Tuesday, 31 December 2024 20:33

ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል ተሸከም ያለው ታስሮ ይጠብቀዋል

Written by 
Rate this item
(3 votes)

ከዕለታት አንድ ቀን የገና ዕለት፤ ቤተሰብ ለእራት እየተዘጋጀ ሳለ አንድ የዘመድ ጥቁር እንግዳ ከተፍ ይላል።
“እንዴት ናችሁ?” ይላል ከደጃፍ።
“ደህና፤ እንደምን ሰነበትክ?” ይላሉ አባወራ።
“እኔ ደህና ነኝ። ዛሬ ጥቁር እንግዳ ሆንኩባችሁ”
“ኧረ ምንም አላስቸገርከንም። ዛሬ ገና እኮ ነው። መልካም ቀን መጥተሃል። ጥቂት ሰላምታ እንደተለዋወጡ፣
“እራት ተዘጋጅቷል። ና እንመገብ” ይሉትና እሺ ብሎ ይቀመጣል።
መሶቡ ቀረበ።
ዶሮው በጎድጓዳ ሳህን ከማዕድ ቤት መጣ። ዙሪያውን ከበቡ፤ ቤተሰብ። መሶቡ ተከፈተና መብላት ተጀመረ።
ቤተሰቡ ውስጥ እጅግ አስቸጋሪ፣ እጅግ ሞገደኛ ልጅ አለ። አመለኛ ነው።
ገና መብላት እንደተጀመረ እንግዳው ፊት አንድ ዕንቁላል ሲቀመጥ፣ ያ ልጅ አፈፍ አድርጎ ዋጠው።
አባት፤ “ኧ፤ አንተ ባለጌ! ከፊትህ ብላ!” አለው።
ልጁ አልተበገረም።
እንግዳው፤ “ግዴለም ተወው። ልጅ አይደለም እንዴ?” አለ።
ባለቤትየዋ ለእንግዳው አንድ የዶሮ ብልት አወጣችለት።
በጥቂት ሰከንዶች ልጅ፣ ያቺን ብልት ያለምንተፍረት ላፍ አደረገው።
አባት፤ የልጁን ክንድ ይዞ በንዴት ጠበጠበው።
እንግዳው፤ “በፍፁም አይገባም። ነውር ነው። ገበታ ላይ ልጅ አይመታም። በጊዜ መምከር ነው እንጂ መደብደብ ተገቢ አይደለም።”
የመጨረሻ ብልት ለሁሉም ወጣ። ያ ልጅ የራሱ እያለለት፣ የእንግዳውን አፈፍ አደረገ። አባት ገና ወዳፉ ሳይከተው እጁን በፍጥነት ይዞ ክፉኛ ደበደበውና ወደ እንግዳው ዞሮ፤ “ይቅርታ ወዳጄ፤ ይሄ ልጄ እጅግ ባለጌ ነው።”
እንግዳው በይሉኝታ፤ “ኧረ ይህን ያህል አላጠፋም። የእኛ ልጅ’ኮ ዶሮውን ከነድስቱ ነው ይዞት የሚሄደው!” አለ።
ይሄኔ አባወራው፤ “አይ፤ ለእሱስ ልጃችንን ደህና አርገን ቀጥተነዋል!” አሉ።
* * *
ከመሰረቱ ያልተቀጣ ከመነሻው ሥነ-ምግባር ያልያዘ ሰው፤ ውሎ አድሮ የማይመለስበት አደጋ ላይ ይወድቃል። “የተማርኩ አይደለሁም ወይ? እኔ አድነዋለሁ” ማለት በፍፃሜው አይሆንም! የኋላ ኋላ ችግር እየሆነ ዋጋ ያስከፍለናል!
አቶ ታደሰ ገብረ ኪዳን የተባሉ የሀገራችን ደራሲ በአንድ መጽሐፋቸው፤ ሚስተር ሮበርት ማክናማራ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ስለ አፍሪካውያን ችግር አውስተዋል። ኢትዮጵያውያንን አንድ ላይ ተሰባስበን ቢያገኙን ኖሮ፣ “በአገራችሁ ለምንድነው ረሀብ፣ ድንቁርና መታረዝና በሽታ የነገሱት? ለምንድነው ወደፊት መራመድ ያልቻላችሁት?” ብሎ መጠየቁ አይቀሬ ነበር። እኛ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማስቀደም የምናደርገው ጥረት የሚመክነው ከቶ ለምንድን ነው? “ከጥረት ማነስ? ጥረታችንን የሚያስተባብር በመጥፋቱ? ወይስ ራሳችን ለራሳችን ፍቱን መርዝ ስለሆንን?” ብለን መጠየቅ ይገባናል።
