አወዛጋቢው የ”ነፃ ፈቃድ”
ግንዛቤ በስንኝ ዳብሮ ሲፈተሽ
[ለግንዛቤ ይረዳን ዘንድ የ‹ነፃ ፈቃድ› የእንግሊዝኛ ትርጉም (‹ፍሪ ዊል›/ Freewill) ሆኖ ይወሰድ፡፡]
የ’ኔ ነፃ ፈቃድ
ምንኩሬ ቢመስልም የረጋ ከጉድጓድ
ድንገት ሲወርድበት ደራሽ ውሃ ኆኖ
የሌሎች ተጽዕኖ፤
ኃይልና ማዕረግ
ሳይፈልግ ይጓዛል በማይወደው ፈለግ፡፡
በዕውቀቱ ሥዩም በዚህች ስንኝ የሚነግረን በባለኃይሎች፣ በባለማዕረጎች ተፅእኖ ነው የእኔ ነፃነት የሚነዳው ነው የሚል፣ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ነፃነት የለኝም ነው የሚለው፡፡ “በነፃ ፈቃድ” (በሰው ልጆች ነፃነት) ይዘት ዙሪያ በተለያዩ ዘመናት የነበሩ ፈላስፋዎች ተፈላስፈውበታል፤ከቅርብ ዘመኖቹ ደግም “ነፃ ፈቃድ” ላይ የተመሠረተው “የግል ነፃነት” የለም ከሚል ድምዳሜ ላይ የደረሱ ብዙ ናቸው፡፡ የነሱንም አስተያየት የተቀበሉ አንቱ የተባሉ ሊቃውንት አሉ፣ለምሳሌ ዝነኛው የ17ኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፋ “ስጋ” እና “መንፈስ” (አካልና ነፍስ) አንድ ናቸው፣ ውሁድ ናቸው፣ ብሎ የደመደመው ባሩከ ስፒኖዛ (Baruch Spinoza) “ነፃ ፈቃድ”፣ ቅዠት ነው ብሏል፡፡ ይህንኑ የሰፒኖዛን ድምዳሜ አልበርት አኒስታይን ተቀብሎታል፡፡ በምክንያታዊነት የሚያምኑ ሁሉ አስተሳሰብ፣ ያላቸው እይታዎች፣ በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረቱ ስለሆኑ፣ ከዚህ አጉራ ያፈነገጡ አይደሉም፡፡
«ነፃነት» የሚሉት፣ ምንድን ነው ምሥጢሩ?
ትርጉሙስ ምን ይላል? የትስ ነው መንደሩ?
ብለው ተቸግረው፣ ማወቅ ለሚጥሩ፣
አውጥተው፣ አውርደው፣
ደብተራ ሊቃውንት፣ ምክር ሰነዘሩ፣
«ነፃነት» የምትሹ፣ አትልፉ በከንቱ!
«የእልም እዣት» ነውና ስረ-መሠረቱ፡፡
እንዲሁም ስለ፤”ስጋ” እና “መንፈስ” የባሩክ ስፒኖዛ ፈላስፋዊ እይታን ባጭሩ ገላጭ የሆነች ስንኝ አነሆ፤
ምስጢረ-ስፒኖዛን በውል ላልተረዳ፤
“መንፈስ” እና “ስጋ” ይመስሉታል ባዳ!
