Tuesday, 24 December 2024 00:00

የጉጂ ትውስታዎቼ

Written by  አብርሀም ገነት
Rate this item
(2 votes)

ክብረ መንግስት

አዶላ ወዩ (ክብረ መንግስት) በጉጂ ዞን አዶላ ወዩ የሚባለው ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ አዶላ ወዩ በቀድሞው ስሟ ክብረ መንግስት መሆኗን ባለፈው ምዕራፍ ጠቅሻለሁ፡፡ ለዚያም ነው ስማቸውን እያቀያየርሁ የምጠቀመው፡፡ ክብረ መንግስት ከኢርባ 60 ኪ.ሜ. ገደማ ትርቃለች፡፡ ከነጌሌ ተነስተን ወደ ኢርባ ለመሔድ ክብረ መንግስትን አልፈናት ስለሔድን፣ አዳራችን እዚያ ለማድረግ ከኢርባ ተነስተን 60 ኪ.ሜ ያህል እንደገና ወደ ደቡብ አቅጣጫ መንዳት ነበረብን፡፡ ደግነቱ ስንመለስ ጎማችን ደህና ስለነበር በመንገድ ላይ አልተቸገርንም፡፡ በዚያ ላይ ቀን ወደ ኢርባ ስንሄድ፣ አዳራችን ክብረ መንግስት መሆኑን አውቀን አስቀድመን አልጋ ስለያዝን፣ ከመሸ ብንደርስም የተቸገርነው ነገር አልነበረም፡፡ ብቻ ግን ክብረ መንግስት ከመግባታችን ወዲያው መብራት ስለጠፋ ትንሽ ቅር ብሎናል፡፡ መብራት በመጥፋቱም የተነሳ ክብረ መንግስትን ዞር ዞር ብለን የመቃኘት ዕድል አልፈጠርንም፡፡ ስለሆነም ራታችንን በልተን፣ ቢራችንን ተጎንጭተን ብዙም ከውጭ ሳናመሽ ወደ መኝታ ክፍላችን ገባን፡፡
በነጋታው እዛው አዶላ ወዮ መረጃ እንዲሰጡን ከቀጠርናቸው ሰዎች መካከል አንዱ በነፃነት የሚናገሩትና የሚያዝናኑት አቶ ቂልጣ ሶርሳ የሚባሉ ጠይም ሰውዬ ነበሩ፡፡ ኦቦ ቂልጣ ሶርሳ (የክርስትና ስማቸውን ነግረውኝ ነበር ግን ረስቼዋለሁ) ወኔያምና ጉልበታም ሽማግሌ ናቸው፡፡ አማርኛ አቀላጥፈው ይናገራሉ፡፡ ታዲያ እኔን ካዝናናኝ ንግግራቸው መሀል፣ አንባቢንም ያዝናና ይሆናል በማለት ጥቂቱን ፅፌዋለሁ፡፡ ቃለመጠየቃችንን ጨርሰን፣ ከነበርንበት ግቢ ወጥተን ወደ ከተማ በመጓዝ ላይ እንዳለን፣ አቶ ቦልቴ ይመስለኛል፣
“ስንት ሚስቶችና ልጆች አለዎት?” ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ኦቦ ቂልጣ፣
“ስድስት ሚስቶችና 36 ልጆች አሉኝ” ሲሉ መለሡ በኩራት፡፡ የሃጂ ዮሐንስ ጋምቤላ ሀያ ስምንት ልጆች ሲገርሙኝ፣ የኦቦ ቂልጣ ደግሞ ሠላሳ ስድስት ልጆች አሏቸው፡፡ ከዚያ እኔ ደግሞ፣ “ግን ክርስቲያን ሆነው ይሄን ያህል ሚስት እንዴት አገቡ?” አልኋቸው፡፡ አቶ ቂልጣ ፈጥነው፣
“ሀይማኖት በእኔ ሚስቶች ምን አገባው?” ሲሉ ጥያቄዬን በጥያቄ መለሱልኝ፡፡ እኔም እንደገና ሌላ ጥያቄ ጠይቄ መከራከሩን ስላልፈለግሁት ዝም ብዬ አለፍሁ፡፡ በመጨረሻ ጋሽ ሳሚ አስቂኝ ምላሽ ያስገኘ ጥያቄ አቀረበላቸው፡፡
“አሁን ሁሉም ሚስቶችዎ በህይወት አሉ?”
“ጠዋት ስወጣ ነበሩ”
በዛው ዕለት ከሠዓት በኋላ ክብረ መንግስትን ለቀን ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ተጓዝን– ወደ ወርቋ ምድር፡፡
ሻኪሶ
ሻኪሶ ስትነሳ መቼም ብዙዎቻችን የምናስታውሳት በወርቅ ማዕድኗ ነው፡፡ አመቻቻችንና አስተርጓሚያችን ኦቦ ሠመሮ እንደነገረን ከሆነ፣ ከዚሁ ከክብረ መንግስት ጀምሮ እስከ ሻኪሶ ድረስ ተራሮች ሁሉ ወርቅ በወርቅ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ አንዳንድ አርሶ አደሮች በእርሻ ማሳቸው ውስጥ ብዙ ክምችት ወርቅ ስላገኙ ባንድ ጊዜ ችግራቸውን አራግፈው ከሀብታሞች ተራ ገብተዋል፡፡ ወርቅ ለማውጣት የመንግስትን ፈቃድ የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በዚሁ አካባቢ ብዙ ሠዎች ባልተደራጀ መልኩ በየስርቻው ወርቅ እንደሚቆፍሩ ይታወቃል፡፡ በክብረ መንግስትና በሻኪሶ ከተሞች መካከል ያለው መንገድ ኮረኮንች ነው፡፡ መንገዱ አስፋልት ሊሆን ጎን ለጎን ቁፋሮ ተጀምሯል፡፡ መንገዱንም የሚያሠሩትም ሼህ መሐመድ አላሙዲን እንደሆኑ ሠምቻለሁ፡፡ ሻኪሶ ላይ ለሚያከናውኑት የወርቅ ማዕድን ማውጣት ስራ ስለሚጠቅማቸው ይመስለኛል መንገዱን በራሳቸው ወጪ የሚያስገነቡት፡፡
ከክብረ መንግስት እስከ ሻኪሶ ባለው መንገድ አይኔ መድረስ እስከሚችልበት ግራና ቀኝ ያስተዋልኩበት ተፈጥሮ ውብ ነው፡፡ ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች፣ ውብ ገላጣ መስኮችና ሜዳዎቹ ላይ የሚግጡ የቤት እንስሳት፤ የሚንቦለቦሉ ንፁህ ምንጮች፣ የገጠር እርሻዎች…. በመሬቱ ውጫዊ ገፅታ ላይ ካስተዋልኩት ጥቂቱ ነው፡፡ ውስጡ መቼም ወርቅ ነው ተብሏል፡፡ ታዲያ በዚህ አካባቢ ወርቅ በብዛት መኖሩን ሳስብ ደስ ቢለኝም ሌላ ነገር ደግሞ እየከነከነኝ ነበር፡፡ ወርቅ ለማውጣት ተብሎ የሚቆረጡ ትላልቅ ዛፎች፣ የሚናዱ ውብ ኮረብታዎች፣ እንዳልሆነ የሚሆኑ ለም የእርሻ ማሳዎች ያሳዝናሉ፡፡ ያን የመሠለ ውብ ተፈጥሮ በማዕድን ቁፋሮ መረበሹ ደስ አይልም፡፡ ምናለ ይሔ ወርቅ በዚህ ለምለም ቦታ ላይ ከሚከማች፣ ለእርሻ በማያመቹ በደረቅና በበርሃማ የአገራችን አካባቢዎች ቢገኝ ስል ተመኘሁ፡፡
