- ቃል ገብተዋል፤ በተግባር ፈጽመዋል!
• በሁለት ወር የተገነቡ ትምህርት ቤቶች፣ የዳቦና የእንጀራ ፋብሪካዎች፣
አስፋልት መንገድና መናፈሻዎች፣ ሱቆችና የስፖርት ማዘውተሪያዎች…
ከሁለት ወር በፊት ነበር የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ “የጎደለውን ሁሉ እናሟላለን” ብለው ቃል የገቡት።
ከካዛንቺስ አካባቢ ለልማት የተነሡ ነዋሪዎች ወደ ገላን ጉራ የገቡበት ሰሞን ነበር - ጊዜው። ከ60 ዓመት በላይ ያለማሻሻያና ያለ እድሳት በእርጅና የተጎሳቆሉና የተፋፈጉ የቀበሌ ቤቶች ውስጥ ነበር ኑሯቸው።
ለልማት ተነሺ ነዋሪዎች በገላን ጉራ የተዘጋጁት ቤቶች ግን፣ አዳዲስ የኮንዶሚኒየም ሕንጻዎች ናቸው። ቤቶቹ ስፋት አላቸው። የግንባታቸው የጥራት ደረጃውን የጠበቀ ነው። የድሮውና የዛሬው አይገናኝም ይላሉ - ለ52 ዓመታት በካዛንቺስ እንደኖሩ የነገሩን ወ/ሮ እታገኘሁ አመሜ።
በእርግጥም በገላን ጉራ አዲስ ኑሮ የጀመሩ 1200 ቤተሰቦች ዕድለኞች ነን ይላሉ። ቤቶቹ ያምራሉ። ነገር ግን…
የልጆች ትምህርት ቤትስ? እስከ መኖሪያ መንደራቸው የሚወስደው ኮሮኮንች መንገድስ? የትራንስፖርት አገልግሎትስ? ብዙ ጥያቄዎች ነበሯቸው።
ከመደበኛ የስራ ቦታ ከገበያ ጋር የተራራቁ ሰዎች እንዴት ይሆናሉ? ቀድሞውኑ ቋሚ የመተዳደሪያ ስራ ያልነበራቸውስ?
የካዛንቺስ ነዋሪ እንደነበረ የገለጸልን ጥላሁን ደለለኝ፣ በረዳትነት እና የተገኘውን ነገር እሰራ ነበር፤ አንዳንዴ ስራ ይኖራል፣ አንዳንዴ አይኖርም ይላል። በገላን ጉራ የተሠጠን ቤትና ሰፈሩ ያስደስታል፤ ነገር ግን መጀመሪያ ላይ የመሠረተ ልማትና የሥራ ዕድል ችግሮች ነበሩብን በማለት ያስታውሳል።
ከካዛንቺስ ተነሥተው ወደ አዲሱ መኖሪያቸው ሲገቡ፣ የአዲስ አበባ መስተዳድር ከጠበቁት በላይ ድጋፍ እንዳደረገላቸው አይደብቁም። ከነባር ሰፈር ወደ አዲስ ሲዛወሩ የሚፈጠርባቸውን የስነልቦና ጫና ለመቋቋም የሚረዳ የማካካሻ ገንዘብ በፍጥነት እንደደረሰላቸው ይገልጻሉ። የዕቃ ማጓጓዣ ድጋፍ በነጻ ማግኘታቸው ከብዙ ጭንቀት እንዳዳናቸው ይናገራሉ። በገላን ጉራ መኖሪያ ቤቶችና በአካባቢው ገጽታ ደስተኛ ናቸው።
ቢሆንም ግን ነዋሪዎቹን የሚያሳስቡ ጉዳዮችም አጋጥመዋቸዋል - የዛሬ ሁለት ወር። በትራንስፖርት፣ በትምህርት ቤት፣ በስራ እጦት እንቸገራለን የሚል ነበር ሐሳባቸው።
ካዛንቺስ የመናኸሪያ አካባቢ ነዋሪ እንደነበረች የገለጸችልን ወ/ሮ ቤቴል ከበደ፣ ወደ ገላን ጉራ የገባችው መስከረም 30 እንደሆነ ታስታውሳለች። የተሰጠን መኖሪያ ቤት ደስ ይላል፤ ሌሎች ነገሮች አልነበሩም ማለት ይቻላል። ጅምር ሥራዎች ብቻ ነበር ትላለች። እዚህ የገባን ሰሞን፣ ክብርት ከንቲባችን አዳነች አበቤ እዚህ ሊጠይቁን መጥተው አነጋግረውናል በማለት ታስታውሳለች።
ቀጠሮ የተያዘለት የተስፋ ቃል የት ደረሰ?
