Saturday, 21 December 2024 20:57

ሐመልማሉ አዳም!

Written by  በተሻለ ከበደ
Rate this item
(2 votes)

      ቀጠሮ አለን፤ ከሥነ- ጹሑፍ ጠቢቡ አዳም ረታ ጋር ፤ ቀኑ ማክሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም ነው። ከባቢው ብርሐን ለብሷል። አዳም ጥቁር ሹራብና ከስክሰ ጫማ አድርጓል። የሆሊውድ አክተር የምታስመስለውን ጥቁር መነጽሩን ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧታል። እንደደረስን ከመልካም ፊቱ ላይ ፈገግታ ደርቦ ተነስቶ በእቅፍ ተቀበለን። ባየሁት ቁጥር በመጽሐፉ “አውራጃ የሚሸፍን ትከሻ…” ያለውን ያስታውሰኛል። አዳም ባለሰፊ ትከሻ ነው፤ ሲያቅፍም ሞላ አድርጎ ነው። 

“ ምን ትፈልጋለህ?” ለሚለው ግብዣችን፤ የአዳም መልስ “ባቅላቫ ” የሚል ነበር። ታዲያ ለምን መስቀል ፍላወር ወደሚገኘው ኮንዲቶራይ አንሄድም በሚለው ተስማምተን፣ ታየም ኮፊን ትተን ወጣን፤ መስቀል ፍላወር አካባቢ ኮንዲቶራይ የተባለ ኬክ ቤት ውስጥ ተሰየምን። እኛ ሦስት ጎረምሶች ኬክ፣ አዳም ደግሞ ባቅላቫ እየበላን ጨዋታው ተጀመረ። በቀኙ በኩል  ተቀምጬ በዓይኑ በኩል ያየኋት ነፍሱ እንደ ጥር ስማይ ንፁህ ነበረች።
ታዋቂው ፈረንሳያዊ  ደራሲ ቪክቶር ሁጎ ስለ ሌላኛው የሀገሩ ልጅ፣  የ20ኛው ክፍለ ዘመን ተደናቂ ደራሲ ሆኖሬ ዲ ባልዛክን፣ ለመግለፅ የተቀመጠበትን ነገረ ሃሳብ ወደ እዚህ ልሳብና ላምጣው፦
“He is the historian of the heart, the anatomist of society, the poet of ambition and despair.”
አዳም ለእኛ ከባልዛክም በላይ ነው። የልባችን ቁስል ወይም የነፍሳችን ስቃይ ተራኪ ብቻ አይደለም፣ ከዛችው ስቃያችንና ቁስላችን ህይወትን እንደ አዲስ ይፈጥራል። የተስፋችንን ሞት ከብስባሹ አውጥቶ በረቂቅ ስነ-ጥበባዊ ብርሃን፣ ጭለማውን ገፎ ወደ ሕይወት የሚያሻግራት  ልዕለ-ሰብ  ነው። በአዳም ድርሰት ውስጥ ሕይወት የሌለው ነገር ምን አለ?  መንገዱ፣ አቧራው፣  የመንገዱ መብራት፣ ድንጋዩ ፣ እንጨቱ ፣ ህንፃው፣ ቤቱ፣ ምግቡ ...  ሁሉም ሕይወት አለው። አዳም የሕይወት ደራሲ ነው።  ለዚህም ነው ሕይወት ላይ የገነነውና የተሾመው። የአዳም ሥራዎች ግባቸውን በቀለም ይወከሉ ከተባለ ሐመልማል አረንጓዴ ነው፤ የሕይወት ቀለም ነውና።