ሻኪሶ ከተማ ሊገቡ ሲሉ አዋጣ የሚባል አንድ ትልቅ ወንዝ ያገኛሉ፡፡ እኛ ሻኪሶ ስንገባ ከቀኑ ወደ 10፡00 አካባቢ ይሆናል፡፡ እንደገባንም ሜላት ፔንሲዮን በሚባል ደረጃውን የጠበቀ ቆንጆ መኝታ ቤት ገብተን አረፍን፡፡ ሜላት ፔንሲዮን ሠፊ ግቢ ያለው ሲሆን፤ ግቢውም ሙሉ በሙሉ በሲሚንቶ የተሠራ ነው፡፡ የሻወሩና የአልጋዎቹ ጥራት ግሩም ነው፡፡ ሌላው ሜላት ፔንሲዮንን እንድንወደው ያደረገኝ ነገር በግቢው ውስጥ ማንኛውም አይነት መጠጥ የሚሸጥበት ግሮሰሪ መኖሩ ነው፡፡ በዚያ የሚያምር ግቢ ቢፈልጉ ግሮሰሪው ውስጥ፣ ቢፈልጉ በረንዳ፣ ቢያሻ ክፍል ውስጥ ሆነው የሚፈልጉትን አይነት መጠጥ እየወሰዱ፣ በስሱ የሚከፈተውን ሙዚቃ እየኮመኮሙ ሲጫወቱ ማምሸት እንዴት ያዝናናል መሠላችሁ! እድላችን ነው መሠለኝ ምሽት ላይ ሻኪሶም መብራት ጠፍቶ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ዝናብ ዘንቦ መንገዱ ሁሉ ጨቅይቶ ስለነበር፣ ጋሽ ሳሚ፣ ተስፍሽ እና እኔ ከአልጋ ቤታችን ወጥተን ራት ለመብላት የተንቀሳቃሽ በተን ስልካችንን ባትሪ እያበራን በጭቃ የዳከርነው መዳከር መቼም አይረሳኝም፡፡ ዝናቡ ከመዝነቡ በፊት በጊዜ አቶ ቦልቴ፣ ሠመሮ እና እኔ የከተማዋን ጥቂት ክፍል ተዘዋውረን ጎብኝተናል፡፡ ሻኪሶ ከተማ ውስጥ ከምንም በላይ የሚበዙት ሞተር ብስክሌቶች ናቸው፡፡ ሌሎች አጎራባች ከተሞች ሁሉ ሞተር ብስክሌት የሚገዙት ሻኪሶ እንደሆነ ሠምቻለሁ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ ዙሪያዋን በወርቃማ ተራሮች የተከበበችው ሻኪሶ ሞቅ ደመቅ ያለች ናት፡፡ ከእራት ተመልሰን፣ የፔንሲዮኑ እንግዳ ተቀባይ ከሆነችው ሚጣ (ብላ ከተዋወቀችን) ቆንጅዬ ልጅ ጋር ቢራና ጅን እየጠጣን ስንጫወት አመሸን፡፡ ሻኪሶ ትዝታዬ ናት፡፡ በሜላት ፔንሲዮን በጣም ጥሩ ምሽትና አዳር ነበረን፡፡ ሻኪሶ የሚያሰነብት ስራ ቢኖረን ኖሮ ከሜላት ፔንሲዮን ንቅንቅ አንልም ነበር፡፡ ግን በተሰጠችን የመንግስት አበል ስራችንን ቶሎ ቶሎ ማጠናቀቅ ነበረብንና ሻኪሶን በአንድ ቀን አደር ቻው ማለት የግድ ሆነ፡፡
ከሻኪሶ— ሀሮዋጩ
ሚያዚያ 10 ቀን 2005 ዓ.ም፤ ሻኪሶ ከተማ ካደርንበት ከምቹው ሜላት ፔንሲዮን በማለዳ ነበር ለባብሰን የወጣነው፡፡ ከሻኪሶ በቀጥታ ተጉዘን የምናርፈው ሀሮዋጩ የምትባል ከተማ ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው አጠቃላይ እቅዳችን እንዲህ ነው! ሀሮዋጮ ደርሰን ተዘጋጅተው የሚጠብቁንን ሽማግሌዎች እናነጋግራለን፡፡ እንደ ጨረስንም ጉዟችንን እንቀጥልና በዚያው ዕለት ዲላ ገብተን እናድራለን፡፡ በነጋታው ደግሞ በጣም በጠዋት ተነስተን ወደ ቡሌሆራ እንሄዳለን፡፡ ቡሌሆራ የኡራጋ ጎሳ አባገዳን ስለቀጠርናቸው እየጠበቁን ነው፡፡ እንግዲህ የሌሎችን ቦታዎች የጉዞ ሁኔታችንን ወደፊት የምንደርስበት ሆኖ ከሻኪሶ እስከ ሀሮዋጩ ያደረግነውን ጉዞ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