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ የገላን ጉራ አዲስ ነዋሪዎችን ለመጠየቅ፣ ጊዜያዊ የዱቄት፣ የዘይትና የቡና ድጋፍ እንዲሁም የመማሪያ ቁሳቁስ ይዘው ነበር የሄዱት። ከነዋሪዎች ጋር ተነጋገሩ። ጥያቄዎችን ሰሙ። ቀድሞውኑ የከተማው አስተዳደር ያሰበባቸው ጉዳዮች ናቸው በአብዛኛው። እናም…
የጎደለውን ሁሉ እናሟላለን ብለው ለነዋሪዎች ቃል ገቡ - ከንቲባ አዳነች አበቤ።
በደፈናው አይደለም።
“ሁሉንም ነገር አመቻቻለሁ። የመንገድ ግንባታ በፍጥነት ጨርሰን፣ የትራንስፖርት አገልግሎት እናቀርባለን” ብለውን ነበር ትላለች ወ/ሮ ቤቴል። “በቀድሞ የስራ ልምዳችሁና ይዛችሁት በመጣችሁትን ሙያ እንድትቀጥሉ ዘዴ እንፈጥራለን። ተጨማሪ የስራ ዕድሎችን፣ የስራ ቦታዎችንና የገበያ አማራጮችን እናሟላለን” ብለው ከንቲባችን ቃል ገብተውልን ነበር በማለትም ታስታውሳለች።
ከንቲባ አዳነች ዕቅዳቸውን በሙሉ በነዋሪዎች ሁሉ ነው በይፋ የተናገሩት።
ዋናውን መንገድ እስከ መኖሪያ መንደር የሚያገናኝ አስፋልት መንገድ ለመገንባት ቃል ገብተዋል። የአውቶቡስ ማዞሪያ ተሰርቶ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚመቻችም ተናግረው ነበር።
የሕፃናት ማቆያ እንዲሁም የቅድመ መደበኛ ትምህርት መዋዕለ ሕፃናት እናዘጋጃለን። ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች፣ አዲስ የትምህርት ቤት ሕንጻ እንገነባለን ብለውም ቃል ገብተዋል።
የሥራ ዕድሎችን በስፋት ለመፍጠርም፣ የወፍጮ አገልግሎትን ጨምሮ የእንጀራና የዳቦ ፋብሪካዎችን እንገነባለን። የስራና ቦታዎችና ሱቆችን እናሟላለን ሲሉም ተናግረው ነበር።
የስፖርት ማዘውተሪያዎችንና መናፈሻዎችንም ሰርተን እናስረክባችኋለን በማለት በርካታ ዕቅዶችን በዝርዝር ለነዋሪዎች ገልጸው ነበር። ብዙ ነገር ለመሥራትና ለማሟላት ነው ቃል የገቡት።
ለዚያውም፣ “ወደፊት እንሰራዋለን፤ በሂደት እናሟላዋለን” አላሉም።
በሁለት ወር ውስጥ ገንብተን እናጠናቅቃለን፤ በሥርዓት አዘጋጅተን እናስረክባለን በማለት ነበር የቀን ቀጠሮ ለነዋሪዎች የሰጧቸው።
በደፈናው ሳይሆን፣ ዕቅዶችን በዝርዝር መግለጽና ቀን ቆርጦ ቃል መግባት አንድ ቁም ነገር ነው። በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘንድ እየተለመደ ቢሄድ ለአገር መልካም ነው።
ነገር ግን፣ ቃል የተገባው በተግባር ይፈጸማል ወይ የሚል ነው ዋናው ጥያቄ።
በተግባር ሥራው ቢጀመር እንኳ፣ በተያዘለት ጊዜ በፍጥነት ተገንብቶ ይጠናቀቃል ወይ?
