Tuesday, 31 December 2024 20:47

የጉጂ ትውስታዎቼ (የመጨረሻ ክፍል)

Written by  አብርሀም ገነት
Rate this item
(1 Vote)

ወደ ቡሌሆራ
ከዲላ እስከ ይርጋ ጨፌ ያለው መሬት ከላይ በረጃጅም ዛፎች፣ ከስር ደግሞ ችምችም ባሉ የቡና ተክሎች ያሸበረቀ ውብ ምድር ነው፡፡ በዲላና በይርጋ ጨፌ መሐል በሙክት የምትታወቀው ወናጎ ትገኛለች፡፡ ይርጋ ጨፌ ስንሄድ ባንወርድም፣ በኋላ ከቡሌሆራ ስንመለስ አረፍ ብለን በአለም ገበያ በስሟ የተሰየመላትን ያንን ድንቅ ቡናዋን ፉት ብለናል፡፡ ይርጋ ጨፌ ሸለቆና ጫካ ውስጥ ውስጥ የተመሰረተች ከተማ ናት፡፡ ውስጧ ራሱ በደን የተሞላ ነው፡፡ ይርጋ ጨፌ ዋናው መንገድ ላይ በጣም ጎልቶ የሚታየው ፈረንጁ ሆቴል ነው፡፡ ስሙ ከምን ጋር የተያያዘ እንደሆነ ባላውቅም ፈገግ አስብሎኛል፡፡
ከይርጋ ጨፌ ጀምሮ ያለው አካባቢ የኮቸሬ ቡና መገኛም ጭምር ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ከጫካውና ከቡናው ባልተናነሠ ውብ ሆኖ የሚታየው በብዛት የሚገኘው የእንሰት ተክል ነው፡፡ ከመንገዱ በግራና በቀኝ የተገማመሱት ጥልቅ ሸለቆዎች የደን፣ የቡናና የእንሠት ሸማቸውን ለብሰው መመልከት ማስደሰቱ! የዚህ አካባቢ የመልክአምድር አቀማመጥና የዕፅዋት ህብር ልዩ ነው፡፡ በስተቀኛችን በጣም በሩቁ፣ የስምጥ ሸለቆ ወሠን ማብቀያ የሆኑት የጋሞ ጎፋ ቅጥልጥል ተራሮች፣ ነጭ ጥጥ የመሠለ ጉማቸውን ተከናንበው ይታያሉ፡፡ ከቅርብ ውቡንና ለምለሙን የጌዲኦ መልክአምድር፣ ከሩቅ እነዚያን ታላላቅ የጋሞ ተራሮች እያዩ መጓዝ በጣም ይመስጣል!
ሸለቆውን ወጥተን ወደ ደጋማው ክፍል ስንገባ፣ መካከለኛ ከፍታ የሚስማማው የቡና ተክል እየሳሳ ከአይናችን እየተሰወረ ሄደ፡፡ በአንፃሩ ወፋፍራም የእንሰት ተክሎች እጅብ እጅብ ብለው በቅለው ይታያሉ፡፡ ከመሀል ጎማችን ለስንተኛ ጊዜ ተነፈሰ፡፡ ጎሚስታውን ረገምነው፤ የኛ ርግማን የሚደርስ ከሆነ ያ ጎሚስታ መቼም አልተረፈም ሃሃሃ!