ከሻኪሶ ሀሮዋጩ ያለው መንገድ ኮረኮንች ሲሆን፣ ርቀቱም 70 ኪ.ሜ ያህል ይሆናል፡፡ ከሻኪሾ የወጣነው የደቡብ ምዕራብ አቅጣጫን ይዘን ነው፡፡ ከከተማው ከመውጣታችን በፊት አፋችንን ማሟሸት ስለፈለግን፣ እኔ ወርጄ ትኩስ የሚበላ ነገር መፈለግ ጀመርሁ፡፡ ሻኪሶ ከእንቅልፏ ገና አልነቃችም፡፡ ፍላጎታችን ትኩስ አምባሻ ካለ እሱን ለመግዛት ቢሆንም፣ አንድ ሁለት ቤቶች ጠይቄ ስላጣሁ ትኩት በዘይት የተጠበሱ ብስኩቶች ገዝቼ ወደ መኪናችን ገባሁ፡፡ ጉዟችንን ቀጠልን፡፡
ጠዋቱ ብርዳምና ዝናባማ ቢሆንም፣ በመኪናችን ውስጥ የተከፈተው ሞቅ ያለ የትግርኛ ዜማ በተለይ ተስፍሽንና እኔን በጣም አነቃቅቶን ነበር፡፡ እኔ የምቀመጠው ጋቢና ስለነበር የሾፌራችንን የተስፍሽን ስሜት ብዙ ጊዜ እጋራለሁ፡፡ ሁላችንም ግን ትግርኛውን በድምጽና በፉጨት አብረን እያዜምን በተቀመጥንበት እንደንስ ነበር፡፡ ተስፍሽ ሾፌር ከመሆኑ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ በውትድርና ስላገለገለ ትግርኛ መስማትም መናገርም ይችላል፡፡ ከዘፈኑ በተጨማሪ ብስኩት አልበላም ከሚለው ከጋሽ ሳሚ በስተቀር ሁላችንም ትኩስ ብስኩት እየበላን ስለነበር ጠዋቱ አልከበደንም፡፡ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን ከኋላ ወንበር ድንገት ያልታሠበ ሳቅ ፈነዳ፡፡ መጀመሪያ እነሱ ሲስቁ ሳይገባኝ እኔም እንደ መሳቅ አልሁና የጠዋቱ ሳቅ የፈነዳበትን ምክንያት ዞር ብዬ ጠየቅኋቸው፡፡ አቶ ቦልቴ መነፅሬ ጠፋኝ ብሎ የሌለ ይቀውጣል፡፡ በኋላ ሲያዩት ለካስ መነፅሩ አይኑ ላይ ነው፡፡ ቦልቴ መነፅሩን አይኑ ላይ ገድግዶ መነፅሬ ጠፋኝ ብሎ ሠመሮንና ጋሽ ሳሚን ውለዱ ሲላቸው ኖሯል ሁለቱም በሳቅ የፈረሡት፡፡ እነ ጋሽ ሳሚ ባያዩት ምናልባትም መነፅሬን ሜላት ፒኒሲዮን ነው የረሳሁት ብሎ ሊመልሰንም ይችል ነበር፡፡ በአቶ ቦልቴ ልበ ቢስነት ከኋላ ተቀማጮቹ ተቀብለን እኔና ተስፍሽም መሳቅ ያዝን፡፡ ዝናባማውና ብርዳማው ጠዋት ሊሸብበው የሚጥረው ስሜታችን በአቶ ቦልቴ ገጠመኝ የበለጠ ተነቃቃ……፡፡
