Saturday, 14 December 2024 13:17

ድምፃዊ ልዑል ሲሳይ በተለይ ለአዲስ አድማስ

Written by  ጋዜጠኛ ናፍቆት፣
Rate this item
(1 Vote)

 “ልዑል ለመጀመሪያ ጊዜ በሙዚቃ ዓለምን ሊዞር ነው”
                     “ለአንድ አርቲስት ዋነኛ ሀብቱ የሙያ ሥነ ምግባር ነው”

       እስከ 11 ዓመት ዕድሜው ድረስ ኮልፌ አስራ ስምንት ማዞሪያ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነው  ያደገው።  ውልደቱም እዚያው ነው፡፡  ስሜቱ ለሙዚቃ እየተሳበ የመጣው ገና በ8 እና 9 ዓመቱ ቤት ውስጥ የነንዋይ ደበበንና  የነ ቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈን በሬዲዮ በማድመጥ እንደሆነ ይናገራል - የዛሬው እንግዳችን ወጣቱ ድምጻዊ ልዑል ሲሳይ፡፡ የልዑል የሙዚቃ ጉዞ ከሜሪጆይ የበጎ አድራጎትና የልማት ማህበር ተነስቶ፣ በክብር ዶ/ር ተስፋዬ አበበ (ፋዘር ቤት) አድርጎ በኮካ ኮላ ሱፐር ስታር አይዶል አቅንቶ፣ “አይነ-በጎ” እስከተሰኘውና ታዋቂነትንና አድናቆትን እስካላበሰው ነጠላ ዜማው ድረስ ይወስደናል። ለመሆኑ ልዑል ከ11 ዓመቱ በኋላ የተወለደባትን ኮልፌን ትቶ  ወደየት ሄደ? ከሜሪጆይ ጋር እንዴት ተገናኘ? ፋዘር ቤትስ ምን ሰራ? “አይነ በጎ” የተሰኘውና ከእቴነሽ ደመቀ ጋር የተጫወተው ነጠላ ዜማ ምን በረከት ይዞለት መጣ? በስሙ የሰየመው “ልዑል” አልበሙ ምን ያህል ተዋጣለት በቅርቡስ ምን አዳዲስ ነገሮች ሊሰራ አቅዷል? በሚሉትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት፣ ዮሴፍ ከልዑል ጋር በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል  ያደረገችው የመጀመሪያው ክፍ  ቃለምልልስ እንሆ ቀርቧል፡፡


          ተወልደህ ያደግከው በታሪካዊቷ የአዲስ አበባ ክፍል በኮልፌ ነው። እንደሚታወቀው ኮልፌ በተለይ የወታደር ልጆች የተወለዱባት ናት። ታላቁ የነፃነት ታጋይ ኔልሰን  ማንዴላም የውትድርና ስልጠና የወሰደባት የቀሰሙባት ናት። ከ11  ዓመትህ በኋላ ኮልፌን ወዴት ትተሃት ሄድክ? እንዴትስ  ወደ ሙዚቃ ህይወት ገባህ?
እንዳልሽው እኔ ኮልፌ  18 ማዞሪያ ነው ተወልጄ ያደግሁት። እስከ 11 ዓመቴም እዚያው ነው ያደግኩት፡፡ እርግጥ ነው ኮልፌ ትልቅ ካምፕ ነበር። አባጃሜ ካምፕ ፈጥኖ ደራሽ። እዚህ ቦታ ብዙ ወታደሮችና የወታደር ልጆች አሉ። እኔም እዚያው በመወለዴ እነሱን እያየሁ ነው ያደግሁት። ነገር ግን የወታደር ልጅ አይደለሁም። ሙዚቃ የጀመርኩት ቤት ውስጥ በሬዲዮ የነንዋይ ደበበንና የነ ቴዎድሮስ ታደሰን ዘፈን ሳዳምጥ ውስጤ ዝፈን ዝፈን የሚል ስሜት ይሰማኝ ጀመር። ከዚያም መሞከር ስጀምር እናቴ፣ አጎቴና ወንድቼ እየሰሙኝና በርታ  እያሉኝ የተጀመረ ነገር ነው። ሰፈርህን ወዴት ትተህ ሄድክ ላልሽኝ፣ በ11 ዓመቴ ከኮልፌ ወደ ብርጭቆ ፋብሪካ የጋራ መኖሪያ መንደር መሄድ ስለነበረብንና እዚያ መኖር ስለጀመርን ነው።
ብርጭቆ ፋብሪካ ኮንዶሚንዬም ስትኖርና እዚያ ትምህርት ስትማር ከሜሪጆይ ጋር መገናኘትህ ሰማሁ፡፡ በምን አይነት መንገድ ነበር በጎ አድራጎት ድርጅቱን ያገኘኸው?
