፃሚ ውስጥ የስነተዋልዶ ጤና፣ የቤተሰብ እቅድ፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ዴስክ ባለሙያ በሪሁ ስባጋደስ ከዶ/ር ይርጉ ገ/ህይወት ጋር በተተመሳሳይ መልኩ እኤአ በ2022 እና በ2023 ለህክምና ባለሙያዎች መመሪያ እና ማኑዋል መዘጋጀቱን ገልፀው በየ5 ዓመት ማኑዋል(መመሪያ) እንደሚሻሻል ተናግረዋል። የስልጠና ማኑዋል የተዘጋጀው ለሚድዋይፉ፣ ነርስ፣ የጤና መኮንን እንዲሁም ለፅንስ እና ማህፀን ህክምና ባለሙያዎች ነው።
ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ማሰልጠኛ ማኑዋል (መመሪያ) ማሻሻያ ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል በማንኛውም የሰብአዊ እርዳታ በሚያስፈልገው ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የስነተዋልዶ ጤና ህክምና (ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት) እንዲያገኙ እና ሴቶች እራሳቸው ለእራሳቸው (selfcare) ህክምና እንዲሰጡ ማድረግ ይጠቀሳል። ዶ/ር ይርጉ ገ/ህይወት እንደተናገሩት እራስ አገዝ የህክምና አገልግሎት (self care) መስጠት በተለይም የስነተዋልዶ ጤና ላይ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ህክምናውን ሰዎች በእራሳቸው ማድረጋቸው ይበልጥ ምቾች ይሰጣቸዋል። ይህን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለእራሳቸው ከመስጠታቸው ጋር ተያይዞ ደህንነቱ ካልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ጋር በተመሳሳይ መልኩ በተጠቃሚዎች ላይ ችግር ሊያስከትል የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል የሚል ጥያቄ ለህክምና ባለሙያው አቅርበንላቸዋል። “ሰልፍ ኬር(self care) ስንል መድሃኒት በቀላሉ የሚገኝበት እና ሰዎች እንደፈለጉ የሚጠቀሙበት ሳይሆን በህክምና ባለሙያ የሚደገፍ ሰልፍ ኬር ማለት ነው። የህክምና ባለሙያው የሚቋረጠውን ፅንስ ለሰልፍ ኬር መሆን ወይም አለመሆኑን ይወስናል። የሚሆን ከሆነ ተጠቃሚዋ መድሃኒት በእራሷ ልትወስድ ትችላለች” በማለት ዶ/ር ይርጉ ገ/ህይወት ምላሽ ሰተዋል። አክለውም ታካሚዋ አገልግሎቱን ስትጠቀም የጎንዮሽ ጉዳት ካጋጠማት የህክምና ድጋፍ ለማድረግ ወደ ህክምና ተቋም (ባለሙያ) መሄድ እንደሚገባት ተናግረዋል። በአጠቃላይ አገልግሎቱን ተጠቃሚዋ የህክምና ባለሙያ ምክር በመከተል የምታገኝ (የምትጠቀም) ነው የሚሆነው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባወጣው መረጃ መሰረት በ1 ዓመት ውስጥ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ4 ጽንስ
መካከል አንድ ጽንስ እንደሚቋረጥ ይገመታል። ከዚህም ውስጥ 25ሚሊዮን ጽንስ ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ የሚቋረጥ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳስቀመጠው ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ በዓለምአቀፍ 45በመቶ ይይዛል። ከፍተኛውን መጠን 97 በመቶ በመሸፈን በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ቀዳሚ ናቸው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ ለእናቶች ሞት ምክንያት ከሚሆኑት 4 ምክንያቶች ውስጥ ይካተታል:: ከፍተኛ የሆነ የደም መፍሰስ፣ ኢንፌክሺን፣ ልጅ ከተወለደ በኋላ በሚፈጠሩ የተለያዩ እክሎች እና ደህንነትቱ ባልተጠበቀ መንገድ ጽንስ ማቋረጥ መንሴዎች ናቸው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ጽንስ ማቋረጥ የእናቶች ሞት መንስኤ በመሆን በዓለምአቀፍ 13በመቶ የሚይዝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ከሰሀራበታች በሚገኙ ሀገራት ደግሞ 50በመቶ ይሸፍናሉ።
በጤና ሚንስቴር እናቶች፣ ህፃናት፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች መሪ አስፈፃሚ ውስጥ የስነተዋልዶ ጤና፣ የቤተሰብ እቅድ፣ ወጣቶች እና አፍላ ወጣቶች ዴስክ ባለሙያ በሪሁ ስባጋደስ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በፊት ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ 36 በመቶ ለሚሆን የእናቶች ሞት መንስኤ ነበር። እንደ ባለሙያው ንግግር ጤና ሚንስቴር ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ላይ የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ስለሆነም ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንስ በማቋረጥ ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶች ቁጥር ቀንሷል።
የፅንስ እና ማህፀህን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የማህፀን ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ይርጉ ገብረህይወት እንደተናገሩት ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ላይ የሚሰራ ስራ ሲሻሻል ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንስ በማቋረጥ ምክንያት የሚደርሱ ችግሮች እንዲቀንሱ ያደርጋል። “ህይወትን ለመታደግ እና የተሻለ ማህበረሰብ ለመፍጠር በጣም ያግዛል ብዬ አስባለው” ብለዋል ዶ/ር ይርጉ ገ/ህይወት። እንዲሁም የህክምና ባለሙያዎች የተሻሻለ ማሰልጠኛ ማኑዋል ማግኘታቸው እውቀት እና ክህሎት ለማሳደግ ይጠቅማቸዋል በማለት ተናግረዋል። ለዚህም እንደምክንያት የጠቀሱት የህክምና ሙያ በየወቅቱ መሻሻል(update) ያለው መሆኑን ነው።
የፅንስ እና ማህፀህን ህክምና ስፔሻሊስት እንዲሁም የማህፀን ካንሰር ሰብ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ይርጉ ገብረህይወት ሰዎች ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ ከመፈፀም ይልቅ መብታቸውን በማወቅ ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተናግረዋል። እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መረጃ እና አገልግሎቱን በመስጠት ላይ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልእክት አስተላልፈዋል።
Monday, 09 December 2024 21:08
ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት
Written by ሃይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Published in
ላንተና ላንቺ