Saturday, 14 December 2024 13:20

ማኅሌታዊው ኮከብ (የዱር አበባ)

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ርዕስ ፦የዱር አበባ
                                ዘውግ ፦ ግጥም
                             የህትመት ዘመን ፦ 2017
                             ገጣሚ፦ ቴዎድሮስ ካሳ
                                       ሲራክ ወንድሙ

        ሁለት ሥጋ’ና ደሞች
ሁለት የሥጋ እስረኞች
ገላን ጥለው እሳት ሆነው
አዎ ... እሳት ሁነው !
 ፍም ነበልባል ፤ ...
ሕይወት አፈር እንዳትባል
 ሕይወት ውኃ እንዳትባል
ሕይወት እሳት ብቻ ሁና !

ሕይወት የዱር አበባ !
ሥነ ግጥም፤ የአፍላነት ወዝ ጠፈጠፍ ነው ከተባለ የሚገለፀው፣ በሌሪክ የግጥም ዘውግ ሆኖ እናገኘዋለን። ሌሪክ፤ ግጥሞች ግላዊ ስሜቶችን ፣ ሀሳቦችንና  ምናኔ ጠቀስ የሆኑ ጥልቅ ስሜቶችን ሙዚቃዊ ቃናና ምት በማላበስ የሚቀርብበት ዘውግ ነው።
በስሜት በተሞሉ ቃላት እንደመልካ ብናኝ የመርጠባቸውና ከውስብስብ ደረቅ ሴራ ይልቅ አንድ አፍታ ወስደው ግላዊ ስሜታቸውን መተንፈስ መቻላቸው እንዲሁም በቅሬታ ውስጥ እንደተገኘ አፍለኛ ሙዚቃ፣ ዜማ ለበስ ቃናን መቸራቸው ከባህሪ ተቆጥሮ የሚለዩበት ድንበር ነው።
 ትንሽ ቁስል
 እድሜ ሙሉ ትዝ የምትል!
የአንቺ ፍቅር
ስር የሚሰድ ከጅማት ስር  
(ገፅ 33 )
ሌሪክ ግጥሞች እንደ ሁሉን ወዳጅ ትንሽዬ ህፃን ናቸው። ያየ አያልፋቸውም፤ ወደ ደረቱ አስጠግቶ ይስማቸዋል። ከልብ፣ ከነፍስና ከስሜት የሚወለዱ ናቸውና ከጠራቸው ጋር በቀላሉ ስምምነት ይፈጥራሉ። ተግባቢ ናቸው፡፡ «ይሄ ልጅ ከሁሉ ነዋሪ ነው» እንደሚባለው አይነት መልከኛ...!
የቴዎድሮስ ግጥሞችም እንዲሁ ናቸው። ስዕላዊ መገለጫቸው ረቀቅ ጠበቅ ያለ ውልን እንደ ዝናር በወገቡ ሸብ ያደረገ ነው።
ከሌሪካዊ የግጥም ዘውግ ባህሪ የሆነው አንዱ፣ የተፈጥሮና የፍቅር ጭብጥ በዚህም መድበል ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እንዲንቀሳቀስ የተዳው ይመስለኛል፡፡  
ተፈጥሮን ስል
ተፈጥሮዬ
ቀዝቃዛ አካል ውስጥ እንደሚዋኝ
ቁስል እንደበዛበት ፍቅር ነው
ረጅም ስሞሽ ያደክመኛል
ዝም ያለ ሰው ይገድለኛል።
(ገፅ 20 )
ፍቅርን ስል
የተጎነጨሁት ወይኑ አልደረቀም
ገና
ጆሮዬ ስር
ስሰማ ያመሸሁት ሙዚቃ አልበረደም።
(ገፅ 27)
ስዕልን ስል
 የህይዎት ጣዕም
የህይዎት ውበት
ቀዝቃዛ ሻይ
እጅሽ መሃል የበረደ፤
ግማሽ እድሜ
አንቺን ሲያስብ የነጎደ ፤
ጅምር ሀሳብ  
ጅምር ግጥም  
          ጠርቶ ያመጣው፤
ውብ ወዘና
ጎረምሳ ሌት የሚጠጣው።  »
(ገፅ 32-33 )
ገጣሚው የሌሊት ፍቅርና ምሰጣ እያዘገመ በስንኞቹ ውስጥ እንዲያደባ የፈቀደ ይመስላል። የውብ ሰመመናዊ የትዝታው ጫፎች፣ የተቋጠሩት በሌሊቱ የዝምዝማት ሸማ ውስጥ ነው። ዘውትር ማኅሌታይ እንዲባሉ በሌት የተወለዱም ጭምር..!!