ሰፈር ቀይረን ወደ ብርጭቆ ፋብሪካ ስንሄድ፣ እዚያው አካባቢ የ6ኛ ክፍል ትምህርቴን ቀጠልኩ። በዚህ ትምህርት ቤት ሀብታሙ ታደለ የሚባል ጓደኛ አፈራሁ። ይህ ጓደኛዬ ሳንጎራጉር ሲሰማኝ “ለምን የኛን ክበብ አትቀላቀልም? ሜሪጆይ የሚባል ልጆችና ወጣቶች የሚያድጉበት ክበብ አለ” ብሎ ነገረኝ። በነገረኝ መሰረት በ11 ዓመቴ የ6ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ሜሪጆይን ተቀላቅዬ፣ ለአምስት ዓመት ያህል አገልግያለሁ። ሜሪጆይ ውስጥ በምሰራበት ጊዜ በቴአትርም በውዝዋዜም በድምጽም ነበር እሰራ የነበረው። በሜሪ ጆይ በሙያ እራስን  ማሳደግና በነገርኩሽ ዘርፍ ሜሪጆይን ማስተዋወቅ ነበር ዋና ሥራዬ። በተለያዩ ት/ቤቶች በመዞር፣ በብሄር ብሄረሰቦች ቀን፣ በተለያዩ ምርቃቶች፤ እድሮች ሳይቀር ሙዚቃ እንሰራ ነበር።
በሜሪጆይ አምስት ዓመት የሰራኸው ተቀጥረህ ነው ወይስ በበጎ ፈቃደኝነት?
በጎ ፈቃደኛ ነበርኩ። ለእኛ በሜሪጆይ ትልቁ ጥቅማችን የነበረው፣ የምንለማመድበት ቦታ ይመቻችልናል። ከዚያ ውጪ ግን በሜሪጆይ በሚደረጉ ማንኛውም የበጎ አድራጎት ስራ ላይ እንሳተፍ ነበር። የተለያዩ አገልግሎቶች እንሰጥም ነበር። የተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀስን እናስተምር ነበር። ቅዳሜና እሁድም በወጣቶች፣ በሴቶችና በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ኮርስ እንወስድ ስለነበር፣ የተማርነውን ትምህርት ለሌሎች እናስተምር ነበር። እንግዲህ ለስራ ስንወጣ ታዲያ በዓመት ሁለት ጊዜም ቢሆን ለሳሙና ተብሎ ሰላሳ እና ሀምሳ ብር ይሰጠን ነበር። እንዳልኩሽ ለእኛ ዋናው ጥቅማችን መድረክ ማግኘታችን፣ የልምምድ ቦታ መመቻቸቱና አሰልጣኞች ማግኘታችን ነበር። እርስ በእርሳችንም የምንማማርበት አጋጣሚ ብዙ ነበር። በስልጠናው አንዱ የጎበዘበትን ነገር ለሌላው እያስተማረ ይቀጥላል። ማለት ነው።
ወደኋላ ልመልስህና ገና በልጅነትህ ቤት ውስጥ ስታንጎራጉር እናትህን ጨምሮ ሌሎች ቤተሰቦችህ “በርታ” ማለታቸው የአንተን ቤተሰብ ለየት ያደርገዋል። አብዛኛው ቤተሰብ “አርፈህ ተማር፣ ትምህርትህ ላይ አተኩር፣ አዝማሪነት ይቅርብህ” የሚል ነው እንደሚታወቀው። በዚህ ምክንያት ብዙ ልናገኛቸው የሚገቡንን ድምጻውያን አጥተናል የሚል ቁጭት ይሰማኛል፡፡ ያንተ ቤተሰብ እንዴት እንዲህ አይነት ድጋፍ አደረገ የሚለው ነገር ደንቆኝ ነው። ምን ትላለህ?
