Saturday, 21 December 2024 21:12

“ትልቅ አርቲስ መሆን እፈልጋለሁ”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ባለፈው ሳምንት ዕትም የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፣ ከወጣቱ
ድምፃዊ ልዑል ሲሳይ ጋር ያደረገችው ቃለ ምልልስ የመጀመሪያ ክፍል ለንባብ
በቅቶ ነበር፡፡ ቀሪውና የመጨረሻው ክፍል እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

” አንብቡት፡፡


ከዚህ በኋላ ነው “ልዑል” የተሰኘው ሙሉ አልበምህ የተለቀቀው?
አዎ በትክክል!
ብዙ ጊዜ አልበም ሲሰራ የአልበሙ መጠሪያ የሚሆነው ከትራኮቹ ላቅ ያለው ስራ ነው፡ አንተ አልበምህን በስምህ የሰየምክበት የተለየ ምክንያት አለህ?
አልበሙን በስሜ የሰየምኩበት ሁለት ምክንያቶች አሉኝ። አንደኛው የብራንዲንግ ጉዳይ ነው። እኔ ገና ጀማሪና አዲስ እንደመሆኔ ስሜን እንዴት አድርጌ በቀላሉ ከሰዎች አዕምሮ ውስጥ ማስረጽ እችላለሁ ከሚል መነሻ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ የአልበሙ ግጥምና ዜማዎች የእኔ አይደሉም። ነገር ግን አንዱን አንስቼ የአልበሙ መጠሪያ እንዳላደርግ ሁሉም ግጥምና ዜማዎች አሪፍ ስለሆኑ ማበላለጥ አልቻልኩም። ስለዚህ እነዚህ በአልበሙ ውስጥ የተካተቱት ስራዎች፣ የኔ ልዑል ጣዕሞችና ልዑል የሚወዳቸው ሥራዎች ናቸው ለማለት አልበሙን “ልዑል” አልነው። ጠቅለል ሲል አንድ የብራንዲንግ ጉዳይ፣ ሁለትም ስራዎቼ የራሴ የምወዳቸው ጣዕሞች ስላሉት ነው ስያሜው ልዑል የተሰኘው። 14ቱም ትራኮች አምኜባቸው ወድጃቸው፣ የሰራኋቸው የልዑል ጣዕሞች ናቸው ለማለት ነው።
“ልዑል” አልበም በአጠቃላይ ምን መልክ አለው? የህዝቡ ምላሽ ምን ይመስላል? እኔ በብዛት ከአልበምህ ሲደመጡ የምሰማቸው “የእኔ ዓመል” እና “መልኬ በቃኝ” የተሰኙትን ነው…..
አልበሙ ከወጣ ባለፈው ህዳር 26 አንድ አመት ሞላው። ተሰርቶ ለመጠናቀቅ ስድስት ዓመታትን ወስዷል። የህዝቡ ምላሽ እጅግ የሚገርምና ከጠበቅኩት በላይ ነው። እንደ ጀማሪነቴም በራሴ ዩቲዩብ ቻናል ነው የለቀቅኩት።
አዲስ አልበም ሆኖ አንተም አዲስ ድምፃዊ ሆነህ---ብዙ የተደከመበትን ስራ በአዲስና በራስህ ዩቲዩብ መልቀቅህ ስጋት አላሳደረብህም?
እርግጥ ይህ ጉዳይ የብዙዎችም ጥያቄና ስጋት ነበር። ነገር ግን ፈጣሪ ይመስገን ከጠበቅኩት በላይ ውጤታማ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት አርቲስቶች በራሳቸው ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጉ የተለያዩ ፕላትፎርሞች ተፈጥረዋል። እድሜ ለቴክኖሎጂ። የአንድ አርቲስት ንብረቶቹ ዘፈኖቹ ናቸው። ከቅጂ መብትም አንፃር፣ ከተጠቃሚነቱም አንፃር አርቲስቶች ስራዎቻቸውን በራሳቸው ዩቲዩብ መልቀቅ መቻላቸው ትልቅ እድል ነው። እነዚህ ስራዎች ለልጅ ልጅም የምናወርሳቸው፣ ተጠብቀው የሚቆዩትም በራሳችን ብንለቃቸው ነው በሚል ድፍረት ነው፤ ልዑል ዩቲዩብ ቻናል ላይ የጫንኳቸው፤ ውጤቱም አሪፍ ነው። እግዚአብሔር ይመስገን። ከገቢ አንፃር ካየነው ቀስ በቀስ ነው የሚመጣው። ነገር ግን እኔ እንደ ትልቅ ስኬት ያየሁት፣ በአዲስ ዩቲዩብ ቻናል ለቅቄውም ከጠበቅኩት በላይ መታየቱና መደመጡ ነው። እኔ አርብ ቀን