• የአገር ምክክርና የሕዝብ ጥያቄ… ለበጎ ነው! ወይም ለክፉ! (እንደ ምክክሩ፣ እንደ ጥያቄው ዓይነት ነው)።
ለሕዝብ ጥያቄ የተሰጠ “ፈጣንና አጥጋቢ ምላሽ” - ከነመዘዙ
የሙሴ ወንድም አሮን፣ “የሕዝብ ጥያቄ” ሲመጣበት ምን ዓይነት ምላሽ እንደሰጠ ታስታውሱ ይሆናል። ምንም ሳያንገራግር፣ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ፍላጎታቸውን አሟልቶላቸዋል። ለወትሮ ጥያቄና ቅሬታቸውን የሚያቀርቡት ለሙሴ ነበር። ሙሴ ግን ለጊዜው ከአጠገባቸው አልነበረም። “ሕገ መንግሥት” ሊያመጣላቸው ወደ ሲና ተራራ ወጥቷል።
እስክመለስ ድረስ፣ ጉዳይ ከገጠማችሁ አሮን እና ሑር አሉላችሁ። እነሱ ዘንድ ቀርባችሁ ጠይቁ ብሏቸዋል ሙሴ - ዘጸአት 24፡14።
ሙሴ ቶሎ አልተመለሰም። ህዝቡም ታውኳል፡፡ ከግብፅ ካመለጡ በኋላ በረኻ ላይ በምግብና በውኃ እጦት የተቸገሩት የእስራኤል ሰዎች፣ በሙሴ ላይ ብዙ ቅሬታዎችን እያቀረቡ በተደጋጋሚ ምሬታቸውን ገልጸዋል። አሁን ደግሞ ወደ ሲና ተራራ ሄዶ ሳይመለስ ሰነበተ። በረኻ ላይ ጥሎን ጠፋ ብለው እያሰቡ ለእሮሮ ተሰናድተዋል፡፡
ለነገሩ ሙሴም ተቸግሯል። መሪ የመሆን ኃላፊነት በጣም ከብዶታል። በየጊዜው የሚፈጠሩ ውዝግቦችና ቅሬታዎች በሙሉ ወደሱ ይመጣሉ። የእሱ ሸክም ናቸው። አንዳንዴ እያግባባ፣ ሌላ ጊዜ እየገሠጸ፣ ጊዜያዊ መፍትሔ እየሰጠና እያበረታታ ከባዱን የስደት ጉዞ ሊመራቸው ጥሯል። ነገር ግን የሚያዛልቀው አልሆነም።
ሁሉንም ጥያቄ ለመመለስና ለአቤቱታዎች ሁሉ ዳኝነት ለመስጠት ቢሞክርም፣ እንደማያዋጣ ገብቶታል። የሥነምግባር መርሖችና የሕግ አንቀጾች፣ የመከባበርና የዳኝነት ሥርዓቶች ያስፈልጋሉ። እነዚህን ፍለጋ ነው ወደ ሲና ተራራ የወጣው።
ሙሴን ተከትለው ከግብጽ የወጡት ስደተኞች ግን ተጨንቀዋል። ሙሴ ከሲና ተራራ ሳይመለስ በጣም ቆይቶባቸዋል። ባዶ እጃቸውን የቀሩ፣ እግዚሄር የራቃቸው መስሏቸዋል። የሚጨብጡት የሚዳስሱት ነገር ፈልገዋል። አሮን ዘንድ መጥተው፣ የሃይማኖት ምልክት፣ የእግዚሄር መታሰቢያ እንዲሰራላቸው ጠየቁት። የሥነ ምግባር መርሖችንና ሕጎችን በወጉ ማወቅ የሚያስፈልግ አልመሰላቸውም። የሃይማኖት ምልክት ብቻውን፣ ሥነ ምግባርና መተዳደሪያ ሕግ እንዲሆንላቸው ጠብቀዋል።
አሮን የወርቅ ጌጣጌጣችሁን ሰብስባችሁ አምጡልኝ አላቸው። የሃይማኖት ምልክት ጥጃ ሰራላቸው። ነገር ግን “ሰራሁላቸው” ብሎ አይናገርም።