እውነትሽን ነው። ወደ ቤተሰቤ ስመጣ እናቴ ሙዚቃ በጣም ትወዳለች። ክፍለ ሀገር ነው ያደገችው፤ ወደ ጉራጌ ዞን፡፡ እናቴ አዲስ አበባ የመጣችው በትዳር ምክንያት ነው። ባደገችበት ጉራጌ ዞን ገና ልጅ እያለች ሙዚቃ ከመውደዷ የተነሳ አባቷም ከከተማ ወደ እሷ ሲሄድም ሆነ (አባቷ የከተማ ነዋሪ ነው) ሌላም ዘመድ ከከተማ ሊጠይቃቸው ሲሄድ የምትጠብቀውና የምትጠይቀው የሬዲዮ ባትሪ ነበር። ሬዲዮ አድማጭ ነበረች። በተለይ የሙዚቃ ፕሮግራሞችን፡፡ እናም አንዳንዴ የሷ ከልክ ያለፈ የሙዚቃ ፍቅር ይሆን እንዴ? ድምጽ ኖሮኝ እንድወለድ ያደረገኝ ብዬ አስባለሁ። ትንሽ ችሎታ እንዳለኝ ስታውቅ እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ወንድሞቼንና እህቶቼ በየተሰጥኦአችን ጠንክረን እንድንሰራ ታበረታታናለች። ሌላው ቀርቶ ማክሰኞ ሀሙስና ቅዳሜ ነበር፣ በሜሪ ጆይ ልምምድ የማደርገውና አንዳንዴ ደክሞኝም በሌላ ምክንያት ከልምምድ ስቀር ትቆጣኝ ነበር።
ለቤተሰብህ ስንተኛ ልጅ ነህ?
ሁለተኛ ልጅ ነኝ። ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ነን። የኔ ታላቅ ወንድም አለ፡፡ መላኩ ሲሳይ ይላል። ኢቨንት ኦርጋናይዘር ነው፣ ፊልም ፕሮዲዩሰርም ነው፣ “ልዑል” የተሰኘውን አልበሜንም ፕሮዱዩስ ያደረገው እሱ ነው። የተለያዩ አርቲስቶች ማኔጀር በመሆንም ይታወቃል።
ወደ ህዝቡ አይንና ጆሮ ዘልቀህ የገባኸው “አይነ-በጎ” በተሰኘውና ከእቴነሽ ደመቀ ጋር በሰራኸው ነጠላ ዜማህ ይመስለኛል። ከሜሪጆይ ወደ ፋዘር ቤት ነው የሄድከው ወይስ “አይነ-በጎ” ነው የቀደመው?