ከሻኪሶ ከወጣን በኋላ ያገኘናት አነስተኛ ከተማ በሌኬሳ ትባላለች፡፡ በሌኬሳ በኦሮምኛ ሸለቆ ውስጥ ያለች ከተማ ማለት እንደሆነ ሠመሮ ነግሮናል፡፡ በርግጥም በሌኬሳ ሸለቆ ውስጥ የተቀረቀረች ከተማ ናት፡፡ የምትገኘውም በአዶ ሻኪሶ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ በዚሁ አካባቢ፣ ከመንገዳችን በስተቀኝ የቆሙት ኮረብታዎችና ገምገሞች በከባድ ጉም ተሸፍነው ነበር፡፡ ከመንገዱ በስተግራ በደንና በጉም የተሸፈኑ ተራሮችን፣ በስተቀኝ ደግሞ በእንሰትና በቡና ተክል ያሸበረቁ ሸለቆዎችን እየተመለከቱ መጓዝ እንዴት ደስ ያሰኛል! የመሬቱ ከፍታ እየጨመረ ስለሚሄድ፣ የመኪናችን ፍጥነትም አዝጋሚ ነበር፡፡ በዚያ ላይ ንጋት ላይ የዘነበው ዝናብ ያንን የቀይ አፈር መንገድ በጣም አንሸራታች ስላደረገው፣ ተስፍሽ በጥንቃቄ ባይነዳ ኖሮ ምናልባትም መኪናችን አያድርገውና አንድ መታጠፊያ ላይ ሽብልል ማለቷ አይቀርም ነበር፡፡
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መንገዱ ጭቃው ምጥጥ ስላለ ጉዟችን በተስተካከለ ፍጥነት ሆነ፡፡ በአሞራ ክንፍ ቅርፅ ተሠርተው ጣሪያቸው በወፍራም ሳር የተከደኑ የገጠር ቤቶች በመንገዳችን ግራና ቀኝ በብዛት ይገኛሉ፡፡ ወላቦ እና ሀንጋዲ የሚባሉ ከተማ ቀመስ አነስተኛ መንደሮችን እንዳለፍን ጥቅጥቅ ያለውን የሀንጋዲ ጫካ አገኘን፡፡ የሀንጋዲ ጫካ ከመንገዱ በግራም በቀኝም በሠፊ መሬት ላይ የተንሠራፋ ማራኪ ደን ነው፡፡ ከሀንጋዲ ጫካ ትንሽ አለፍ እንዳልን፣ ከመንገዱ በስተቀኝ ከፍተኛ ተራሮች ይታያሉ፣ ተራሮቹ በነጭ ጉምና በደመና ተሸፍነዋል፡፡ በተለይ ጉሙ ለተራሮቹ ልዩ ውበትን አላብሷቸው ነበር፤ ጉሙ እየተትጎለጎለ ከተራሮቹ አናት እስከ ግርጌው ሸለቆ ድረስ ይወርዳል፡፡ አካባቢውን እስክናልፈው ድረስ ከዚህ በጉም የተሸፈነ የተራራ መልክአምድር ላይ አይኔን አልነቀልሁም፡፡ መልክአምድር ማየት እወዳለሁ፡፡
ሱኬ ወረቀታ የምትባለዋንና ሌሎችንም ትንንሽ ከተማ ቀመስ መንደሮች አቋርጠን ሀሮዋጮ ከተማ ደረስን፡፡ እንደደረስንም ከጉዞ ቡድናችን ምሳ የሚበላው ምሳ ሲበላ፣ መብላት ያልፈለግነው ደግሞ የሀሮዋጮን ቡና ፉት አልንና ጊዜ ሳናጠፋ ወደ ስራችን ተሠማራን፡፡ ሀሮዋጮ በፊት ሰሎሞ ተብላ ትታወቅ ነበር፡፡ ሀሮዋጮ ከተማ ካስተዋልኩት ነገር አንዱ ቤቶች በራቸው በቆርቆሮ ሳይሆን በተጠረበ እንጨት መገጠሙን ነው፡፡ እኔ ያየኋቸው ሁሉም ቤቶች እንደዚያ ናቸው፡፡ ምናልባት ባካባቢው እንጨት እንደልብ ስለሚገኝ ይሆናል በሩን በእንጨት የሚገጥሙት፡፡ ትንሿ ሀሮዋጮ የኡራጋ ወረዳ ዋና ከተማ ብትሆንም ምግብ ቤቶች እንጂ አንድም ሆቴል አልነበራትም፡፡ ሀሮዋጮ ዙሪያዋን ቡና አብቃይ በሆኑ ገጠሮች የተከበበች የቡና ሀገር ናት፡፡