ጮርሶን፣ ገደብን እና ገርባ ከተሞችን አልፈን፣ በግራርና በሳር በተሸፈነው ዝቅ ያለ ቦታ ላይ ስንደርስ፣ ፊት ለፊታችን ነጭ ጋቢ የለበሱ ሁለት ሰዎች ተመለከትን፡፡ እነዚህ መሆን አለባቸው አልሁ በሀሳቤ፡፡ እውነትም አባገዳውና ተከታዮቻቸው በጊዜያዊ የማረፊያ ሠፈራቸው (ካምፓቸው) ሆነው እየጠበቁን ኖሯል፡፡ አባገዳው የኡራጋ ጎሳ አባገዳ ናቸው፡፡ ከመኪናችን ወርደን ለአባገዳውና ለወጣት ወንድ ልጃቸው የከበረ ሰላምታ አቀረብንላቸው፡፡ ከዚያም ተያይዘን አባገዳው ጊዜአዊ ማረፊያቸውን ወዳሠሩበት ሠፈር ሽቅባ ወጣን፡፡ ይህ አባገዳው ጊዜያዊ ሠፈር ያደረጉበት አካባቢ ሙሪ ቀበሌ ተብሎ ይጠራል፡፡ ስፍራው ከቡሌሆራ ከተማ በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ብቻ የሚርቅ ሲሆን፣ የሚተዳደረውም በዚያው በቡሌ ሆራ ወረዳ ስር ነው፡፡ አባገዳውና ተከታዮቻቸው ጊዜያዊ ሠፊ ዳሳቸውን በጣሉበት ራስጌ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ይገኛል፡፡ ከሰፈሩ ግርጌ እስከ አስፋልቱ ያለው ሠፊ መሬት ደግሞ በቁጥቋጦና በሳር የተሸፈነ ነው፡፡ በላይ ትልቁ ዋርካ፣ በመሀል ሠፈሩ፣ በታች ደግሞ ሠፊው ቁጥቋጧማ መሬት ከተማ ለሠለቸው ሠው መንፈስ ማደሻ ተመራጭ ቦታ ነው፡፡ ለነገሩማ እንደ ገጠር ለአርምሞ የሚስማማ ምን አለ? ችግሩ ገጠር ሁሉ ነገር ተሟልቶ አይገኝም፡፡ እናም ወዲያው ደግሞ ከተማ ይናፍቃል፡፡ አባገዳው ለጊዜያዊ ማረፊያው ያሠሩት ቤት ከላይ ሲያዩት እንደነገሩ ቢመስልም ውስጡ ግን ማለፊያ ነው! ወንበሮች፣ ብዙ ቁጥር ያላቸው መኝታ ክፍሎች፣ የእህል ማከማቻዎች፣ የእሳት ምድጃዎች….. አሉት፡፡ ቤቱ በቀጫጭን እንጨትና በሳር የተሠራ ነው፡፡ ወደ ላይ ቁመቱ አጭር ቢሆንም የመሬት ለመሬት ወርዱ ግን ሽሙልሙልና ረጅም ነው፡፡ በዚያ ቅጥልጥል ቤት አባገዳው ከሚስቶቻቸው፣ ልጆቻቸውና በስራቸው ካሉ የገዳ ስርዓት ባለስልጣኖች ጋር ይኖራሉ፡፡ አንድ አባገዳ የስምንት ዓመት የስልጣን ጊዜውን እስኪጨርስ ድረስ በየቦታው እየተዘዋወረ የተለያዩ ስነስርዓቶችን ይከውናል፤ ቋሚ መቀመጫ አይኖረውም፡፡