ደሳስ የሚሉ ወቅት የወለዳቸው የህይወት የሞቅታ እቅፍ ያባባቸው ስንኞች ልክ እንደልብ ምት በረገጡት አፈር ላይ ሲዘሉ፣ ብርሃን እቅፍ ውስጥ ተወልደው ጊዜን ለመገዘት ሀሳብ ያላቸው፤ ምሽት ያላቸው ፤ ምኞት ያላቸው አይነት ናቸው። የተቃኑበት ለጋ ሰመመናዊ የወቅት ትንፋሽ፣ በፀዓዳማው የሳቅ ወንዝ እያሳሳቀ እንደሚወስዳቸው ወጣት ውበቶች ናቸው።
ለዚህም ይመስለኛል በግጥም ላይ የሚስማሙ በርካታ ምሁራን፤ አንባቢና ግጥም አድናቂያን ለግጥም የተመረጠ የሚሏት ወቅት ወጣትነትን ነው። ወጣትነት ለግጥም ገና የፈካ አበባ እንደማለት ነው። የእንቡጥነት ዘመኗን ባጅታ ብቅ ባለች አበባ ላይ ዓይን ይራኮታል። ጓጊና ቀጣፊ መዳፎች የእጆቻቸው መንገድ አበባና አበባዋ ጋር ብቻ ይሆናል።
Catharsis የሚባለው ጥንታዊው የግሪክ ፅንሰ ሀሳብ ውስጥ ስለ ግጥምና ስሜታዊ መግለጫን በተመለከተ እንዲህ የሚለው ማብራሪያ ትዝ አለኝ፡- Poetry provides a means for young people to articulate complex emotions that they may struggle to express verbally. Writing or reading poetry can serve as a cathartic release, helping them process feelings related to identity, relationships, and life transitions.
እኔም ለዚሁ አንድምታ እቀርባለሁ።
ለጋነት ለየትኛውም ኪነ ጥበባዊ ውልደቶች (በተለይም ለግጥም) መልከኛው ሰሞን ነው።
ምርጥ ግጥም ማለት
ቃላት ያልነካው ነው፤
ምርጥ ግጥም ማለት
 በሁለት ፍቅሮች መኃል፤
ያለ ዝምታ ነው
(ገፅ 88 )
ወጣትነት የለጋነት ቤት ከመሆን ባለፈ የስስነት ቋቱ ነው። ከዚያ በላይ ያለው እድሜ የተግሳፅና የምክር እጀታዎች የሚበዙበት ሲሆን፤ ከዚህ በታች ያለው ደግሞ ልክ በSigmund Freud  early childhood experience theory መሰረት፣ ደስታዎቻችንን በአፋችን የምናስስበት ሰሞን ነች። ይህም ከቆዳ መገልበጥ በፊትና በኋላ ብለን ልንጠራው እንችላለን። ከመገልበጡ በፊት ያለው ጊዜ መነካት ወደ ስሜትና ትርጉም የሚቀርብበት ለጋ ወቅት ነው።
ምሁራኑ ለስነ ጥበብ የተመቸ የሚሉትም ይህቺኑ ዕድሜ ነው። ገጣሚነትና ሁሉን አቀፍ ሚናነትም እዚሁ ጋ በስፋት የሚነሳ ዓብይ ጉዳይ ነው። መሳሳቱና ህመሙን ያወጀበት ታዛ ላቅ ሲል የብዙ ግፉዓን ነፍሶች ማፅናኛ ድንኳን ይሆናል። ይህን ጉዳይ በተመለከተ ገጣሚው ራሱም በገፅ 97 ላይ ይህንኑ ፈርጅ እንዲህ ይዳስሰዋል፡-
 እሳት!
እሳት!
 እሳት!