ነፃነት እና አላፊነት
የ”ነፃ ፈቃድ” (የግል ነፃነት) እና አላፊነት በጣም አወዛጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ግለሰብ ወንጀል ይፈጽማል፣ ከዚያም ግለሰቡ ለሠራው ወንጀል ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ያንን ድርጊት ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ምርጫ እያለው፣ ድርጊቱን ፈልጎ ያደረገው ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ የዘመናችን ሳይንስ የሰው ልጅ ነፃነት ሆነ የግል ፍላጎት ነፃ አተገባበር፣ ራሱ ነፃ የሚለው አስተሳሰብ እንደ ብዥታ ነው የሚወስደው፡፡ ምክንያቱም የሰው ተግባር ሲመነዘር እንደ “በራሂ”፣ “ሆርሞን”፣ ነርቭ (ኒውሮን)፣ ግንኙነት ነው የሚወሰደው፡፡ ጠቅለል ብሎ ሲታይ ግንኙነቶች ሁሉ፣ እንደ ማንኛውም ዓለም ላይ ያሉ የሕያው አካላት በሚስተናገዱበት ሥርዓት፣ ሁሉ ነው የሚስተናገዱት፡፡ እነሱም አወቃቀሮቻቸው “በበራሂዎች” የሚወሰኑ፣ ኬሚካላዊ ውሁዶች ናቸው፣ በሁሉም ህያው አካል ይኽው መንገድ ነው የሚያገለግለው፣የሰውን ልጅ ልዩ የሚያደርገው ልዩ “የበራሂ” ወይም ሌላ ሥርዓት የለውም፡፡
ወንጀሉ በሳይንስ መነፅር ይታይ ከተባለ ደግሞ፣ ሁሉም ተግባር ከግለሰብ ነፃነት ውጭ የሚፈጸም መሆኑን ነው የምንረዳው፡፡ ተግባራት የሚከናወኑት አንጎል ውስጥ በተከሰተ ኤሌክትሪካዊ፣ ኬሚካዊ፣ፊዚካዊ፣ ወዘተ ውስብስብ ግንኙነቶችና ሂደቶች ነው፡፡ ያንን ሥርዓት የገነቡት ደግሞ በህያው አካል ውስጥ ያሉ “በራሂዎች” ናቸው፣ “በራሂዎችም” በረጅም የሕያው ዝግመተ-ለውጥ ጉዞ እና ድንገታዊ ለውጦች የተመሰረቱ ሲሆኑ፤ የነሱን ተግባር፣ሂደት፣ግለሰብ የመቆጣጠር አቅም፣ችሎታ፣ብሎም ነፃነት የለውም፡፡ ሂደቱ ምንም ዓይነት የግል ነፃነት ወይም የግል ውሳኔን አያመለክትም፡፡ ይህም ማስረጃ እያለ የ”ነፃ ፈቃድ” ብሎም “በነፃነት መኖር” የሚያምኑ ግለሰቦች፣ ጉዳዩንም ከተገነዘቡ ወዲያ የግል ነፃነት መኖርን ያምናሉ፣ ድርጊቶችን የሚፈጽመው በግለሰቦች ፍላጎት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ከተባለ ደግሞ ጅብም ሆነ ውሻ የፈለገውን ነው የሚያደርግ፣ ስለሆነም ይህ ማለት “ነፃነት” ልዩ የሰው ልጅ ተግባር ማስተናገጃ ስጦታ ነው ብሎ ለመወሰድ ያዳግታል፡፡
ከግል ምርጫ ፍላጎት አንፃር የሰውን ልጅ ፍላጎት በተመለከተ አንድ ተፈጥሮያዊ ግንዛቤን አወሳለሁ፡ ይህም “ወሊድን” እና “ወላድን” ይመለከታል፡፡ በመሰረቱ ስቃይ የሚሻ ግለሰብ (በሽተኛ ካልሆነ በቀር) አለ ብሎ ለማመን ያዳግታል፡፡ እናቶች በወሊድ ጊዜ ለማሰብ የሚዘገንን ስቃይ ይደርስባቸዋል፡፡ ሁኔታው ያን ዓይነት ስቃይ የደረሰባት ወላድ፣ እንደገና ሌላ ልጅ ለመውለድ ይቅር እና ስለወሊድ በጠቅላላ ለመስማት አትፈልግም ብሎ መገመት ያስችላል፡፡ ግን ወላድ (የወሊድ ስቃይ የደረሰባት) “በምርጫ” ሌላ ልጅ ለመወለድ ፈልጋ፣ በወሊድ ሂደት እንደገና ትሰቃያለች፣ ለምን? ብሎ መጠየቅ ያሻል፡፡