ትልቁ ዋርካ ስር ሦስት ሠዓታት የፈጀውን ቃለ መጠይቅ ከአባገዳውና ተከታዮቻቸው ጋር አደረግን፡፡ ስንጨርስ አባገዳው እንደ ሪል እስቴት በተራ የተለጠለጠ ዳሳቸውን አስገብተው አስጎበኙን፡፡ ጉብኝቱን ስናበቃ፣ አባገዳውንና ተከታዮቻቸውን አመስግነንና ተሰናብተን ወደ ቡሌ ሆራ ከተማ አቀናን፡፡ ቡሌ ሆራ የቀድሞ መጠሪያ ስሟ ሀገረ ማርያም ነው፡፡ ሀገረ ማርያም የሚለው ስም ኦሮምኛ አይደለም ወይም በኦሮምኛ ትርጉም አይሰጥም ተብሎ ነው የከተማው ስም ወደ ቡሌሆራ የተቀየረው፡፡ ቡሌሆራ ከሞያሌ 300 ኪ.ሜ ገደማ ትርቃለች፡፡ ለሞያሌ ስለምትቀርብ ከሌሎች የጉጂ ከተሞች በተሻለ የንግድ እንቅስቃሴ ይደረግባታል፡፡ በሞያሌ መስመር በመገኘቷም የተነሳ ፀጉረ ልውጥ (የሠላም ስጋት) የሆኑ ሠዎች ወደ መሀል ሀገር ለመግባት እንደሚጠቀሙባት ይታመናል፡፡ ቡሌሆራ ያደርኩት ሰላም ግሮሰሪ በሚባል ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ከሌሊቱ 5፡00 ላይ የክፍሌ በር በሀይል ተንኳኳ፡፡ አልጋዬ ላይ ወጥቼ ተጋደምሁ እንጂ አልተኛሁም ነበር፡፡ በሩ በድጋሜ ተንኳኳ፡፡ ማንኳኳቱ እኔን ብቻ ሳይሆን በጎረቤት የተገኙትን ጭምር የሚቀሰቅስ ነበር፣ በዚያ ላይ ፋታ የለውም፡፡ አንኳኪው ክፍሌ ውስጥ የተቀመጠውን አምባሻ የሚያክል ነጠላ ጫማ ተጫምቼ በሩ ዘንድ እስክደርስ እንኳ ፋታ አልሠጠኝም፡፡ ተናደድሁ! በሩን ስከፍተው አንድ መለዮ የለበሰ ወጣት ፖሊስ መሳሪያውን አቆልቁሎ አንግቶ ቆሟል፡፡ ከደረጃው በታች ደግሞ ቁጥራቸውን በትክክል የማላስታውሰው ፖሊሶች ቆመዋል፡፡
“ምንድን ነው?” አልኩት በሩን ገርበብ አድርጌ እንደቆምኩ፤ ፖሊስ መሆኑን ሳይ ቁጣዬን አረገብኩ፡፡ አልጋ አከራዩ ቢሆን ኖሮ ልጮህበት ነበር፡፡ ፖሊሱ የያዘውን መታወቂያ አቀበለኝና፣ “ይሄ ያንተ ነው?” ሲል ጠየቀኝ፡፡ መታወቂያው ምሽት ላይ ለአልጋ አከራዩ የሠጠሁት የመስሪያ ቤት መታወቂያዬ ነው፡፡
“አዎ” ስል መለስኩለት፡፡
“ከየት ነው የመጣህ?” ሲል ጠየቀኝ፤ ፖሊሱ ፈጠን ባለ አነጋገር፡፡
“ከአዲስ አበባ”
“መቼ?”
“ዛሬ”
“ለምን?”
“ለመስክ ስራ”
“ስንት ቀን ነው ምትቆየው?”
“አንድ ቀን፤ ነገ ከዚህ እወጣለሁ”
“ታዲያ የቀበሌ መታወቂያ የለህም?”
“ነበረኝ፤ ግን እቤት ነው ጥየው የመጣሁ”
“ምንድን ነው የምትሰራው?”
“የመንግስት ሠራተኛ ነኝ፤ መታወቂያው ላይ አላየኸውም እንዴ? ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ይላል እኮ”
“እሱንስ አይቼዋለሁ” አለኝ የሚጠይቀው ሲያልቅበት ቃላቶቹን እየጎተተ፡፡
“ምንድን ነው? ችግር አለ?” አልኩት፡፡
“አይ፣ የምናጣራው ነገር ስላለ ነው፡፡ መጠየቅ አንችልም እንዴ?” አለኝ፡፡
“እሱማ መብታችሁ ነው፣ ግን እንቅልፍ ላይ በሌሊት….”
