Monday, 16 December 2024 00:00

እጩ ፕሬዝዳንት ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም

Written by  ግሩም ሰይፉ
Rate this item
(1 Vote)

  ስፖርቱ በስፖርተኛ ስፖርቱን ባሳለፈ ይመራ የሚለውን ሃሳብ ከሚያንፀባርቁ አንዱ ነኝ። ከ15 ዓመታት በላይ በሯጭኘት ቆይቻለሁ። ፅናት ፤ ፍጥነት ወቅታዊ ብቃት የስፖርት ቋንቋዎች ናቸው። እነዚህን ቋንቋዎች ስፖርተኛ ቢሰራቸው ስፖርተኛ ቢያስተዳድራቸው በጣም የቀለለ ይሆናል።
የስፖርት ስርዓትና ህግ ምንም እንኳ አመራር ሆኜ አይመለከተኝም ብል አሠልጣኝ ዳኛ አለ። አመራር ስትሆን ለስፖርት የቀረበ ሲሆን ስልጠናውም ዳኝነቱም የቀለለ ይሆናል። ዓለምአቀፍ ህግና ደንብን ተከትሎስፖርተኛን መምራት የሚል አቋም ነው የማራምደው። ይህን ስፖርቱ የስፖርተኛ ብቻ ነው እያልኩ አይደለም። በስፖርቱ አጥንተው ተምረውና ሰርተው ጥሩ ደረጃ የደረሱ ሊኖሩ ይችላሉ ። በተግባር ስፖርተኛ ሆነው ያለፉ ወደ አመራር የሚመጡ ከሆነ አጠቃላይ እድገቱን ሊያግዝ ይችላል ።
እጩ ፕሬዝዳንት ሆኖ መቅረቡና ፉክክሩ
በስፖርት ቋንቋ ካወራን ሁሉም ተወዳዳሪ የራሱን ቀለምና ሃይል ይዞ ነው የመጣው። የሚናቅ ተወዳዳሪ አለ ብየ አላስብም። ሁሉም የነራሱን ልምምድ አድርጎ የየራሱን አቅም ይዞ ይመጣል። ሁሉም ለመስራት ነው። እጩ ፕሬዝዳንቶቹ ይህ ጠንካራ ጎን ይህ ደካማ ጎን አላቸው ብዬ አልጠቅስም። ነገር ግን እኔ የተሻልኩ ነው ብዬ አስባለሁ። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ከማንም በላይ አውቀዋለሁ። በአትሌቶች ተወካይነት ያገለገልኩት ውጤታማ ተወዳዳሪ በሆንኩበት ወቅት ነው። የአትሌቶች መብትን ለማስከበር በስፋት ስንቀሳቀስ ነበር። የኢትዮጵያ አትሌቶች ቤታቸውን መረከብ አለባቸው የሚለው እንቅስቃሴ ተፈጥሮ እነ ኃይሌ ገዛኸኝና ደራርቱ  ወደ ስፖርት አስተዳደር እንዲመጡ አድርገናል። በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በምክትል ፕሬዝዳንትነት ለአራት አመታት ሰርቻለሁ። ከኦሎምፒክ ኮሚቴው ጋር የሰራሁበት ልምድም አለኝ።
ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ስመጣ የቅንነት ችግር የለብኝም። በቅንነት ፌዴሬሽኑን እንደማስተዳድርና ህግና ስርዓቱን እንደማስከብር አምናለሁ። ስራ አስፈፃሚ ያፀደቀውን በልበሙሉነት ለማስፈፀም፤ ከማንም ተፅዕኖ ሳይኖርብኝ እሠራለሁ።
አትሌቲክሱን በደንብ አውቀዋለሁ። የስልጠና ስርዓቱን ለማስተካከል ፍላጎት አለኝ። የባለድርሻ አካላትን ሐሳብ አስተባብሬ ለመንቀሳቀስ ነው እቅዴ።
በስፖርት መሠረተ ልማትና በተለይ በመሮጫ ትራክ ላይ
ታላላቅ አትሌቶች ያፈራች አገር በትራክ ችግር ውስጥ መሆን የለባትም።
በአዲስ አበባ ስታድየም በአበበ ቢቂላና በስፖርት አካዳሚ ያሉት ትራኮች በቂ አይደሉም። የሚገርመው  ትራክ ብርቅ ሆኖብን በዓለም አትሌቲክስ የትራክ ውድድሮች ጥሩ ውጤት እያስመዘገብን መቀጠላችን ነው። ወደ ፌዴሬሽኑ አስተዳደር ስንመጣ አሁን ካለው በተሻለ የአትሌቲክስ መሠረተልማቶችን እንዘረጋለን። በመሮጫ ትራክ ግንባታ የተሟለ አቅም እንዲኖረን የብዙ  አገራት ተመክሮዎችን አጥንተን ወደ ስራ የምንገባበት ነው። በእኔ አመለካከት የመሮጫ ትራክ ለመዘርጋት የግድ ስታዲየም መገንባት አያስፈልግም። ትራኮችን በገላጣ ሜዳ፤ በጫካዎች ፤ በዮኒቨርስቲዎችና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማንጠፍ ይቻላል። የፌዴሬሽኑን አመራርነት ተረክበን በሚኖረን የስራ ዘመን አንድ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ትራክ በስራ ለማወል እቅድ ይዘን ነው። በሌላ በኩል የአሸዋ ትራክም ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ እጅግ ወሳኝ ነው። ፌዴረሽኑ የሚጠቀመው ብቸኛው የአሸዋ ትራክ በለገጣፎ የሚገኘው ነው። ተጨማሪ ሁለትና ሶስት የአሸዋ ትራኮች ለመስራት ነው የምናስበው። ባለ6 እና ባለ8 መም የአሸዋ ትራክ ገላጣ ሜዳ ተደላድሎና ፍሳሽ ተበጅሎት በቀላሉ ሊሰራበት ይችላል። በአዲስአበባ እና በሌሎች ክልሎች ይህን አይነት የስፖርት መሠረተልማት ለውጥ እንፈጥራለን።
ብሔራዊ ቡድን በተመለከተ
ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ካስፈለገ ቅድሚያ መሠጠት  ያለበት በአጭርና መካከለኛ ርቀቶችና በሜዳ የስፖርት ተግባራት ላይ ነው። ውጤታማ በሆንባቸው የረጅም ርቀት ውድድሮች ተተኪዎች ለማፍራት ከአጭር ርቀት ጀምሮ በ800 እና በ1500 ውድድሮች አትሌቶችን በብሔራዊ ቡድን ይዞ በመስራት ይሻላል። በአጭርና መካከለኛ ርቀቶች ለዓለም አቀፍ ውድድሮች የሚያበቃ ሚኒማ የምናሟላበት አሰራር መፍጠር ነው የማስበው። በሌላ በኩል ብሔራዊ ቡድን ካስፈለገን በሜዳ የስፖርት ተግባራት  በዝላይና በውርወራ ስፖርቶች ለዓለምአቀፍ ውድድሮች ብቁ የሆኑ አትሌቶች ለማግኘት ነው። በሳይንሳዊ የስልጠና መንገድ አቅም ያላቸውን አትሌቶች በጥናት መልምሎ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ተይዘው ከተሰራ ለውጥ ይፈጥራል። በዚህ መልኩ ለሚገነባ ብሔራዊ ቡድን ደግሞ በልምምድ ሜዳ በመሮጫ ትራክና በስፖርት ቁሳቁሶችና መሣሪያዎች የተሟላ መሠረልማት መገንባት የግድ ይሆናል።
በአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ደረጃ ስለመያዝ አለምአቀፍ ውድድሮችን ስለማዘጋጀትና በዓለም አትሌቲክስ አመራር ሆኖ ስለመግባት
በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ስር የሚካሄዱ ውድድሮች ዓለምአቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ያሟላ የለም። ለምሳሌ ጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ከአምስት አገራት የተወሰኑ ተሳታፊዎች ስላሉት እንጅ ዓለም አቀፍ ልኬትና ደረጃ ማረጋገጫ የተሰጠው አይደለም። በአገር ውስጥ የሚካሄዱ ውድድሮች በዓለም አቀፍ አሰራር በባለሙያዎች ልኬትና ደረጃ ተሰርቶ የማረጋገጫ ሰርተፍኬት ያስፈልጋቸዋል። በኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ የሚመዘገብ ሰዓት ወደዓለምአቀፍ ውድድር የሚወስድ መሆን አለበት። በአገር ውስጥ ውድድሮች መወሠንም የለብንም። በአገሪቱ ስታድየሞች የሚነጠፉ ትራኮችና ተያያዥ መሰረተ ልማቶች አህጉራዊ ና ዓለምአቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚችሉበት ደረጃ መገንባትና የብቃት ማረጋገጫ እንዲኖራቸው በሚያስችል አቅጣጫ ለመሥራት እንጥራለን።
ኢትዮ ትሬል የተራራ ሩጫን በማዘጋጀት ያገኘነውን ልምድ ወደ ፌዴሬሽኑ እናመጣዋለን። ኢትዮጵያ በዓለም የተራራ ሩጫ ፌዴሬሽን ውስጥ መግባት አለባት። የኢትዮጵያ የተራራ ሩጫ መሥፋፋት  ለኢትዮጵያ አትሌቶች ተጨማሪ  የውድድር እድል የሚፈጥር ነው።
የኬንያ አትሌቲክስ በዓለም የአትሌቲክስ አመራርና አስተዳደር ውስጥ በቂ ውክልና እያገኘ መምጣቱን በቁጭት ተመልክተን መንቀሳቀስ አለብን። ኬንያዎች በዓለም አትሌቲክስ ማህበርና በዓለምአቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በተለያዩ የኃላፊነት ገብተው መሥራተቸው ዓለምአቀፍ ውድድሮች የማዘጋጀት እድላቸውን አስፍቶታል፤ በአትሌቲክስ መሠረተልማቶችና የእድገት አቅጣጫዎች የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ናቸው። በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን  በኩል በዓለም አትሌቲክስ ውስጥ አመራር እንደሚነያስፈልግ አስበን በዚያ አቅጣጫ መሠረት ጥለን የምናልፈበት ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። በምንቆይበት የስራ ዘመን ይለህን ማሳካት ባንችል ኢትዮጵያውያን ሙያተኞች በዓለም አትሌቲክስ አስተዳደር  መግባት አለባቸው ብለን ነው የምንሰራው።
የአትሌቶች ሙዚየም የታሪክ ማስታወሻ
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የራሱ ሙዚየም እና የሪከርድ ክፍል እንዲኖር እንሰራለን። የአትሌቶቻችን ታሪክ በተሟላ ሁኔታ ሰንዶ የሚያስቀምጥና የታሪክ ማስታወሻ ቸሚሆን ቀአግባቡ የተደራጀ ሙዚየም ያስፈልገናል። አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከየት ወደ የት እንደመጣ የሚያሳይ ይሆነናል።
በመጨረሻም
ፌዴሬሽኑን አገለግላለሁ እንጅ በፌዴሬሽኑ እገለገላለሁ ብየ አላስብም። እንደ አለቃ ሳይሆን እንደመሪ ተቀምጬ መሥራት እፈልጋለሁ። እቅዴ ስፖርቱን በአንድነት የምንመራበትን መንፈስ ለማሳደግ ነው። (ይቀጥላል)

Read 227 times