በወሊድ ሂደት ለስቃይ የተዳረገች ወላድ፣ ከተገላገለች ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ ስቃይን የሚያስረሱና የደስታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ ሁለት የተለያዩ “ሆርሞኖች” አካሏ (ሰውነቷ) አመንጭቶ በደም ዝውውር አማካኝነት ያሰራጫል፡፡ በተጨማሪም እናት ለሕፃን ልጇ ያላት ፍቅር እየፀና ይሄዳል፣ ይህም ስሜት በዘመድ አዝማድ ደስታዊ ስሜት ታግዞ ወላድ ያለፈችበትን ስቃይ በሙሉ እንድትዘነጋ ያደርጓታል፡፡ ስቃይዋን ያስወገደላት አንድ ዓይነት “ሆርሞን” እንዲሁም ደስታ ያመነጨላት ሌላ ዓይነት “ሆርሞን” ነው፤ ሁለቱም ኬሚካዊ ውሁዶች ናቸው፡፡ ስለሆነም በዚህ ሂደት ወላድ እናት ነፃነት አልባ ነው(ምርጫዋ በኬሚካል ውሁዶች ስለተወሰነ)፣ ብሎም እናት የኬሚካል ውሁዶች ተገዥ ሆነች ማለት ነው፣ የግል ነፃነት / ነፃ ፈቃድ የላትም ማለት ነው፡፡
ይህ በፍልስፋና አከራካሪ የሆነ ጉዳይ፣ ቀለል ባለ መልኩ በአማርኛ ስንኞች ተስተናግዷል፡፡ ከነሱም የተለያዩ እያታዎችን ያንፀባርቃሉ ብዬ በማመን ጥቂቶችን አወሳለሁ፡፡ የመጀመሪያው ስንኝ ባለቤት (ደራሲ/Author) ደማሙ ብእረኛ መንግሥቱ ለማ ነው፡፡ የስንኙ ዋና አላማ ሃሜትን ለማኮላሸት ሲሆን፣ እሱ በእንግሊዝ አገር ተማሪ በነበረበት ዘመን የተደረሰ ነው፡፡ በዚያው ዘመን እዚያው አገር የሚማሩ ጥቂት ሴት ተማሪዎች ነበሩ፣ከነሱም በከፊል ሜሪ ታደሰ (የክቡር አቶ ማሞ ታደሰ እህት፣ በኋላም በአንድ ሚኒስትርነት ደረጃ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት ለብዙ ዘመን ያገለገለች)፣ ሚሚ ወልደ ማርያም (በጣሊያን ወረራ ዘመን በፈረንሳይ አገር የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት የብላቴን ጌታ ወልደ ማርያም ልጅ)፣ እና ሶፍያ አብረሃ (የታወቀው ጋዜጠኛ የገዳሙ አብርሃ ታላቅ እህት፣ በኋላም በአንድ የሚኒስትርነት ደረጃ ይመስለኛል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መ/ቤት ለብዙ ዘመን ያገለገለች)) ይገኙባቸዋል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት ስሞች የተወሱት ደማሙ ብእረኛ ታሞ በነበረበት ጊዜ ሊጠይቁት ሄደው እንደነበረ በግል ታሪኩ ስላወሳው ነው፣ ትረካው እንሆ፡፡
ወጣቱ ደማሙ ብእረኛ፣ ከነዚህ ልጃገረዶች አንዷን፣ ሜሪ ታደሰ ሲኒማ ቤት እየጋበዘ ያዝናናት ነበር፣ የፍቅር ስሜትም ትቀሰቅስበታለች፡፡ ከዚያም አንድ ምሽት ከሲኒማ ቤት ተመልሰው ሲሸኛት፣ መኖሪያ ክፍሏ ልትገባ ስትል፣ ጎተት አድርጎ ለመሳም ሞክሮ፣ ያተረፈው በጥፊ ጆሮው መናጋት ነበር፡፡ ይህ ድርጊት በሃሜት መልክ በየቦታው ሲነዛ፣ በተለይ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች አማካኝነት (አምባሳደሩም ሳይሰሙ አልቀሩም)፣ ሃሜቱን ለማክሰም ተማሪዎች በተሰበሰቡበት፣ አንዲሁም አምባሳደሩ ክቡር አቶ አበበ ረታ በተገኙበት፣መንግሥቱ ለማ ድርጊቱን አምኖ በምትከተለዋ ስንኝ ድርጊቱን ይፋ አደረገው፣ ሃሜቱም በዚያው ከሰመ፡፡ መንግሥቱ ለማ “በጠራ ጨረቃ” በሚል ስያሜ የከተባት ሃሜት አኮላሽ ስንኝ እነሆ፡፡
