Saturday, 14 December 2024 11:59

በብልጥ አትሞኝ፣ በሞኝ አትመራ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

  አንድ ባለፀጋ ሊሞት ሲል ኑዛዜ ማድረግ ፈለገና፣ ሦስቱንም ልጆቹን ጠርቶ ከመናዘዙ በፊት አንድ ጥያቄ አቀረበላቸው።
“ለመሆኑ ወፍ ለመሆን የምትችሉ ቢሆን ኖሮ፣ የትኛዋን ዓይነት ወፍ ለመሆን ትፈልጋላችሁ?” በመጀመሪያ የመለሰው ታላቅየው ልጅ ነበር። እሱም፤ “እኔ ሁልጊዜ እየቀማችና እየዘረፈች የምትኖረውን ጩልሌ መሆን ነው የምፈልገው” አለ።
ሁለተኛው ልጅ- “እኔ ሸመላ የምትባለውን የወፍ ዓይነት ለመሆን ነው የምፈልገው። ሸመላ ከባልንጀሮቿ ጋር በማህበር በአንድነት ሆና ትበርራለች። እኔም እንደዚህ ማድረግ እወዳለሁ” አለ።
ሦስተኛው ልጅ- “እኔ ዝዬ ለመሆን ነው የምፈልገው። ይህቺ ወፍ ረዥም አንገት ያላት ናት። አንዳች ነገር ለመናገር ባሰብኩኝ ጊዜ ከልቤ እስከማወጣው፣ ይህን ረዥሙን አንገት እስኪያልፍ ድረስ ብዙ ጊዜያት አገኛለሁ” አለ።
አባትዬው ሁሉንም መልስ ካዳመጠ በኋላ፣ ጩልሌ ለመሆን ለተመኘው ልጅ፤ “ሰላምና የሀቀኝነት ሥራ ባለበት አገር ያለኝን ርስቴን በሙሉ አውርሼሃለሁ። በሸፍጥ ለመቀመጥ አይመችህምና።”
ሸመላ ለመሆን ለተመኘውና በማህበራት ለመኖር ላሻው ልጁ፤ “ስምምነት የሌለበትና የጦርነት አገር በሆነው የአገራችን ክፍል ያለኝን ርስቴን ሁሉ አውርሼሃለሁ። በዚህ የሚኖሩ አውሬዎችና ቂማቸውን በእኛ ላይ ሊወጡ የሚፈልጉ ክፉዎች ሲመጡ ታበርድልናለህና።”
ለሦስተኛው ልጅ እንዲህ አለው፤ “አንተ ብልህና ጥንቁቅ በመሆንህ ውርስ አያሻህም። የሚበቃህንና የሚያስፈልግህን በጥበብህና በበሳል ተግባርህ ልታገኘው ትችላለህ”
ውሎ አድሮ ይህ ሦስተኛ ልጅ የአገር መሪ ሆነ።
***
ብልህ መሪ ማግኘት መታደል ነው። ቀማኛና ጩልሌ መሪ ማግኘት መረገም ነው። ብልህ መሪ ሸፍጥ አያጠቃውም። ብልህ መሪ በአስተዋይነቱ ለመምራት እንጂ በብልጥነቱ አታሎ እንደ መንጋ ለመንዳት አይሻም። ብልህ መሪ፤ አውሬዎችንና ቂማቸውን በእኛ ላይ ሊወጡ የሚፈልጉ ክፉ ሰዎችን ሁሉ እንደየአመጣጣቸው ይመልሳቸዋል- እንደየብልህነታቸው ድል ይመታቸዋል። ብልህ መሪ አስቦ ይናገራል። እንደ ዝዬ አንገተ- ረዥም ስለሆነ የልቡን ለመናገር ጊዜ ይወስዳል። አመዛዝኖ እንጂ በግልፍተኝነት፣ አጢኖና አርቆ- አስቦ እንጂ ከአፍንጫው ባልራቀ መንገድ ጊዜያዊ ድልን ለመጎናጸፍ ብሎ የችኩል መልስ አይሰጥም። በራሱም ጥበብና ዕውቀት ይተማመናል እንጂ በቡድኑና በወገኑ ግፊት ዘራፍ አይልም። እንዲህ ያለ በሳል መሪ ያገኘ ህዝብ፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ተቋም ወይም ድርጅት በለስ የቀናው ነው! እጁን ታጥቦ የሠራው እንዲሉ። ሁሌ በትላንት መመካትና በትላንት መታበይ አያዋጣንም።” በጠቅል ጊዜ ያልተማረ
 ማዘኑ አይቀርም እያደረ” ማለት ዕውነትነት ቢኖረውም እንኳ፣ በዚያ ተገልግለን ፍሬ ካላፈራን፣ የዛሬን ትምህርት ከመቆርቆዝ አናድነውም። ያኔ ያኔ ነበር። ዛሬ ዛሬ ነው። ከያኔዎቹ በከፊልም ለዛሬ መቆርቆዝ አዋጥተዋል። ያባት ዕዳ ለልጅ ነውና!