ጉጂ ውስጥ በነበረን ቆይታ የሀሮዋጮ አጋሮቻችን ያደረጉልንን ፈካ ያለ አቀባበልና ግብዣ ሁልጊዜም የማስታውሰው ነው፡፡ ደግሞም የትኛውም ወረዳ ላይ እንደዚያ አይነት አቀባበልና ግብዣ አልተደረገልንም፡፡ የወረዳው የባህል ባለሙያዎች— እነ ሙሉጌታ፣ አቦ ትመቻላችሁ! ፍቅር ናችሁ፡፡ አመስግነናል፡፡ ቢደርሳችሁም ባይደርሳችሁም አሁንም በድጋሚ በአዲስ አድማስ እናመሰግናችኋለን፡፡
የሀሮዋጮ ስራችንንና ግብዣችንን እንደጨረስን ጉዟችንን በቀጥታ ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ቀጠልን፡፡ ዲላ ገብተን ማደር ይኖርብናል፡፡ ከዚያ በፊት ግን አንድ ድንቅ ስፍራ እናያለን፡፡
ጌቱጌሻ— የቅርብ ሩቁ ፏፏቴ
ይሄንን ቦታ የማየት ዕድሉን በማግኘቴ እድለኛ ነኝ፡፡ ሀሮዋጮ ከተማ ውስጥ እያለን ሙሉጌታ የሚባለው ወጣት በመንገዳችን ላይ ፏፏቴ እንዳለ ነግሮኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ቦታው ከመንገድ ሩቅ መስሎ ስለታሰበኝ፣ ከመኪና ወርደን እናየዋለን ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ ሌሎችም ጓደኞቼ አላሠቡትም! ምስጋና ለአስተርጓሚያችንና አመቻቻችን— ለሠመሮ ይገባዋል! እሱ ነው ቦታውን ወርደን እንድናየው ሀሳቡን ያቀረበልን፡፡ ጌቱጌሻ የሚገኘው የዲላን መስመር ይዘው ከሀሮዋጮ ከተማ ወጣ እንዳሉ ነው፡፡ ጌቱጌሻ፡፡ ጎቱ በኦሮምኛ ፏፏቴ ማለት ነው— የጌሻ ፏፏቴ እንደማለት፡፡ መኪናችንን ዳር አስይዘን አቁመን እንደወረድን ያገኘነው አነስተኛ ሜዳ ነው፡፡ ወደ ሸለቆው አፋፍ ቀረብ ስንል፣ ነጭ አረፍ የሚደፍቅ ፏፏቴ በውብ ጫካ መሀል ነጭ መቀነት መስሎ እየተወረወረ ሲወርድ ተመለከትን፡፡ ቅርብ ይመስላል፣ ወደ ፏፏቴው ለመውረድ ግን አልደፈርንም፡፡ ከጌቱጌሻ በታች ያለው ሸለቆ እጅግ ውብ ነው! ሸለቆው ጥቅጥቅ ባለ ጫካ የተሞላ ነው፡፡ እኛ ከቆምንበት ባሻገር ባሉት የሸለቆው የተራራ ራሶች ላይ ደግሞ ጉም ሰፎ ይታያል፡፡ ፏፏቴው፣ የሸለቆው ልምላሜ እና ተራራውን ያሸበተው ጉም በአንድ ላይ ሲታዩ ጌቱ ጌሻን በውበት ላይ ውበት የደረበ የተፈጥሮ ፈርጥ አድርጎታል! እኛም ከዚህ የተፈጥሮ ገጸ በረከት የምንችለውን ያህል በካሜራችን ቀረጽን፡፡