ግንባታዎቹ በፍጥነት ተጀምረዋል። ነገር ግን፣ የግንባታ ሥራ እስከ ተወሰነ ጊዜ ድረስ ቁፋሮውና ጥድፊያው ይታያል እንጂ፣ ወዲያውኑ ዓይን የሚገባ በግልጽ የሚታይ መልክ አይኖረውም። እንዲያውም ከሥራው ብዛት የተነሣ፣ ግንባታው የሚጠናቀቅ፣ ለውጤት የሚበቃ፣ አገልግሎት የሚጀምር፣ ለወግ ለማዕርግ የሚደርስ አይመስልም። “ይሄ ሁሉ ሥራ አንድ ላይ ተጀምሮ በጊዜ ያልቅ ይሆን?” የሚል ጥርጣሬ መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ደግሞም ከባድ ነው። በኃላፊነት ስሜት ካልበረቱ፣ ቃልን አክብረው የመተግበር፣ የታቀደውን የመፈጸም የዕለት ተዕለት ትጋትና ክትትል ካልታከለበት አይሳካም።
ቃል በተግባር ሲፈጸም አላየንም ማለት ግን አይደለም። በአዲስ አበባ፣ ከዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ጀምሮ እስከ አንደኛው ዙር የኮሪደር ልማት ድረስ፣ በርካታ ፕሮጀክቶች ለውጤት በቅተዋል። ቃልን በተግባር የመፈጸም፣ የተጀመሩ ግንባታዎችን በፍጥነት የማጠናቀቅ ጠንካራ የሥራ ባህል ሲፈጠር አይተናል።
ቢሆንም ግን፣ ወደፊትስ ይቀጥል ይሆን? እዚህኛው ፕሮጀክትስ ይሳካ ይሆን? ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
በሁለት ወር ገንብተን ሁሉንም እናሟላለን የሚለው የከንቲባ አዳነች አበቤ የተስፋ ቃልም በዚሁ ዓይን ልናየው እንችላለን? ለገላን ጉራ ነዋሪዎች የገቡት ቃል በተግባር ይፈጸም ይሆን?
ጊዜው ደርሷል። ሁለት ወር ሞልቶታል - ቃል በተግባር።
እውነትም፣ ግንባታዎቹ በፍጥነት ተጠናቅቀዋል። አገልግሎት መጀመራቸውን ለማብሰርና ከነዋሪዎች ጋር ሆነው ፕሮጀክቶቹን ለማስመረቅ ከንቲባ አዳነች አበቤ ሰሞኑን በገላን ጉራ ተገኝተዋል።
የሕጻናት ማቆያ እንዲሁም የቅድመ መደበኛ ትምህርት መዋዕለ ሕጻናት ተገንብተው በቁሳቁስ ተሰናድተዋል።
የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች አዲስ በተገነባ ባለ አምስት ፎቅ ሕንጻ ውስጥ ትምህርት ጀምረዋል - የትምህርት የደንብ ልብስ እንዲሁም የመማሪያ ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው።
ከዋናው መንገድ ጋር የመኖሪያ መንደሩን የሚያገናኝ 1.6 ኪሎ ሜትር አዲስ የአስፋልት መንገድም አስቸጋሪ ነው ተብሎ ቢገመትም፣ በፍጥነት ተገንብቶ ተጠናቅቋል
20 አውቶቡሶችን የሚያስተናግድ ማዞሪያ በሰፊው ተገንብቷል።
በርካታ ሱቆችና የስራ ቦታዎችም ለነዋሪዎች ተላልፈዋል።
የእንጀራ ማዘጋጃ ማዕከልም አመቺ አዳራሽ ተገንብቶለት፣ ደረጃቸውን በጠበቁ ቁሳቁሶች ተደራጅቶ ለአገልግሎት ተዘጋጅቷል። በሦስት ፈረቃ ለ270 እናቶች የሥራ ዕድልና የመተዳደሪያ ገቢ ያስገኝላቸዋል።
በቀን 60 ሺ ዳቦ ማምረት የሚችል የዳቦ ፋብሪካም ተከፍቷል።
ምርጥ ዳቦ እያመረትን ነው ይላል - ጥላሁን ደለለኝ። መጀመሪያ ላይ የነበሩብን የመሠረተ ልማት ችግሮች አሁን ተስተካክለው፣ ወደ ስራ ገብተናል ብሏል ጥላሁን።
ቦታው ሰፊ ስለሆነ፣ ሥራችንን ለማስፋፋት ማሽኖች ይጨመራሉ። በብዛት ገዝተው ለሚሸጡ ሰዎች ቅናሽ እናደርጋለን፤ የ10 ብር ዳቦ በ7 ብር እናስረክባቸዋለን፤ እኛም ግን ተጨማሪ የመሸጫና የማከፋፈያ ቦታዎችንም ለማዘጋጀትም እያሰብን ነው በማለት ዕቅዳቸውንና ተስፋቸውን ገልጾልናል - ጥላሁን።
ለ20 ሰዎች የሥራ እድል እንደከፈተላቸውና በሰዓት 5 ሺ ዳቦ የማምረት ዓቅም እንዳለው ጥላሁን ተናግሯል።
