Tuesday, 17 December 2024 21:03

የዘንድሮ የሺህ ጋብቻ አፍሪካውያን ጥንዶችንም ያካትታል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የሺህ ጋብቻ ኹነትን በማዘጋጀት የሚታወቀው ያሜንት ኃ. የተ.የግ.ማ፤ ሦስተኛውን የሺህ ጋብቻ ጥር 18 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ያካሂዳል፡፡ በዚህ ኹነት ላይ 1ሺ ኢትዮጵያውያን ጥንዶችና 250 የሚደርሱ ከአፍሪካ አገራት የተውጣጡ ጥንዶች የሰርግ በዓላቸውን እንደሚያከብሩ ታውቋል፡፡

የሺህ ጋብቻ ትልቁ ዓላማ፣ የኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ህዝቦችን የካበተ ባህላዊ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት አጉልቶ በማሳየት፣ አዲስ አበባን “የሃኒሙን ማዕከል” ማድረግ እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

የኹነቱ አዘጋጆች ሦስተኛውን የሺህ ጋብቻ አስመልክቶ ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 6 ቀን 2017 ዓ.ም በሃርመኒ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

ዘንድሮ በሚካሄደው የሺህ ጋብቻ በተቻለ መጠን ከሁሉም ብሔርና ብሔረሰቦች የተውጣጡ ጥንዶች የሚሳተፉበት እንዲሆን እየተሰራ መሆኑንና ሙሽሮች ለሠርጋቸው የሚያወጡት ምንም ዓይነት ወጪ እንደማይኖር በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡

የሺህ ጋብቻ የሠርግ ሥነሥርዓትና ባህላዊ ካርኒቫል፤ ከሠርግ ድግስ ጋር የተያያዙ፣ ለዘመናት የቆዩና ሥር የሰደዱ ጎጂ ማኅበራዊ አመለካከቶችን ለማስወገድና ወደ ለውጥ የሚያመራ ማኅበረሰባዊ ውይይት ለማንሳት እንደሚረዳ የተነገረ ሲሆን፤ ቤተሰብ በማህበረሰብ ግንባታ ውስጥ ያለውን ፋይዳ በማጉላት፣ ለበጎ አስተሳሰብ መጎልበት መሠረት መሆኑን ለማሳወቅ እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡

የሺህ ጋብቻ፤ የውጭ አገር ጎብኚዎችን በመሳብ ከቱሪስት ፍሰት የውጭ ምንዛሪ ግኝትን መፍጠር፣ የባህል ልውውጥ መድረክ በመፍጠር ሃገሪቱ ለህዝቦች አንድነት መጠናከር እንዲሁም ለሰላምና ለባህሎች ዕድገት የምታደርገውን ጥረት መደገፍ አላማው ነው ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ያሜንት ኃ. የተ.የግ.ማህበር ኹነቱን በተሻለ መንገድ ለማስተዋወቅ፣ አርቲስት ተስፋዓለም ታምራትና ባለቤቱን ቃልኪዳን አበራ እንዲሁም አርቲስት ይገረም ደጀኔና ባለቤቱን ፅዮን ዮሴፍን የየሺ ጋብቻ አምባሳደር አድርጎ ሾሟል፡፡

ለዚህ ኹነት ያስፈልጋል ተብሎ የታቀደው አጠቃላይ በጀት ከ68 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

”ቤተሰብን መመስረት አገርን መገንባት ነው" የሚል መሪ ቃል ያለው ያሜንት፤ የመጀመሪያውን የሺ ጋብቻ ኹነት በ2005 ዓ.ም 500 ጥንዶችን በመዳር ማከናወኑ ይታወሳል፡፡

ድርጅቱ በመጀመሪያው ዙር ለተጋቡ ጥንድ ሙሽሮች የ10ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን በሸራተን አዲስ ያከበረላቸው ሲሆን፤ ለሁለተኛው ዙር ሙሽሮች የመልስ ጥሪ በግዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ ተደርጎላቸዋል፡፡

 

Read 222 times