• ከ125 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል
• ፌዴሬሽን ከተመሰረተ 70 ዓመቱ ነው
• የተጣራ ሀብቱ ከ257 ሚ.ብር በላይ፤ ከ114 ሚ. በላይ ዓመታዊ ገቢ
እጩ ስራ አስፈፃሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው
እጩ ፕሬዝዳንት በነበረ ጊዜ ስለምርጫው ፉክክር...
የዘንድሮው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምርጫ ከጅምሩ አጓጊ የሆነው በተለያዩ ምክንያቶች ነው። ከዚህ ቀደም የፕሬዝዳንት ምርጫው በዚያው ፌዴሬሽን አካባቢ መወሰኑ ተቀይሯል። ከተለያዩ ባለድርሻአካላት ተወዳዳሪዎች መምጣታቸው ከመነሻው ፉክክሩን ፈጥሯል። በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የምርጫ ዘመቻዎች መደረጋቸውና ሐሳቦች መንሸራሸራቸውም ውድድሩን አሟሟሙቆታል።
በመጀመሪያ ከሰባት እጩ ፕሬዝዳንቶች ተርታ ስገባ ሁሉንም ተወዳዳሪ በእኩል አክብሮት ነው የተመለከትኩት። በተለይ ዋንኛ ተፎካካሪዎች ከነበሩት 4 እጩዎች አንዱ ሆኜ ስለገባው ትኩረቴን ስቦታል። ከእኔ ባሻገር ሶስቱ እጩዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በስፖርቱ ያለፉ ናቸው። ገብሬና ስለሺ በስፖርተኝነት ታሪክ ያላቸውና በፌዴሬሽን አስተዳደር ገብተው የሰሩ ናቸው። የተከበሩ ዱቤ ጁሎም አትሌቲክሱን በከፍተኛ ባለሙያነትና ሃላፊነት አገልግለዋል። እነሱ ፌዴሬሽኑ ላይ መስራታቸውና ያላቸውን አቅም ሁሉም ማወቁ ፉክክሩን ያጠነክረዋል።
እኔ ወደ ፌዴሬሽኑ አስተዳደር ለመግባት ከእነሱ የምለየው በክለብ አመራርነት ለአትሌቲክስ እና ለአትሌቶቹ ከማደርገው ልዮ ድጋፍ ተያይዞ ወደ ምርጫው መግባቴ ነው። አዲስ ፊት ከማየት ከተለየ የአስተዳደር ልምድ አንፃር በፌዴሬሽን ለውጥ መፍጠር የሚቻልበት እድል ሰፊ እንደሆነ ነበር የማምነው።
በአጠቃላይ የተሻለ አስተዳደር የተሻለ ውጤት የተሻለ ለውጥ ከመፈለግ አንፃር ሁሉም ባለድርሻዎች ምርጫውን በጉጉት እንዲከታተሉ ሆኗል።
በአትሌቲክስ ያከናወናቸው ተግባራት
ብዙ ያን ያህል ትልቅ ታሪክ ያለኝ ሰው ነኝ ብየ አላስብም። አገሬን ስለምወድ፤ አገሬን የሚያሳይ ፤ አገሬን የሚገልፅ፤ አገሬን የማይበት መነፅር አትሌቲክስ ነው። ሰንደቅ አላማን ከፍ የሚያደርግ፤ የአገር ፍቅር ስሜትና አልሸነፍ ባይነት በአትሌቲክስ ውስጥ አገኛለሁ። በዚህ ምክንያት የተለየ ትኩረት እሰጣለሁ። ከልጅነት ጀምሮ ለስፖርቱ በተለይ ለሩጫ ከፍተኛ ፍቅር ነበረኝ። በትምህርት ቤትም እወዳደር ነበር። ቤተሰቤ ወደ ትምህርቱ እንዳዘነብል በማድረጉ ኤሌክትሪካል ኢንጅነሪንግ ተማርኩ። ከዚያም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኛ ሆኜ ሳገለግል 17 ዓመታት ሆኖኛል። ተቋሙን ከተቀላቀልኩ ከ1 ዓመት በኋላ ወደ አመራርነት ገባሁ ። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሚድል ማኔጅመንት ውስጥ ከ10 ዓመታት በላይ እየሰራሁ ቆየሁ። በምክትል ስራ አስፈፃሚነት ደግሞ እያገለገልኩ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል። የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ላይ መስራት የጀመርኩት ከዚሁ ጋር ተያይዞ ነው። በክለቡ ቦርድ ማኔጅመንት ሳገለግል 6 ዓመት ሆኖኛል። የቦርዱ ሰብሳቢ ነኝ ። በክለቡ ያለውን የአትሌቲክስ ክለብ የምመራው እኔ ነኝ። ኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ከኛ በፊት በአትሌቲክስ ይታወቅ የነበረ ቢሆን ለተወሰኑ ጊዚያት ደብዝዞ ጠፍቶ ነበር። ወደ ክለቡ አመራር ከመጣን በኋላ የለውጥ አቅጣጫዎችን በመንደፍና ለለውጥ የሚያግዙ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ከሰራን በኋላ በክለቡ አስተዳደር ፤ ስልጠናና የአትሌቶች አያያዝ ላይ አሰራሩን በመቀየሩ በምሳሌነት የሚጠቀስበት ደረጃ ላይ አድርሰነዋል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮ ኤሌክትሪክ አትሌቲክስ በብሔራዊ ቡድን አቅም እየተሰራበት ሲሆን አገርን በተለያዩ ዓለምአቀፍ ውድድሮች የሚያስጠሩ አትሌቶችን ይዘን እናገኛለን። በአትሌቲክስ የኢትዮጵያ ጠንካራ ክለቦች ከሚባሉት መከላከያና ባንኮች ተርታ የምንሰለፍ ሆነናል። በኤሌክትሪክ ክለብ አትሌቶች ደሞዛቸው ከ1800 ብር በአሁኑ ወቅት 30 እና 40 ሺህ ብር ደርሷል። ይህም በአትሌቶችና በዙርያቸው ላሉ ባለሙያዎች ትኩረት የፈጠረ ከመሆኑም በላይ ለብዙዎች ክለቦች ተምሳሌት ሆኖ እየተጠቀሰ ነው ። በተጨማሪ ሪከርድ ለሚሰብሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከተለያዩ አገራት የወሰድነውን ተሞክሮ በመንተራስ ስፖንሰሮችና ድጋፍ ሰጭዎችን እያስተባበርን የገንዘብ ሽልማቶችን እየሰጠን ነው። በዚህ አሰራር የዓለም ሪከርድ ያስመዘገቡ አራት አትሌቶችን የሸለምን ሲሆን ወደፊትም ባህላችን አድርገን የምንቀጥለው ነው። በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ግዙፍ መሠረተልማቶች ላይ ለስፖርቱ የሚያግዙ ግንባታዎች እንዲካተቱ በማነሳሳትም ሰፊ ተግባራት ተከናውነዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለ ስድስት መም ዘመናዊ የአትሌቲክስ ትራክ ለክለቡም ለአገርም በቻይና ኩባንያ እያስገነባን ሲሆን እደ ቅርጫት ኳስና ለሌሎች ስፖርቶች የሚሆኑ ስፖርት ማዘውተሪያዎችን በማስፋፋት እየሰራን ነው። የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች ሲያልቁ የኢትዮ ኤሌክትሪክ ክለብ ብቻ ሳይሆን መላው የአገሪቱ ስፖርት ተጠቃሚ የሚሆንበትን አሰራር ነው የምንዘረጋው። እንደ ክለብ ለአትሌቶች የልምምድና የመኖርያ ካምፖችን የመገንባት ራዕይም ያለን ሲሆን በአትሌቲክስ ልዮ አቅም ባላቸው ክልሎች የሚሰሩትን በስፖንሰርሺፕና በተለያዮ ድጋፎች እያጠናከርን ለመሥራትም እናስባለን።
ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የሚያስበው
አትሌቲክስ ትልቅ የዲፕሎማሲ መድረክ እንደሆነ ነው የማስበው። በአመራር ውስንነት የሚፈጠሩ ችግሮች ፤ በየአራት አመቱ ኦሎምፒክ በመጣ ቁጥር የሚፈሰው የአትሌቶቻችን እንባ፤ በአትሌቶች ምርጫ የሚያጋጥሙ ውዝግቦችና የአሰልጣኞች መገፋፋት... በአትሌቲክሱ ዙርያ ያሉ አገርና ህዝብን የሚያስጨንቁ ሁኔታዎችን ማስቀረት አለብን። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ እግር ኳስ ሁሉ አትሌቲክስን የዕለት ዕለት ህይወቱ አካል ሊያደርርገው ይገባል። ኦሎምፒክና ዓለም ሻምፒዮና በመጣ ቁጥር የሚያጨበጭብበት የሚያለቅስበት ስፖርት ሆኖ እንዲቀጥል ሳይሆን የህይወቱ አካል ሆኖ በየቀኑ የሚያስበው የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚያደርግበት እንዲሆን ነው። በሶስት የዓለም ሻምፒዮናዎችና በኦሎምፒክ ራሴን ስፖንሰርሺፕ በማድረግ የኢትዮጵያን አትሌቶች ዓለም አቀፍ ተሳትፎ ታዝቢያለሁ። በዓለም አቀፍ የስፖርት አስተዳደር የኢትዮጵያ ውክልና ያነሰ መሆኑ በጣም የሚያስቆጨኝ ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ውስጥ ያላት ውክልና እንዲያድግ መሥራት ይኖርብናል። ኬንያውያን በዓለም አትሌቲክስ ማህበርና በዓለምአቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስ የገቡበትን አሰራር ትምህርት በማድረግ በእኛ ፌዴሬሽን በኩል እንቅስቃሴዎች ያስፈልጋሉ። ዓለምአቀፍ ውድድሮች በማዘጋጀት ያለውን አቅምም በትኩረት ልንሰራበት ይገባል። የዓለም አገር አቋራጭ ኬንያ ሞምባሳ ላይ ሲካሄድ አስታውሳለሁ ኢትዮጵያ በዚያ ደረጃ የስፖርት መሠረተልማትን በመገንባት መሠል ውድድሮችን ወደ የምናስተናግድበት አቅምና አቅጣጫ መግባታችንን ተስፋ አደርጋለሁ።