በእያንዳንዱ ሰው ነፍስ ፤ የምትፈላውን
 የውበት ወርቅ ሐርር ፤ ጎንጉኖ ሲለብሳት
 እጅግ ያሳዝናል
እንዲህ ያለው ወዳጅ ፤
በቁሙ ‘ሚቃጠል
ገጣሚ ይባላል።
(ገፅ 91 )
ቴዎድሮስ ካሳ በውስጡ ሺህ ዓመት ህይወትን የታዘበ፣ ያየ ያስተዋለ በሚመስል ልክ ብዕሩ የበረታች ወጣት ነው። ቀድሞ ከዘመን መንቃት ዕድሜን ማስከተል፣ የአሪፍ ትውልድ መገለጫ ነውና ቴዲ ከነብስ የሚወለዱ ግጥሞች ባለቤት ነው። ስንኞቹን ለጋነት አይጎበኛቸውም። ለዘብ ብለው የሚተፉት ስሜት ልብ ውስጥ የሚቀሩ ናቸው። የሚቀሩም ብቻ ሳይሆን አንባቢን መያዝ የሚችሉ በሳሎች ናቸው። የታደለ ዘመን እንዲህ ያሉ ብሩህ ወጣቶችን በወቅት አፈሩ ላይ ያጎነቁላል።
“የዱር አበባ”ን በተመለከተ የቴዎድሮስ ካሳ mystical ማጫወቻዎቹ ውስጥ እሳትን ... ናፍቆትን እና ዝምታን እንድንመለከት እፈልጋለሁ።
እሳት
ከግሪክ አፈታሪካዊ ትርክቶች በመነሳትና እሳት ሰርቆ አሰቃቂ የቅጣትን ፅዋ ከተጎነጫት ፕሮማቲየስ በመነሳትና እሳት የመጀመሪያውና ትልቁ የሰው ልጅ የግኝት ውጤት መሆኑን በመጠቅለል በፊደል ተሰርተው እሳት ከሚረጩ ስንኞች ጋር እናዘግማለን።
ተመልከችው እርሱን
 ፍቅር አጠውልጎት ፤
 ናፍቆት ፍም አድርጎት
 ፍም እሳት ነበልባል ፤
 በአካሉ አለሁ ቢልም
የለም እንዳይባል!
(ገፅ 89)
ግጥሞቹ በባህሪያቸው እሳታዊ ውበት፣ እሳታዊ ናፍቆታዊ ምስሎችንና መሰል ድምፆችን ያዘሉ ሲሆኑ፤ የአንባቢው ልብ ላይ ያለውን ተመሳሳይ ስሜታዊ ሻማ ለመለኮስ ያለመ ይመስላል። በሚስቲሲዝሙ አለም እሳት ብዙውን ጊዜ እንደተለዋዋጭ ኃይል ይታያል። የመንፃትን ሂደት ቆሻሻዎችን (ያደፉ የሀላፊ ጊዜ ማንነታዊ ጥላዎችን ) በማቃጠል እና እንደገና ማደስ እንዲሁም ዳግመ ውልደት መፈከሪያ አንዱ መንገድ ነው።
(ፊኒክስ በእሳት ወላፈኑ እርር ብላ ራሷን ዳግመኛ እንደምትወልደውም እንደማለት..! )
እሳት ነፍስን ለማንፃት በአምልኮ ስርዓቶች ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ ይውላል።
ሕይወት ድጋሚ
በዓይኖችሽ ውስጥ እንድትወልደኝ
 እፈልጋለሁ።
 አፍ አፉን ቢስሙት የማይጠግቡት ፍቅር
ሆኜ
መወለድ እፈልጋለሁ።
(ገፅ 99 )
እሳት የመለኮት መገኘት አንዱ መንገድ ሆኖም ይቀርባል፤ ለምሳሌ ያህል፡- በክርስትናው አውድ  በሙሴ ታሪክ ውስጥ የሚቃጠለው ቁጥቋጦ፣ የእግዚአብሔርን መገኘት ሲያመለክት፣ በሂንዱ የእምነት ዳራ  ደግሞ የእሳት አምላክ በሰዎችና በመለኮታዊው አካል መካከል አስታራቂ ተደርጎ ይቆጠራል።
 ከዚህም ባሻገር እሳት የእውቀትና የመገለጥ ምልክት ፣ የጥፋትና የትርምስ ፣ የመንፈሳዊ መነቃቃት ተምሳሌትና በግለሰብ አውድ ውስጥ እንደ ፍቅር ፣ ከፍተኛ ፍላጎትና ኃይለኛ ስሜቶችን ሊወክል ይችላል። እሳት በብዙ መተርጎም መተንተን ከሚችሉ ግዙፍ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ነው። ለዚህ ይሆን ቴዎድሮስ በአንድ ግጥሙ እንዲህ የሚለን፡-
ወደ እሳት ሲጠሩህ ክንፎችህን ዘርጋ
ልቦናህን ከፍተህ  አይኖችህን ዝጋ ፥           
ቅለበዉ ጠጠሩን ፥
የወንጭፉን ሩሕ ፥       
“እንሂድ” በላቸዉ ፥ ለስቃይ ሲጠሩህ ፥                            
ታገለዉ ወጀቡን ፥          
ግፋዉ ማዕበሉን ፥             
 ዝለቀዉ አፀዱን ፥                                          
 ተቀበለዉ ስሙን ፥      
 [ የሰዉ ልጅነቱን ]                                            
 ዉደደዉ ሙላቱን ፥                                          
 ዉደደዉ ጉድለቱን ፥                                        
 አፍቅረዉ ጥመቱን ፥     
 አፍቅረዉ ቅናቱን  ፥      
 የአካል እንግልቱን    
     [የሰዉ ልጅነቱን]                
(ተናገር ለሁሉም  ሰው ከልብሱ በታች ፍም እሳት መኾኑን! )
(ከገፅ 76-77 )
ናፍቆት
“Nostalgia is a form of suffering.”
