Saturday, 21 December 2024 20:21

“ቡናችን” ወደ ዓለም ገበያ እየሄደ ነው። ይቅናው።

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

- ቡና ጠጪ ይጭነቀው?.... ምን በወጣው? የቡና ምርትን መጨመር እየተቻለ!

 

የቡና ዋጋ የማይቀመስ እየሆነ ነው ብሏል የሰሞኑ የዎል ስትሪት ጆርናል ዘገባ። በዓለም ገበያ የአንድ ኪሎ ቡና ዋጋ ከ7 ዶላር በላይ ሆኗል። ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ዕጥፍ ገደማ ነው ብሏል- ጋዜጣው። እጅግ እየናረ የመጣው ግን ከጥቅምት ወር ወዲህ ነው።
በሁለት ወር ልዩነት የአንድ ኩንታል ቡና አማካይ ዋጋ፣ ከ520 ዶላር ወደ 730 ዶላር አሻቅቧል።
በ1969 ዓ.ም የተመዘገበውን ከፍተኛ ዋጋ በመብለጥ የዘንድሮው ዋጋ አዲስ ሪከርድ ሆኖ ተመዝግቧል።
ቡና ፉት ማለት እንደ ቻይና በመሳሰሉት አገራትም እየተለመደ ስለመጣ ገበያው ሰፍቷል። ዋጋውም ባለፉት ወራት ወደ ላይ ሲጨምር ነበር። ከጥቅምት ወር ወዲህ ያሻቀበው ግን ከብራዚልና ከቬትናም የቡና ምርት ችግር ጋር የተያያዘ ነው።
ዘንድሮ የብራዚል የቡና አዝመራ ከመድረሱ በፊት፣ በዝናብ እጥረት እንደተጎዳ የደቡብ አሜሪካ የቡና ገበያ ባለሙያ ገልጸዋል። ከዝናብ እጥረት በተጨማሪ በሞቃት የአየር ጸባይ የዘንድሮ የቡና ፍሬው ጫጭቷል። ለከርሞ ፍሬ መያዝ ያለባቸው የቡና ዛፎችም ስለጠወለጉ ምርታቸው እንደሚቀንስ ባለሙያው ገምተዋል።


ከሌሎች ኋላ ተነስተው በቡና ምርት ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱት የቬትናም ገበሬዎችን ችግር ገጥሟቸዋል። የዓመቱ ዝናብ ጊዜውን ጠብቆ አልጣለም። እንደምንም ለፍሬ የደረሰው ቡና በሚሰበሰብበት ወቅት ደግሞ ኃይለኛ ዝናብ ድርቅና ጎርፍ መጣባቸው። የገበሬዎችን ሥራ እንደአወሳሰበው የጋዜጣው ዘገባ ይገልጻል።
በእርግጥ የቡና ዋጋ እንዲህ እንደተሰቀለ አይቀርም። የዋጋው ውድነት ቡና ጠጪዎችን የሚፈታተን ከሆነ ፍጆታቸውን ይቀንሳሉ። በተለይ አዳዲስ ለማጅ የቡና ደንበኞች የዋጋ ውድነቱን የመሸከም ትዕግሥት ብዙም አይኖራቸውም። ምክንያት፣ ከቡና ጋር የሚያራርቅ ሰበብ ይሆንባቸዋል።ይህም ባይሆን ግን፣ የቡና ምርት አንዴ ሲበላሽ መልሶ ይሻሻላል። የሌሎች አገራት ገበሬዎች ይገቡበታል።
ለጊዜው ግን ዋጋ አሻቅቧል። እስኪወርድ ድረስም እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራት ለቡና ገበሬዎችና ነጋዴዎች ልዩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። በተለይ ለኢትዮጵያውያኑ።
ሐምሌ ወር ላይ የዶላር ምንዛሬ ተሻሽሎላቸዋል። ወደ ውጭ የሚላከው የቡና መጠንም ጨምሯል።
በዚህ ላይ የዓለም የቡና ዋጋ በጥቂት ወራት ውስጥ እንዲህ ሲያሻቅብ፣ ለኢትዮጵያ የቡና ገበሬዎችና ነጋዴዎች ተጨማሪ ልዩ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። እስከ መቼ ዋጋው እያሻቀበ እንደሚቀጥል ባይታወቅም፣ ዋጋው በተወሰነ ደረጃ ተመልሶ እንደሚቀንስ ነው የሚጠበቀው። እስከዚያው ግን፣ከቡና ኤክስፖርት የሚገኘው ጥቅም ዘንድሮ ከሌሎቹ ዓመታት ሁሉ የላቀ እንደሚሆን ግን አያጠራጥርም።
የአገር ውስጥ ቡና ጠጪዎች ግን ፈረደባቸው። ከኑሮ ውድነት ጋር ተደማምሮ የቡና ዋጋ መጨመሩ ይጎዳቸዋል።
ምናልባት ግን ወደ መፍትሄ ያመራ ይሆናል። የቡና ምርት እየጨመረ ሊሄድ ይችላል።


