የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበርን በአንድ የስራ ዘመን ለአራት አመታት አገልግያለሁ። ማህበሩን በአዲስ መልክ ያደራጀን ሲሆን ሌሎች ማህበራቶች በየክልሎቹ እንዲቋቋሙ አድርጊያለሁ። ማህበሩን በምንመራበት ወቅት ከማናጀሮች ያልተከፈለ 26 ሚሊዮን ብር ወደ አትሌቶች እንዲከፈል ሰርቻለሁ። ማናጀሮች ለአትሌቶች ላለመስጠት የያዙትና የተጠራቀመ ብር እንዲመለስ አድርገን ችግር ያለባቸው አትሌቶች ሁሉ ክፍያ ተፈፅሞላቸዋል። ከዚያን ወዲህ ተመሳሳይ ችግር ተፈጥሮ አያውቅም።
በፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በስራ ዘመናችን በተከናወኑ ሁሉም ተግባራት ንቁ ተሳትፎ ነበረኝ። በፌዴሬሽን የቪፒአር ጥናት ተሰርቶ ወደ ስራ እንዲገባ አድርገናል።
በእጩ ፕሬዝዳንትነት ከመቅረቡ በፊት
አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑን ለመወዳደር ከመምጣቴ በፊት በስፖርት አመራር ውስጥ ባልቆይም፤ ከስፖርቱ ግን አልራቅሁም። በኢትዮጵያ ስፖርት ምሳሌ ለመሆን የሚበቃ የእግርኳስ ፕሮጀክት አቋቁመናል። አዲስ አበባ ውስጥ ጃክሮስ በሚባል ሰፈር ያለውን ማህበረሰብ አስተባብሬ የተመሠረተ ነው። አርቴፊሻል ሳር የተነጠፈባቸው ሁለት ሜዳዎችን አሰርተናል። ከ8-10 ፤ ከ11-13 እና ከ14-18 እድሜ እርከኖች በፕሮጀክቱ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል። የቀድሞ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ ከአሰልጣኞቹ አንዱ ሲሆን የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲው የስፖርት ምሁር ዶክተር ዘሩ በላይም አብረውን እየሰሩ ናቸው። እኔ እግርኳስ እየተጫወትኩ ነው ያደግኩት ስለሁሉም ስፖርት በደንብ አውቃለሁ። ሩጫ ዋና ስራዬ ነው ህይወቴም ነው። ታዳጊዎች ወደ ሩጫ ስፖርት ግቡ ብትል አይቻልም። ሩጫ ከባድ ስፖርት ነው። በስፖርት ውስጥ ቆይተው ከበሰሉ በኋላ በወጣትነት እድሜ ወደ ሩጫ ሊገቡ ይችላሉ። ልጆች ኳስ ተጨዋችም ሯጭም ሊሆኑ ይችላሉ። በስፖርት ውስጥ ግን መሆን አለባቸው። በእግርኳስ ፕሮጀክታችን ውጤታማ እንቅስቃሴ እያደረግን ከመሆኑም በላይ በሌሎች ስፖርቶችም የምናደርጋቸው ድጋፎች አሉ። በሜዳ ቴኒስና በቅርጫት ኳስም በሙያተኞች ታግዘን እየሠራን እንገኛለን።
በፌዴሬሽን አመራር ላይ ያለው አስተያየትና ቁጭት
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓለም ላይ ከሚጠቀሱ ትልቅ ፌዴረሽኖች አንዱ ነው። በበነበረው የፌዴሬሽን አመራር በዓለም ሻምፒዮናዎች ፤ በዓለም አገር አቋራጭና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ጠንካራ ውጤቶች ተመዝግቧል። ቀኦሬጎንና በቡዳፔስት በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የተመዘገቡ ውጤቶች ይደነቃሉ።
ኦሎምፒክ በመጣ ቁጥር ግን የተለያዩ ጭቅጭቆች ይፈጠራሉ። ውጤትም ጥሩ አይደለም። ወደፌዴሬሽን አመራር ለመምጣት ስንወስን ውዝግቦች እንዳይኖሩ ለመስራት ነው። ስፖርቱ የጋራ ሆኖ መቀጠል ይኖርበታል። የነበረው ፌዴሬሽን ባስቀመጣቸው ጠንካራ አቅሞች ላይ ለመስራት ነው ወደ ስልጣን የምመጣው። ጉድለቶችን እየሞሉ ለመሄድ ነው። አትሌቲክስ ተግባራዊ ስራ የሚጠይቅ ነው።
ከአትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች አሉ። የብሔራዊ ቡድን አትሌቶች ምርጫ ፤ የምርጫ መስፈርቶችና የስልጠና ስርዓት በተያያዘ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል። የፈረሰው የብሔራዊ ቡድን አሰራር ተመልሶ መመሥረት አለበት። አትሌቶች በሚገባቸው ደረጃ መያዝና መደጎም አለባቸው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚገኝ ድጋፍ መንቀሳቀስ ይኖርበታል። መንግስት ፤ባለሐብቶች ፤ የውጭ ኩባንያዎች ጋር ፌዴሬሽኑ ተባብሮ እንዲሰራ እናደርጋለን።
ከአሰልጣኞች የሙያ ብቃት በተገናኘ ያሉትን ችግሮች የሚያስተካክሉ እርምጃዎች ያስፈልጋሉ። በስፖርት መሠረተ ልማትና ማዘውተሪያ ስፍራዎች ክፍተቶች አሉ። በሁሉም ላይ እንሰራለን።
በተለይ በስፖርቱ መሰረተ ልማት የነበረኝን ተመክሮ መጥቀስ እፈልጋለሁ።
በለገጣፎ የሚገኘው የአትሌቲክስ ፌዴሽኑ የአሸዋ ትራክ ሐሳቡን አመንጭቼ፤ ከተማ አስተዳደሩን አስፈቅጄ ከፌዴሽኑ ጋር ተባብረን አሰርተነዋል። ከዚህ በመነሳት የነበሩ ልማቶችን በማደስና አዳዲሶቹ ለመሥራት ነው። የትራክ ችግርን ለመፍታት እፈልጋለሁ። (ይቀጥላል)
Monday, 16 December 2024 00:00
እጩ ፕሬዝዳንት ስለሺ ስህን
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