ያመጡልኝን የወርቅ ጌጣጌጦች “እሳት ላይ ጨመርኳቸው፤ ጥጃ ሆኖ ወጣ” ብሎ ነው የሚናዘዘው። እጄ የለበትም ለማለት የፈለገ ይመስላል።
የሆኖ ሆኖ፣ አሮን ለጊዜው ሕዝብን ያረካ ቢመስለውም እንዳሰበው አልሆነለትም።
ሕዝቡም እንደተመኘው ቢያገኝም በጎ ለውጥ አላመጣለትም።
ይልቅስ፣ ሙሴ ከሄደበት ሲመለስ፣ “የኔ ወገን” “የእገሌ ወገን” የሚል የጎራ ክፍፍል ነው የተፈጠረው። በዚያው ቀን ሦስት ሺ ሰዎች አልቀዋል፤ ተጨፍጭፈዋል።
የሕዝብ ጥያቄና የለውጥ ሩጫ መጨረሻው እንዲህ ሊሆን ይችላል።
ለሕዝብ አቤቱታ የተሰጠ የቅጣት ዛቻ - ቀንበራችሁ ላይ እጨምርባችኋለሁ!
ከሙሴ በኋላ በሌላ ዘመን የተተረከ ሌላ ምሳሌ እናንሳ፡፡
በዛሬ ቋንቋ “የህዝብ ጥያቄ” ብለን ልንገልጸው እንችላለን፡፡ እነሱ ግን “የህዝብ ስሞታ” ወይም “የአገር ሽማግሌዎች አቤቱታ” ይሉታል፡፡ እናም በትህትና አቤቱታቸውን ለአዲሱ ንጉስ አቀረቡ፡፡ንጉስ ሮብዓም ይባላል፡፤የንጉስ ሰለሞን ልጅ ህዝብ ተሰብስቦ ቅሬታውን ለንጉሱ ገለፀ፡፡ የህዝብ ጥያቄ ቀረበ፡፡
የቀድሞ ንጉስ ብዙ ታክስ ጭኖብን ተቸግረናል፡፡ ብዙ በደሎችንም ፈጽሞብናል፡፡ ቀንበሩ ከብዶናል፡፡ አሁን ሸክማችንን ቀንስልን፡፡ መከራችንን ተውልን አለ፤ የአገሬው ህዝብ፡፡
አቤቱታቸውን ያቀረቡት በታላቅ ትህትና በጨዋ ወግ ነው፡፡ የአመፅ ጠረን የለውም፡፡ ለመዳፈር የፈለጉ አይመስሉም፡፡ ደግሞስ ከመንግስት ጋር መጣላት ምን ይጠቅማቸዋል?
መንግስትን በአመፅ ማንገጫገጭና ማንቀጥቀጥ ቢችሉ፣ ምን ያተርፋሉ? እንደ ጀብዱ ከቆጠሩት እንደ ጀግና እንታያለን ብለው ሊያስቡ ይችላሉ፡፡ ክብር እናገኝበታለን አኩሪ ታሪክ ይፃፍልናል ሊሉ ይችላሉ፡፡ አንዳች አዲስ ለውጥ ይመጣና አብዮት እንፈጥራለን ብለው ቢጠብቁ አይገርምም፡፡ የለውጥ ተስፋ ጥንትም ነበር፡፡ ዛሬም አብሮን አለ፡፡ ወደፊትም ይኖራል፡፡
የዘመናችን የፖለቲካ ጩከቶችና ባንዲራዎች ከግራም ከቀኝም የ“ለውጥ” አርማ የሚያራግቡ የለውጥ መፈክር የሚያስተጋቡ ናቸው፡፡
“የህዝብ ጥያቄ” የሚል ዲስኩር ከመንግስትም ይሁን ከተቀናቃኞቹ በኩል ሲታወጅ ወይም ሲለፍፍ ለመስማት ሞክሩ፡፡ “የለውጥ ጥያቄ” ከሚል ትርጉም ጋር ነው ወደ ጆራችን የሚደርሰው፡፡
ነገር ግን የለውጥ ዲስኩርና የህዝብ ጥያቄ ለበጎም ለክፉም ነው፡፡ ወደ ላይ ከፍታ ወይም ወደ ባሰ መቀመቅ፡፡