ጭኜው ቅዳሜና እሁድ በዩቲዩቡ ብዙ ሰው አይቶታል፡፡ በቲክቶክና በተለያዩ ፕላትፎርሞች ዘፈኖቼን በደንብ አገኘኋቸው። እኔ ሰርፕራይዝ የሆንኩበት ነው። አሁን በዩቲዩብም ገቢ እየመጣ ለስራው ያወጣሁትን እየመለሰ ነው። በጣም የሚገርምሽ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ 26 እና 27 አልበሞች ወጥተዋል። ከግማሽ በላይ ያህሉ በራሳቸው ዩቲዩብ ነው የጫኑት፤ አዳዲስ ቲዩብ እየከፈቱ። ይህ ጥሩ ጅማሬ ነው። ከቅጂ መብትም አንፃር የቴክኖሎጂውን መራቀቅ ተከትሎ፣ ነገሮችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል። ስለዚህ ከዚህ ለመዳን በራስ ዩቲዩብ መጫን ትልቅ አጋጣሚ ነው። እኔ ደግሞ የቴክሎጂውንና የሶሻል ሚዲያውን ጉዳይ ወንድሜ መላኩ ሲሳይ ያግዘኛል እናም እድለኛ ነኝ። በሌላ በኩል በዩቲዩብ ጭኛለሁ ብዬ ዝም አላልኩም፤ ያልተቋረጠ የሬዲዮ ማስታወቂያም ሰርቼ ነበር፡፡ የማስታወቂያ ጉዳይ ሊዘነጋ የማይገባው ጉዳይ ነው። ምንም ስራ ጥሩ ቢሆን ማስተዋወቅ ግን ወሳኝ ነው። እኔ አልበሜን ለማስተዋወቅ ያልገባሁበት ቀዳዳ የለም። አንድም ስኬታማ ያደረገውና ዩቲዩብ ቻናሌንም እንዲታይ ያደረገው የፕሮሞሽኑም ጉዳይ ነው። ለምሳሌ “የኔ አመል” የተሰኘው ቪዲዮ ያለው ስራዬ ከ11 ሚሊዮን በላይ ተመልካች አግኝቷል። ሌሎችም በሚሊዮን የሚቆጠር፣ 900 ሺህ፣ 800 ሺህ፣ 600 ሺህ እይታ ያላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተደመጡ እያደጉ ነው ያሉት።
ይህንን ቃለ ምልልስ የምናደርገው አልበምህ በወጣ በአንድ አመቱ ነው። ሰሞኑን እጅህ ከምን?
ባለፈው አመት በ2016 ዓ.ም በአልበም የመጀመሪያው በኮንሰርትም የመጀመሪያው ነበር - “ልዑል” አልበም። የእኔ አልበም ከተለቀቀ በኋላ ደከም ብሎ የነበረው የሙዚቃው ዘርፍ መነቃቃት ሲጀምር ነው ሌሎችም በድፍረት መልቀቅ የጀመሩት። እኔም አልበሜን እንዳወጣሁ በሦስት ወይም በአራት ወሩ “ልዑል” የተሰኘ ኮንሰርት በሚሊኒየም አዳራሽ በስኬት መስራት ችያለሁ። ቅድም እንዳልሽው እኔ እድለኛ ነኝ። ሰኔ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ሰው በጠበቅነው ልክ ግጥም ብሎ ጥሩ ኮንሰርት መስራታችንም አልበሙን የበለጠ ተወዳጅና ተደማጭ እንዲሆን አነቃቅቶታል። የኮንሰርቱ ቪዲዮም ላልታደሙት እንዲደርስና እንዲታይ በዩቲዩብ ቻናሌ ለቅቄዋለሁ።
እጅህ ከምን ላልሽኝ …. በቅርቡ ከእስራኤል ሀገር የሚጀምር የሙዚቃ ሾው ይኖረኛል። ቀኑም በፈረንጆች አዲስ አመት ዋዜማ ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥ ቀኑን ቁርጥ አላደረጉም፤ ግን በነገርኩሽ ቀናት አካባቢ ይሆናል። ከእስራኤል በፊት እዚሁ አዲስ አበባ አንድ ሾው ይኖረኛል። ወይ ከፍ ብሎ በኮንሰርት ደረጃ ካልሆነም ሚኒ ኮንሰርት ሆኖ በሆቴል ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ እሱን ጊዜው ሲደርስ የምናየው ይሆናል። በአውሮፓም ደረጃ በንግግር ላይ ያሉ የሾው ሂደቶች አሉ። ስምምነቶቹና ንግግሮቹ እያለቁ ሲሄዱ በጊዜው ይፋ እያደረግናቸው እንሄዳለን ማለት ነው። በቅርቡ የሚወጣ አንድ ነጠላ ዜማም በማጠናቀቅ ላይ ነኝ። ርዕሱ “አልቻልኩም” ይሰኛል።
ከሙዚቃ ጉዞዎችህ ምን ትጠብቃለህ?