ወፍጮዎች ተተክለዋል - 50 ኩንታል ጤፍ ለመነሻ ተሰጥቶናል።
የእህልና የበርበሬ ወፍጮች አመቺ የስራ ቦታ ተገንብቶላቸው ተተክለዋል። የካዛንቺስ ነዋሪ እንደነበረና አሸዋ ሜዳ አካባቢ ወፍጮ ቤት ይሠራ እንደነበር የነገረን አደም መሐመድ፣ አሁን በገላን ጉራ የተተከለው ወፍጮ ቤት 10 ሆነን ሥራ ለመጀመር ተዘጋጅተናል ብሏል።
በራችንን አንኳኩቶ የመጣ ዕድል ነው፤ የእህል እና የበርበሬ ወፍጮዎች ተተክለው የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶላቸዋል፤ ለመነሻም 50 ኩንታል ጤፍ በመኪና አምጥተው አቅርበውልናል በማለት በአዲስ አበባ አስተዳደርንና ከንቲባ አዳነች አበቤን ያመሰግናል።
ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳይኖረን ሁሉንም ነገር እያሟሉልን ነው።
ሱቅ ለማግኘት ፈልጌ ነበር ያለችን ቤቴል ከበደ፣ የዕድል ጉዳይ ሆኖ እንዳሰብኩት አልሆነም፤ ፍትሐዊ እንዲሆን በዕጣ ነው የተደረገው ትላለች። አሁን የእንጀራ ማዘጋጃ ማዕከል ውስጥ ገብታለች። የሙከራ ሥራ አጠናቅቀው መደበኛ ምርት ለመጀመር እንደተዘጋጁም ገልጻልናለች።
“10 ሳንቲም አላወጣንበትም። በልማት ተነሺዎች ስለሆንን ሥራ የለንም። የሥራ ቦታው ተገንብቷል። ምጣዶችና የኤሌክትሪክ መስመር ተሟልተውልናል። የገቢ ምንጭና የስራ መነሻ ገንዘብ ስለሌለን፣ የአዲስ አበባ አስተዳደር የሥራ መነሻ ድጋፍም ሰጥቶናል” ትላለት - ቤቴል።
“ምንም ዓይነት ቅሬታ እንዳይኖረን፣ መጀመሪያ ለመሞከሪያ የሚሆን የተወሰነ ጤፍ ገብቶልናል። ከዚያም የሥራ መነሻ 50 ኩንታል ጤፍ ገብቶልናል” በማለትም ታመሰግናለች።
“ሰርተን እንለወጥ እያልን ነው። በርትተን ከሰራን... ወደፊት እንለወጣለን” በማለትም፣ የብርታታችንን ያህል ውጤት እናገኝበታለን ብለው እንደሚያስቡ ገልጻለች።
የተጋገረ እንጀራ፣ ገዢ እና ተመጋቢ አያጣም ለማለት ይሆን? ገበያ ያገኙ ይሆን? በእርግጥ ገበያው ሰፊ ነው።
ትምህርት ቤቶች በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎት ያቀርባሉ። ብዙ እንጀራ ይፈልጋሉ። በገላን ጉራ ለ500 አረጋውያንና ለአቅመ ደካሞች የምገባ አገልግሎት ለመስጠት የተቋቋመውን አዲስ ማዕከልን ጨምሮ፣ በአዲስ አበባ በርካታ ተመሳሳይ ማዕከላት በየቀኑ እንጀራ የሚያቀርብላቸው ይፈልጋሉ። ፖሊስ ጣቢያዎችም እንዲሁ። ሆቴሎችም አሉ።
ገበያተኛው ብዙ እንደሆነ የገለጸችልን ቤቴል፣ “የአዲስ አበባ መስተዳድር የገበያ ትስስር እንደሚፈጥርልን በተደጋጋሚ ነግሮናል። አትጨነቁ… እናንተ አምርቱ እንጂ፣ እኛ የገበያ ትስስሩን እንፈጥራለን ብለውናል” ትላለች።
ከሩቅ የሚጣሩ ውብ የስፖርት ስፍራዎች
በጣም የሚያምሩ ሁለት የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ተሠርተዋል። የሕጻናት መጫወቻ ለብቻው አለ። የወላዶች መመልከቻ ስፍራ የተዘጋጀለት ነው። የእግር ኳስ ሜዳም በዙሪያው ምቹ የመመልከቻ ወንበሮች ተሟልተውለታል።
በአሸዋማ ቦታ እግር ኳስ ሲለማመዱ የነበሩ ታዳጊዎች፣ አሁን ደረጃውን የጠበቀ “አርቴፊሻል” ሜዳ አግኝተዋል። ለዚያው ሙያተኛ አሰልጣኝ ጭምር።
የእግር ኳስ አሠልጣኝ ሽዋንግዛው ጸጋዬ እንደሚለው ከሆነ፣ ሜዳው ለልጆች ጤንነት ተስማሚ ነው። ቢወድቁ የመላላጥ ጉዳት አይደርስባቸውም። ከዚህም በተጨማሪ ሜዳው በጥራት ስለተሰራ፣ የቴክኒክና የታክቲክ ስልጠናዎችን በተሟላ መንገድ ለመስጠት ያመቻል ብሏል - አሠልጣኝ ሽዋንግዛው።