ፎቶ ተነስተን ወደ መኪናችን ስንቀሳቀስ ሦስት የአካበቢው ነዋሪዎች ወደ እኛ መጡ፡፡ ከእኛ ጋር ለመቀራረብና ለማውራት መፈለጋቸው ከገጽታቸውና ከሁኔታቸው ያስታወቃል፡፡ ጊዜ ቢኖረን ብዙ ነገር እንጠይቃቸው ነበር፡፡ ሁላችንንም ያስገረመን ነገር፣ ያ ቅርብ መስሎ የሚታየው ፏፏቴ አጠገቡ ለመድረስ ከ1 ሰዓት በላይ በእግር እንደሚያስኬድ መስማታችን ነው፡፡ “አዎ፣ ሸለቆው ቅርብ አስመስሎት ነው እንጂ ፏፏቴው ለመድረስ ሩቅ ነው” ነበር ያሉን እነዚያ የአካባቢው ሠዎች፡፡
የጎቱ ጌሻ አጭር ቆይታችንን አጠናቀን መንገዳችንን ቀጠልንና ሀሩ የሚባል የገጠር ከተማ ደረስን፡፡ ዕለት አርብ የሀሩ የገበያ ቀን ስለሆነ፣ ገበያተኛ ሰዎችና አጋሰስ ፈረሶች በመንገድ ላይ በአንድነት ይጅመለመሉ ነበር፡፡ ሀሩ የደገኞች ገበያ ናት፡፡ ሀሩ ከተማን እንደወጣን ያለው አካባቢ ሌሎች አይነት ዛፎች ሳስተው ቀርከሀ የሚበዛበት ደጋማ ስፍራ ነው፡፡ በተጨማሪም ፈረሶች በብዛት መስኩ ላይ ፈሰው ይታያሉ፡፡ ከዚህ በመቀጠል ያገኘናት የያማ ወረዳ ዋና ከተማ የሆነችውን አንፈሌኮላ ከተማን ነው፡፡
ሰፊውንና ለምለሙን የጉጂ ዞን ወጥተን ጌዲኦ ዞን ገብተናል፡፡ ጉጂና ጌዲኦ የሚጋሩት ረጅም የመሬት ወሰን አላቸው፡፡ ጌዲኦ ዞን እንደገባን በመጀመሪያ ያገኘናት ተለቅ ያለች ከተማ ቡሌ ናት፡፡ ቡሌ የተቆረሰ ድፎ ዳቦ በየበራፉ በብዛት የሚቸረቸርባት ከተማ ናት፡፡ ቡሌ ከተማን በመውጣት ላይ እንዳለን ዝናብ መጣል ጀመረ፡፡ ከዚህ በኋላ ያለው መንገድ ወደ ታች የሚያምዘገዝግ ቁልቁለት ነው! ይህ ቁልቁለት የታላቁ የምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ መግቢያ አፍ ነው፡፡ በብቁው ሾፌራችን አማካኝነት ሚትሱብሻችን ቁልቁለቱን ወርዳ ወደ ስምጥ ሸለቆው የሀገራችን ክፍል በሰላም አስገባችን፡፡ ዲላ ስንደርስ ዝናብ አስድሞ ዘንቦ ኖሮ መሬቱ በሙሉ ጨቅይቶ ነበር፡፡
ዲላ
ዲላ በጉዟችን እስካሁን ካገኘናቸው ከተሞች ትልቋ ናት፡፡ ዲላ የጌዲኦ ዞን ዋና ከተማ ናት፡፡ ዲላ ዙሪዋን በእርሻ ሀብት በታደሉ ለም ገጠሮች የተከበበች ናት፣ በጣም የምትታወቀው በቡና ነው፡፡ ዲላ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ከሚማረው ታናሽ ወንድሜ ጋር አብረን አመሸን፡፡ አዳራችንን ዲላ አድርገን ቡሌሆራ የሚጠብቁን አባገዳ 2 ሠዓት ላይ ድረሱልኝ ስላሉን ትናንቱን ከጠዋቱ በ12፡00 ዲላን ለመልቀቅ ተነጋግረን ነበር ወደየመኝታችን የገባነው፡፡ እኔ የተንቀሳቃሽ ስልኬን የማንቂያ ጥሪ (አላርም) 12 ሠዓት አድርጌ ሞልቼው ስለነበር የተነሳሁት ከሁሉም ቀድሜ ነው፡፡ ከተጣጠብኩ በኋላ ሁሉንም የስራ ጓደኞቼን በስልክና በራቸውን በማንኳኳት ቀሰቀስኳቸው፡፡ እኛ ብንነሳም ተስፍሽ ተነስቶ መኪናዋን ካላስነሳ የኛ ብቻ መነሳት የትም ስለማያደርሰን ተስፍሽ እስኪነሳ ክፍሌ ውስጥ ቁጭ ብዬ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ተስፍሽ ለባብሶና ተጣጥቦ ወጥቶ የመኪናዋን ሞተር ማስነሳቱን ስንሰማ፣ እኔና ወንድሜ የኔን ሁለት ቦርሳዎች ይዘን ካደርንበት ክፍል ወጣን፡፡ ከክፍሉ በመውጣት ላይ እንዳለን፣ ተስፍሽ መኪናችን አጠገብ ቆሞ ከሆቴሉ ዘበኞች ጋር የምሬት ንግግር ሲናገር በጨረፍታ ሰማሁት፣ “ጎማ ምናምን” ያለ መሠለኝ፡፡ “ጎማው ተንፍሶ እንዳይሆን ብቻ” አልሁኝ በሃሳቤ፤ በጥርጣሬና በስጋት ተረበሽሁ፡፡ የፈራሁት አልቀረም ደርሼ ስመለከት ያ መናጢ ጎማ እንደ ልማዱ ተኝቷል፡፡ የጥናት ቡድኑ አስተባባሪ እንደመሆኔ ጉዞው እንዲሰምር ቀዳሚ ሀላፊነት አለብኝ፡፡ በጉዟችን እስካሁን የገጠሙን ችግሮች ሁለት ናቸው፡ የኢርባው አባ ገዳ ቁጣና የመኪናችን የጎማ ችግር፡፡ ከሁሉም የከፋው ችግር ጎማችን ነበር፡፡
ለጊዜው የምወስነውን ስላላወቅሁ ለጥቂት ደቂቃዎች ዝም ብዬ ቆሜ ሳስብ ቆየሁ፡፡ 2 ሠዓት ላይ ቡሌ ሆራ መድረስ ይኖርብናል፡፡ ጎማችን ተንፍሷል፣ መሰራት አለበት፡፡ ለማሰራት ደግሞ ጎሚስታዎች እስኪከፍቱ ድረስ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ ተስፍሽን ምናልባት ተቀያሪውን ጎማ ገጥመን ይሄኛውን ባይሰራም ጭነነው መሔድ እንችል እንደሆነ ስጠይቀው፣ “በአንድ ጎማ እማ በጭራሽ አልሄድም!” አለኝ፡፡ የመኪናው ደህንነት ከማንም በላይ እሱን ስለሚመለከት በውሳኔው ጣልቃ መግባት አልፈለግሁም፡፡
እዛው ዲላ ቆየንና ጎሚስታ ፍለጋ መዘዋወር ጀመርን፡፡ ከስንት ፍለጋ በኋላ አንድ ጎሚስታ ተከፍቶ አገኘን፡፡ ከሠመሮ ጋር ሆኜ ገና ከመኝታችን ከተነሳን አንስቶ የስራ ስልክ እደውላለሁ፡፡ ቡሌሆራ የቀጠሩን አባገዳ ስናረፍድባቸው ቀጠሮውን እንዳይሰርዙት ሰግቻለሁ፡፡ ጎማችን እየተሠራ፣ እኛ ደግሞ ቁርስ ለመብላት በእግር እየተንቀሳቀስን ባለበት ሰዓት መልካም ዜና ሰማሁ፤ አባገዳው ይጠብቋችኃል ችግር የለም የሚል ዜና፡፡ ዜናውን ለሁሉም ጓዶቼ አበሰርኳቸውና ቁርሳችንን በደስታ በላን፡፡ ጎማችን ተሠርቶ እንዳለቀም፣ እስከ ሞያሌ ድረስ በተዘረጋው አስፋልት የደቡብን አቅጣጫ ይዘን ከዲላ ወጣን፡፡

Read 898 times