Tuesday, 31 December 2024 20:43

የአዲስ አፍሪካ ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል - በዓለማቀፍ ውድድር ውስጥ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራሮች፣ ሰራተኞችና ሠልጣኝ የበጎ ፈቃድ ዲፕሎማቶች በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡና አሁን በመገንባት ላይ የሚገኙ የአዲስ አፍሪካ አለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል፣ የአድዋ ድል ሙዚየምንና የኮረደር ልማት ስራዎችን ሰሞኑን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ጉብኝት ብቻም አይደለም፡፡ “በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ ግዙፍ ስራዎች” በሚል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትዓለም መለሰ ተሰጥቷቸዋል፡፡
የስልጠናው ዓላማ በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የበጎፈቃድ ዲፕሎማቶች በመዲናዋ የተሰሩና እየተሰሩ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለውጭው ዓለም በማስተዋወቅ የሃገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነው፡፡ ከእነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ ደግሞ የመጀመሪያ የሥራው ምዕራፍ በመገባደድ ላይ የሚገኘው የአዲስ አፍሪካ ዓለማቀፍ ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አበቤ ስለማዕከሉ ሲናገሩ፤ አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችና ጉባኤዎች መነሃሪያነቷን የምናረጋግጥበት፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በኩራት የምንመሰክርበት ይሆናል ነው ያሉት፡፡
የዛሬ ጽሁፋችን የአዲስ አፍሪካ ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፣ በቀጥታ ወደዚያ ከመሻገራችን በፊት ግን ዓለማቀፍ ተሞክሮዎችን በጥቂቱ ለማስቃኘት ወደድን - ለግንዛቤ ያህል፡፡ ከአሜሪካው ቦስተን ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል እንጀምር፡፡
ማዕከሉ፤ በዓመት 1.6 ሚሊዮን እንግዶችንና ተሳታፊዎችን ባስተናገደበት ዓመት፣ ለሆቴል ቢዝነሶች ብቻ የ900 ሚሊዮን ዶላር ገበያ እንዳስገኘላቸው ተመዝግቦለታል። በዓመት ከ500 በላይ ዝግጅቶችን እንደሚያስተናግድ የሚነገርለት ማዕከሉ፤ እስካሁን ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከ2.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ በ2022 የታተመው ሪፖርት ይገልጻል።
