Saturday, 14 December 2024 12:22

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

• ከ125 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል
                    • ፌዴሬሽን ከተመሰረተ 70 ዓመቱ ነው
                    • የተጣራ ሀብቱ ከ257 ሚ.ብር በላይ፤ ከ114 ሚ. በላይ ዓመታዊ ገቢ


       የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ከሳምንት በኋላ 28ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ያደርጋል ። ታህሳስ 12 እና 13 ላይ በስካይላይት እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ጉባኤ ፤ በቀጣይ አራት አመታት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን የሚመሩትን ፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ይመረጣሉ።  
በተለይ ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት የሚደረገው ፉክክር ትኩረት እየሳበ መጥቷል። በእጩ ፕሬዝዳንትነት  ከቀረቡት እንዲሁም መካከል   አራቱ ተወዳዳሪዎች የምርጫ ዘመቻውን በማጧጧፍ ላይ ናቸው።   የቀድሞዎቹ አትሌቶች ስለሺ ስህንና ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ፤ የተከበሩ አቶ ዱቤ ጁሎ እና ኢንጅነር ጌቱ ገረመው መሆናቸው የምርጫ ፋክክሩን አጓጊ አድርጎታል።
በአትሌቲክሱ ውስጥ አትሌት ሆነው ያለፉ፤ በዓለም አቀፍ መድረኮች ደማቅ የውጤት ታሪክ የፃፉ፤ የኢትዮጵያን ክብርና ዝና ያገዘፉ፤ በስፖርቱ መስክ ከፍተኛ ትምህርት የቀሰሙ፤ የአትሌቲክስ አስተዳደሩን ለረጅም ዘመን ያገለገሉ፤ የአትሌቶችን ጥቅምና መብት በማስከበር የሠሩና ተምሳሌት የክለብ አደረጃጀት የፈጠሩ... እጩ ፕሬዝዳንቶች  ናቸው።
በኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ስፖርት ከ125 ዓመታት በፊት በትምህርት ቤቶችና በወታደራዊ ካምፖች በመዘውተር  እንደተጀመረ ይነገራል፡፡ ስፖርቱን በበላይነት የሚመራው ተቋም ‹‹ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን›› በሚል መጠሪያ ከተመሠረተ ደግሞ ከ70 ዓመታት በላይ ሆኖታል። በዓለም አቀፉ የስፖርት ህግ መሠረት  የተቋቋመው ፌዴሬሽኑ የሀገሪቱን ሕግና ደንብ ጠብቆ በሕዝብ፣ በመንግስትና በድርጅቶች ድጋፍ  ይንቀሳቀሳል። አህጉር አቀፍና ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተግባራትን ያከናውናል።  የወጣቱን ትውልድ ግንዛቤና ተሳትፎ በማጠናከር የላቀ ችሎታ ያላቸው ምርጥ ስፖርተኞች ያፈራል ። በአለም አቀፍ ደረጃ የአገራችንን ተወዳዳሪነትና ተጠቃሚነት ማስፋትን ዓላማው ያደርጋል ፡፡
 ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር፣ ከአዲዳስ ኩባንያ፣ ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን፣ ከምስራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅንና ከአቻ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ጋር  የሚሰራ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር(IAAF)፤በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን (CAA) እና በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሪጅን (EAAR) አባልነቱም  ይታወቃል ፡፡
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ በሚያዘጋጃቸው 10 የሀገር ውስጥ ወድድሮች   በሁለቱም ፆታዎች ከ5900 በላይ አትሌቶች ፤ ከ1000 በላይ የስፖርት ባለሙያዎችና ከ8000 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ይሆናሉ።
በአንድ የበጀት ዓመት ለአገር ውስጥ ውድድር፤ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮች፤ ለሽልማት፤ ለአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማዕከላትና ፕሮጀክቶች ስልጠና ድጋፍ እንዲሁም በአስተዳደራዊ ወጭዎች ከ126 ሚሊዮን ብር በላይ ይከፍላል፡፡
ከወጭዎች መካከል ለሀገር ውስጥ ውድድር ከ15.37 ሚሊዮን ብር በላይ ለአህጉራዊና አለም አቀፍ ውድድሮች እስከ 64 ሚሊዮን ብር ወጭ  እንደሚያደርግም መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተጣራ ሃብት ከ257 ሚሊዮን   ብር በላይ ሲሆን ከስፖንሰርሺፕ እና የተለያዩ ምንጮች ደግሞ ከ114 ሚሊዮን  ብር በላይ ገቢ ይሰበሰባል።
በ28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ የሚመረጠው አዲስ አመራር ስፖርቱን ወደተሸል ምዕራፍ ለማሸጋገር ከፍተኛ ኃላፊነት የሚኖርበት ይሆናል። ስፖርት አድማስ ከእጩፕሬዝዳንቶቹ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ የተለያዩ አጀንዳዎች ተዳስሰዋል።  ከዓለማችን ምርጥ ፌደሬሽኖች ተርታ ለመግባት መከናወን ያለባቸው ተግባራት፤ መከናወን ያሰባቸው  የአዲስ አበባ ስታድዬም ትራኮች የማሟሟቂያ ሜዳና የሜዳ ላይ ተግባራት የሚከናወንባቸውን በዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ተቋማት በአመራር ደረጃ ስለመግባታቸው ሃላፊነት ስለማግኘት፤ የአለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮችን ስለማዘጋጀት የአትሌቲክስ ልህቀት ማዕከል ለመገንባትና የአትሌቲክስ ሙዚዬም ለማደራጀት ተወያይቷል።

Read 231 times