አዳም የዘመናችን ተጋዳሊ ነው። የስነ-ጽሑፍ ማዕምሩ ቴዎድሮስ ገብሬ ስለ ሐዲስ ሚቶሎጂ (ዘመናዊ ተጋዳሊ) ሲያትት፤“ ... የሐዲስ ሚቶሎጂ ዓቢይ ጉዳይ የግለሰቡ ልቡና እና ዩኒቨርሳዊ ቁርኝት ነውና ለነባሮቹ (ለብሉይ ሚቶሎጂ) ‘ፍፁማን’ እውቅና አይሰጥም። እንደ ብሔርተኝነት፣ ጎሰኝነት፣ መልክአ ምድራዊ ውሱንነት ያሉ ጽንስ ሐሳቦች በሁለንታዊ፣ ዓለም አቀፋዊ ባሕሎች መረታት አለባቸው ብሎ ያምናል” ይላል (በይነ ዲሲፕሊናዊ የሥነ ጽሑፍ ንባብ ፥ 94- 95)።
በዚህም ምክንያት አዳም “የሃሳብ ማዕከል” እንዲሆን እፈልጋለሁ። ለም ? ቢያንስ ቢያንስ በሦስት ማዕከላዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ምክንያት፦
አንደኛ የወል እሳቤያችን ነፍስያ  ከአዳም የብዕር ምጥ ስለምትከፈል፤ ሁለተኛ  ህዝባዊ ፖለቲካችን በአዳም የስነ- ጽሑፍ  ፍልስፍና ሐርነቱን (Emanicipation) ስለሚጎናፀፍ፤ ሦስተኛ ማህበረሰባዊ ውጥንቅጣችን በትስስር ፍኖት በአዳም ሰራሽ ሕጽናዊነት  ህልውናውንና ድኅነቱን ስለሚያገኝ ነው።  
ይህን የተመረጠ ውይይት እናንተ ጋር ለማድረስ የመረጥኩት ዘዴ እንደ ወረደ ባደረግነው የውይይት ቅርጽ ነው። ለየት ቢልባችሁ ሕግ የተከተለ ቃለ መጠይቅ ሳይሆን፣ ለመጨዋወት በተገናኙ አራት ሰዎች መሐል የተደረገ ውይይት መሰል ጨዋታ በመሆኑ ነው። ውይይታችንን የግል ምልከታ አድርጌ ላለመፃፍ የወሰንኩበት ምክንያት ደራሲው በእኔ አተያይ እንዳይቀነበብና አንባቢዎችም የደራሲውን ምላሽ በየራሳቸው መንገድ እንዲረዱትና ለአተረጓጎምም ክፍት ለማድረግ በማሰብ ነው። በተረፈ ግን ቀስ ተብሎ እየተብላላ፤ ከተቻለም ምን ማለቱ ነው? ተብሎ እየተጠና ቢነበብ እጅግ ፍሬያማ ነገር ይወጣዋል ብዬ አምናለሁ። በውይይቱ ላይ የተሳተፍነው—እኔ፣ ጋዜጠኛ ሐብቱ ግርማና የቴአትር ባለሙያ የሆነው ገዛኸኝ ድሪባ ነበርን።
አዳም፤ ጨዋታችን ለአንባቢ እንዲደርስ መልካም ፍቃድህ በመሆኑ በቅድሚያ በአንባቢዎቻችን ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
ሀብቱ:- አዳምሻ አራታችንን የሚያስማማ ተረት እንዴት መስራት እንችላለን?
እሱን ለመስራት ነው መታገል ያለብን ብዬ እማስበው። “ፍትሃ ነገስቱን” የሚቀበል አለ፤ “ብሔር ብሔረሰቦችን “ የሚቀበል አለ፤ “መሃል ሰፋሪም“ አለ። ስለዚህ አዲስ ታሪክ መፍጠር ያስፈልገናል፤ በተጨማሪም ለህልውናችን አዲስ መዋቅር መፍጠርም ግድ ይለናል (so we need to make a new story and new structure for our existence)። ምን ይሰማሃል በዚህ ጉዳይ ?