በጠራ፣ ጨረቃ፣ በኩለ፣ ሌሊት፤
አይኖቿ፣ እያበሩ፣ እንደ፣ ከዋክብት፣
“ሳማት፣ ሳማት” አሉት፣ “ዕቀፍ ዕቀፋት”፡፡
አላወላወለም፣ ወጣቱ፣ ታዘዘ፣
ወገቧን፣አንገቷን፣ በእጇና እጁ ያዘ፡፡
ከንፈሩ፣ በረአድ፣ ወደ፣ አፏ፣ ተጠጋ፣
----ምንም፣ እንኳ፣ ጡቷ፣ እንደሾህ፣ ቢዋጋ፣
ጣቷ በመሆኑ፣ የጉማሬ፣ አለንጋ፣
ጆሮው፣ ግንዱን፣ ሰማው፣ በጥፊ፣ ሲናጋ፡፡
በጠራ፣ ጨረቃ፣ በእኩለ ሌሊት፣
ዋ፣ጀማሪ፣መሆን፣ዋ፣ ተማሪነት፣
ዋ፣ ትዛዝ፣ መፈጸም፣ ዋ፣ ምክር፣ መስማት፡፡
ሳማት ሳማት ብለው ያዘዙት አይኖቿ ናቸው፣ እንደ ትዕዛዝም እንደ ምክርም ሊቆጠር ይችላል፤ ከአይኖቿ በተጨማሪ ወዳጆቹ/ጓደኞቹ አሳስተውታል፣ ከላይ የነበረችውም የጠራች ጨረቃ አስተዋጽኦ ሳታደርግ አልቀረችም፡፡ በተጨማሪም ድርጊቱን በዚህ መልክ የፈጸመው ገና ጀማሪ፣ ተማሪ በመሆኑም ነበር (የመንግሥቱ ለማን ግለ ታሪክ ይመልከቱ)፡፡ ከአላፊነት ለመሸሽ የተደረጉ ጥረቶች ሁሉም የአካባቢ ተፅዕኖዎች ናቸው፡፡ እነሱም ደራሲው በሰነዳቸው ቃላት ተብራርተዋል (ጀማሪነት፣ትዛዝ መቀበል፣ምክር መስማት)፡፡
እንዲሁም ሁለት የገጠር ጎረምሶች በጉርምስና ዘመን የጦር መሣሪያ (የጠመንጃ) ባለቤት ለመሆን በቅተው፣ በታጠቁት መሳሪያ ተማምነው፣ አንድ ግለሰብ ላይ ጥቃት ሰንዝረው ሸፈቱ (ከአካባቢው ተሰወሩ)፡፡ የተደበቁበት (የሸፈቱበት) አካባቢ (ደን/ ጫካ) ስለታወቀ፣ ምራቅ የዋጡ ዘመዶቻቸው ጥይት በማይደርስበት ርቀት ላይ ሆነው ሁኔታውን ይጠባባቁ ነበር፣ ሲርባቸው/ሲጠማቸው እጅ ይሰጣሉ ብለው፡፡ ዘመዶቻቸው የጠረጠሩትም እውን ሆነ፣ ጎረምሶቹ ከሰአታት በኋላ በርሃብም፣በውሀ ጥምም ተጠቁ፣ ብሎም እጅ ሰጡ፡፡ በዚህ ሂደት ነው ጉዳዩን ከራሳቸው “ግል ነፃነት” ለማላቀቅ የሞከሩት፤ያም ለዚህ ያደረሱን የታጠቅናቸው የጦር መሣሪያዎች ናቸው ብለው በመደምደም፡፡
“ቤልጅግ” እንጨት ልቀም (ስበር)፣”አልቢን” ውሃ ቅዳ፤
ጎትተህ፣ ጎትተህ፣ ባመጣኸው እዳ፡፡
እንጨቱ ለምግብ ማብሰያነት እንዲያገለግል፣ ውሃውም ለውሃ ጥም መቁረጫ እንዲሆን ነው፡፡
ጸጋዬ ገብረ መድኅን ደግሞ መሸ ደግሞ አምባ ልውጣ! ብሎ በሰያማት ውብ ስንኙ፣ ተግባርን እንደ ሱስ አድርጎ ነው የተመለከተው፤ “ነፃ ፈቃድ” አይታይበትም፡፡ (እሳት ወይ አበባ ከምትባለዋ የግጥም መድበል የተወሰደች)፡፡
አምባ ወጥቼ እኩል-ሌሊት፣ ስለት ገብቼ
በስሟ
ከርሞ ሰይጣን በሷ አስቶኝ፣ ልገላገል
ከሕመሟ
ጠበሏ አፋፍ በጨረቃ፣ ደጋግሜ ማሕሌት
ቆሜ
ሆዴ ቃትቶ ባር ባር ብሎ፣ እርቃኔን ከሷ
ታድሜ
ደጀ ሰላሟን በአራት እግር፤ ተንበርክኬ
ተሳልሜ
በሥጋዬ እሚነደውን፣ በጸሎት ላቤ አጣጥሜ
እፎይ ብዬ አመስግኜ፣ ውዳሴየን ደጋግሜ.....