የለውጥ ሩጫ ሽቅብ ከመከራ የሚያወጣ ወይም ቁልቁል ወደ ገደል የሚያዳፋ ሊሆን እንደሚችል ለማወቅ አይፈልግም- አብዛኛው ፖለቲከኛ አብዛኛው ህዝብ፡፡
አገርን የሚያሻሽሉና የሚያበላሹ የለውጥ ታሪኮችን ብናውቅ እንኳ በፖለቲካ ውዝግብ ውስጥ ተጠምደን እንዘነጋዋለን፡፡
በደፈናው “የለውጥ ሩጫ” ይናፍቀናል፡፡
“የህዝብ ጥያቄ” ይማርከናል፡፡ ምን አይነት ለውጥ እንደምንፈልግ በዝርዝር ሳናስብበትና ሳንነጋገርበት ምን ዓይነት “የህዝብ ጥያቄ” እንደሚያስፈልግ ሳገናዝብና ለማመሳከር ሳንሞክር በሆታ እንስማማበታለን፡፡
የዘመናችን ፖለቲካ እንደዚህ ሆኗል፤ በእልፍ አቅጣጫ የተበታተነ ቢሆንም በደፈናው “ለውጥ” በሚል መፈክር ይስማማል፡፡
በለውጥ ማግስት እንደገና እየተበታተነ ይራበሻል፡፡ ለጥቂት ጊዜ ቅስሙ ተሰብሮ በምስቅልቅል አገሬው ተጎሳቁሎ፣ እርስ በርስ ተወጋግዞና ተወነጃጅሎ፣ ለለውጡና ለውጤቱ የየራሱን ትርጉም እየሰጠና የየራሱን ሰበብ እየለጠፈ…. ማዝገም ወይም መተከዝ ይጀምራል፡፡ ከ10 ወይም ከ15 ዓመት በኋላ የዛሬ ታዳጊ ልጆች ወደ ወጣትነት እድሜ ሲደርሱ፣ በአዲስ ጉልበት እንደገና እንደ አዲስ ይጀምሩታል፡፡ ለአዲስ የለውጥ ዲስኩር ትኩስ ተሰላፊና አጃቢ፣ አሯሯጭና ማሟሟቂያ ማገዶ ለመሆን ይቸኩላሉ፡፡
የለውጥ ሩጫ ለከፉም ለደጉም ሊሆን እንደሚችል እንደገና ተዘንግቶ የህዝብ ጥያቄ ህዳሴ ሊያሳድግ ወይም ለውድቀት ሊዳርግ እንደሚችል እንደገና ተረስቶ፣ የለውጥ ሩጫና ጫጫታ ይበራከታል፡፡”የህዝብ ጥያቄ” በሚል ሰበብ ምን አይነት ለውይ እንደሚያስፈልግ ሳያሰላስል በደፈናው ተሰብስቦ ያሰለፋል፡፡
የታሪክ ዑደቱ እንደገና ይጀመራል፡፡
የተበታተኑ ብጥስጣሽ ሀሳቦችንና የተምታቱ እልፍ ምኞቶችን በውስጡ ታቅፎ በአደባባይ በጋራ ይጮሃል፡፡ እልፍ ሀሳቦችን በብዥታ ይሸፍናቸዋል፡፡ ግራ ቀኙን አብጠርጥሮ የቅርብና የሩቁን አጣምሮ አይመለከትም፡፡
የዛሬ ሀሳቡን ለማጥራትና የዛሬ ተግባሩን ለመምረጥ ከትናንት ታሪክ አይማርም፡፡
የዛሬ መፈክርና እርምጃ…. ለነገ ምን ዓይነት ውጤትና መዘዝ እንደሚያመጣ አሻግሮ አያይም፡፡
ዳፍንት አስተማማኝ ጋሸና ከለላ፣የሁልጊዜ መመኪያ አለኝታ የሚሆንለት ይመስል….. ከትናንት ሳይማር የነገን ሳያብሰለስል ዛሬ በደፈናው “የህዝብ ጥያቄ” እያለ ይነሳል፡፡ የለውጥ ሩጫ ይመኛል፡፡
ከዚህ አንፃር ሲታይ የድሮው የአገር ሽማግሌዎች አቤቱታና የህዝብ ስሞታ ከዘመናችን የለውጥ አባዜ፣ ከዛሬው የፖለቲካ ዳፍንት በእጅጉ ይሻላል፡፡
