አንጋፋው የሙዚቃ ባለሙያ ኤልያስ መልካ የቅንብር አሻራውን ያሳረፈበት የድምጻዊ አብርሃም በላይነህ (አብርሃም ሻላዬ) “ቀን በቀን” የተሰኘ አልበም ሊወጣ መሆኑ ተነግሯል። በአልበሙ ወጣትና አንጋፋ ባለሞያዎች እንደተጣመሩበት ተጠቅሷል።
የፊታችን ታኅሳስ 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በድምፃዊው የዩቱዩብ ቻናል ለአድማጭ በሚደርሰው በዚሁ አልበም ላይ፣ የዚህ ትውልድ ቀለም የሆኑት ኤልያስ መልካና ሚካኤል ሃይሉ (ሚኪ ጃኖ) በላቀ ደረጃ በሙዚቃ ቅንብር የተጣመሩበት ሲሆን፤ ወንደወሰን ይሁብ፣ መሰለ ጌታሁን፣ ናትናኤል ግርማቸውና አንተነህ ወራሽን የመሳሰሉ የግጥምና ዜማ ሞያተኞች በአልበሙ ላይ ተሳትፈዋል።
“ቀን በቀን” አልበምን ሰርቶ ለማጠናቀቅ 9 ዓመታትን እንደፈጀ ተነግሯል።
ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት ለሙዚቃ አድማጮች ባደረሰው “ሻላዬ” የተሰኘ ባሕላዊ ነጠላ ዜማው ከፍተኛ ተወዳጅነትና ዕውቅናን ያተረፈው አብርሃም በላይነህ (አብርሃም ሻላዬ)፤ ለዓመታት በለቀቃቸው ነጠላ ዜማዎቹ በሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ከፍ ያለ ዝናን ከማትረፉም በላይ፣ “እቴ ዓባይ” በተሰኘ ስራውም በ“All African Music Award" አሸናፊ መሆኑ ይታወሳል፡