ወደ ፋዘር ቤት  ነው ቀድሜ የሄድኩት። በእርግጥ ሜሪ ጆይም እያለሁ ፋዘር ቤት እሄድ ነበር፡፡ ያኔ ፋዘር የሚያተኩሩት ቴአትርና ፊልም በማስተማር ላይ ነበር። ያን ጊዜ ደግሞ ፊልም በብዛት የሚመረትበትና የሚበዛበት ጊዜ ነበር። ለኔ በደንብ  የረዳኝ ነገር የፋዘር የስልጠና ቦታ ፒያሳ እንደመሆኑ፣ ወደ ከተማ ወጣ እንድልና የተለያዩ ሰዎችን የመተዋወቅ ዕድል መፍጠሩ ነው። ፋዘር ቤትም ወደ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዚ ልምምድ አድርጌአለሁ። እዚያ በምለማመድበት ጊዜ የኮካ ኮላ ሱፐር ስታር አይዶል የመወዳደሩ ዕድል ገጠመኝ። ስወዳደር ሁለተኛ በመውጣት አጠናቅቄ የ75 ሺህ ብር ተሸላሚ ሆንኩኝ። ይህ የሆነው ከ10 ዓመት በፊት በ17 ዓመት እድሜዬ ነበር፡፡ የኮካ ኮላን አይዶል ማሸነፌ ወደ ኢንዱስትሪው በደንብ እንድቀላቀልና ብዙ ሰዎችን እንዳውቅ ረዳኝ ማለት ነው። ይህ አጋጣሚ ደግሞ በአንድ ኹነት አማካኝነት “ኤክስፕረስ” ባንድን እንድቀላቀል መንገድ ከፈተልኝ። ያ ኹነት የፍቅረኞች (ቫላንታይንስ ዴይ) ሲከበር ከባንዱ ጋር እንድሰራ ጆርካ ኢቨንት ጋበዘኝ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አጋ አባተንና ቡድኖቹን አመሰግናለሁ። ምክንያቱም ኤክስፕረስን ከሚያክል ባንድ ጋር እንድሰራ ነው ዕድል የፈጠረልኝ። ብዙ ነገር ረድቶኛል አጋ።
“አይነ- በጎን” ከመስራትህ በፉት የኮካ ኮላ ሱፐር  ስታር አይዶል አሸናፊ ሆነሃል፣ ፋዘር ጋር ሰርተሃል፣  ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር አንድ መድረክ ላይ ሰርተሃል ማለት ነው?
በትክክል!
አሁን ስለ “አይነ-በጎ” ትንሽ እንጨዋወት?
በጣም ጥሩ፡፡ ከላይ አንቺም የገለጽሻቸውን ስራዎች ከሰራሁ በኋላ በምን መልኩ  ወደ ህዝብ ልምጣና ልገናኝ ብዬ በማስብበት ጊዜ፣ የፋዘር ድርሰት የሆነውና ታደለ በቀለና ሂሩት በቀለ በጋራ የተጫወቱትን “አይነ-በጎ”ን የመስራት ሀሳቡ መጣ። በዚያን ጊዜ እነ ዳዊትም “ገላዋ”ን ሰርተው ውጤታማ የሆኑበትና ዘፈኖችን ሪሚክስ ማድረግ ፋሽን የሆነበት ጊዜ ነበር። “ገላዋ”ም የፋዘር ድርሰት ነው እንደሚታወቀው። እናም “አይነ-በጎ”ን ከእቴነሽ ደመቀ (ከኤክስፕረስ ባንድ) ጋር ሰራሁት ማለት ነው። ይህንን ስሰራ 18 ዓመቴ ነበር።
እውነት መናገር “አይነ-በጎ”ን ስትሰራ 18 ዓመት የሞላህም አትመስልም ነበር። ሙዚቃውም ከእቴነሽ ጋር ጥምረታችሁም የተዋጣለት ነበር። ለነገሩ አንተ ዕድለኛ ነህ መሰለኝ… ከጅምሩ  አሁን እስካለህበት ድረስ የነበረህ የሙዚቃ ጉዞ ብዙ አባጣና ጎርባጣ የበዛበት አይደለም…  ያ ማለት ምንም አይነት ፈተና አላጋጠመህም ማለቴ ሳይሆን በአብዛኛው ብዙ መከራ አላጋጠመህም… ይህ ደግሞ እድለኝነትንም ይጠይቃል… ይመስለኛል፡፡ ልክ ነኝ?