የውጪ ሾውን በተመለከተ ለእኔ አዲስና ሞክሬው የማላውቀው ነው። ጥሩ የሆነ ታዳሚ ይመጣል ብዬ ነው የምጠብቀው። እኔ በበኩሌ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዘጋጀሁ ነው። ዝግጅቴ ከራሴ ስራዎች በተጨማሪ የሌሎች የምወዳቸውን ድምፃውያን ስራዎች ያካተተ ነው።
ለምሳሌ የማን የማን ዘፈኖች ላይ እየተዘጋጀህ ነው… ከራስህ ስራዎች በተጨማሪ?
የቴዎድሮስ ታደሰ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ የንዋይ ደበበን፣ የጋሽ ማህሙድ አህመድና የጋሽ ጥላሁን ገሰሰ፡፡ እነዚህ አምስት አርቲስቶች ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጌ እየተዘጋጀሁ ነው።
የእነዚህን አንጋፋ አርስቶች ሥራ ክለብ ውስጥም ትጫወታቸው ነበር?
አዎ በደንብ።
አሁን ክለብ መጫወት አቆምክ?
አዎ ካቆምኩ ቆየሁ። አልበሙ ከመውጣቱ አራት ወይም አምስት ወር በፊት ነው ቀድሜ ያቆምኩት።
ክለብ ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ሰራህ?
ወደ ስድስት ዓመት ሰርቻለሁ። ያው የምሽት ክበብ ራስን በኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ሙያ ለማሳደግ የሚረዳ መድረክ ነው። አንዳንድ አርቲስት ራሱን በኢኮኖሚ ለመደገፍ ሙሉ ትኩረቱን ክለብ ላይ ያደርጋል። አንዳንዱ ደግሞ በሳምንት አንድ ጊዜ ክብብ እየሰራ ጎን ለጎን አልበም እየሰራ ይቀጥላል። እኔም በ6 አመት ውስጥ ለአንድ ዓመት ክለብ ያልሰራሁበት፣ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ እየሰራሁ አልበሙ ላይ ትኩረት አድርጌ ነበር ቆየሁት። ለምሳሌ ለሦስት ዓመት ያህል ሸራተን አዲስ “ኦፊስ ባር” ነበር ሀሙስና ቅዳሜ የሰራሁት። በኦፊስ ባር ያለማቋረጥ ለሦስት ዓመት ሰርቻለሁ፡፡ ከእነሱ ጋር ሳቆም ደግሞ ሁለት ዓመት ከምናምኑን የተለያዩ ክለቦች በሳምንት አንድ ቀን አልፎ አልፎ ሁለት ቀንም እየሰራሁ የማገኘውን ገንዘብ እየቆጠብኩ፣ እንደ ወጣትነቴ ብዙ ነገሮች ቢያምሩኝም ከእነዚያ ነገሮች እራሴን እየገታሁ፣ ከወንድሜ ጋር በመተጋገዝ ነው፣ የአልበሙን ስራ ከዳር ያደረስኩት። የአልበሙን ወጪ የሸፈንነው እኛው ነን። ወንድሜ ከገንዘብም ባሻገር በብዙ ነገር ነው የሚደግፈኝ፡፡ ከኢቨንት ከአርቲስት ማኔጀርነት ባሻገር ጎበዝ ደራሲም ነው። “ማህረቤ” የተሰኘ በጊዜው ውጤታማ የሆነ ፊልም ደርሶ ፕሮዲውስ በማድረግ ለእይታ አብቅቷል። ቃልኪዳን ጥበቡና ኤልያስ አማን ተውነውበታል።
በተለያየ ዘርፍ ኪነጥበቡን እየተጠበባችሁበት ነዋ?