ሌላኛው ከዓመት በፊት የተመረቀው “አቢጃን የኤግዚቢሽን ማዕከል”፣ በምዕራብ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ከሰሀራ በታች ትልቁ የኤግዚቢሽን ማዕከል ነው ይባልለታል። ማዕከሉ በ130 ሚሊዮን ዶላር የተገነባ ሲሆን፤ 7 ሺ ካሬ ሜትር የኤግዚቢሽን አዳራሽ አለው። የጣራው ከፍታ 15 ሜትር ነው። ማዕከሉ 5 ሺ ተሰብሳቢዎችን የሚያስተናግድ የጉባኤ አዳራሽ እንዲሁም የአስተዳደር ሕንጻዎችን ያካትታል። መድረኩና ወንበሮቹ ተገጣጣሚና ተጣጣፊ ስለሆኑ፣ አዳራሹ ኤግዚቢሽን ለማሳየትም ያገለግላል። 800 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችም ተዘጋጅተውለታል። በውስጡ የእንግዳ ማረፊያ ወይም ሆቴል ባይኖረውም፣ የባሕር ዳርቻ መዝናኛ አጠገብ የተገነባ በመሆኑ ጠቅሞታል። ለአካባቢው ነዋሪዎች ጥሩ ገበያ ያመጣላቸዋል። ለአገሪቱ ለአይቮሪኮስት የቱሪዝም ገቢ እያስገኘላት ይገኛል።
በአገራችን አዲስ አበባ እየተገነባ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል፣ ከቱሪዝም ገቢ በተጨማሪም፣ በርካታ ጥቅሞችን ያበረክታል። በዙሪያው የቢዝነስና የስራ ዕድሎችን የሚያስፋፋ፣ የእድገትና የብልጽግና ግንኙነቶችን የሚፈጥር የኢኮኖሚ መነሃሪያ (Hub) በመሆን ያገለግላል። ባሕላዊ፣ ጥበባዊና ማኅበራዊ ፋይዳዎችን የሚያበራክትም ነው - አገልግሎቶቹ በዓይነታቸው ብዙ ናቸው።
ይህም ብቻ አይደለም። የኢንዱስትሪዎች፣ የቴክኖሎጂዎች፣ የምርቶችና የአገልግሎቶች ዓለማቀፍ ኤግዚቢሽን ሲዘጋጅ፣ የዕውቀት ሽግግርን ያቀላጥፋል። የኢንቨስትመንትና የቢዝነስ አማራጮችን ይከፍታል። የንግድና የገበያ ግንኙነቶችን ለመፍጠር፣ ውል ለመፈራረም፣ ሽያጭና ግዢ ለመጀመር መልካም አጋጣሚዎችን ይፈጥራል። ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችንና ዝግጅቶችን የሚያስተናግድ አገር፣ በዓለማቀፍ የዲፕሎማሲና ኢኮኖሚ መድረክ ተሰሚነቱ ይጨምራል። የኢኮኖሚ ድርሻው እያደገ ይሄዳል።
አዲስ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽንና ኮንቬንሽን ማዕከል 5ሺ እና 2ሺ ተሳታፊዎችን የሚያስተናግዱ ትልልቅ አዳራሾች ፣ ለኤግዚቢሽኖች እንዲሁም ለጉባኤዎች በስምንት ንዑስ አዳራሽ በርካታ ስብሰባዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚያስችል ነው። በአዲስ አበባ ትልቁ ባለ 5 ኮኮብ ሆቴልም ተገንብቷል፤ 980 የእንግዳ ማረፊያዎችን መያዝ የሚችል እንዲሁም ከመስቀል አደባባይ በመቀጠል የሚጠቀስ ትልቅ አደባባይ፣ እንዲሁም ሁለት “የአምፊ ቲያትር” ስፍራዎችም እየተገነቡና እየተዘጋጁ ነው።
በዓለም የኤግዚቢሽንና የኮንፈረንስ ቱሪዝም ካርታ ላይ የኢትዮጵያ ስምና ድርሻ ጎልቶ እንዲታይ የሚያደርግ ሰፊ ፕሮጀክት ነው። ከተጓዳኝ ግንባታዎች ጋር 15 ሄክታር ይሸፍናል። በዓለም ደረጃ የመወዳደርና ተመራጭነትን የማግኘት ብቃት እንዲኖረው ታስቦ የተገነባ መሆኑ ይነገርለታል፡፡
መዲናችን አዲስ አበባ ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችን፣ ጉባኤዎችንና ስብሰባዎችን በአንድ ማዕከል የማስተናገድ አቅም አልነበራትም ፣ ይህን የአገራችንን ጉድለት የሚያሟላ ማዕከል ተገንብቶ ወደ ፍጻሜው እየደረሰ ያለው ፕሮጀክት፤ ለከተማችንና ለአገራችን ተጨማሪ የስበት ማዕከል እንደሚሆን ይታመናል፡፡