ይህን ጥያቄ ለመመለስ ያለጥርጣሬ፣ ልብ በልብ መገናኘት ያስፈልገናል። የእኔ ማደግ የሌላው ማነስ ነው የሚለውን አስተሳሰብ አሽቀንጥረን መጣል አለብን። ሁሉን ውንጀላ መንግሥት ላይ ማነጣጠር አይገባንም። ከግለሰብ፣ እስከ ማህበረሰባት፣ ከማህበረሰብና ተቋማት እስከ መንግሥት የየራሳችንን ሙዳ መውሰድ አለብን። ሌላው ጉዳይ አለመናበብ ነው።
አለመናበብ ትልቅ አደጋ ነው። ህግ አውጪው፣ ህግ ተርጓሚውና ህግ አስፈፃሚው አካል ሲጣጣሙ ካየን የበለጠ አደጋ አለ። አለመግባባት ጠፋ ወይም ተዛባ ማለት የአገር ህልውና ሥርዓት ተዛባ ማለት ነው። የህዝብን ጥርጣሬ የሚፈበርኩ ውሳኔዎች አለመረጋጋትን ሲፈጥሩ ወደ አደጋ ያመራሉ። በሀገራችን አደጋ እንዳይፈጠር ከማድረግ ይልቅ ከመጣ በኋላ የመዝመት ባህል አለ። ለአገሪቱ ደህንነት አስጊ አካሄድ ነው።
እንደ ናይጄሪያ የሥልጣን ሹመኞች መቃብርን ገንዘብ ማስቀመጫ ማድረግ ደረጃ መድረስ፣ የአፍሪካን የሙስና ደረጃ ጣራ እያመላከተን ባለንበት ሰዓት፣ እኛስ ወዴት እያመራን ነው? ብለን መጠየቅ ይገባናል። ሐብት የማጋበስ ልማድ አንዴ ከጀመረ ማደጉን አያቆምም። በርናንድ ሾው፤ There is no little pregnancy እንዳለው ነው። (የእርግዝና ትንሽ የለውም እንደ ማለት)።
ያለጥናት የእግረኛ መንገድ ይሠራል፤ የእግረኛ መንገድ ይፈርሳል። ተሰርቶ ሊጠናቀቅ የደረሰ ግዙፍ ህንፃ ከፕላን ውጭ ነው ተብሎ ይፈርሳል። መመሪያ ይወጣል፤ ፉርሽ ባትሉኝ ይባላል። ሁሉንም መሸከሚያ ትከሻ ያለው ህዝብ ይታገሣል። ዛሬ የቀረን ከመነሻው “የማፍረስ መጠባበቂያ ህግ መደንገግ ነው!” ማንም ተጠያቂ፣ ማንም ኃላፊ የለም ለጥፋቱ።
“ድክመቶቻችንን ለማስወገድ መተራረም አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ሒስን ስለምንጠላ ሒስ ደርዳሪን እንደ ጦር እንፈራለን። ወቀሳን በፀጋ መቀበል አናውቅበትም። ሰውን ላለማስቀየም እየተባለ ችግሮችን ሸፋፍነን ማለፍ ይቀናናል። … ማስተዳደር ማለት ረግጦ ወይም አዋርዶ መግዛት ይመስለናል። በመሆኑም የበቀል ልጆችን መፈልፈል ብሔራዊ መለያችን ሆኗል። ለችግሮቻችን መፍትሔ ሳናገኝላቸው እየቀረን፣ በችግር ላይ ችግር እየተደራረብን፣ በልማት ወደፊት መግፋት አቅቶናል። በኋላ ቀርነታችን እያንዳንዳችን ጥፋተኞች መሆናችንን አምነን መቀበል አልቻልንም። አንዳችን በሌላችን ማሳበብና እራሳችንን ነፃ ለማውጣት መቀበጣጠር እንጂ ለውድቀታችን ኃላፊነትን መውሰድ አልተማርንም” ይሉናል በዚያው መጽሐፍ። ያ መጽሐፍ ይህን ያስመዘገበን በ1999 ዓ.ም ነው። ዛሬስ? የተጠቀሱት ችግሮች በመቶ ተባዝተው ይገኛሉ። ብዙ የተዛቡ ሕግጋት ለአንድ ተረት ምቹ ሆነው እናያለን። ያንን ልብ ካላልን፣ የባሰ ችግር ውስጥ እንገባለን። ይህ ወቅታዊ ተረት፤”ብላ ያለው ተጋግሮ ይጠብቀዋል፤ ተሸከም ያለው ታሥሮ ይጠብቀዋል!” የሚለው ነው።

Read 799 times