አዳም:- አቅጄ አልነሳም፣ ይሄን ልስራ ያንን በማለት አይመጣም! ልብ ወለድ ስፅፍ ይሄን ተረክ (story) ልፃፍ ብዬ አልቀመጥም። የሆነ ተረክ አለ እሱን ትተርካለህ። አቅደህ አትፅፍም ፤ ዝም ብዬ ስኖር ተረክ ያጋጥመኛል፤ እፅፋለሁ። እንጂ እንዲህ ማድረግ አለብኝ ብዬ አልዘረዝርም። ያ’ ሌላ መንገድ ነው፤ የእኔ አይደለም። እኔ በስፖንታኒየስ (Spontaneous) በኩል ነኝ። የሆነ የተያያዙ ተረኮች ይገጥሙኛል፤ እነሱን እሰራለሁ። ጠዋት ተነስቼ ድርሰት ልፃፍ አልልም፤ ተነስቼ ወንበሬ ላይ አልቀመጥም፤ ልፅፍም እችላለሁ ፣ ቶሎ ልነሳም እችላለሁ፣ ወይም ላዛጋ እችላለሁ አላውቅም ሃሃሃ ....የስነ ጥበብ ትረካ (Art narrative) እና የፖለቲካ ተረካ (political narrative)ተለያዩ ናቸው። የጋራ ነገር ሊኖራቸው ይችላል።
ተሻለ፦ በዚህ ዘመን ስነ ጥበብ ራሱ ፖለቲካ አይደለም?
አዳም፦ ሁሉም ነገር ፖለቲካ ነው። ንድፈ ሀሳብ (theory) እና ፍካሬ ግን የየራሳቸው ባህሪ አላቸው። ግን እንዴት ነው የተወከሉት የሚለው ጉዳይ ነው ወሳኙ፤ እንጂ ሁሉም ቦታ ፖለቲካ አለ። ምድር ላይ ስትኖር ተረካ (Narrative) ውስጥ ሁሉም ነገር አለ። አየር፣ ሳይንስ፣ ሃይማኖት-- ብቻ ሁሉም ነገር አለ። .... እዛ ውስጥ በማርያም እሚምል አለ፤ ከሦሰት ሺህ ዓመት በፊት ግን አልነበረም ወዘተ ...
ሀብቱ፦ አሁን እንኳን በራሱ እሚምል ነው ያለው ሃሃሃ ..
አዳም፦ ጥያቄህን ግን መልሼልሃለሁ?
ሀብቱ፦ መልስህን ሳይሆን መንፈስህን ነው የፈለግኩት፤ ደርሶኛል ቆንጆ ነው...ልክ አሁን እንዳለንበት የሚያደክም ዘመን .... ማለትም የዛሬ 40 ዓመት የተከሰተ ነገር እንደገና ሲከሰት ይደክማል ስልችት ይላል። አንዳንድ ቀን መውጪያ ቀዳዳ ይጠፋል። እንደው መውጫ የሚሆን አንተ ያየኸው መንገድ ይኖር ይሆን፤ የ ታዘብከው ? ....ጥሩ የምታስብበት የሚመስለኝ የአብዮቱን መንገድ የምታውቀው ነው። እኛ ከአብዮቱም የባሰ የቀውስ መንገድ ላይ ስላለን፣ በወል እንደዚህ አይነት ዘመንን እንዴት ነው መሸከም ያለብን? እንዴት ነው ጎበዝ መሆን ያለብን? እንደ ግለሰብም እንደ ማህበረሰብም?