ገና ከደጅዋ እልፍ ሳልል፣ ደሞ ይምጣ የቁም
ሕልሜ?
ሌት በጥምቀቷ የነጣው፣ነጋ፣ደፈረሰ ደሜ፡፡
ለሷ እንጅ ለኔ አልያዘልኝ፣ አዬ የስለት
አታምጣ!
በውጣ ውረድ በጠበል፣ ባሣር ወዜ ቢገረጣ
ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፣ መሸ ደግሞ
አምባ ልውጣ!
(“ከርሞ” የሚለው ቃል “በአምና” ቢተካ
የተሻለ ይመስለኛል)፡፡
ረቀቅ ባለ መንገድ ሲፈተሽ፣ ጉዳዩ ከሃይማኖት ጋር ይወሳሰባል፡፡ በቅርብ ምሥራቅ በተመሠረቱ ሃይማኖቶች (የዩሁዲያውን እምነት እንዲሁም በክርስትና እና በእስልምና) እና ሌሎች ጥቂት ሃይማኖቶች ፈጣሪ ሁሉን (የተደረገን፣ በመደረግ ላይ ያለን እንዲሁም ወደፊት የሚደረገውን) ያውቃል ብለው ያምናሉ፣ ይሰብካሉም፡፡ ስለሆነም እግዚአብሔር ከሚያውቀው ውጭ ምንም ተግባር ሊፈጸም ስለማይችል፣ ግለሰቦች ነፃ ብለው የሚወስኑት ሁሉ በቅድሚያ በፈጣሪ የሚታወቅ ስለሆነ፣ የት ላይ ነው ነፃነቱ? ወይም “ነፃ ፈቃዱ” ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡፡
ሁሉም ጉዳይ በቅድሚያ የተወሰነ ነው የሚለውን አስተሳሰብ አንፀባራቂ የሆኑ ስንኞችን፣ በእኔ እይታ የዘመኑ ቁንጮ ባለስንኝ፣ በዕውቀቱ ሥዩም፣አበርክቶልናል፡፡
አቤል እና ቃየን
በሰላም ሰፍሮ ሳል “ምድር” ባላት ዛፉ
ባ’ዳኙ ሲመታ፣ አቤል ጫጩት ወፉ
ቃየን ጠጠር ነበር፣ ለባለወንጭፉ፡፡
(የተለመደው ስያሜ “ቃየን” ሳይሆን “ቃኤል” ነው)፡፡ ስንኝቱ የምትገልጥልን አቤል በመሰረቱ ለሞት የተዘጋጀ መሆኑን ነው፡፡
ዳዊትና ጎልያድ
እግዜርና ዳዊት፣ አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ፣ ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ተገዶ፣ለሽንፈት ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል፣ ስንኳንስ በጠጠር፡፡
ጎልያድ መሸነፉ እየታወቀ ነው ከዳዊት ጋር የተፋለመው፡፡
“ነፃ ፈቃድ” (የግል ነፃነት) በረቀቀ መልኩ እንደነ ሰፒኖዛ ባሉ ፈላስፋዎች ተተችቷል፤ አይኒስታይንም የስፒኖዛን እምነት (እይታ) ተቀባይ ነው፤ ያም በዩኒቨርስ ውስጥ የሚስተናገዱት ተግባራት ሁሉ በማይገቱት የተፈጥሮ ህግጋት የተጠረነቁ/ የተጠረነፉ ናቸው ይላል፡፡ ስለሆነም ከነዚህ የዩኒቨርስ ህግጋት ውጭ የሚከሰት ነፃ ኩነት የለም ይላሉ፡፡ ከግለሰብ አንፃር ሲፈተሽ ህግጋት እንደ አካባቢ ተፅዕኖ መወሰድ ይገባቸዋል፡፡ የኛም የተለያዩ ደራስያን በስንኞቻቸው ይህንኑ እይታ በተለያዩ ደረጃዎችና ይዘቶች አንፀባርቀዋል፡፡