የቬትናም ገበሬዎች የቡና ምርት ከ30 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ ገበሬዎች ያነሰ ነበር። ዛሬ፣ ከኢትዮጵያ ምርት የሚበልጥ ሦስት ዕጥፍና ከዚያ በላይ የቡና መጠን ያመርታሉ። በሠላሳ ዓመታት ውስጥ የኢትዮጵያ ምርት ስላልጨመረ አይደለም። የኢትዮጵያ ምርት እንደጨመረ ዓለማቀፍ የቡና ምርት መረጃ ያሳያል። ከ2 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 6 ሚሊዮን ኩንታል።
የቬትናም የቡና ምርት ግን በሠላሳ ዓመታት ውስጥ ወደ 15 ዕጥፍ ደርሷል። ወደ 20 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ።
የዓለም የቡና ምርት ከ60 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 110 ሚሊዮን ኩንታል የጨመረው በቬትናም ገበሬዎች ብርታት ነው ማለት ይቻላል። ለነገሩ፣ ባለፉት 30 ዓመታት በኮሙኒዝም ምክንያት ታግዶ የቆየው የግል ኢንቨስትመንት ከተፈቀደ ወዲህ እንደ ቬትናም የቀናው አገር የለም - በእርሻም በኢንዱስትሪም።
ከጠቅላላ የአፍሪካ የቡና ምርት፣ የቬትናም ምርት ይበልጣል።
15 ሚሊዮን ኩንታል የነበረው የብራዚላውያን የቡና ምርት፣ ዛሬ ወደ 30 እና 35 ሚሊዮን ኩንታል ደርሷል - እንደ አየሩ ሁኔታ።
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን መስሪያ ቤት እንደገለጸው ከሆነ፣ ከሐምሌ ወዲህ በአራት ወራት 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ተሸጧል - በ647 ሚሊዮን ዶላር።
ብዙ ምርት ለመላክ ገበሬዎችንና ነጋዴዎችን ያነሣሣቸው ነገር ቢኖር ነው።
ምን ያህል እንዳነሣሣቸው ለማየት ያህል፣ በመንግሥት ቀደም ሲል የተገመተውን ዕቅድና በተግባር የታየውን የንግድ መጠን ማነጻጸር እንችላለን።
ብዙውን ጊዜ የመንግሥት የግምት ዕቅድ እንደ ሰማይ የራቀ ምኞት ይመስል የለ! የቡና ገበሬዎችና ነጋዴዎች በአራት ወራት ውስጥ 1 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ወደ ውጭ ይልካሉ ተብሎ ነበር በመንግሥት የተገመተው። “ዕቅድ” ብለው ነው የሚጠሩት። መንግሥት ቡና ተክሎ የሚለቅም ያስመስሉታል።
ዕቅድ የሚባለው በራስ ለሚከናወን ስራ ነው መቼም። ገበሬዎችና ነጋዴዎች ለሚሰሩት ነገር፣ መንግሥት “ዕቅድ” አወጣሁ ቢል ብዙም ትርጉም አይሰጥም። በእርግጥ መንግሥት ብዙ ገቢ ስለሚያገኝበት፣ አስቀድሞ “የግምት ትንበያ” ማዘጋጀቱ ጠቃሚ ነው። “ዕቅድ” ከማለት ይልቅ “ግምት”፣ ወይም “ትንበያ” ቢል ይሻላል ለማለት ነው።
የሆነ ሆኖ፣ መንግሥት 1 ሚሊዮን ኩንታል ቡና ወደ ውጭ እንደሚላክ ቢተነብይም፣ በተግባር ግን ከትንበያው በ50 በመቶ የሚበልጥ ምርት ተልኳል። 1.5 ሚሊዮን ኩንታል። በእርግጥ ብዙ ምርት ተላከ ማለት የጥራት ደረጃው እንደ ዓምናው ነው ማለት አይደለም። እዚሁ ሊቀር ይችል የነበረውም ነው የሚላከው። እናም አማካይ ዋጋውን ዝቅ ሊያደርገው ይችላል።


እንዲያም ሆኖ፣ በቡና የውጭ ንግድ ላይ አስገራሚ ለውጥ እንደታየ አያጠራጥርም።
የጥቅምት ወርን ለይተን ብናይ፣ ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር፣ ዕጥፍ ያህል የቡና ምርት ወደ ውጭ ተልኳል።
አምና 177 ሺ ኩንታል፣ ዘንድሮ 351 ሺ ኩንታል።
በዚህ አያያዙ የሚቀጥል ይመስላችኋል? ሊቀጥል ይችላል። የቻይና ኩባንያዎች ብቻ፣ ቢያንስ ቢያንስ 1 ሚሊዮን ኩንታል የኢትዮጵያ ቡና ለመግዛት ማቀዳቸውን ገልጸዋል።
እናም በዚህ አያያዙ፣ በዓመት ውስጥ እስከ 5 ሚሊዮን ኩንታል የሚደርስ ቡና ወይም ከዚያ በላይ ወደ ዓለም ገበያ መሄዱ ይቀራል?
ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ፣ ምናልባትም እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገቢም ሊያመጣ ይችላል።
በእስከ ዛሬ ዓመታዊ የቡና ኤክስፖርት ከፍተኛው መጠን 3 ሚሊዮን ኩንታል ነው። የዐሥራ አምስት ዓመታት መረጃዎችን ስናይ ግን በአብዛኛው ከ2 እስከ 2.5 ሚሊዮን ኩንታል ነው- የአራችን የቡና ኤክስፖርት።

Read 342 times