Milan Kundera:
ሩህሩህነት አምጦ የወለዳቸው የአሁንም ሆኑ የሀላፊ ጊዜ የህይወት ውልብታዎች በናፍቆት ስም የቆሙበት በራፍ መፅሐፉን እፁብ ለማድረግ ምስጠት ከሰጡ ነገሮች ውስጥ አንዱ ነው። ናፍቆት በስስ ዝማሬ የተደረሰባቸው ንዝረታዊ እሳታዊ መታመቆች ስለናፍቆት መጮህ ብቻም ሳይሆን በእምባ መሬት ላይ አስቁመው ህመምን የሚያስናፍቁ ናቸው። መሻታቸው ተፈጥሮ ፣ ስክነት ፣ ዝምታና ሌላም ሌላም ነገር ቢሆን፣ የታሰሩበት ገመድ ግን ናፍቆት ነው። ስጥም ያለ ደስ የሚሉ ልጃገረድ ስንኞች ውስጥ ፈገግ ያለ ህይወት....
ዛሬ ሌሊት
 ሕልም አየሁ፡፡
የሚጣፍጥ ወይነ-ጠጅ አፌን ሲሞላው፤
 ከአፌ ወይነ-ጠጅ ሲፈልቅ
 የወይን ፍሬ ሁኜ ፤
በቀጭን አረንጓዴ ሐረግ ላይ ተንጠልጥዬ ፤
ቀረፋ የተሞላ ንፋስ ሲያወዛውዘኝ
መብሰል ቆዳዬን አሳብጦት
ልፈነዳ ... ቅብትት ብዬ ... ቀልቼ ፤
(ገፅ 95)
ዝምታ
ዝምታ አንዳንድ ግጥሞቹ በዝምታ እንደሚፈስሱ ፀባየኛ ወንዞች ይመስላሉ። ጉልበታቸው እርጋታ ሆኖ አገኛቸዋለሁ። ልስላሴ ውስጥ እንደተገኘ ኩልል ያለ መፍሰስ አንዱ የዚህ መፅሐፍ ባህሪ ነው። ከባህሪነቱም ባሻገር በህይወቲቱ ሌማት ላይ ተንጠራርቶ ከሚዘግናት እፍኞቹ ወይም በመኖሩ ከሚገደው ነገሮቹ መሀል የዝምታ ባንዲራ አንዱና ዋነኛው ነው።
በሚወዳቸው ትዝታማ ሌቶቹ ውስጥ የሚወለዱ አጋጣሚዎቹ ዝም ያሉ ይምሰሉ እንጂ እሱ ተውሶ የሚሰጠን የትርጓሜ አሀድ ከመርቀቅ አይዛነፍም። ግጥሞቹም ሆነ ስንኞቹ ውስጥ ያደረው ሰው (ገጣሚው) ዝምታ ወዳድነቱ ከስክነታዊ አፍታዎች ጋር አዛምዶታል የሚል መደምደሚያ አለኝ። ያም የጥሩ framework ስራን በመፅሐፉ ውስጥ እናገኛለን።
ሌላው የተሰበሩ ዜማዎች ወጀብ መፅሐፉን ከስሜት ቅለት አንፃር ሊያደክሙት እንደሚችሉ ባምንም፣ የዚያን ያህል ጨለማ የጎላባቸው እንዳልሆኑ ግን መስክር ቢሉኝ ዓይኔን አላሽም። መሳጭነቱ ላይ የተዘሩት እነዚያ ፊደላት እሳታማ ናቸው። በውሃ የሚጠፉ ሳይሆኑ በእምባ ተግ የሚሉ አይነት ወደረኞች...! ሰመመን ያጫራቸው ግልፍተኛ ቁጭቶችም በጊዜ በዘመንና በህይወቲቱ ላይ ጥርሳቸውን ነክሰው ከእንግዲህ አልወድቅም የሚሉበት ታዛ በራሱ የጥንካሬ መንፈስን ናፋቂነትና ቅናት የሚያሳድሩ ናቸው። በዚህም ገጣሚው የተመስጥኦ ፍጆታዎቹ ብዬ ከብዙ በጥቂቱ ከለቀምኳቸው ጉዳዮቹ ውስጥ ዝምታ  አንደኛው ሲሆን፤ ለኪነ ጥበብም ሆነ ለመኖር ብስለት በርግጥም በዝምታ ውስጥ የታሸች መንደር ህይወት ናት።
ማኅሌታዊነት