ከተማችን በጣም እያደገች እየተለወጠች ነው። ተወዳዳሪነቷ እየጨመረ ነው። ግን በኮሪደር ልማት ብቻ እንዳልሆነ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ይናገራሉ። በእርግጥ የኮሪደር ልማቱም ሰፊ ነው። መሀል ከተማውን በስፋት ያካለለ፣ ከ130 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ርዝመትን የሚሸፍን የኮሪደር ልማት ከተማዋን ከዳር ዳር እያዳረሰ ነው ማለት ይቻላል። ነገር ግን ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ወጣ ስትሉም ብዙ አዳዲስ ግንባታዎችን ታያላችሁ። ጸዳ ያሉ መኖሪያ ቤቶች በብዛት እየተሰሩ ነው። ለኮሪደር ልማት የተነሱ ነዋሪዎች ምትክ መኖሪያ ቤት እንዲሁም የቤት መሥሪያ ምትክ ቦታ እየተሰጣቸው ነው። ነዋሪዎች በነጻ የሚገለገሉባቸው የመዝናኛና የመናፈሻ ስፍራዎች በአረንጓዴ መስክና በፏፏቴ ተውበው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
በመሀል ከተማ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታ ከአኩሪ ታሪካችን ጋር የተያያዘ ጥሩ ነገር ፈጥረናል። የትልቅ ታሪክ መዘክር ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በግንባታው ጥራትና ውበት፣ በጠቅላላ ይዘቱና በተሟላ አገልግሎቱ ምን ያህል ተመራጭነትን እንዳገኘ በተግባር አይተናል። የኮንፈረንስ ቱሪዝም ስበት ለመሆን ችሏል። ከመሀል ከተማ ወደ ዳር ወጣ ብለን ደግሞ ሌላ ግዙፍ ማዕከል እየጨመርንበት ነው። አዲስ አበባ የዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችና ጉባኤዎች መነሃሪያነቷን የምናረጋግጥበት፣ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከልነቷን በኩራት የምንመሰክርበት ይሆናል።
ኢትዮጵያ በአመቺ ጸጋዎች የታደለች አገር እንደሆነች የገለጹት የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፤ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችና ሀብቶች፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችና ውበቶች አሏት። የአፍሪካ አንድነት መሥራችና የአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ ናት። ቢያንስ ቢያንስ በዓመት አንዴ የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ይካሄዳል። አገራችን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መሥራችም ናት። የተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የሚገኘው በአዲስ አበባ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ የተመድ ተቋማት በአዲስ አበባ ከትመዋል። ይሄ ሌሎች አገራት የማያገኙት ዕድል ነው። የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከላት ተብለው የሚጠቀሱ የዓለማችን አገራት በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ኢትዮጵያ ከእነዚህ መካከል አንዷ ናት።
በታሪካዊ ሀብቶችና በተፈጥሮ ጸጋዎች የታደለች ቢሆንም ግን፣ በዓለም አቀፍ ቱሪዝምና ኢኮኖሚ ውስጥ ተገቢውን ጥቅምና ድርሻ እያገኘች አይደለችም። በተመድና በአፍሪካ ሕብረት ስር የተካተቱ ብዙ ተቋማት በከተማችን አሉ። ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችንና ጉባኤዎችን ማካሄድ ይፈልጋሉ። እዚሁ አገራችን ውስጥ ቢሆንላቸው ይመርጣሉ - ብዙዎቹ። ነገር ግን፣ ተስማሚ ማዕከላትና አማራጮች ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት ያማትራሉ።
ትልልቅ ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽኖችን በብቃት ለማስተናገድ የምንችልበት፣ ዓለም ዓቀፍ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት የሚሰጥና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የተሟሉለት ማዕከል በብቃት ሳናሰናዳ ስለቆየን በየዓመቱ ብዙ ዕድሎችን ያስቀርብናል። የአገራችንን ኢኮኖሚ ሊያሳድጉ የሚችሉ የሥራና የገበያ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም ዕድሎች ዓይናችን እያየ ያመልጡን ነበር። አሁን ግን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ጥራቱን የጠበቀና የተሟላ አገልግሎት የሚሰጥ ማዕከል ተገንብቷል ፤ብለዋል የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - አዲስ ዓለም ዓቀፍ ኤግዚቢሽንና ጉባኤ ማዕከል።
የማዕከሉ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሲሳይ ገመቹ እንደሚሉት፣ የግንባታውን ጥራትና ውበት በርካታ ባለሙያዎች አይተው መስክረውለታል። ትልቁን አዳራሽ ሁለገብ አዳራሽ ይሉታል - ለስብሰባም ለኤግዚቢሽን ማሰናጃም ይሆናል። 5 ሺ ተሳታፊዎችን ማስተናገድ ይችላል። ዲዛይኑ የሕንጻውን ንድፍ በግላጭ የሚያሳይ “ስቲል ስትራክቸር” እንደሆነ ጠቅሰው፣ በባለ ሙያዎችም ሆነ በተመልካቾች ዐይን ሲታይ ያምራል ብለዋል። ለእያንዳንዱ የስብሰባ ወይም የኤግዚቢሽን ይዘት በሚስማማ መንገድ አዳራሹን ለማስጌጥ እንዲያመች ታስቦበት የተሠራ እንደሆነም ገልጸዋል።
በርካታ ሺ ሰዎችን በአንዴ የሚያስተናግድ ሰፊ አዳራሽ ቢሆንም፣ አየር እንደልብ ስለሚያንሸራሽር፣ የጣሪያው ከፍታም 28 ሜትር ስለሆነ የሙቀት መቆጣጠሪያ አያስፈልገውም። በተፈጥሯዊ ብርሃን አዳራሹን የሚያጥለቀልቁ ረዣዥምና ሰፋፊ መስኮቶች አሉት። የፊልም ምስሎችን ለማየት ወይም የኤሌክትሪክ መብራት መጠቀም ካስፈለገም፣ መስኮቶቹን ሙሉ ለሙሉ መጋረድ ይቻላል።
ሁለት የምግብ አቅርቦት ማስተናበሪያ ስፍራ፣ እንዲሁም የእረፍት ሰዓት የሻይ የቡና መስተናገጃ ሰፊ ቦታ አለው። ከአዳራሹ ሥር በታችኛው ፎቅ ወደ ተዘጋጁት በርካታ የመጸዳጃ ቤቶች የሚያደርስ መተላለፊያ የሚገኘውም በዚሁ አቅጣጫ ነው። በአዳራሹ ሌላኛው ጎን የክብር እንግዶች መቆያ ቦታና ተጨማሪ የመጸዳጃ አገልግሎት ስፍራዎች ተሰርተውለታል።
የኤግዚቢሽን አዳራሽ - በ5 ሺ ካሬ ሜትር ስፋት
ከሁለገብ አዳራሽ ቀጥሎ ከላይ የምናገኘው ትልቅ አዳራሽ ዋና አገልግሎቱ ለኤግዚቢሽን ነው። መካከለኛ አዳራሽ ነው ይሉታል - ዋና ስራ አስፈጻሚው ሲሳይ ገመቹ። አንድ ሺ ሰዎችን ያስተናግዳል። ዘና ያለ መንፈስ እንዲኖረው፣ አየር በደንብ እንዲንሸራሸር፣ የተፈጥሮ ብርሃን በሰፊው እንዲያስገባ ታስቦበት የተሰራው አዳራሽ፣ ጣሪያው 28 ሜትር ቁመት አለው።
ከአንድ አቅጣጫ በኩል፣ ከአዳራሹ አጠገብ የመጋዘን ክፍሎች አሉት። በሌላኛው አቅጣጫ ደግሞ ቢሮዎችን ይዟል። በአጠቃላይ ከኤግዚቢሽን ዝግጅት ጋር የተዛመዱ አገልግሎቶችን ሁሉ እንዲያሟላ ተድርጎ ነው የተሠራው።