***
መታወቂያን ይዤ፤ ክፍሌን ዘግቼ ገባሁ፡፡ ፖሊሶቹ አንድ ሁለት ቤት እያንኳኩ ካጣሩ በኋላ፣ “የተኛ ሠው አንረብሽ በጊዜ ነው ማጣራት ያለብን” እየተባባሉ ወደ ግቢው በር ሄዱ፡፡ አልጋ አከራዩን፣ “መታወቂያ በጊዜ ተቀበል እንጂ” ብለው ማስጠንቀቂያ ሠጡትና ከግቢው ወጡ፡፡
እኔ በአጋጣሚ እንቅልፍ ስላልወሰደኝ ነው እንጂ፣ በዚያ ሠዓት ብዙ ሠው ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ነው፡፡ ጥልቅ እንቅልፍ ላይ ያለን ሠው በዚያ ሠዓት ቀስቅሶ፣ ከየት መጣህ? ለምን መጣህ? ማለት ደግሞ ልክ አይደለም! ለጥያቄው ሊሰጥ የሚችለው መልስም ምናልባት በህልሙ ሲያየው የነበረውን ሊሆን ይችላል ሃሃ፡፡ ሰላማዊ ሠዎችን በማይረብሽ ሁኔታ፣ ፀረ ሰላሞችን ለመጠየቅ የተሻለ ሠዓት፣ የተሻለ ዘዴ ቢፈለግ ጥሩ ነው እላለሁ በበኩሌ፡፡
እነዚያ ፖሊሶች ከመምጣታቸው በፊት፣ ምሽት ላይ ወጥቼ የእግር ጉዞ አድርጌ ነበር፡፡ ከዚያ አስቀድሞ የጣለው ዝናብ መንገዶቹን በሞላ አጨማልቋቸው ነበር፡፡ ሀገረ ማርያም አንድ የአስፋልት መንገድ ያላት ከተማ ናት፡፡ እሱም ዋናው አውራ ጎዳና ነው፡፡ የተቀሩት የውስጥ ለውስጥ መንገዶቿ በበጋ በአቧራ፣ በክረምት በጭቃ ነዋሪዎቿን የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ለነገሩ ከአውራ ጎዳናው ወደ ውስጥ የሚያስገቡ የመንገድ እጥፋቶችም ቢሆኑ ጥቂት ናቸው፡፡ በዚያ ዕለት የአየሩ ፀባይ ቀዝቃዛ ቢሆንም፣ ቡሌሆራ የአየር ንብረቷ ሞቃታማ እንደሆነ ሠምቻለሁ፡፡ ቡሌሆራ በሁለቱም ስሞቿ የተሰየሙ ሁለት ትልልቅ ሆቴሎች አሏት— ቡሌሆራ ሆቴል እና ሀገረ ማርያም ሆቴል፡፡ በመካከለኛ ደረጃ ደግሞ፡- ብርሀን ሆቴል፣ ዳዋ ሆቴል፣ ሐዊ ሆቴል፣ መልካሶዳ ሆቴል፣ ቦሀና ሆቴል፣ ታዬ ሆቴል፣ ቤቲ ሆቴል….. የሚባሉ ሆቴሎች አሏት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ፣ እኔ በተዘዋወርሁበት ሠዓት በሙዚቃ የሚደልቁትና ሞቅ ደመቅ ያሉት ታዬ ሆቴል፣ ሐዊ ሆቴል እና ዳዋ ሆቴል ናቸው፡፡ ትንንሽ ምግብ ቤቶች፣ ግሮሠሪዎችና የሙስሊም ምግብ ቤቶች ብዙ ናቸው፡፡
በነጋታው ቡሌሆራን ለቀን ፊታችንን ወደ ሰሜን አዞርን፡፡ በዚህ ጥናታዊ ጉዞ የመጨረሻችን ወደሆነውና ያልተጠበቀ የጉብኝት ጉርሻ ወዳገኘንበት አቢጀታና ሻላ አብረን እንሄዳለን፡፡ እኔ የሚቀናኝ አቢያታ ማለት ነው፡፡
አቢያታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ— ያልታሰበው ጉብኝት
የጥናት ቡድናችን መደበኛ ስራውን አጠናቋል፡፡ የቡሌሆራ ስራችንን እንደጨረስን ገብተን ያደርነው ሀዋሳ ነበር፡፡ ሠመሮም በሻሸመኔ አድርጎ ወደ ነጌሌ ለመመለስ ስለወሰነ አብሮን ሀዋሳ ገብቶ አደረ፡፡ ማፍቀር የማልፈልገው መለየትን ስለምፈራ ነው የሚል አባባል አለ አይደለ? ምንም እንኳን የኛ ፍቅር ጾታዊ ባይሆንም፣ ለብዙ ቀናት ያህል አብሮን ሲጓዝ፣ ሲበላ ሲጠጣና ሲጫወት፣ በስራ ሲያግዘን ከነበረ ሠው ጋር መለያየት ይጨንቃል፡፡ ባር ባር ይላል! ግን ሁሉም ነገር እስኪለምዱት ነው፡፡ የሠው ልጅ ሽህ ጊዜ እየተለየ ሽህ ጊዜ ከአዳዲስ ሰው ጋር መልመድ ይችላል! በርግጥ ከተለየን ሠው ጋር እንደ ነበረን ግንኙነት መጠንና ሁኔታ ይወሰናል፡፡ እናም ለቀናት አብሮን የቆየውን ሠመሮን ተሠናብተን፣ በነጋታው ጉዟችንን ከሀዋሳ ወደ አዲስ አበባ አዞርን፡፡
አቢያታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክን የጎበኘነው ሳናስበው ነው፡፡ እኛ ያቀድነው ላንጋኖ ለመግባት ነበር፡፡ ነገር ግን በመንገድ ስናልፍ የፓርኩ ግቢ ውስጥ ሠጎኖችን በማየታችን ሀሳባችን በአንዴ ተቀየረ! አቢያተ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ በሚለው ግቢ አጠገብ ስናልፍ እኔ በመጀመሪያ የታዩኝ ትልልቅ ጥቋቁር የዱር እንስሳት ናቸው፤ ጥቁር ሠጎን ያለ አይመስለኝም ነበር፡፡
“ሠጎን! ሠጎን!” አሉ ሁሉም ጓዶቼ፡፡
“ኧረ እንውረድና በደንብ እንያቸው!” አልኩኝ በጉጉት፡፡ ተስፍሽ ምንም ሳያመነታ መኪናዋን ዳር አስይዞ አቆማትና አቶ ቦልተና እና እኔ ወረድን፡፡ አስፋልቱን ተሻግረን አጥሩ ጥግ በስተውስጥ ከሚንቀዋለሉት ሠጎኖች ጋር ፎቶ ለመነሳት አጥሩን በስተውጭ ታከን ቆምን፡፡ ካሜራውን የያዝኩት እኔ ስለነበርኩ ከቆምኩበት ወደ ኋላ ሄጄ አቶ ቦልቴን ከሠጎኖች ጋር ፎቶ ለማንሳት ካሜራውን ስዘረጋ፣ ግቢው በር ላይ የቆመው ዘብ ተጣርቶ፣ እጁን እያወዛወዘ ፎቶ ማንሳት እንደማይቻል በምልክት ነገረኝ፡፡ አቶ ቦልቴ እና እኔ ወደ ግቢው በር ሄድንና ለዘቡ ሰላምታ ልንሠጠው ስንል፣ እሱ አስቀድሞ ወታደራዊ ሠላምታ አቀረበልን፡፡ ከዚያ ተጨባበጥንና ፓርኩን መጎብኘት እንደምንፈልግ ነገርነው፡፡ ዘቡ ወደ ውስጥ ሄደን እንድንጠይቅ የፓርኩን ቢሮ አመለከተን፡፡
ዘቡ የጠቆመን ቢሮ ስንገባ፣ ጎልማሳው ሠራተኛ ከሌላ እንግዳ ጋር እየተነጋገሩ ስለነበር ትንሽ ቆመን መጠበቅ ነበረብን፡፡ ሲጨርሱ ሠውየውን ሠላም አልናቸውና ጉዳያችንን ነገርናቸው፡፡ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ሠዎቹ ካልጠመሙ በስተቀር የባህልና ቱሪዝም ሠራተኞች ማንኛውንም የቱሪስት ስፍራ በነፃ እንዲጎበኙ ይፈቀድላቸዋል፡፡ እኛም ጥረታችን ያቺን የጉብኝት ገንዘብ ሳናወጣ በነፃ ለመዝናናት ነው ሃሃሃ፡፡ አቶ ቦልቴ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ለስራ ስለመምጣታችንና ፓርኩን መጎብኘት ስለመፈለጋችን ሲያስረዳ፣ የእኔ አይን አንድ ግዙፍ ነጭ ነገር ላይ አርፎ ነበር፡፡ ያ ድቡልቡል ነጭ ነገር የተቀመጠው የሀላፊው የቢሮ ጠረጴዛ ላይ ነበር፡፡ ቀረብ ብዬ በእጄ መዳሰስ ስጀምር፣ “የሠጎን እንቁላል እኮ ነው” አለኝ አቶ ቦልቴ፡፡ ትልቅነቱ አስገርሞኝ! እንቁላሉን እያገላበጥኩ እያየሁት እያለ፣ ሠውየው ወደ ሌላ ቢሮ ሄደን እንድንጠይቅ ስለነገሩን፣ እንቁላሉን አስቀምጨው ከአቶ ቦልቴ ጋር ወጣሁ፡፡
ተስፍሽና ጋሽ ሳሚ በይፈቀድልናል ተስፋ መኪናችንን የፓርኩ ግቢ ውስጥ ይዘው ገብተዋል፡፡ አቶ ቦልቴ እና እኔ የሠጎኑን እንቁላል ካገኘንበት ቢሮ ፈንጠር ብሎ ወዳለው ቢሮ ሄድን፡፡ እዚያም አንድ እድሜያቸው በአርባዎቹ መጨረሻ የሚገመት የወታደር መለዮ የለበሱ ቆፍጣና ጎልማሳ ወታደራዊ ሠላምታ ሠጡን፡፡ ከዚያም ወደ ቢሮው መሩን፡፡ ቢሮው ደጃፍ ላይ ስንደርስ ኃላፊው በአጋጣሚ ከቢሮ ብቅ ሲሉ አገኘናቸው፡፡ ሠላምታ ሠጠናቸውና ገና የመጣንበትን መስሪያ ቤት መጥራት ስንጀምር፣ “ከባህልና ቱሪዝም ነው የመጣችሁ? ትናንት ከሚኒስትሩ (ከአቶ አሚን አብዱልቃድር) ጋር አዋሽ ስብሰባ አንድ ላይ ነበርን፡፡ ግቡ!” አሉን፡፡ ደስ አለን! ሃላፊውን ቢቻል አብሮን የሚሆን አንድ አስጎብኚ እንዲመድቡልን በትህትና ጠየቅናቸው፡፡ ኃላፊውም ወታደራዊ ሠላምታ ሰጥቶ ወደ እሳቸው የመራንን ያንን ቆፍጣና ሠውዬ፣ “አብረኻቸው ሂድ” አሉት፡፡
እንዲያስጎበኙን የተመደቡልን ቆፍጣና ሠውዬ አቶ ቡሎ ዋተቻ ይባላሉ፡፡ የፓርኩ ስካውት (ጠባቂ) ናቸው፡፡ እነ ተስፍሽን መኪናዋን ይዘው ወደፊት እንዲመጡ ጠራናቸውና ከአቶ ቡሎ ጋር ሆነን የአቢያታ ሻላ ጉብኝታችንን ጀመርን፡፡
ግራርና ረጃጅም ሳሮች በሚበዙበት የፓርኩ ክፍል መሐል ለመሐል በተዘረጋው የጥርጊያ መንገድ ስንጓዝ፣ ከሰጎኖች ሌላ መጀመሪያ የተመለከትነው የሜዳ ፍየሎችን ነበር፡፡ ከመኪና ወርደን ጎን ለጎን ሲሄዱ የነበሩ ሁለት ወንድ የሜዳ ፍየሎችን ፎቶ አነሳናቸው፡፡ ወንዶቹ የሜዳ ፍየሎች ከሴቶቹ የሚለዩት ቀንድ ስላላቸው ነው፡፡ እነዚያ ሁለት የሜዳ ፍየሎች ጎን ለጎን ዘና ብለው ሲጓዙ ወግ የጀመሩ ይመስሉ ነበር፡፡ የፓርኩን አብዛኛው ክፍል ገበሬዎች ሠፍረውበታል፡፡ ወደ መኪናችን ተመልሰን ገብተን መንቀሳቀስ እንደጀመርን ቡላና ጥቁር ቀለም ያላቸው ግዙፍ ሠጎኖች በአጠገባችን ሲንጎማለሉ ተመለከትን፡፡
“ስንመለስ እናገኛቸዋለን? ወይስ አሁን ወርደን እንያቸው?” ስል ጠየቅኋቸው፤ አቶ ቡሎን፡፡