አዳም፦ እኔ የማደርገው ዝም ብዬ ማየት ነው። ምክንያቱም አንዳንድ ክስተቶችም ሆኑ ሁነቶች ጥልቅ ሀሳብን ይጠይቃሉ፤ ማሰብ አለብህ፣ መመርመር አለብህ። ሁሉም መድኃኒት ፈላጊ መድኃኒት ቀማሚ አይለም፡፡ እኔ በቃ ተረክ እፅፍልሃለሁ፤ በዛ ተረክ ውስጥ የሆነ ነገር ለመንገር እሞክራለሁ። በተረኮቼ ውስጥ አልወግንም። በዛ ውስጥ የማስታውሰውን ነው የምፅፈው። ምናልባት እኔን ራሴንም የሚያስከፉኝ ሊሆን ይችላል። ግን እዛ ውስጥ ፍርድ ሳልወስድ ማስቀመጥና ትንቢታዊ (predictive) እንዲሆኑ የማድረግ ነው የእኔ ስራ። የእኔ ድርጊት የመተረክ ፣ አስተማስሎ (Representation) የመስራት እና መጪውን የማሳየት ነው። ከዚህ በተረፈ ነብይ (የብሉይ ዘመን ነብይ) ነው የሚመልሰው ... ባቅላቫ መብላትም ሕይወት ነው ሃሃሃ ...
ሀብቱ:- ጉዞውን እንወደዋለን። ትግሉ፣ መማሩ፣ መውደቁ፣ ተጋድሎ ቆንጆ ነው። ተጋድሎ ነው አይደል ሰውን ሰው ያደረገው? ተመስገን ማለቱ፣ ሌሊት እንቅልፍ ማጣቱ፣ ጧ! ብሎ መተኛቱ አይደል?
አዳም:- እርግጠኛ አይደለሁም .... የግድ መስቃየት አለብህ? ይሄ ድርጊት አዲስ ፍልስፍና የመፍጠርም ሊሆን ይችላል። ከችግሩ ለመውጣት የሚያፈናጥርህ እሳቤ ወይም የአስተሳሰብ መንገድ (Concept system) ፈጥረህ አዲስ አለም የማበጀትም ሊሆን ይችላል። ይሄን ሁሉ ግን አንድ ደራሲ ላይመልሰው ይችላል። ከእኔ መጠየቅ ያለብህ ሀቀኛ (authentic) መሆኔን ነው። የምትፈጥራቸው ገጸ ባህርያት ሀቀኛ መሆን አለባቸው… ከአንድ ደራሲ ሁሉንም ነገር መጠበቅ ሊያስቸግር ይችላል ።
ገዛኸኝ፦ ድርሰቶችህን ሀቀኛ የሚያደርጋቸው ምንድን ነው? ድርሰቶችህን ስናነብ ህይወት አላቸው። ማለት ቴክስት ብቻ አይደሉም፤ በተለይ የገጸ ባህርያት ግንኙነትን ብንመለከት ጥርት ያለ የህይወት መሰናስል አለው፤ ሕይወትን ነው የምትፅፈው። በዚህ ልክ እንዴት ሊሳካ ቻለ?
አዳም፦ በስሜት ሕዋሳቶቼ ነው የምረዳቸው፤ በቃ ያ’ ነው ለእኔ መለኪያው። ርቀት ከተሰማህ ግን ውስጥህ አልደረሰም፤ በስሜትህ አትለካውም። ግጥም ሳነብ በሃሳቡ ሳይሆን በስሜት ሕዋሳቶቼ ነው የምለካው (I just Feel it)፤ በቃ ውስጤን ሊነካኝ ይገባል። ውስጥህ ሲነካ ፀጉርህ ይቆማል፣ የሆነ አይነት መመስጥን ይፈጥርልሃል። የሆነ ጥልቀት ያለው ህመምም ይሁን ደስታ ይጋባብሃል፣ እንደዛ ከሆነ ልክ ነው። በአመክንዬ ላላስረዳህ እችላለሁ። ሃያሲ ሌላ ነገር ነው፤ የሚያይበት መንገድ ይለያል። መዓት መፅሐፍ አለ የሚነበብ ግን አይነካህም፤ ሁሉም አይዳብሱህም።