በትክክል! በእርግጥም እኔ የሙዚቃ ጉዞ የተሻለ ነው። በእኔም በኩል ከፍተኛ ጥረት ነበር። ለነገሮች አዕምሮዬን ክፍት የማድረጌም ጉዳይ አንዱ ለስኬት ዋነኛ ነገር ነው። የቤተሰቤም ሙሉ ፈቃደኝነት ታክሎበት፣ እኔም በአካባቢዬና በዙሪያዬ ያሉ ዕድሎችን ለመጠቀም ጥረት ማድረጌ እንዲሁም የአርት ሰዎችን ደፈር ብዬ ቀርቤ ማነጋገርና መወያየት መቻሌ ነገሮች እንዲሳኩልኝ ረድቶኛል ብዬ አምናለሁ።
በዚህ ሁሉ ጉዞህ የትምህርትህስ ጉዳይ ጎን ለጎን ቀጠለ?
ትምህርቴንም እየተማርኩ ነበር። በእርግጥ 10ኛ ክፍልን ከተፈተንኩ በኋለ፤ መማር የምፈልገው ሙዚቃ ስለነበር 11ኛና 12ኛ ክፍልን መማር አልፈለግኩም። ቀጥታ ያመራሁት ወደ ተፈሪ መኮንን (እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ) ነው፡፡ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት ለመግባት የ12ኛ ክፍል ውጤት ይጠይቅ ነበር። እኔ ደግሞ 12ኛ አልደረስኩም። ስለዚህ በ10ኛ ክፍል ውጤቴ ተፈሪ መኮንን ፒያኖ መማር እንደምችል ተነገረኝ። ለሁለት አመት ፒያኖ ተምሬ በማይነር ደግሞ መሰንቆ እየተማርኩ ወደ አልበም ስራ በመግባት በኢኮኖሚ ራስን ለመደገፍ የምሽት ክበብ መስራት ተጀመረ፡፡ ከዚህ ሁሉ ድካም ጋር  ጠዋት እየተነሱ ት/ቤት መሄድ ከባድ ሆነ። ስለዚህ የተፈሪ መኮንን ትምህርት አቋርጬው ስራውን ቀጠልኩ ማለት ነው።
“አይነበጎ”ን ከሰራህ በኋላ ጋሽ ታደለ በቀለን አገኘኸው? ካገኘኸው ምንስ አስተያየት ሰጠህ?
እውነት ለመናገር ጋሽ ታደለን ያገኘሁት አይነ በጎን ከሰራሁ ከአመት ከምናምን በኋላ ነው። ስራው በሚሰራበት ጊዜ የድርሰቱ ባለቤትና ፍቃድ ሰጪ ጋሽ ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) ስለነበሩ እኔም ደግሞ ጋሽ ታደለን የማገኝበት መንገድ ስላልነበረ ለጊዜው አልተገናኘንም ነበረ። በአንድ አጋጣሚ አግኝቼ አለመነጋሬ፣ እንደ አንድ ድምፃዊ እሱንም አግኝቼ አለማወያየቴ ቅሬታ እንደፈጠረበት ሰማሁኝ። ይህን ነገር ከሰማሁ በኋላ መሳፍንት ቤት አንድ ልዩ ፕሮግራም በማዘጋጀትና ጋሽ ታደለን እንዲታደም በማድረግ እንደ ይቅርታም እንደ አክብሮትም ልዩ ምሽት አዘጋጅተን ጋሽ ታደለም ደስ ብሎት አሳልፈናል። በዛ ምሽት ስለ አይነ-በጎ ስለሰራንበት መንገድ አድናቆቱን ገልጾ ቅር የተሰኘው እንደ ድምጻዊ አስተያየት እንዲሰጥ አለመጠየቁ እኔም ልጅ እንደመሆኔ እሱን አፈላልጌ አለማግኘቴ እንጂ በስራው ላይ ቅሬታ እንደሌለው ስለ ስራውም ፋዘር እንደነገሩት ገልጾ አበረታቶኛል። ከዚያ በኋላም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከጋሽ ታደለ ጋር ተገናኝነተናል። ጋሽ ታዴ አዎንታዊ አስተሳሰብ ያለው መልካም ሰው ሲሆን  ቀና ቀና አስተያየቶችን ሰጥቶኛል “አይነ-በጎ” በህዝብ  ዘንድ የተወደደ እኔንም ከህዝብ ያስተዋወቀኝ አይን ከፋች ስራ ነው።    
ሌላም ተጨማሪ ነጠላ ዜማ አለህ አይደል?