አዎ በሚገባ። በብዙ ድጋፍ ውስጥ ነው የመጣሁት፡፡ ነገር ግን አንድ ጀማሪ አርቲስት ምን ችሎታና አቅም ቢኖረው፣ በገንዘብም በሙያም ደጋፊ ከሌለው በጣም ይቸገራል። ከዚህም አልፎ የሙያ ስነምግባርና መልካም ባህሪ ከሌለው ያለውንም ነገር ያጣል። ምክንያቱም ያለውንም ነገር በአግባቡ መጠቀም አይችልም። ስለዚህ ለአንድ አርቲስት ብቻ አይደለም ለማንኛውም ሰው የሙያ ዲሲፕሊንና መልካም ባህሪ ያስፈልገዋል። ይሄ ከሌለ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል ማለት ነው። እኔን የጠቀመኝ ሜሪጆይ በምሰራበት ጊዜ ቅዳሜና እሁድ ኮርስ እንወስድ ነበር ብዬሽ አልነበር? እነዚህ ኮርሶች ለእኔ ትልቅ የጉዞ ስንቅ ሆነውኛል። አሁን ታዳጊ ወጣቶች በኪነጥበቡ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ብቅ ብቅ የሚሉ ልጆች ላይ በግሌ የማስተውላቸው ችግሮች ስላሉ ነው። ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆነው የሚጠብቋቸው የሚመስላቸው አሉ። ይህ አስተሳሰብ ልክ አይደለም። እኔ ይሄ የምነግርሽ ነገር ለነዚህ ታዳጊዎች ትምህርት የሚሆን ከሆነ፣ እኔ የመጣሁት ከደሀ ቤተሰብ ነው። ነገር ግን ክለብ በምሰራበት ጊዜ እኔም ወንድሜም ከምናገኘው ነገር በአግባቡ ነበር የምንጠቀመው። እንደነገርኩሽ እንደወጣትነታችን ብዙ ነገር ቢያምረንም፣ ጫማም ሆነ ልብስ አያጓጓንም ነበር። ከዚያ ቆጥበን ለአላማችንና ለኪነ-ጥበቡ ስራ ነበር የምናውለው። ከዚህ በተጨማሪ ዲሲፕሊን አለን። ትልልቅ አርቲስቶችን ስናገኝ ሥነ-ስርዓት ባለው መልኩ አናግረን አክብረን ነው የምንሸኘው። ሰውን የሚያቆየው ባህሪው ነው…. አይደለ?
ልክ “መልኬ በቃኝ” እንደተሰኘው ስራህ ማለት ነው?
ትክክል! የሙያ ዲስፕሊን ያለኝ መሆኑ፣ በትህትናና በስነ-ምግባር ሰዎችን መቅረቤ፣ ከግጥምና ዜማ ደራሲዎችም ሆነ አቀናባሪዎች ቀና የሆነ ምላሽ እንዳገኝ ስለረዳኝ ውጤታማ ስራ መስራት ችያለሁ። በአጠቃላይ ሰው ጥሩ ስነምግባርና የሙያ ዲስፕሊን ከሌለው ተሰጥኦ ብቻውን ዋጋ የለውም።
እኔ የምልህ ….. አልበምህ የወጣ ሰሞን ሰይፉ ፋንታሁን ከነፒጃማው እቤትህ መጥቶ በተኛህበት ሰርፕራይዝ ያደረገህ የእውነት ነው ወይስ ድራማ ነው?
በጭራሽ ድራማ አይደለም፤ የእውነት ነው፡፡ ከወንድሜ ጋር ተማክረው ያደረጉት ነው፡፡ ያ አጋጣሚ ደግሞ ብዙ ሰው ጋር ተደራሽ ሆኖ ሳላስበው ለአልበሜ ትልቅ ፕሮሞሽን ነበር የሆነኝ፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር በውጪው የመዝናኛ ዘርፍ ላይ የተለመደ ነገር ቢሆንም፣ ለእኛ አገር ትንሽ እንግዳ ነገር ነውና የሰውን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ በዚሁ አጋጣሚ ሰይፉን በጣም አመሰግናለሁ፡፡ ሰይፍሽ ከዚያ በኋላ በሬዲዮም በማስታወቂያም ብዙ ረድቶኛል፡፡ ከሰይፉ ሾው በኋላ ብዙ ነገሮች ቀና ሆነውልኛል፡፡
ልዑል በሙዚቃ ራሱን ምን ደረጃ ላይ ማግኘት ነው ህልሙ?
እኔ እንደ አንድ ድምፃዊ ትልቅ አርቲስት የመሆን ህልም ነው ያለኝ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያ እንደ እነ ጥላሁን ገሰሰ፣ አስቴር አወቀ፣ ማህሙድ አህመድ፣ ሙሉቀን መለሰና፣ ንዋይ ደበበ ያሉትን ያፈራች ሀገር ናት፡፡ ወደ ዘመናችን ስንመጣ ቴዲ አፍሮን፣ ጎሳዬ ተስፋዬን፣ እነ ጂጂን መጥቀስ እንችላለን፡፡ እነሱ ደግሞ ተተኪ ይፈልጋሉ፡፡ እኔም እነሱ ደረጃ ላይ ከመድረስ የተለየ አይደለም ህልሜ፡፡ እነሱ ደረጃ ለመድረስ ካለምሽ እንደነሱ ጥረት ድካምና የሙያ ፍቅር ብሎም የሙያ ዲሲፕሊን ያስፈልጋል፡፡ እኔም እነዚህ ሀብቶች አሉኝ ብዬ ነው የማስበው፡፡ በአጠቃላይ ትልቅ አርቲስት መሆን እፈልጋለሁ፡፡

Read 282 times