ገዛኸኝ፦ ይሄንን የተረዳሁት እንዴት ነው? ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድን በዘመኔ ቢያንስ ሦስቴ አንብቤዋለሁ። በሦስቱም ጊዜያት የተለያየ ነገር ነው የተረዳሁት፤ ይሄ ደግሞ ህይወት ካልሆነ እንደ እድሜ የሚነሳ ወይም የምንገነዘበው ነገር አይኖረውም።
አዳም፦ ሀቀኛ (Authentic) ማለቴ .... እውነታን ወክለሃል ብሎ የሚነግርህ ካለ ያ’ ህይወት ነው። ለምሳሌ እዚህ ውስጥ የሰባት መንገዶች ወግ (ጠረጴዛው ላይ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ መፅሐፍ ነበር) እውነታውን አይተኻል? አላየህም! 1967 ዓ.ም ነበርክ? አልነበርክም ! ግን የሆነ ነገር ከመፅሃፍ ያገኘህ ይመስልሃል ወይም አግኝተኻል። ትርጉም (meaning) እርስ በራሱ የተያያዘ ነገር አለው፤ በስሜት ትደርስበታለህ። ለዚህ ነው የስሜት ሕዋስህን መረዳት አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት ... ይሄ ሃያሲ የሚሰጥህ ትርጉም አይደለም። ሃያሲ ከሰጠህም የሚሰጥህ አለማቀፋዊ ትርጉም ነው። ንባብ ላይ የሚያጋጥምህ ነርቭህ ውስጥ የሚቀመጥ ስሜት ወይም ተመስጦ (affection) ነው።
ተሻለ፦ ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ በጣም ከባድ ድርሰት ነው። በተለይ የሰባት መንገዶች ወግ በጣም ከባድ ስራ ነው። እኔ ሳነበው እውነት ለመናገር፣ ልናገረው የማልችለው ዓይነት ህመም ነበረው፤ የተወሰነ ቀን ተደብሬያለሁ፣ አዝኛለሁ። ስሜቴን ክፉኛ በጥብጦት ነበር። አሁንም ሳነበው ያው ህመም ተመልሶ ይቀሰቀሳል። እኔ የአብዮቱን ዘመን በግለ ታሪክ፣ በአካዳሚክ ስራዎች፣ በፍልስፍና ስራዎች፣ በስዕል ኤግዚቢሽኖች፣ በአብዮቱ ዘመን በነበሩ ጋዜጦችና የፓርቲ ልሳኖች ሳይቀር ለማንበብ ያቅሜን ሞክሬያለሁ። ያንተን ድርሰቶች ያህል የሚያነቃንቀኝ ግን አላገኘሁም። የአንተ ስራዎችን ነው መለኪያ የማደርጋቸው። ለዚህም ደራሲው ያንን ሁነት ወይም ክስተት ሲፅፍ ተራ የመፃፍ ድርጊት ብቻ አይደለም። ህይወት ሆነው የተገለጡበትን መንገድ እና አቅም ጭምር ነው እኔ የተገነዘብኩት። ምክንያቱም አንድ ተረክ (Story) አለ ተረካ (Narrative) የማይቆም ከሆነ እዛ ተረካ (Narrative) ውስጥ ርዕዮተ ዓለም (Ideology)፣ መዋቅራዊ ስነ ዕውቀት (structural epistemology)፣ ባህላዊ ልምምዶች እና ጉዳዮች (Cultural Practices and materials) ሳይወዱ በግድ ይገባሉ። በተጨማሪም የደራሲው መሻት (intention of the author )ይኖራል። እኔ ደራሲው ሞቷል (The Death of the Author) በሚባለው ሀሳብ አልስማማም። ይህ ከሆነ ደግሞ መጪውን የማለም ብሎም ነገን የመስራት ምኞቱ አብሮ ይቀሰቀሳል ወይም ይጠ’ራል (Imagined future )።