አዎ፤ ይሄኛው ስራዬ ከኤክስፕረስ ባንድ ጋር አይነ-በጎን ከሰራን በኋላ አልበም ለመስራት ፈለግኩ። ምክንያቱም የኔ ትልቁ ህልሜ አልበም መስራት ነው። አልበም ለመስራት ግጥምና ዜማዎች በምፈልግበት ሰዓት ብዙ ፈተናዎች ነበሩት። እኔም የምፈልገውን አይነት ግጥምና ዜማ፤ አለማግኘት፤ ደራሲዎችም የእኔን ልጅነት በማየት እምነት አለመጣላቸው የምፈልገውን አይነት ግትምና ዜማ ለማግኘት ፈተና ሆኖብኝ ነበር። በዚያ ፈተና ውስጥ ስጓዝ የኤክስፕረስ ባንዱ ክብረት ዘኪዎስ እኛ ጋር በተለያየ ጊዜ ተሰርተው ግን ያልወጡ ትራኮች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ ዜማዎችን ብትሰማ ጥሩ ነው ብሎ የተለያዩ ስራዎችን ያስደምጠኛል። እነዛን ስራዎች ጥሩ ጥሩ ዜማዎች ሰማሁ። ግን የሰራቸው ሰው ማነው? የሚለው ላይ አተኮርኩ። ያንን ሳጣራ “ሴት ናት” የሚል ዘፈን ያለው ድምጻዊ ደጎል መኮንን መሆኑን አወቅኩ። ይህንን ሰው ፈልጌ ማግኘት አለብኝ ጥሩ ጥሩ ስራዎች ነው የሚሰራው ብዬ ስነሳ ደጎል መኮንን ከዚህ የሙያ ዘርፍ እንደወጣና ሥውን እንደማይሰራ ሰማሁ። ከአዲስ  አበባ ወጥቶ ደሴ መኖር ከጀመረ እንደቆየም ጭምር ተነገረኝ። ከዚያ በኋላ ስልኩን ማፈላለግ ጀመርኩ። እንደ ምንም ብዬ ስልኩን አግኝቼ አዋርቼው አሳምኜው አዲስ አበባ እንዲመጣ አደረግኩ። የመጣው  ለአልበም ስራዬ ቢሆንም አልበሙ እስኪሰራ ድረስ “ቀረሁ እንጂ” እና “ሰላም ትሙት” የተሰኙ ሁለት ነጠላ ዜማዎች ከአልበሙ በፊት ለአድማጭ አደረስን። “ቀረሁ እንጂ” በጣም የተደመጠና የተወደደ ስራ ሲሆን “ሰላም ትሙት” እምብዛም አልተደመጠም። የዜማውም የግጥሙም ሀሳብ እንግዳና ለህዝቡ ጆሮ ከበደው መሰለኝ አልተደመጠም። ከአልበሙ በፊት ሌላም “ስለሀገር ኢትዮጵያ የተሰኘ” የተለያዩ ሙዚቃዎች የተካተቱበት ከቨር፣ የ10 ደቂቃ ስራ ልዑል በተሰኘው የራሴ ዩቲዩብ ቻናል ላይ ለቅቄ ነበር። ከቨሩ እንደ ዩቲዩብ መክፈቻም ነው የተጫነው። እንደ ነጠላ ዜማ ሪሚክስ ያልሆነና የመጀመሪ ስራዬ የምለው “ቀረሁ እንጂ” የተሰኘውን ስራዬን ነው።
(ይቀጥላል)


Read 374 times