Saturday, 14 December 2024 12:46

ህልምና እውን

Written by  ኢ.ካ
Rate this item
(5 votes)

የአጭር አጭር ልብወለድ)
                        

        በእውን የምናውቀው ነገር ትንሽ እንኴ ዝንፍ ሳይል በህልም ቁልጭ ብሎ ሲታየን ግርም ይላል። ይሄ ለሁለት ሳምንት ደጅ የጠናሁበት ህንፃ ቁልጭ ብሎ በህልሜ ታየኝ። አፍታም ሳልቆይ ደግሞ እንደ ፊልም ሌላ ትዕይንት ተከሰተ። እዚያው መ/ቤት ላለ አንድ ባለስልጣን 300 ብር በእጁ ሳቀብለው “እጅ ወደ ላይ!” የሚል ድምድ ከኋላዬ ተሰማኝ። ዞር ስል ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ፖሊሶች ጠብመንጃቸውን ወደኔ ደግነዋል።
 ፖሊሶቹ ከኋላ ከኋላ እኔ ከፊት ከፊት ማለቂያ የሌለው ደረጃዎች እንወርዳለን። ስንወርድ… ስንወርድ… ላቤ በግንባሬ ይወርዳል፣ ደረጃውን ግን አያልቅም። የደረጃዎቹን መጨረሻ ሳላውቅ ከፍተኛ የበር ኳኳታ ከእንቅልፌ አባነነኝ። ቤቱ ወለል ብሏል- በማለዳዋ ፀሃይ። በድንጋጤ ከአልጋዬ ወርጄ በሩን ስከፍት ቁንጮው ተስፋዬ ነው። ጠዋት ጠዋት ጫማዬን የሚጠርግልኝ ሊስትሮ። ሙሉ በሙሉ ከእንቅልፌ ለመንቃት ሻወር ገባሁ።
***
መቼም ከዚህ በላይ መታገስ ጊዜንም ገንዘብንም ማባከን ነው። መኪናው የኔ፤ ላቤን ጠብ አድርጌ የገዛሁት! ታዲያ የባለቤትነት ፈቃድ (ሊብሬ) ለማውጣት እንዲህ መባከን አለብኝ? እያልኩ ስብከነከን ነው የሰነበትኩት። አንድ ሁለት ጓደኞቼን ሳማክር “በእጅ አትልም እንዴ” አሉኝ። እኔ ደግሞ እንዲህ ያለ ነገር አልወድም። ለሁሉም መፈጠር ያስፈልጋል! እኔ የሥራ ልምዱ የለኝም! ለማነው የሚሰጠው? እንዴት ነው የሚሰጠው? ጓደኞቼ ነገሩን በደንብ ያውቁታል። “እዚያው በሩ ላይ ለዚሁ ስራ የተሰማሩ አሉልህ” አሉኝ። ትዝ አለኝ፤ ሁለት ሦስት ጊዜ ጠጋ ብለውኝ ነበር-ሁለት ወጣቶች። “ጋሽዬ አሁኑኑ እናስፈፅምልዎታለን” ሲሉኝ እንዳልሰማ ሆኜ  አልፌአቸዋለሁ። ለነገሩ እኔን ያስፈራኝ ብያዝስ የሚለው ነው። በምንም ጉዳይ ቢሆን ወህኒ መውረድ አልፈልግም። የታሰረ ሰው እንኳ ጠይቄ አላውቅም፡፡ “ደሞ ጉቦ ሰጥቼ እስር ቤት ልግባ?” ስላቸው፤ “የምን እስር ቤት ነው የምታወራው? እራሳቸው ናቸው የሚጨርሱልህ!” አሉኝ። የሌሊቱ ህልሜ ፍራቻ ቢጤ ቢፈጥርብኝም ልቤን አጀገንኩት።


