Saturday, 21 December 2024 20:35

ደረጀ በላይነህ ከወዴት አለህ?

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(2 votes)

፨ ደረጀ ለዕውነት እና ለሥነ-ጽሑፍ ራሱን የገበረ ኀያሲ ነው። በቃላት ኃብቱ፣ በምሰላ ብቃቱ፣ በአገላለፅ ስልቱ፣ በብዕር ትባቱ፣ በማይሰለች አተራረኩ በአፍቃሬ ሥነ-ጽሑፍ ልብ ውስጥ ያለ ሰው ነው። በመጽሔት እና በጋዜጦች ላይ(በተለይ በዚኹ አዲስ አድማስ) ለረዥም ዓመታት ሳይታክት ጽሑፎቹን አስነብቦናል። በተጨማሪም የግጥም፣ የአጭር እና ረዥም ልብወለድ፣ የታሪክ እና የኂስ መጽሐፍ ሰጥቶናል። በ2013 የወጣው “ኂሳዊ ዳሰሳ” ቅጽ 1 ቢለን ቀጣዩን እየናፈቅን 4 ዓመት ኾነን። ደረጀ ኂስ ሲጽፍ “ጓደኛዬ ነው፣ ይከፋዋል” እያለ በወገንተኝነት አይደለም። ኹሌም ለዕውነት ታማኝ ነው። በተቸረው የቃላት ክምችት ተችቶን ቢኾን እንኳ በጉጉት እንጨርሰዋለን። ለካ ኂስም እንደ ልብወለድ ይጻፋል? እንላለን። የዓለማየሁ “ሐሰተኛው በዕምነት ሥም” ላይ ሲጽፍ የጀመረበትን መንገድ እንደ ምሳሌ እንጥቀስ፦
‹‹ደራሲያን ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ወንበር ካልናቁ፣... መቅረዛቸው በንባብ ዘይት ጢም ካለች፣ ምናባቸው የሚለጠጥበትን አድማስ በገበያና ቁሳቁስ ካልደፈኑ... ነበልባላቸው ወደ ግግር ፍም፣ የነፍሳቸው ዳንስ በሰማይና በምድር ወሰን አልባ ኮከብ በመኾናቸው እርሻቸው የቀለዘና ባለፍሬ መኾኑ አይቀሬ ነው።›› (ኂሳዊ ዳሰሳ፣ 84).. ደረጀ እንዲህ አንድን ጽሑፍ መግቢያውን አንብበን ብቻ የርሱ መኾኑን የምንለየው። ቃላትን ሸሟሙኖ መዳር ይችልበታል። እናም ይህቺ የኂስ መጽሐፉ በቅጽ 1 ብቻ በመቅረቷ ደረጀ በላይነህ ከወዴት አለህ? ብለን እንድንጠይቅ አስገድዶናል። (የ‹መጽሐፈ ጨዋታ› ፕሮግራሙን እና አልፎ አልፎ ጣል የሚያደርጋቸውን የአዲስ አድማስ ጽሑፎቹን ሳንዘነጋ)
፨ አዲስ በሚወጡ መጽሐፎቾ ነፍሳችን ተወጥራ ስትቆይ ወደኋላ መለስ ብለው ኩልል ብለው በሚፈሱ ቃላት የተጻፉትን አንብበው ስሜትን ማርገብ ያስፈልጋል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ “የደመና ሣቆች” ነው። 