ሰፊ የትዕይንት አዳራሽ - በተገጣጣሚ ግድግዳም ሲከፋፍሉት ደግሞ ሰባት ንዑስ አዳራሾች፡፡ አራተኛ ፎቅ ላይ የምናገኘው ሰፊ አዳራሽ፣ 2 ሺ ሰዎችን ማስተናገድ ይችላል። ለትልቅ ጉባኤ ሊያገለግል ይችላል። ስዕሎችን ለማሳየት ወይም ሌላ ለእይታ የሚቀርቡ ድግሶችን ለማዘጋጀትም የአዳራሹ ቅርጽ ይመቻል። ተመልካቾች በአንዱ ጫፍ ገብተው፣ በእይታ ድግሶችን ተስተናግደው ዓይናቸውን ረክቶ በሌላኛው ጥግ ይወጣሉ። ካስፈለገ ደግሞ ረዥሙ አዳራሽ ውስጥ ተገጣጣሚ ግድግዳዎች ተዘርግተው፣ ለንዑስ ስብሰባዎች የሚያገለግሉ 7 መካከለኛና አነስተኛ አዳራሾች ይወጣዋል። ግድግዳዎቹ ተጣጣፊ ተገጣጣሚ ቢሆኑም፣ ከመደበኛ ግድግዳ አይተናነሱም። ድምጽ አያሳልፉም፤ ሲታዩም ያምራሉ ብለዋል - የማዕከሉ ዋና ስራ አስፈጻሚ።
አዳራሹ አራተኛ ፎቅ ላይ ቢሆንም፣ ከበቂ በላይ መተላለፊያዎች አሉት። በየአቅጣጫው በተሠሩ በርካታ ሰፋፊ ደረጃዎች አማካኝነት መግባትና መውጣት ይቻላል። ከደረጃዎች ጎን “ስካሌተሮች” አሉ። ከእነዚህ በተጨማሪም አሳንሰሮች (ሊፍቶችን) መጠቀም ይቻላል።
የአዳራሾቹን አገልግሎት በትክክል ለማከናወንና ለመቆጣጠር የሚያገለግሉ የቴክኒክና የቴክኖሎጂ ክፍሎችን ጨምሮ፣ የጥበቃና የክትትል ስራውም በሚገባ እንደታሰበበት ስራ አስፈጻሚው ያስረዳሉ። የጥበቃ ስራዎችን በምሳሌነት አንስተው ሲናገሩ፣ ዋናዎቹ ቁልፍ ነገሮች የባለሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ናቸው ይላሉ። ኤግዚቢሽኖችና ጉባኤዎች በተቃና ሁኔታ እንዲካሄዱ ነው - የጥበቃ አስፈላጊነት። አዘጋጆች፣ ተሳታፊዎችና ተመልካቾች የተሟላ ምቹ አገልግሎት እንዲያገኙም ነው - የጥበቃ አላማው።
ለዚህም የጥበቃ ካሜራዎችና መከታተያ ቴክኖሎጂዎችን አሟልተናል ይላሉ - አቶ ሲሳይ። የጥበቃ ባለሙያዎች የተሰብሳቢዎችን ትኩረት በማይረብሽ ሁኔታ ስራቸውን እንዲያከናውኑም በቂ ስልጠና ይኖራቸዋል።
ከኤግዚቢሽንና ከጉባኤ አዳራሾች በተጨማሪ፣ ማዕከሉ ሌሎች በርካታ ግንባታዎችንንና አገልግሎቶችን ያካትታል። ባለ 5 ኮከብ ሆቴል - 980 የእንግዶች ማረፊያ ያለው። ከአዳራሾቹ አጠገብ የተገነባው ሆቴል፣ ስራው አልቋል ማለት ይቻላል። ተቀብቶ አጊጦ አምሯል። በሆቴል አገልግሎት በከተማችን በትልቅነቱ ቀዳሚነትን የያዘ ሆቴል እንደሚሆን የተናገሩት ከንቲባ አዳነች አበቤ፤ 980 የእንግዳ ማረፊያዎችን መያዝ ይችላል ብለዋል። የአገልግሎቱ ጥራት ከስካይ ላይት ጋር በእኩል ደረጃ የሚቀመጥ ነው ብለዋል። ነገር ግን የአዳራሾችና የሆቴል ግንባታ ጉዳይ ብቻ አይደለም።
ሰፊ የስበት መናኸሪያ
እዚህ አካባቢ ምንም ሆቴል አልነበረም ይላሉ - ከንቲባ አዳነች። አሁን ሦስት ሆቴሎች ተሰርተዋል። አራተኛው ከማዶ በኩል አለ። ተደማምረው 1400 የእንግዳ ማረፊያ አገልግሎት የማቅረብ አቅም አላቸው። ምርጥ ምርጥ አፓርትመንቶች በአካባቢው ተሰርተዋል። ለሕዝብ አገልግሎት ክፍት የሚሆኑ አረንጓዴ ስፍራዎችና ተቋማትም እየተዘጋጁ ነው። ፊት ለፊት ለሚ ፓርክ አለ። ሰፊ ነው። ከመስቀል አደባባይ በመቀጠል የሚጠቀስ የከተማችን ትልቅ አደባባይ ነው። ከኤግዚቢሽንና ከጉባኤ ማዕከሉ ጋር ተያይዞ ነው ስራው የሚከናወነው።
ይህም ብቻ አይደለም። የአዳራሾችና የሆቴል ግንባታዎችን ጨምሮ፣ በተጓዳኝ የሚካሄዱ የፓርክና የተለያዩ አገልግሎቶች ግንባታዎች ብዙ ናቸው። ከአዳራሾቹ አጠገብ በሁለት አቅጣጫ፣ ሰፋፊ አምፊቴአትሮች እየተገነቡና እየተዘጋጁ ነው።

 

Read 333 times