አዳም፦ መኖር አለበት ፤ እንዳለ ሁነቱን ብቻ ካስቀመጠ የአስተማስሎ (Representation) ስራ ብቻ ይሆናል። ከዛ በመውጣት እመርታ (Emergent) የሆነ ነገር ያስፈልጋል። ምናባዊ ነገር ስታስገባ የዛ ተረክ የመባያ ጉዳዮች (motives value) ይጨምራል፤ ውጥረቱ (Intensity)ይጨምራል ። ምክንያቱም መነሻው ሀቀኝነት (authenticity )ስለሆነ ነው፤ እናም ትቀበለዋለህ ። እመርታ (Emergent ) ገጸ ባህርይ ሲሆን ትንቢት ይኖረዋል ግን መነሻው ሀቀኝነት (Authenticity) መሆን አለበት። ለአንዳንድ ሰዎች እርካታ የማይሰጥበት ምክንያት ምንድን ነው? .... የሆነ የሚያሸንፍ ነገር ይፈልጋሉ። ውስጣቸው መከፋፈል ይኖርና “የእኔና የእሱ“ የሆነ አይነት ክፍፍል ይፈጥራሉ …. በዛም ስሜታቸውን ይጎዱታል (They Betray their feelings)። ማንኛውም የሰነ ጽሁፍ ወይም የስነ ጥበብ ስራ የሆነ ዐይነት የዋህነት ይጠይቃል። መነሻ ቅንነትን ይጠይቃል፤ እንደዛ ካልተነሳ ይሞታል። እንደዛ ደግሞ ለመሆን ራስህን መተው አለብህ፤ ራስህን እንደ ገዳማዊ መርሳት አለብህ፤ ከራስ መፅዳት ግድ ነው። ትዕቢትህን (Ego) ቢያንስ ስትፅፍ መተው አለብህ ። አለበለዚያ ነገሩን አታገኘውም (you never get the point).... አሪፍ ብትፅፍም አይመጣም። ሌላው ራስ ወዳድ ሊሆን ይችላል ...ተጨማሪ ባቅላቫ እፈልጋለሁ ሊል ይችላል ሃሃሃ ....
ሀብቱ፦ ለምንድን ነው ትልቅ ትህትና የሚያስፈልገው? ራስን መካድ ለምን ያስፈልጋል? በተቃራኒው ተገልብጦ ኃይለኛ፣ ጉልበተኛ ፣ እኔ ያልኩት ነው የሚሆነው ቢል ለምን ከደራሲነቱ ጋር አይገጥምለትም?
አዳም፦ አንደማስበው ከምንኖርበት ዓለም ጋር የተገናኘ ነው (I think it is connected to the universe)፤ በሃሳብ ደረጃ ከተለመደው ተሞክሮ (Experience) መነጠል አለብህ።
ተሻለ፦ ይሄን የእሳቤ ለውጥ (paradigm shift) እንዴት አገኘኸው? ሁሉም ሐበሻ ትዕቢቱን አፍንጫው ስር፣ ንግስናውን በልቡ ይዞ የሚኖር ነው ፤ የዕድል ቀኑን ጠባቂ ነው። እኔም ብሆን ሌላው እድሉን ብናገኝ ገራፊዎች ነን። ታዲያ አንተ እንዴት በተለየ መንገድ ሄድክ? ከሃገር መውጣትህ ነው? ወይስ ሌላ ተሞክሮ አለህ?
አዳም፦ ዓለም ሰፊ ነው። ሕጽናዊነት ከዚህ ጋር የሚገናኝም ነው። ብዙ ነገር አናውቅም፣ ብዙ ነገር አላውቅም ። ላስቅህና ምን ያህል አላዋቂ እንደሆንኩኝ እንኳን አላውቅም (Even I don’t know how much I’m ignorant ሃሃሃ....