9 ዓመት ወደኋላ። “የደመና ሣቆች” የደረጀ የመጀመሪያ ረዥም ልብወለዱ ነው። ታሪኩ እንደ ልጅ ጠባይ ኹሉ ከአንዱ ወደ ሌላው እየዘለለ ጉርምስና እስኪደርስ ይሯሯጥና ከምዕራፍ አሥራ ሦስት ጀምሮ እንደ ዕድሜው ብስለት ረጋ እያለ ይጨርሳል። መጽሐፉ ኹለት ክፍሎች አሉት። ክፍል አንድ እስከ ገጽ 158 ይሄድና ክፍል ኹለት ከ161 - 227 ይደርሳል። ደረጀን በኂሶቹ የተዋወቀው ሰው የሱን ድርሰቶች ለማንበብ ይጓጓል። በተለይ ረዥም ልብወለዱን - እኔ ስመኘው ቆይቻለኹ። ከጊዜያት በኋላ “የደመና ሣቆች” እጄ ገባ። አነበብኩት። ኾኖም ይህ ስሜት ተሰማኝ፤ ‹‹ደረጀ ከልብወለድ ይልቅ ኂስ ብቻ ቢጽፍ ይሻለዋል።››። (ይህን ስል አጫጭር ልብወለዶቹን እና ግጥሞቹን ሳላነብ ነው።) ለበድሉ ዋቅጅራ እና ዮሐንስ ኃብተማርያም ከልብወለድ ይልቅ ግጥም እንደሚሻል ኹሉ፣ ለእንዳለጌታ ከበደ ከግጥም ይልቅ ልብወለድ እንደሚሻለው ኹሉ፣ ለደረጀ በላይነህም ከ(ረዥም) ልብወለድ ኂሱ ይሻለዋል አስብሎኛል።(ግጥሞቹን ሳነባቸው እመለሳለኹ።) ምክንያቱን ላስረዳ፦
፨ ልብወለዱ በክፍል አንድ ‹ደጀኔ› የተባለው ገጸባሕሪ ስለ ልጅነቱ የሚተርከው ነው። ስለ ልጅነት በርካታ መጽሐፎች ተጽፈዋል። በመጀመሪያነት የሚጠቀሱትን እነ “ልጅነት” ፣ “ግራጫ ቃጭሎች”ን ጨምሮ “የብርሃን ፈለጎች” ፣ “ኬርሻዶ” ... ወዘተ ይጠቀሳሉ። “የደመና ሣቆች” ስለ ልጅነት የተጻፈው፤ አኹን ላይ ተቀምጠን ስለ በፊት ስናስብ ‹‹እንደዚህ ነበር እኮ!›› የምንለውን በዚያ ጊዜ እንደኾነ ተደርጎ ነው። በልጅነት አመዛዛኝነት፣ ምክንያታዊነት የለም ፍላጎት እና ስሜት እንጂ። ካደረግን በኋላ ነው ስሕተት መኾን አለመኾኑን የምንረዳው። የደረጀ ‹ደጀኔ› ግን ያመዛዝናል። ደራሲው የልጅነት ታሪኩን ዘመን ለማሳየት በትውስታ መልክ(ልብወለድ ሳያደርገው) ቢጽፈው አንደኝነቱ አያጠራጥርም። እንደ ልብወለድ ተደርጎ ሲቀርብ ግን ብዙ እክል ገጥሞታል። የልጅነት ታሪክን በልጅነት ትውስታ ላይ ተመስርቶ በዐዋቂነት አስተሳሰብ እና ቋንቋ፤ እንደ ዘመኑና እንደ ልጅነት ሳይኾን እንደ አኹን የዕድሜ ደረጃ የተጻፈ ነው። የቋንቋውን ልቀት እና የአተራረክ ስልቱን ስናይ በአንደኛ መደብ ከሚተረክ(በህፃን ልጅ) በሦስተኛ መደብ ተራኪ ቢተረክ የተሻለ ይመስላል። ለታሪኩ አካሄድ አመቺ የሚኾነው ግን ‹እኔ› እየተባለ ሲተረክ ቢኾንም ለህፃኑ ያሸከመው ቋንቋ፣ የተጫነበት አስተሳሰብ ለጉልበት ብዝበዛ የዳረገው ነው። የ‹ደጀኔ›ን ዕድሜ ስናይ እስከ ምዕራፍ አሥራ ሦስት ድረስ ወደ ኹለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ያልገባ ታዳጊ ነው። ታላቅ ወንድሙ(አስማማው) ለአብዮት አፈሳ እንኳ ያልበቃ “ልጅ” ኾኖ የሱ ታናሽ ‹ደጀኔ› ግን የሚናገርበት ቋንቋ፣ የሚያስበው ሃሳብ አባቶቻቸው እንኳ የማያስቡትን ነው። ‹ደጀኔ› እና ጓደኞቹ ዕድሜያቸው ትንሽ ኾኖ የሚወያዩበት ጉዳይ የዐዋቂ ነው። ‹‹መጥፎ ጊዜ ተወለድን!