የታሪክ የመጨረሻ ክፋቱ፤ በተደገመ ቁጥር የበለጠ ዋጋ ማስከፈሉ ነው- ይላሉ። በሀገራችን መንግሥታት በተቀያየሩና ነባሩ ፈርሶ፣ መጪው ተወልዶ አንገቱ እስኪጠና ድረስ ምንጊዜም አንድ ጠባብ የመንሸራሸሪያ ኮሪደር ሳይፈጠር ቀርቶ አያውቅም። ይህ ኮሪደር በሁለት የታፈኑ ክፍሎች መካከል እንዳለ የመተንፈሻ ቦታ ያለ ነው። ይህ የመተንፈሻ ቦታ ትክክለኛ ሳንባ ያላቸው ብቻ አየር የሚወስዱበትና አረፍ፣ ሰከን ብለው የሚተነፍሱና የሚያስቡበት ነው። ይህ የመተንፈሻ ቦታ ከአብዮት ወይም ከአንዳች ዓይነት መንግስታዊ ለውጥ በኋላ “ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ” “የሽግግር መንግስት” (Interim)፣ “መረጋጊያ ኮሚሽን”፤ “የዕውቀትና የእርቅ ኮሚሽን” (Truth and Reconciliation Commission) እንደማለት ነው። ይህ ኮሪደር ከጦርነት በኋላ ፋታና እፎይታ ሲገኝ የቆሰለውን ለማከም፣ የፈረሰውን ለመገንባት፣ የሞተውን ለመተካት፣ የባሰበትን ለመገላገል፣ ካሣ ፈላጊው ገድሉን ለመደርደር፣ ተሿሚው  ቢሮውን ለማጠን፣ ነጋሲው ዘውድ  ለማማረጥ የሚያገኘው የመተንፈሻ ቦታና ጊዜ እንደማለትም ነው። ፓርቲዎች ተፈረካክሰው፣ ድርጊቶች አብጠው ፈንድተው እንደገና መልካቸውን ለማበጀት፣ ራሳቸውን ደግመው ለመሥራት ሲሞክሩ፣ የተሳሳተው ሲያቀረቅር፣ ያልተሳሳተ የመሰለው “ያለ እኔ ማን አለ!” በማለት ቀና ቀና ሊል ሲቃጣው፣ አይሞቀኝ አይበርደኝ ባዩ ደግሞ አንዴ ከረባት ሊያስር፣ አንዴ ቁልፉን ሊፈታ ሲያኮበኩብ፣ በመካከል የሚገኝ የአየር ጊዜ፣ የመተንፈሻ ሰዓት ነው። ይህ ወቅት “ምን ይቀጥል ይሆን?” በሚልና አብዛኛው ሰው በግምት ይህ ይሆናል፣ ያ ይፈርሳል፣ ያ ይሾማል፣ ያ ይወርዳል፣ ያ ባለበት ይረግጣል የሚልበት ጊዜ ነው። በቦታውና በሰዓቱ ፈጦ እስኪመጣ ድረስ፣ ዕውነቱ ግን መካከል ተቀምጦ የሚስቅበት ሁኔታ ይፈጠራል።
(We all dance around and guess
The truth, sits in the middle, and laughs.