“የለም አሁን ነው እሚሻል” አሉኝ፡፡ ወረድንና እነዚያን ግዙፍ ሠጎኖች መቅረብ ጀመርን፡፡ ስንቀርባቸው ይሸሹናል፤ አሁንም ጠጋ ስንላቸው ራቅ ይሉናል፡፡ ግፋ ቢል ቢሮጡ ነው እንጂ አይበሩ! ቅድም የተከለከልነውን ፎቶ አሁን ከሠጎኖቹ ጋር እንደ ጉድ ተነሳን፡፡ ስንጨርስ ከአቶ ቡሎ ጋር መኪናችን ውስጥ ገባንና እያወራን ቁልቁል ወደ ሻላ ሀይቅ መጓዝ ጀመርን፡፡ ሙቀቱ ጠንከር ብሏል፡፡
ስለ ሠጎን አቶ ቡሎ ከነገሩንና እኔም ከማውቀው ጥቂቱን ላካፍላችሁ፡፡ ሠጎኖች በጫጩትነታቸው ተመሳሳይ ቡላ ቀለም ቢኖራቸውም፣ እያደጉ ሲሄዱ ወንዱ ጥቁር ይሆናል፣ ሴቷ ቡላ ቀለሟን እንደያዘች ትቀጥላለች፡፡ አቶ ቡሎ እንዳሉን፤ በፓርኩ ውስጥ ያሉ ሠጎኖች እስከ 140 ኪ.ግ ድረስ ይመዝናሉ፡፡ ሠጎኖች ጾታዊ ተራክቦ የሚያደርጉበት ወቅት ሲመጣ ቀለማቸው መለወጥ ይጀምራል፡፡ በዚህ ወቅት ወንዱ በሴቷ አጠገብ እየተጎማለለ ማሽኮርመም ይጀምራል፡፡ ሴቷም ብትሆን ባንዴ እሺ አትለውም፤ ታለፋዋለች፡፡ በአጠገቧ እያለፈ እያገደመ የተለያዩ ምልክቶችን ሲያሳያት፣ ከፈቀደችው እሷም መወደዷን በተለያዩ ምልክቶች አፀፋ ታደርግለታለች፡፡ በዚህ ጊዜ ሴቷ እና ወንዱ ሠጎኖች ልዩ የሆነ ጭፈራ ይጨፍራሉ፡፡ በቅርብ ርቀት እየተያዩ ይደንሳሉ፡፡ ይህ አእዋፍ በተራክቦ ወቅት የሚያሳዩት ጭፈራ በሳይንሳዊ አጠራሩ Courtship dance በመባል ይታወቃል፡፡ ይህንን ሁሉ ሂደት ካለፉ በኋላ ከተፈቃቀዱ ሴቷ እና ወንዱ አካል ለአካል ይገናኙና ተራክቦ ይፈፅማሉ (በአጋጣሚ የወንዱን ሠጎን ብልት አይተናል፤ ቀላል አይደለም!)፡፡ ይህ ሁሉ የሚሆነው እንግዲህ ሴቷ ያሽኮረመማትን ወንድ ሠጎን ከፈቀደችውና ከወደደችው ነው፡፡ ካልፈቀደችው ግን ገና በሩቅ ሲመጣባት ሮጣ ትሄዳለች፤ ትሸሸዋለች! ወንዱም በዚህ ጊዜ ከፍተኛ ሀፍረት ስለሚሰማው በስርቻው ገብቶ ይደበቃል፡፡ ለብዙ ጊዜም ወጥቶ ዕድሉን ላይሞክር ይችላል፡፡ በሌላ በኩል፣ ሁለት ወንድ ሠጎኖች አንዲት ሴት ሰጎን ካፈቀሩ በመካከላቸው ከፍተኛ ፉክክርና ግጭት ይፈጠራል፡፡ ሁለቱ ወንዶችም እርስ በርስ ይደባደባሉ፡፡ ያሸነፈው ሴቷን በእቅፉ ያስገባል ማለት ነው፡፡ ሴቷ እና ወንዱ ሰጎኖች ተፈቃቅደው አንድ ላይ ከሆኑ በኋላ እስከመጨረሻው ባልና ሚስት ይሆናሉ፡፡ ሴቷ እንቁላል ጥላ 46 ቀን ሞልቶት እስኪፈለፈል ድረስ ባልና ሚስቱ እንቁላሉን እየተፈራረቁ ይጠብቃሉ፡፡ የመፈልፈሉንም ስራ ቢሆን የሚያከናውኑት በጋራ ነው፡፡ ሰጎናዊ ህይወት እንዲህ ይቀጥላል፡፡
በአቢያታ ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ ለሠጎኖችና ለሌሎችም እንስሳት ውሐ በገንዳ ይሰጣቸዋል፡፡ በተለይ ለሠጎኖች ፍሩሽካም ይደፋላቸዋል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ ፓርክ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቲክቶክ ዝነኛ የሆነው ባለ ማርሹ ከርከሮም ይገኛል፡፡