›› እያሉ የሚነጫነጩ ናቸው። ይህም የታሪኩን ፍሰት ያደናቅፈዋል፤ በምናብ ለመሳል(Imagine ለማድረግ) እንዳይመች ያደርገዋል። እንግዲህ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ኾነው ነው “ተዓምር” የሚያስቡት።
፨ የደራሲው የቋንቋ እና የአተራረክ ብቃት ሳንመራመር እንድናልፈው ቢያደርገንም፤ ገጸባሕሪው ‹ደጀኔ› ሲተርክ ከአቅሙ በላይ የኾኑ ቃላትን፣ ከዕድሜው በላይ የኾኑ አገላለፆችንና ትዝብቶችን ያንጸባርቃል። ‹ደጀኔ› ከዕድሜ ዕኩዮቹ ልቆ የትልቅ ሰው ስሜት ይሰማዋል። ኩልል ያለውን የታሪኩን ፍሰት የሕፃን ያልኾነ ድምፅ ያናጥበዋል። እንደ “አጥቢያ”ዋ እርጥባን የቋንቋው ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ ይከታል። እሷም የተለየ ንባብ ወይ አስተዳደግ ሳይኖራት የሰላ ቋንቋ ትጠቀማለች። ‹ደጀኔ›ም በሕፃንነቱ አባቱ ስለሞተ ኃላፊነትን ገና በልጅነቱ ስለተቀበለ ነው እንዲህ ሊያስብ የቻለው እንዳንል ታላላቆች እንዳሉት ደጋግሞ ነግሮናል። በምሳሌ እንይ፦ ልጅ ኾነን ኹላችንም የበዓል ቀን፤ ዒድም ይኹን ጥምቀት ስንሔድ ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ይህንን ስሜት በዚያ ዕድሜያችን መግለፅ አንችልም። ‹ደጀኔ› ግን ትልቅ ሰው እንኳ መግለፅ በማይችልበት አኳኋን በዚያ ዕድሜው ይገልፃል።
‹‹በዜማው ውስጥ ኾድ የሚያስብስ ነገር፣ አንዳች ልብ የሚያስደስት ስሜት፣ ወይም የኾነ ሊተረጎም የማይችል ቋንቋ ወይም ፉጨት፣ በነፍስ ሃዲድ ላይ ይንከባለላል። ነፍስ የምትለው ነገር አላት። ግን ለማንም አይሰማም። ራሷ ሰምታ፣ ራሷ ትሥቀው ወይም ታለቅሰው እንደኹ እንጂ!››(23) ተዓማኒነትን የሚያጠራጥር አንድ ትንሽ ልጅ ሊናገረው የማይችል ነው። ‹‹ትርሲት እንደምንጭ የሚፍለቀለቅ ገጽታ ነው ያላት!›› 41፣ ‹‹[በጥምቀት ቀን ጭፈራ] ሰማዩ ዋይ እስኪል ያስተጋባሉ። መሬትም አቧራዋ እንደ ነበልባል ምላስ እስኪያወጣ ይጨፈራል።›› 43፣ ‹‹ተፈሪ ኬላ ወደ አንድ መሶብ የሚዘረጉ ብዙ እጆች ... ያሉባት ትንሽ ከተማ፣ የአንድ ቤተሰብ መኖሪያ ናት። የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ፣ ብዙ ወንዝ ተሻግረው የመጡ፤ ነገር ግን ብዙ ልዩነታቸውን ጥለው ልባቸው አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መናኸሪያ ነች ብሎ ለመናገር ብዙ ምልክቶች ሊመዘዙባት የሚችል የሲዳማ ደቡባዊ ክፍል ናት።