እንዲል ሮበርት ፍሮስት።)
በሀገራችን የፋታ ጊዜ ወይም የመተንፈሻ ኮሪደርን በአግባቡ የተጠቀምንበት ወቅት ነበር ለማለት አያስደፍርም። በገጠመን የመተንፈሻ ጊዜ ሁሉ ለአሸናፊው በማጨብጨብ፣ አሊያም ከተሸናፊው ጋር ሙሾ በማውረድ የምናጠፋው ዕድል ቁጥር-ስፍር የለውም። “በጣም አንጣላ፤ ከታረቅን እንዳይቆጨን” የሚለውም፤ “ከመታህ ድርግም፣ ከዋሸህ ሽምጥጥ!” የሚለውም “አምሳም ታለበ መቶ ያው በገሌ” የሚለውም፣ “አፌ ዝም ብሎ እጄን ይጎራረሱበታል” የሚለውም… ሁሉም የየራሱን ዘፈን በማዳመጥ ጊዜውን ያሳልፍና ኋላ ብልጡ ሲብለጠለጥበት ፀጉሩን ይነጫል። አምባገነኑ “ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አረግናቸው” ሲለው “ዋ ነዶ!” እያለ ማድቤት የተሰቀለ ጭስ የጠጣ ጠመንጃ እንደነበረው ይተርካል። የጀግና አገር እንደነበረው በቁጭት ያወሳል። ሁሉም ካለፈ በኋላ! ራሱን እስኪነካው ድረስ ሌላው ተሸወደ ብሎ በኩራት ይስቃል። “የኔ ድንግል ሲጠፋ ሰው አልሰማም። የሷ ግን የባሰ ነው፤ አደባባይ ወጣ!” አለች፤ እንደተባለችው ልጃገረድ፤ አሟሟትንና አወዳደቅን በማወዳደር መገበዝ እንደ ገድል ተቆጥሮ የነበረበት ጊዜም ጥቂት አይደለም።
በጊዜያዊና ዘላቂ መንግሥት መካከል፣ በጊዜያዊና ዘላቂ ዓላማ መካከል፣ በጊዜያዊና ዘላቂ ሰው መካከል የመተንፈሻ ቦታ፣ የመሸጋገሪያ ኮሪደር አለ፣ ነበረ፣ ይኖራል። አገር የሚገነባው ይህን ዐይነቱን ሥፍራ ልብ በማለትና ትኩረት በመስጠት ነው። ብልጥ መሪ ሄዶ ብልህ መሪ እስኪገኝ፣ አፍአዊ አለቃ ተወግዶ ልባም አለቃ እስክናፈራ፣ ለቋሳ ፓርቲ ፈርሶ ጠንካራ ፓርቲ እስኪተባ፣ ጊዜው የደረሰ ተሰናብቶ ጊዜው ያልደረሰ እስኪተካ፣ ስግብግብ ምሁራዊ አመለካከት እስኪከስምና ጥልቀት ያለው ደግ አስተሳሰብ እስኪናኝ፣ ረጋና ሰከን ብሎ አገርንና ህዝብን የሚያስብ ዜጋ መኖር ይኖርበታል። ከአድልዎና ከሙስና ከዘፈቀደ አመራር የሚወጣው፣ ከተንሸዋረረም፣ አንደኛውን ዳፍንተኛ (Obscurant) ከሆነም አተያይ ለመዳን የሚቻለው በመማር፣ በማስተዋልና በቅንነት በማሰብ ነው። ለሀገር የሚበጅ ረብ- ያለው ዕውቀትና ሙያ ሳይጨብጡና ስለ ነገ አንዳችም ራዕይ ሳይዙ፣ በግምገማ ኃይል ብቻ ሌላውን እያወረዱና እያዋረዱ መጓዝ ሁሌ አይመችም። ሁሉን ለምዕራብ አማልክት ትቶም ብሔራዊ ህልውና አይገኝም። ለኃያላን ተስያለሁ፤ ከእገሌ ተዋውያለሁ፣ ከእገሌ ተማምያለሁ፣ በእገሌ መጀን ብያለሁ፣ ቢሉ የራስ አገራዊ የሰው ኃይል በተቀናጀ ንጣፍ ላይ ካልተገነባ፣ የራስን አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ካልተቻለና የራስን መተማመን ካልፈጠሩ፣ የውጪው ትርፍ ነው። ዋናውን ይዞ ይሄዳል እንጂ ዋና አይሆንም። ደካማ አገር፣ ከደካማ አገር፣ ውሽልሽልን ከውሽልሽል አቆራኝቶ ለማቆም ምንም ዓይነት ማሰሪያ ገመድ አይገኝም። አብሮ ለመውደቅ ያግዝ እንደሁ እንጂ እውነተኛ ህብረት አይፈጥርም። ቴሌዎች “የኬብል ብልሽት” የሚሉት ዓይነት ሳይሆን አይቀርም።
ከወፍ ወፍ ይለያልና ጭልፊቱን፣ ሽመላውንና ዘዬውን ያልለየ ህዝብ ምኔም ከችግር አይወጣ። ሁሌም ከአደጋ አያመልጥም። ብስለትና ብልህነት እጅግ ወሳኝ ነው። ብልጥ መሪ በዕለት በዕለቱ ጉዳይ ዐይንን ያውራል። ሞኝ መሪ በጭፍንና በእልህ ገደል ይከታል። በብልጥ አትሞኝ፣ በሞኝ አትመራ የሚባለው እንግዲህ ለዚህ ነው!

Read 1313 times