ምን አይነት ለውጥ እንደሚፈልጉ አስበውበታል፡፡ መንግስት ከጫነባቸው ቀንበር ለመገላገል ነው የሚፈልጉት እና በታክስ ሸክም የነጠበ ትከሻቸውን ቀና ለማድረግ፣ የተጎሳቆለ ኑሯቸውን ለመጠገን፣ ከውድቀት ለማንሰራራት ነው የተመኙት፡፡
የተምታቱ እልፍ ምኞቶችን የተበጣጠሱ ሀሳቦችን ይዘው አልመጡም፡፡
መላ ቅጥ አለው - ሀሳባቸው፡፡
መንግስት እሽሩሩ እንዲላቸው አልጠየቁም፡፡ አጉርሰን አልብሰን አላሉም፡፡
መንግስት ጅራፉን እንዲሰብስብ፣ እግሩን ከትከሻቸው ላይ እንዲያነሳ ብቻ ነው የጠየቁት፡፡ ኑሯችንን ስራችንን እንምራ በሚል መልእክት ስር የታቀፈ ነው የሀሳባቸው ቅጥ፡፡
ዘዴውንም ተናግረዋል ታክስ ቀንስልን፡፡ በግርፊያ አትቀጥቅጠን የሚል ነው የዘየዱት መላ፡፡
በእርግጥ ወርቃማው የንጉስ ሰለሞን ዘመንን ነው እያማረሩ የነበሩ፡፡ በእስራኤል ምድር ደህና ሰላ ሰፈነባት ዘመን ፣የንጉስ ሰለሞን ዘመን ብቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጥበብና ግንባታ የተስፋፋበት ዘመንም ነው፡፡ ነገር ግን፣ የመንግስት ግንባታ ሲበራከት የዜጎች ኑሮ ይጎሳቆላል፡፡ ኑሮ ያወደዳል፡፡ በዜጎች ላይየግዴታ ሸክሞች እየበዙ እየከበዱ ይመጣሉ፡፡ ቅሬታቸውም ይሄው ነበር፡፡
ምኞታቸውም አዲሱ ንጉስ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ ምኞታችን ያሳካል ብለው በተስፋ ቢጠብቁ አይገርምም፡፡ በደፈናው ለውጥ መጥቷል፡፡ በቀድሞ ንጉስ ቦታ ሌላ አዲስ ንጉስ ዘውድ ደፍቷል፡፡
ምንም እንኳ ከዘመናችን የለውጥ አምልኮ በእጅጉ የተሻለ መላቅጥ ያው ሀሳብ የያዙ ቢሆኑም፣ ምክክራቸው በቁም ነገር ላይ ያተኮረ ቢሆንም፣ “የለውጥ ሩጫ” ለበጎ የሚበጅ ብቻ ሳይሆን ለክፉ የሚዳርግ ሊሆን እንደሚች አልጠበቁም፡፡
ንጉሱ የአገር ሽምግሌዎችን አቤቱታ ሰማ፡፡ “የህዝብ ጥያቄ” አደመጠ፡፡ መቼም፣ እያንዳንዱ ንጉስ የየራሱ ዝንባሌና ባህርይ፣ የእውቀት መስክና የሙያ ልምድ ይኖረዋል፡፡ ሁሉንም ነገር ማወቅ ሁሉንም ስራ በጥበብ ማከናወን አይችልም፡፡ ምንም የማይሳነው ሁሉን አዋቂ አምላክ አይደለም፡፡ ለዚያም ነው አማካሪዎችና ሙያተኞች የሚያስፈልጉት፡፡
የአዲሱ ንጉስ አማካሪዎች የየራሳቸው የመፍትሄ ሀሳብ አቀረቡለት፡፡ ክፉና ደጉን ከታሪክ ያዩ አስተዋይ አማካሪዎች፣… “ ህዝብ ያቀረበው አቤቱታ ክፋት የለውም፡፡ የዓመፅ ጠረን የለውም፡፡ በጎ ነው ፡፡ የተጫነባቸው ታክስ ቀንስላቸው፡፡ የሚደርስባቸውን በደል አስቀርላቸው ብለው ለንጉሱ ተናገሩ፡፡