ጠመዝማዛውን ቁልቁለት ከወረድን በኋላ በኢትዮጵያ በጥልቀቱ ቀዳሚ ከሆነው የሻላ ሀይቅ ደረስን፡፡ ሻላ ዙሪያውን የተፈጥሮ ፍል ውሀዎች ሞልተውበታል! እነዚህ ፍል ውሀዎች ሦስት ደረጃ አላቸው፡ አንደኛው ለብ ያለ ሲሆን፣ ከብቶችም ሆኑ ሌሎች እንስሳት ይጠጡታል፡፡ ሁለተኛው በጣም የፈላ ሲሆን፣ ሠዎች ከተለያዩ በሽታቸው ለመፈወስ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ሦስተኛው እጅግ በጣም የሚያቃጥል ፍል ውሃ ሲሆን፣ የአካባቢው ሰዎች ድንችና እንቁላል ለመጥበስ ይጠቀሙበታል፡፡ እኛም እነዚህን ሁሉ ፍል ውሀዎች እየተዘዋወርን በአድናቆት ጎብኝተናል፡፡
በፓርኩ ውስጥ ካየሁት ነገር ጎልቶ የሚሳልብኝ በፍል ውሀዎች የሚጠቀመውና የሚታጠበው ሠው ብዛት ነው፡፡ በነዚያ ፍል ውሀዎች ሴቶችም ወንዶችም ርቃናቸውን ብቻ የሚከልል ልብስ ጣል አድርገው በነፃነት ይታጠባሉ፡፡ ሻላ ሀይቅ ላይ ራቁታቸውን ጎን ለጎን የሚዋኙ ሴቶችና ወንዶችም ብዙ ናቸው፡፡ ሀይቁ አካባቢ ከሚታዩት ሰዎች መካከል የሚበዙት ኮረዳ ሴቶችና ወጣት ወንዶች ሲሆኑ፤ እኔ እንዳየኋቸው ሁሉም የዚያ አካባቢ የገጠር ነዋሪዎች ናቸው፡፡ ይህንን ሁሉ የህዝብ ትዕይንትና ድንቅ ተፈጥሮ ከጎበኘን በኋላ የሄድነው የሻላ ጎረቤት ወደሆነው ወደ አቢያታ ሀይቅ ነው፡፡ አቢያታ ከሻላ በስተሰሜን ይገኛል፡፡ የአቢያታ ሀይቅ በተለይ በባለቀለም የፍላሚንጎ አሞራዎች የተሞላ ነው፡፡ እነዚህ የፍላሚንጎ መንጋዎች ከክንፋቸው መሐል ሀምራዊ ቀለማቸውን ሸልቀቅ አድርገው በሀይቁ ላይ በህብረት ሲበሩ አቤት ማስደሰታቸው! ነገር ግን አቢያታ ሀይቅ አደጋ ላይ ነው! እንዳየሁት በጥቂት ዓመታት ውሀው ሸሽቶ መላጣ የቀረው መሬት በጣም ሠፊ ነው! ሀይቁ በየዓመቱ በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ እየሸሸ ከቀጠለ መድረቁ የማይቀር ነው፡፡
ውቡን የአቢያታ—ሻላ ሀይቆች ብሔራዊ ፓርክ እንወቀው፣ እንጎብኘው! እንታደገው! አቢያታ ሀይቅ አሁን እያገገመ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡ ምስጋና ይሄን የተፈጥሮ ጥበቃ ስራ ለሰራችሁ፡፡
ኢትዮጵያ ከምናስበው በላይ በተፈጥሮም በባህልም ባለፀጋ ሀገር ናት፡፡ ይሄን ጥቂት ከአካባቢው ርቆ ተጓጉዞ ያየ ይመሰክራል፡፡ እንዲህ እየተጓዝን ሀገራችንን የምናይበት ወቅት ዳግም እንዲመጣ እመኛለሁ፡፡ አዎ፣ ሀገሪቱ ብዙ ችግር አለባት፡፡ ችግሩም መፍትሔውም ያለው ግን እኛው ሰዎቿ ዘንድ ነው፡፡ ሀገራችንን የምናውቅ ምክንያታዊ ሰዎች ብንሆን መልካም ነው እያልኩ፣ የጉጂ የጉዞ ማስታወሻዬን በዚሁ እቋጫለሁ፡፡

 

Read 645 times