›› 60፣ ‹‹ብቻ ተፈጥሮ ራሱ አንዳች ኮርኳሪ ስሜት አላት። ስለ ሰው... ስለ አምላክ... ስለ ፍጥረት... ስለ ሕይወት በግድ እንዲታሰብ የሚያደርጉ የተፈጥሮ ነፍሳት ይደንሳሉ። በልጅ ልብማ የባሰ!›› 52፣ ‹‹ሰው ከተፈጥሮው በኋላ በኑሮው ደጋግሞ ሳይወለድ አይቀርም።›› 100 ... ወዘተ ሌላም ብዙ መጥቀስ ይቻላል።
፨ ደራሲው ‹ደጀኔ›ን ኹሉ ነገር የሚገባው፣ ቶሎ የሚረዳ አድርጎ ስሎታል። አኹን ተቀምጦ ሲያስብ ‹‹ለካ እንደዚህ ነው!›› የሚለውን ሳይታወቀው ለገጸባሕሪው ሰጥቶታል። ካደገ በኋላ ሊረዳው የሚችለውን ጉዳይ በዚያ ዕድሜው አላብሶታል። አንድ ነገር ሲፈጠር ‹ገብቶኛል፣ ተረዳኋቸው› የሚል ነው። ሳይነግሩት ወዲያው የሚረዳ እሳት የላሰ። አኹንም ምሳሌ እንጥቀስ፦ ከጓሮ እየገቡ ፍራፍሬ ይሰርቃሉ። የአንድ ጓደኛቸው ቤት ጓሮ ገብተው ሰርቀው ሲወጡ ተሰራቂው አላወቀም ነበር። ‹ደጀኔ› ስላላወቀ ያዝንለታል። እንዲህም ይላል ‹‹... ግን ምን ይደረግ?... ሕግ ነው! የቡድኑ ሕይወት ነው! በየተራ እንሰርቃለን! ... አንዳንዱ ፍራፍሬ ... ሌላው እሕቱን ይሰረቃል!... ልጅነት ነው፣ አንቀያየምም።›› 40፣ ‹‹... ወይ ልጅነት! ...ወይ ፍቅር! የዕድሜ ስሜት ስለኾነ ... ብዙ ብርቅ አይደለም።›› 48። አሥራ አምስት ዓመት በቅጡ ያልሞላው ታዳጊ እንደዚህ እያለ ይመራመራል? ደራሲው ይህ ይጠፋዋል ብዬ አላስብም፤ ትውስታውን ‘እንደ ወረደ’ ስለዘረገፈው እንጂ። ባይኾንማ ይህን ህፃን የአኹን “ደረጀ”ነቱን አያላብሰውም ነበር። ከመተቃቀፍ እና ጉንጭ ከመሣም የዘለለ የማያውቅ ይህን ቁጭ ብሎ ሊያስብ አይችልም። ‹‹ሌላው የገረመኝ የአያቴ ቤት ጎጆ መኾኑ ነው። እኛ ጋ ሲመጡ ሳያቸውና አለባበሳቸውን፣ የሚሰጡኝን ገንዘብ ሳስብ ቤታቸው ቆርቆሮ ነበር የመሰለኝ። ትንሽ ገረመኝ።›› 52 እያለ የሚደነቅ ህፃን ነገር ቶሎ የሚገባው፣ ‹አወይ ልጅነት!› የሚል መኾኑ . . . . . ጓደኛቸው (ምንዳ) የሠራውን “ጀብድ” ቁጭ ብለው ይተርክላቸዋል። ‹ደጀኔ› ግን አያምነውም። ይጠረጥራል። ከዚህ በፊት ያደረጋቸው ነገሮች(ምንዳ) ላለመታመኑ ምክንያት ቢኾኑም ይህን ያህል ወሬው ሳይጀመር መጨረሻውን መረዳት ከባድ ነው።(62)...፣ ስለ እናቱ ሐገር ‘ገጠርነት’ መልሶ ለእናቱ እየነገራት እሷ ሳትስማማ ስትቀር ‹‹የተወለደችበት ቦታ ስለኾነ ሙገሳውን እንጂ ነቀፋውን ለመቀበል ዝግጁ አልነበረችም።››(66) ይላል - ትንሹ ልጅ።