የትናንትን ታሪክ ያልተገነዘበ፣ የነገን መዘዝ ያላስተዋለ የንጉስ ባለሟል ግን በዚህ አይስማማም፡፡ የህዝቡን አቤቱታ ሰምተህ ቀንበራቸውን ካነሳህላቸው የተጫነባቸውን ታክስ ከቀነስክላቸው ይጠግባሉ፡፡ ይንቁሀል፡፡ ደካማ ነው ብለው ይዳፈሩሃል፡፡ ቀንበራቸውን አክብደው፡፡ ተጨማሪ ታክስ አሸክማቸው ብሎ ይመክራል-አላዋቂ የንጉሱ ባለሟል፡፡
በእርግጥ፣ ብዙ ሰው አንዴ መንገድ ከተከፈተለት ማቆሚያ የለውም፡፡ ጥጋብ አይችልም፡፡ ልኩን አይጠብቅም፡፡ መከባበር አይገባውም፡፡ በትህትና ስታስተናግደው አናትህ ላይ መፈናጠጥ ያምረዋል፡፡ የሚበጀውን አያውቅም፡፡ ኑሮውን በነፃነት መምራት አይችልም፡፡ ነፃነት ማለት መረን ይመስለዋል፡፡
ኑሮን የመምራት ነፃነት ማለት ኑሮን የመምራት ሃላፊነት ማለት እንደሆነ አይገነዘብም፡፡ አደብ የሚያስገዛ ቀንበር ካልተጫነው፣ ብቅ ሲል ካልተኮረኮመ፣ ወጣ ሲል ካልተቀጠቀጠ፣ እጅና እግሩ በእስር ሰንሰለት ካልተቀየደ፣ በዘፈቀደ አገር ምድሩ ላይ መፈንጨት ያምረዋል፡፡
ነፃነት አናቱ ላይ እየወጣበት የስካር ስሜት እያደናበረው፣ ያጋጠመውን ሁሉ እየተራገጠ ወደ ገደል ይንደረደራል- ለህዝብም ለራሱም አይበጅም፡፡ ሌላውን ይፈጃል፤ ጦስ ይሆናል፡፡
ራሱን መግዛት አይሆንለትም፡፡ በገዥ እግር ስር ይንበረከካል፡፡ ታዛዥ ተገዢ ይሆናል፡፡ እየተረገጠ አፈር ይከድነዋል፡፡ እየተነዳ እንጦሮጦስ ይወርዳል፡፡ ወይም ሌሎችን ተገዢ ለማድረግ ከአናታቸውን ካልረገጥኩ ይላል፡፡
የጥሩና የመጥፎ፣ የክፉና የደግ፣ የሀጥያትና የፅድቅ ድንበሮችን ለመለየትና ለማነፃፀር የማይችል፣ መስመርና ሚዛን የሌለው፣ ሀላልና ሀራም የሚደባለቁበት መረን ይሆናል፡፡
ሲያቀርቡት …. ጓዳ ጎድጓዳውን ሁሉ ካልበረበርኩ፣ የሁሉንም ሰው ቤት ከላስተዳደርኩ በሁሉም ንብረት ላይ ካላዘዝኩ ይላል፡፡
ሲያሞግሱት የህዝብ አርበኛ ነኝ እያለ እንዳሰኘው ይጋልባቸዋል፡፡ እያዋከበ ይነዳቸዋል…. ይዟቸው መቀመቅ ይገባል፡፡
ፊት ከሰጡት እጅ እንደሰጡ ይቆጥረዋል፡፡ በሀሳቡ ከተስማሙለት ትክክል ተናግረሃል ካሉት ሁሉንም ታውቃለህ ያሉት ይመስለዋል፡፡
ይቅርታ ከጠየቁት እንደ ድክመትና እንደ ፍርሃት ይቆጥረዋል፡፡ ዘውዳቸውን ቀምቶ ቤተመንግስታቸውን ወርሶ፣ በትረ ስልጣናቸውን ነጥቆ ይቀጠቅጣቸዋል፡፡..
