በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ከነበረው አገልግሎት በመነሳት
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስተዳደርና ኮሚቴዎች ከ20 ዓመታት በላይ አገልግያለሁ።
አትሌቲክሳችን የኢትዮጵያ ብራንድ ነው። አትሌቲክስ ማለት ኢትዮጵያ ነው። አሁን ያለበት ሁኔታ ከዚህ ቀደም ከነበረው ክፍተቶች ይታዮበታል። ከፌዴሬሽኑ አስተዳደር ውጭ በቆየሁባቸው ጊዚያት ከአመራር፤ ከአሰራርና ከዕድገት አንፃር ያሉትን ችግሮች በደንብ ተመልክቻለሁ።
በውድድር ደረጃ የተሻለ ሂደት ቢኖርም አትሌቲክሱ አደጋ ላይ እየወደቀ መጥቷል። በተለይ ከፓሪስ ኦሎምፒክ 1ወርቅ ይዘን ስንመለስ አትሌቲክሱ መታመሙን ያረጋገጥንበት ነው። የተሟላ አስተዳደር እና መሪ የሌለው ፌዴሬሽን መሆኑን በማስተዋል አንዳንድ ነገሮች እንዲስተካከሉ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሁሉ እስከመፃፍ ደርሻለሁ።
አሁን ፌዴሬሽኑን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት ስመጣ አትሌቲክሱን ለመለወጥና ወደነበረበት ለማምጣት ነው።
በውጭ በነበርኩበት ወቅት ቀደም ሲል አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩ እንደ አዲስ አበባ ስታድየም አይነት የስፖርት ማዘውተሪያዎች መዳከማቸው አበሳጭቶኛል። የኢትዮጵያ ሻምፒዮናን ዱንካን ተጥሎ የሚካሄድበት ሁኔታም አሳዝኖኛል።
ፕሬዚዳንት ከሆንኩ የተሻለ ለመስራት ከዓለም አትሌቲክስ ማህበርና ከአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ጋር የነበረኝን ትውውቅ በመጠቀም ያሉትን ችግሮች ለማስተካከል ነው። የክልል ፌዴሬሽኖችና ክለቦች በአሰራርም በአደረጃጀትም ተዳክመዋል። ይህን መልሶ ወደነበረበት ለመቀየር ነው የማስበው ። የአትሌቲክስ ማናጀሮች ከክልሎችና ክለቦች አትሌቶችን በየጊዜው እየመለመሉ መሥራት የሚችሉት ትክክለኛ አደረጃጀትና አሰራር ሲኖር ነው። በስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነርና ምክትል ኮሚሽነር በመሆን ያገለገልኩበት ልምድ አለ። በተወካዮች ምክርቤት በባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አሁን እየሰራሁ መሆኑ ለስፖርቱ ያለኝን ቅርበት የሚያሳይ ነወሰ። አሁን የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት ለመሆን ከበቃው ውስጥ ገብቼ ለአትሌቲክስ የተሻለ መሥራት እንደምችል አምናለሁ።
ስፖርቱን ባለሙያ ይምራው ሲባል
ስፖርትን መምራት ያለበት ባለሙያና ባለቤቱ ነው። ክፍተቶች አሉ እንጅ ደራርቱም በዚህ አስተሳሰብ ነው ስትመራ የቆየችው። በአመራር ውስጥ ያለው የርስ በእርስ መገፋፋት ነው የሚያበላሸው። ባለሙያዎችን የማቅረብ፤ የማምጣትና የማሰራት ችግር ነው ያጋጠመው እንጅ በሌላው ዓለም ያለው ተሞክሮ ነው እንዲካሄድ የሚፈለገው።
ስፖርቱን ለመምራት የሮጠና የተማረ ቢሆን ይመረጣል። ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን ስለሆነ ያንን ለመምራት ዘመናዊ የአስተዳደር ዲዛይን መፍጠር ያስፈልጋል።
በዓለምአቀፍ ግንኙነትና ቋንቋ መበልፀግም ተገቢ ነው። በአገር ውስጥ ስልጠና ለማካሄድና ውድድሮች ለማዘጋጀት አመራሩ አጠቃላይ እውቀቱ ካለው የተሻለ ነው የሚሆነው። ስፖርተኛ ሆኖ ያለፈና በስፖርቱ ከፍተኛ ትምህርት የቀሰመ ሁለቱንም አጣምሮ የያዘ ወደ አመራሩ ቢመጣ ይመረጣል። እኔ ለምሳሌ ሯጭ ነበርኩ ከዚያም በትምህርት ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪየን ከዚያም ማስተርስ የሰራሁት በስፖርት ነው። በስፖርቱ ላይ በአሁኑ ወቅ በሌክቸረር ማዕረግ እየሰራሁበት ነው።
ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት ለመምራት ስወዳደር “ የአትሌቲክስ ትንሣኤን ማብሰር “ የሚለውን መርህ በማንገብ ነው። ይህን ለማሳካት በሁሉም አቅጣጫዎች ለመሥራት ነው የማስበው። በተለይ የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ ከእድገት ጋር የተያያዘ ስለሚሆን በታዳጊዎችና ወጣቶች ስልጠና ላይ ሰፊ ተግባራትን በማከናወን እሰራለሁ። እንደ አገር ዘመናዊ ትራክ ያስፈልገናል።
Saturday, 21 December 2024 20:34
እጩ ፕሬዚዳንት ዱቤ ጁሎ
Written by ግሩም ሰይፉ
Published in
ስፖርት አድማስ