፨ ደራሲው፣ ይህ ጥያቄ እንዳይነሳበት ይመስላል፤ እንዴት እንደ ትልቅ ሰው ያስባል? የሚለው ጥያቄ እንዳይነሳ ገጽ 52 ላይ ለመመለስ ይሞክራል። ‹‹የእኔ ልብ ደግሞ ኹሉን ነገር ዕቃ አገላብጦ እንደሚያይ ገበያተኛ አገላብጣ ታያለች። እናቴ ደስ አይላትም። “ኧረ አንተ ልጅ ቀስ ብለህ ዕደግ! ... እንዴት ነው የሚያስበው? ዞር በል!” ትላለች።›› ይለንና ቀጥሎ ‹‹አንዳንዱ ትልቅ ኾኖ አያስብም፤ አንዳንዱ ትንሽ ኾኖ ያስባል።››(57) እያለ እንዴት እንደ ትልቅ ሰው ያስባል? ለሚለው ጥያቄ የትልቅ ሰው ምላሽ ይሰጣል። ‹ደጀኔ› ሌላው ቢቀር የሚጨፍሩበትን መዝሙር የሚተነትን ነው። ቡሄን እንደሌሎች በዓላት የማይወዱት ሥጋ ስለማይበላበት እንደኾነ ይነግረንና፦ ቡሄ .. ቡሄ.. በሉ
ልጆች ኹሉ፣
ቡሄ መጣ፣
ያ... መላጣ፣
ቅቤ ቀቡት፣
ፀጉር ያውጣ። ‹‹የሚባለውም በጾም ስለሚውል ሳይኾን አይቀርም።›› 55 ይላል። አንድ ትንሽ ልጅ መጨፈር መጫወቱን እንጂ ‹አሃ እቺ ግጥም የተገጠመችው ለዚህ ነው?› ብሎ እንደማይጠይቅ ልጅ ኾኖ ያለፈ ኹሉ ያውቀዋል።
፨ ታሪኩ ልብወለድ እንዳይመስል የሚያደርገው ሌላው ምክንያት ‹ደጀኔ› ስለ አንድ ነገር ሲያስብ ወዲያው ያሰበው ነገር ዕውን ይኾናል። በዚያ ዐውድ ላይ ያልነበረን ሰው ድንገት ካነሳ ያ ሰው ሊመጣ እንደኾነ እንረዳለን። ወይም ከሰው ጋ በሌላ ጉዳይ እያወራ ሌላ ነገር ካሰበ ያሰው እንደሚፈፀም እናምናለን። ለኔ ይህ ሳቢነቱን ቀንሶብኛል። ለምሳሌ ‹‹ልጆች እያፈሱ ነው። ድንገት አንተንም እንዳይወስዱህ!›› እያለች እናቱ በጭንቀት ስትመክረው እና ስትቆጣው፣ ጎረቤታቸውም መጥታ ጉዳዩን ስታጠነክር በመኻል እሱ ‹‹ትርሲት ትዝ አለቺኝ›› ይላል። ወዲያው እናቱም ‹‹ትርሲትን አገኘሃት?›› ብላ ትጠይቀዋለች። ሌላ ቦታም እንዲሁ ጓደኛው ‹‹ቅድም ከሰው ጋር አየኹህ›› ሲለው ‹‹ከማን ጋ?›› ብሎ እየጠነቀ ጠያቂው ማንነቱን ሳይናገር ‹ደጀኔ› ጥድፍ ብሎ ትርሲት እንደኾነች ግልፅ ያደርግልናል። ለዚህ ነው ታሪኩ የተጻፈው በትውስታ ዘገባ ነው ያልኩት። ደራሲው ጉዳዩን ቀድሞ ስለሚያውቀው የገጸባሕሪውን አኹናዊ አካሄዱን ሳይታወቀው ገትቶበታል። ተጨማሪ ምክንያትም ‹ደጀኔ›ን አለዕድሜው አሳድጎታል። ከላይ በቋንቋው እና በአስተሳሰቡ እንደተባለው ኹሉ ሌላ ምሳሌ ወደ ኹለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት የገባበት ጊዜ ነው። ይህ ወቅት የወጣትነት፣ የእሳት ዘመን፣ ከሌላው ጊዜ የበለጠ ነፃነት የሚገኝበት፣ ራስ ብቻ ልክ ተደርጎ የሚታመንበት ወቅት ነው፤ ሱስ በአብዛኛው የሚጀመርበት ጊዜ። ‹ደጀኔ› በዚህ ዕድሜው ላይ እያለ አብሮት በሚቅመው ጓደኛው ‹‹ገርል ፍሬንድህ ደስ ትላለች።›› ይባላል። እንዲህ ሲባል ደስስ ሊለው፣ ጓደኛውን የበለጠ ሊወደው ነበር የሚገባው። ግን ‹ደጀኔ› እንዲህ ይላል፦ ‹‹“ትምሕርትህን ተማር። ለኹሉም ትደርስበታለህ።” ቢለኝ ነበር ደስ የሚለኝ›› ይላል። ‹እንዲህ ቢመክረኝ› ተብሎ የሚታሰበው ካለፈ በኋላ እንጂ በጊዜው እንደዚህ ይባላል ማለት ዘበት ይመስለኛል።
፨ ስንቀጥል. . . ደራሲው ደረጀ ተደጋጋሚ በልጆቹ ወሬ መኻል እየገባ ይረብሻቸዋል። በድርሰት ውስጥ ገጸባሕርዮቹ እንደ ዕድሜያቸው፣ እንደ አስተዳደጋቸው፣ እንደ ሰፈራቸው የየራሳቸው ባሕሪ አላቸው። ስለዚህ ገጸባሕሪያቱ የሚያወሩትን፣ የሚሰሩትን ደራሲው ማስተላለፍ አለበት እንጂ ‹‹ውይ! ባሕሉ አይፈቅድም፣ ሃይማኖቱ አይፈቅድም›› እያለ በፍርኀትም ኾነ በተሽኮርማሚነት ማሳለፍ የለበትም። ደረጀ በተሽኮርማሚ ብዕሩ መኻል እየገባ ያቋርጣቸዋል። ገጸባሕሪያቱ መናገር እየፈለጉ ‹‹ተው አንተ!›› እያለ ይቆጣቸዋል። ተደጋጋሚ ለመታየት ተኳኩላ ወጥታ ሲያዩዋት ግን እንደምታፍር ሴት ይሽኮረመማል። ምሰሌ ልጥቀስ፦ ‹ምንዳ› የተባለው ገጸባሕሪ ከአዋሳ ስለመጡት ሴቶች ለ‹ደጀኔ› ይናገራል። ‹ደጀኔ›ም ይቀጥላል። ‹‹አሚናና አብራት የምትመጣው ፀሐይ እኛን “ባሌ” ስለሚሉን ደስ ይለናል። ትልልቅ ሴቶች ናቸው፤ ግን ዕውነት ይመስለናል። በተለይ ምንዳ ብዙ ይናገራል። ብዙ ነገር ይላል። ብልግናውን ከየት እንደሚያመጣው አናውቅም። በተለይ ዲላ ዘመዶቹ ጋ ከርሞ ሲመጣ የማያመጣው ወሬ የለም።››(51) ብሎ ‹ደጀኔ› መናገር እየፈለገ ደራሲው መጥቶ አቋርጦት ሌላ ትረካ ውስጥ ይከተዋል። ምሳሌ ልጨምር፦ ‹ሙሉ› የምትባል ሴት ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ቤቷ ሔዶ ያለውን ኹነት እየተረከ ደራሲው በመኻል መጥቶ ሌላ ሌላ ነገር እንዲያስብ ያደርገውና እሱንም እኛንም አረሳስቶን ያልፋል።
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡- @NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 276 times