ወይ በፍርሃት ማምለክና ማንቆጥቆጥ እየተንቀጠቀጠ መገበር ወይም ደግሞ ሌሎች ሰዎችን ማዋረድ መርገጥና መዝረፍ ነው የሚታየው፡፡
እውነታውን እያየ ሰዎችን ለማስደሰት ሲል የዋሹትን ሁሉ እየተቀበለ ያስተጋባል ያራግባል፡፡
ሲበድሉትም ትልቅ ደግነት እንደዋሉለት ያመሰግናቸዋል፡፡ ሲያዋርዱትና ሲያሰቃዩት አባት ልጁን እንደሚቀጣ ለኔ አስበው ነው ይልላቸዋል፡፡ ሊፈትኑኝ ፈልገው፣ እንድጠነክርና እንድፀና አልመው፣ የምህረት ፀጋ ሊሰጡኝ፣ በሰላማዊ ሽልማት ሊለግሱኝ ስለወደዱ ነው ብሎ በውርደቱ ልክ ያከብራቸዋል፡፡
በስቃዩ ልክ ይቀድሳቸዋል፡፡
የዘረፉትን ያህል ይባርካቸዋል፡፡ እንደረገሙትም ይመርቃቸዋል፡፡ አማኛቸው፣ አገልጋያቸው፣ ባሪያቸው፣ ታዛዣቸው ይሆናል፡፡ በሀሳብም በተግባርም በመንፈስም ይነዱታል፡፡
ፊት ከሰጡት ደግሞ…. ቂላቂል ንግግሩን እንደ ጥበብ ቆጥረው እንዲያደንቁት ይመኛል፡፡ አይን ያወጣ የውሸት ወሬውን ፀሀይ እንደሞቀው እውነት ተቀብለው እንዲስማሙ እንዲቀበሉና እንዲያጨበጭቡ ይጠብቃል፡፡ ሲያቆስላቸው ተቆርቋሪያችን ነው ማለት አለባቸው፡፡
ውጋትና ቁርጠት ሲሆንባቸው፣ ሲያሳምማቸውና ሲያንፈራፍራቸው መድሃኒታችን ነው ብለው ማመስገን መደገፍና ማገዝ ይኖርባቸዋል፡፡ በጭፍን እንዲያምኑትና፣ እንዲታዘዙትና በባርነት እንዲያገለግሉት ይፈልጋል - ፊት ከሰጡት፡፡
አንገት መድፋት ወይም አንገት ማስደፋት፡፡
ፊት ከነሳኸው ቁጣህ ያንቀጠቅጠዋል፡፡ ቅስሙ ይሰበራል፡፡
ፊት ካሳየኸው ይተፋብሃል፡፡ መቃብር ይቆፍርልሃል፡፡
የሰው ግንኙነት እንዲህ ሲሆን በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ እንደ ቡችላ ይሆናል፡፡ በድፍረት ከነካከው እግርህ ስር ቱስ ቱስ እያለ ይከተልሃል፡፡ ፊት ከሰጠኸው አልጋህ ላይ ይወጣል፡፡ ቤት ውስጥ ይፀዳዳል፡፡
ኮስታራ ቁጡ ሲያገኝ ደግሞ ጭራውን ይቆላል፡፡
ፈርተህ ከሮጥክለት አንበሳ ይሆንብሃል፡፡ ጥርሶቹን አግጥጦ ያሳድድሃል፡፡ ተኩስ ከሰማ ደግሞ አገር መንደሩን ጥሎ ይጠፋል፡፡ ነገር አለሙ ይደበላለቅበታል፡፡ የምድር ጫፍ ድረስ ካልሮጠ ከአደጋ ያመለጠ አይመስለውም መሸሸጊያ መደበቂያ ይናፍቀዋል፡፡ ድምደፁን አጥፍቶ ይሸመጥጣል፡፡