ሲለምኑኝ እምቢ ብዬ ራሴ ሄድኩላቸው- ጉዳይ ፈፃሚዎቹ ጋ። ጉዳዩን በጥሞና አደመጡኝና ከኔ የሚጠበቀውን ደግሞ ማስረዳት ጀመሩ- በየተራ። ንግግራቸው አጭርና ቀጥተኛ ነው፤ ያልተንዛዛ። ጉዳዩን ለሚፈጽመው ሃላፊ 800 ብር ትሰጣለህ ካሉኝ በኋላ ወደ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ገቡ። ገንዘቡን በምን ብልሃት ለሃላፊው እንደምሰጠው ማስረዳት ያዙ። ጉድ ፈላ! እኔው ነኝ እንዴ የምሰጠው?... ድሮም የፈራሁት ይሄንኑ ነው። የተቻለኝን ያህል ተከራከርኳቸው። እንደምንም ብለው አሳመኑኝ- ምላሳቸው ጤፍ ይቆላል። ሁለት ካኪ ፖስታ አስገዙና ገንዘቡ እንዴት በሰነዶቹ መሃል መግባት እንዳለበት አሳይተውኝ፣ የቢሮ ቁጥሩን ነገሩኝ- የቢሮ ቁጥር 52 ነው። “በቃ ልሂድ?” ጠየቅኋቸው። “ይሂዱ” አሉኝ - ልጃቸውን ወደ ት/ቤት እንደሚልኩ ወላጆች በስስት እያዩኝ። ደግነታቸውና ትህትናቸው ሆዴን አባባው። ፍርሃቴ ጠፋ! እነዚህንስ በደንብ እክሳቸዋለሁ እያልኩ የተባለው ፎቅ ላይ ደረስኩ። በመጀመሪ ዓይኔ ውስጥ የገባው ቢሮ ቁጥር 35 ነው… ግራና ቀኝ እያማተርኩ እርምጃዬን ቀጠልኩ… 34…33…32…31…25 በቃ! አለቀ። ተሳስቼ እንደሆነ ብዬ አንዱን የቢሮ ቁጥር በጣም ተጠግቼ ስመለከት ድንገት በሩ ተበረገደ፡፡ “በስመዓብ!” አለችና እያማተበች ወደ ኋላዋ አፈገፈገች- ቀይ ውብ ወጣት። ደንግጫለሁ፤ ደግነቱ ከቆምኩበት ሳልነቃነቅ ተመልሳ ወጣችና፤
“ምን አጥተው ነው?” አለችኝ ስሜቷን ለማረጋጋት እየሞከረች
“ቢሮ ቁጥር 52ን ፈልጌ…”
“ቢሮ ቁጥር 52?”
“አዎ 52”
“ኧረ እዚህ መ/ቤት ከ35 በላይ  ቢሮዎች የሉንም”
ተሳሳትኩ እንዴ? አልኩኝ ለራሴ፤ “ይሆናል“ አለች፤ ውቧ ወጣት ጎላ አድርጋ ድምጿን።
አልተሳሳትኩም! ፈጽሞ አልተሳሳትኩም! አልኩኝ- በልቤ። በእጄ ያለውን ኪስ ወረቀት መደባበስ ጀመርኩ- ወዲያው ደግሞ በደመ-ነብስ ከፈትኩት፣ አንዲት ነጠላ ወረቀት ከላይ ታየችኝ። ሳላቅማማ መዝዤ አወጣኋት- በትላልቅ  ፊደላት የተፃፈ ነገር አየሁ፡፡ በፍጥነት አመቻችቼ ወደኔ አዞርኩት- ለማንበብ። ምድር ሰማዩ  ዞረብኝ!
“ሙስና የዕድገት ጠር ነው!” ይላል።
ግራ ቀኙን አየሁና ወረቀቷን ጨቧቡጄ ኪሴ ሸጎጥኳት። በካኪ ውስጥ ያለውን ነገር ሁሉ መሬት አራግፌ አየሁኝ… ሁሉም ዶሴ አለ - 800 ብሬ ግን ቀልጣለች።
የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም አልኩኝና፣ በህልሜ በፖሊሶች ታጅቤ የወረድኩትን የማያልቅ ደረጃ መውረድ ተያያዝኩ፡፡
የጸሃፊው ማስታወሻ፡- ከላይ የተተረከው ድርሰት በእውነተኛ ገጠመኝ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡

Read 356 times