“የዱር አበባ” ጥዑማዊ የሌት ትዝታዎች ፣ የሌት ዝማሬዎች የአበባ ገላቸውን የበተኑበት አይነት ሜዳ ነች። ማህሌታዊ አቋቋሟ ልጅነት ነው። ውበት ነው። ስስነት ነው። «ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ.. » እንዳለው ፀጋዬ፣ የዱር አበባንም በሌት አምባ የሚያስወጣት ብዙ መዝሙሮች ፣ ብዙ መናፈቆች ፣ ብዙ ትዝታዎች አሏት።
ናፍቆት የወለደው ትኩስና ገር ፍቅር፣ በርጋታ የታሸው ከበቢ ውስጥ እየተትጎለጎለ የሚወጣው የዝምታ እጣን ፣ ካሸለቡ ግዑዝ ተፈጥሮ ጋር በነፃነት በደስታ መስከርና ሌላም ሌላም የሌት ማኅሌቶቹ ውስጥ የሚታዩ ድምፀቶች ናቸው።
ከርዕሶቹ ጀምሮ ብንነሳ
- የሌሊት ሹክሹክታ
- የሌት ወራጅ ሀሳብ 1 , 2 , 3
- የአንድ ምሽት ሀሳብ
የሚሉ እና ብዛት ያላቸው ሌሊት አወዳሽ ስንኞች በመፅሐፉ ውስጥ በብዛት ይታያሉ።
በዚህም ግጥሞቹ ማኅሌት የቆሙ ኮከቦች ይመስላሉ። መቋሚያ ፅናፅሉ ናፍቆት ሲሆን እሳት እሳት የሚሉ አበባማ ስንኞች ውስጥ ወዙን እንደ ሉባንጃ እየበተነ ማሂጠንቱን ይቋጥራል።
እንደከርቤ ውብ ጉም
እንደሎሚ ሽታ
አበባ እንዳየ ንብ
እኔ እወድሻለሁ...
(ገ/ክርስቶስ ደስታ )
እንደመውጫ፡- አበባን ከስነ ዓለማዊ አተያይ (cosmological outlook) በመነሳት እንመልከትና ላብቃ፦
ልክ እንደ እሳት ሁሉ አበባ በ cosmological point of view (የስነ ዓለም አተያይና ትርጓሜ )  ውስጥ በርካታ ፍቺዎችን ያዘለ ነው። ስነ ህይወታዊ ዝግመተ ለውጥን በተመለከተ አበቦች ( የአበባ ተክሎች ) የመራቢያ አወቃቀሮች ሲሆኑ፤ በዝግመተ ለውጥ ሂደት ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ይነገራል። የመራቢያና የጄኔቲክ ልዩነትን በማመቻቸት የአበባ ብናኞችን ይስባሉ። ይህ የህይወት ትስስርንና በአፅናፈ ሰማይ ውስጥ ያለውን የዝግመተ ለውጥ እንዲሁም የመላመድ ሂደቶችን ሊያመለክት ይችላል።ይህንንም ተከትሎ የህይወት ኡደት እና ሽግግር ሌላኛው ምልከታ ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ አበቦች ብዙ ጊዜ ለአጭር ጊዜ የሚቆዩ ናቸው። (ምናልባትም ይሄን ይሆን ህይወት የዱር አበባ ያለን? )
 ይህ በአፅናፈ ሰማይ ውስጥ ላለው ጊዜያዊ ተፈጥሮ ተምሳሌታዊ አሀድ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል።
በዚህም የልደት ፣ የእድገት ፣ የመበስበስ እና የመታደስ ጭብጦችን ያሳያል።
 እኒያን የልጅነት ወቅት አበቦች
 የጣዕም ወራት ጣዕሞች ፤
እኒያን ፣... ትናንሽ ክንፎች
 ትናንሽ ለስላሽ ላባዎች ፤
እኒያን ፣...