የሰው ግንኙነት በዚህ መልክ የተረዱ የንጉስ ቀሽም አማካሪዎች የመፍትሄ ሳይሆን የጭካኔ ሀሳብ ቢታያቸው አይገርምም፡፡
የህዝቡ አቤቱታ “አባትህ ቀንበር አክብዶብናል አንተ አውርድልን የሚል ነው”፡፡ አንተ ግን ፊት አትስጣቸው ብለው ለንጉስ ሀሳብ አቀረቡ፡፡
“ትናሺቱ ጣቴ ከአባቴ ወገን ትወፍራለች” ብለህ ለህዝብ መልስ ስጣቸው ብለው ነገሩት፡፡ ወንዳወንድነትን ለመግለፅ የሚያገለግል የቅኔ አባባል ነው ያመጡለት፡፡ “ትንሿ የአካሌ ክፍል” የሚል ትርጉም አለው፡፡
በዚህም አላበቁም፡፡ እንዲህ መልስላቸው አሉት፡፡
አባቴ ከባድ ቀንበር ጥሎባችኋል፡፡ እኔ ግን ከቀንበራችሁ ላይ እጨምራለሁ፡፡
አባቴ በአለንጋ ገርፏችኋል፡፡ እኔ ግን በጊንጥ እገርፋችኋለሁ በላቸው ብለው የውሳኔ ሀሳብ አቀረቡለት፡፡
ይህንኑም ለህዝብ ተናገረ፡፡
በለዘብታ ከማስተናገድ ይልቅ “ጽኑ ምላሽ” ሰጣቸው፡፡
ፊት አትስጣቸው፡፡ አለበለዚያ ይደፍሩሃል፡፡
ጨክነህ ወንዳ ወንድነትህን ብታሳያቸው ያከብሩሃል፤ ይፈሩሃል፤ ይገዙልሃል እንደማለት ነው፡፡
አብዛኛው ህዝብ አመፀ እስራኤል ለሁለት የተከፈለችው የኔ ነው ይላል ትረካው፡፡ ከዚያ ወዲህ ሰላም አላገኘችም፡፡ ሦስት ንጉሶች ብቻ ናቸው አገሪቱን ጠቅልለው ለመግዛት የቻሉት፡፡ ለዚያውም የሶኦልና የዳዊት ንግስና በእርስ በርስ ግጭት የተመሰቃቀለ በጦርነት የተተራመሰ ነው፡፡ በንጉስ ሰለሞን ዘመን ብቻ ነው እስራኤል ሰላም ያገኘችው ለ40 ዓመታት ብቻ፡፡ ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለሁለት ተከፍላ በጠላትነት በሚተያዩ ጎራዎች የምትጠራ ሆናለች፡፡ ብዙም ሳይቆይ በተለይ ከዛሬ 2800 ዓመታት ወዲህ ለበርካታ ምእተ አመታት የውጭ ሃያል መንግስታት የሚፈራረቁበት የመከራ ምድር ሆናለች፡፡
Saturday, 14 December 2024 11:58
“ቅር ካላችሁ ቀንበራችሁን አከብዳለሁ” ወይስ “ያሻችሁን ብትጠይቁ እሰጣለሁ”
Written by ዮሃንስ ሰ
Published in
ነፃ አስተያየት