ስለዚህ እንዴት ነው የምታውቀው? የነገሮችን መያያዝ ትረዳለህ ... ሁለት ነገሮች ተወደደም ተጠላም በግንኙነት ህግ ውስጥ ነው የሚኖሩት (this thing and that thing they have a certain connection) እንደዛ ነው ህልውናቸው ሚያስቀጥሉት .... ደንቆሮዎች ናቸው ግን በግንኙነት እምቃት (Potential) ነው ህልውናቸው ሚቀጥለው ... ይሄን በአግባቡ መገንዘብ ያስፈልጋል።
ለምሳሌ ይሄንን መፅሐፍ ስንት ቀን ይዘኸው ዞርክ? ብልህ አታውቅም ... ስንት ገፅ እንዳለው ብጠይቅህ ላታውቅ ትችላለህ ... ይሄንን አንብበኸዋል? (ብለርቡን ማለቱ ነው)...ስንት ቃላት አሉት? ብልህ አታውቅም ... ህይወትም እንደዛ ነው .... እናም ይሄንን መረዳት ያስፈልጋል።
መፃፍ ስጀምር ነገሮችን አላውቅም ከሚል ነው የምነሳው ... ስለዚህ የመፃፍ ድርጊት ራሱ የመማር ድርጊት ነው ። መረዳት እና አንዳንዴም የአንባቢዎችን ነገር መከተል ....እናም በአራዳ ቋንቋ አለማካበድ ነው ሃሃሃ ...
ገዛኸኝ፦ ብዙ ጊዜ በድርሰትህ ውስጥ ከእውነታው ዓለም ጋር የሚገጥሙ ታሪኮችን እናገኛለን። የአስተማስሎና የልዋጭ (Metapho) ሀሳቦች እንዴት ነው ከታሪክ ድርሳናት እና ከሀቀኝነት (authenticity) ጋር የሚዋሃዱት (sync የሚሆኑት?
አዳም፦ በእውቀት ውስጥ ሁለት ዓይነት ክፍፍል አለ፤ ስነ ጥበብና ሳይንስ ... እነዚህ ሁለቱ የተያያዙ ናቸው ለማለት ነው። በግርጌ ማስታወሻ ሃያሲ ጠቅላላ ይቀርባል ... ሃያሲው ሳይንሳዊ ነገሮችን ይበረብራል፣ መረጃ ይሰበስባል፣ ይተነትናል ወዘተ። ዋናው ክፍል ደግሞ ሕይወት ነው፤ ስለዚህ ሁለቱንም በአንድ ላይ የማቅረብ እንዲሁም የማገናኘትም ነው፤ የስነ ጥበብ እና የሳይንስና መጎዳኘት ነው (The integration of art and science)።
ገዛኸኝ፦ ታክሲ ውስጥ ስንገባ ሹፌሩ መንጃ ፈቃድ ይኑረው አይኑረው አናውቅም ። ይናደድ አይናደድ አናውቅም በቃ ዝም ብለን እንገባለን...
አዳም፦ መፃፍም ልክ እንደዛ ነው። በሂደት ነው የሚዳብረው፤ የተሳሳተውን ከዛ በኋላ ታቀናለህ፣ ታርማለህ።
ተሻለ፦ የአንተ ስራዎች ግን ይሁነኝ ተብለው የሚሰሩ ናቸው። እንደውም አብዛኛዎቹ ስራዎችህ ፕሮጀክቶችም ናቸው ብል እውነት ነው፤ ደግሞም ልክም ነኝ። በፅንስ ሀሳብ ደረጃ ብዙ ማለት ቢቻልም ....እንጀራ (ሞዴል ብቻ አይደለም)፣ ሕጽናዊነት (ፍልስፍና ብቻ አይደለም)፣ ታሪክም ሆነ አብዮት (የአንድ ወቅት ክስተት ወይም ሁነት አድርጐ የመተረክ ጉዳይ ብቻ አይደለም)፣ ማህበረሰብ (የአስተማስሎ ጉዳይ ብቻ አይደለም)፣ ፖለቲካ (ትችት ብቻ አይደለም) ወዘተ ... በመሆኑም ደራሲው በደንብ አቅዶ እንደሚሰራ ግልፅ ነው....
አዳም ፦ ሕጽናዊነት ግራጫ ቃጭሎች ላይ ያለው መግቢያ ንድፈ ሃሳባዊ (theoretical) ይመስላል ግን የጠራ አይደለም (Vague) ነው ...
(ይቀጥላል)

Read 613 times