 ደማም ከንፈሮች
 ስኳር ስኳር ፤ የሚሉ ልቦች ፤
እኒያን ፣...
የፀዳል ሳቆች
 አንፀባራቂ ራቁቶች ፤
ማደግ ... ወዴት ወሰዳቸው!?
(ገፅ 56)
 ከዚህም ባሻገር አበባ በሰው ልጅ የባህል ታሪክ ውስጥ የተለያዩ ትርጉሞችን ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ውበት፣ ፍቅር እና መንፈሳዊነት ያሉ ጥልቅ ፅንሰ ሀሳቦች በአበባ ይወከላሉ። በስነ ዓለማት ዳራ መሰረት፤ ትርጉምንና ትስስርን ለማግኘት የሚደረጉ ሙከራዎችን ያንፀባርቃል።
የዓይኔን ልቦናዬን ፤
ቅንድቤን
 ከንፈሬን
 ልቤን
 ኩላሊቴን
 :
ተመልከተኝ እኔን
ገላው የረገፈ አበባ መሆኔን!
(ገፅ 80)
በአበባነት መፈከሪያ ተደርገው የሚቆጠሩት እነኚህ የህይወት ዘለላዎች በመድብሉ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ተሰጥቷቸው በአጀብ ሰፍረው ይታያሉ። ገጣሚው ህይወትን በአበባ ቅንጣት ይመስላታል። ቀጥሎም እሳትን ያስከትለዋል።
በግሌ ቴዎድሮስ ካሳ በዚህ መድበሉም ሆነ ባልታተሙ ግጥሞቹ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ጋር ህይወትን ፣ ፍጥረትን ፣ ጊዜን ፣ ሰውነትንና መሰል ጉዳዮችን የሚያይበት መንገድ ተቀራራቢነቱ የዘውድና የጎፈር አይነት የመገላበጥ የእድሜ ልዩነት ይመስለኛል።
በርግጥ ፀጋዬ እሳት ሲል ከላይ በፈከርነው መሰረት ውድመትና ጥፋትን (አብዮት) አይነት የሞት ጥላዎችን ሲሸሽ፣ ቴዎድሮስ በበኩሉ፣ ልክ እንደ ወፊቱ (ፊኒክስ ) በመቃጠል መሻገርን (ዳግመ ውልደትን) ናፋቂ ሆኖ እናገኘዋለን።
መፅሐፊቱም ለገበያ የዋለችው በመጨረሻዋ የህዳር ቅዳሜ በመሆኑ ከህዳር መታጠን ጋር ተቃጥሎ በመጪዎቹ ወራት ውስጥ ለመታደስ ይሆናል ብለን እንጠርጥር ! ካልጠረጠርን ምኑን ሀበሻ ሆንን!?
ይሁኔ በላይ «ገላጋይ» በሚለው የበዕውቀቱ ስዩምን ግጥም ተውሶ በዘፈነው አንድ ዘፈን «በአንድ ዱር ይበቅላል ብትርና አበባ» የምትል ስንኝ አለች። ሰውን ከዱር አበባነት ከመሰልነው ዘንድ ከአበባው ይልቅ በትሩ ባሳደደን የቁጭት ድምፅ ውስጥ ፤ ሳይቀጠፉ መርገፍን በህይወት ላይ መተከዝ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
«ኧረ ወይኔ ህይወት! »
በተለይ ይህን መድበል በማነብበት ወቅት (በ1985 ይመስለኛል) ታትሞ ለአንባቢ የቀረበው የአንጋፋው ደራሲ አዳም ረታ መፅሐፍ ከሆነው ማህሌት ውስጥ «የአበቦች ታሪክ» የሚለውን አጭር ፅሁፍ እያስታወስኩ መቃበዜን አንባቢ ተረድቶ በሽግግር እንዲጋበዝልኝ ስል በውል ባልጠይቅም እሺ ለሚለኝ ግን አልሽኮረመምም።



Read 308 times