Saturday, 04 January 2025 21:00

የአዲስ አድማስ ትዝታዬ አጽቆች!

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(2 votes)

ሕይወትን ወደ ኋላ ማየት፣ትዝታን መጎንጎንና መፍተል፤ማዳወርና ፈትሾ፣ስለ ነገ ማስላት የሰው ልጆች ልዩ ተፈጥሮ ነው ብዬ አምናለሁ። እኔም ሰው ነኝና ትናንቴን ስቆፍር ብዙ ትዝታዎች ከፊቴ ድቅን እያሉ ምልዐትና ጉድለቴን እንደ መስታወት ያሳዩኛል። በርግጥም፣ ትናንት ማለት ዛሬ የቆምንበት መልክና ቁመና የተሠራበት፣ማንነታችን የቆመበት ዐምድ ነው። ስለዚህም ዓለም ላይ የምናደንቃቸው ገድሎች፣የምናፍርባቸው ነውሮች፣ ድንገታዊና ዕለታዊ ክስተቶች አይደሉም።ተዘርተው የበቀሉ፣በቅለው የጸደቁና ፍሬ ያፈሩ ናቸው። ይሁንና ወይንም ሆነ ሆምጣጤ ያፈሩበት የየራሳቸው ሰበብና ገጠመኝ አላቸው።
በብርቱ ገበሬ የተኮተኮተ እርሻ በዳዋ እንደማይዋጥ ሁሉ፣ የሰው ልጅም በቅሎ ፍሬያማና ውጤታማ የሚሆንበት የየራሱ መስክ አለው። የዓለማችን ክዋክብት፣የታሪካችን ቁንጮ ስሞች የገነኑት፣አሊያም የኮሰመኑት በዋዛ አይደለም። አርተር ሾፐን ሀወር ጠርጣራነቱንና ጥላውን መሸሹን የተፈጥሮ ሰበብ ብቻ አድርገን ልንከስሰው አንችልም። ሚሎሶቪችና ሒትለርም እንደዚሁ ሰበባቸው ብዙ ነው። ናፖሊዮን ቦናፖርት ዐለምን ያንቀጠቀጠው ጠመንጃ በታጠቀ ቀንና ከዚያ በኋላ አይደለም። የሚበርርባቸው ክንፎች ያቆጠቆጡት ገና እናቱ ማኅጸን ውስጥ ባሩድ ሲታጠን በጦር ሜዳ ነበር። ምናልባትም የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት፤ ገና በጽንስነቱ የእናቱን የጦር ውሎ ፉከራና ሽለላ እያዳመጠ አድጓል።
ከእኛም ወገን እንደማሳያ ብንቆጥራቸው ታላላቅ የሚባሉት የሀገራችን ጀነራል መኮንኖች እንኳ የበቀሉበትና የተኮተኮቱበት ሥር አላቸው። ለምሳሌ ሜጀር ጀነራል መርዕድ ንጉሤን በልጅነታቸው የኮተኮተችው ሞግዚታቸው ሃደ ኩሊ ናት። የሃደ ኩሊን አስተዋጽዖ ጀነራሉ እንደ ቀልድ አያዩዋትም፤የኋላ ቁመናቸውን የትልቅነታቸውን መልክ የሰጠቻቸው እንደሆነች በማስታወስ፣ የመከረቻቸውን ምክሮች ሳይቀር በማስታወሻቸው መዝገበው ያሰሉታል።
ሌላው ሜጀር ጀነራል ደምሴ ቡልቶም ጀነራልነታቸው ልጅነታቸው ውስጥ እንደነበር፣ የልጅነታቸው ዳና ይመሰክርልናል። በዚያም ከእጃቸው የማትለየውን ጦራቸውን፣ የተማሪነት መኝታ ክፍላቸው ድረስ ይዘዋት የተጓዙት፣ በደመ-ነፍስ እንዳይደለ እንመዝናለን። ያም ብቻ ሳይሆን ያደጉት በጀግኖች ጉያ እንደነበረ የሕይወት ታሪካቸው ያሳየናል። የፖሊስ መኮንኑና ስመ-ጥሩው የደርግ አባል ደበላ ዲንሳም ተመሳሳይ ታሪክ ስላላቸው፣ መለኪያዎቻችንን ወደ ትናንት መመለስ ተገቢ እንደሆነ እንመለከታለን። ብቻ ለማንኛውም ማሳያዬን ከዚህ በላይ ሳላረዝም ልቋጭና፣ ወደ ዋናው ሀሳቤ ልጓዝ። ወደ ራሴ ትናንት ዘወር ብዬ ጠባቧን የትዝታ ዐለሜን ለመቃኘት ብዕሬን ላንሳ።
ታዲያ ዋናው ነገር የትዝታዬ ቀንዶች ከፍታ፣የጥበብ ፍቅሬ መዐዛ የሚቀዳበት ሠፈር የት ነው?...ብዬ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ቀናትና ዓመታት መበርበር ነው። ለእኔ ጋዜጣዋና የተባ ብዕር ያለው ጋዜጠኛ ተፈሪ መኮንን ትውውቅ ቅርብ ለቅርብ ናቸው። ተፈሪ ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በሚጽፍበት ጊዜ እኔ ትጉህ የጋዜጣዋ አንባቢ ነበርኩ። ያለማጋነን በሰንበት ሪፖርተር ጋዜጣን ሳላነብብ ቁርሴን አልበላም ነበር። ያኔ “ደላላው”የሚለውና በከበደ ደበሌ የሚዘጋጀው ዐምድ ምርጡ ነበር። እንደዚሁ ጋዜጠኞቹ ገዛኸኝ ጌታቸውና ተፈሪ የሚጽፏቸው ሸጋ ሸጋ መጣጥፎች ነበሩ። ታዲያ አንድ ቀን የምወድደው የሪፖርተር ጋዜጠኛ ተፈሪ መኮንን የሚያበሳጭ ጽሑፍ መጻፉ አበሳጨኝና የስልክ ቁጥሩን ከሰዎች ፈልጌ ሙልጭ አደረግሁት፤”ጽሑፎችህን በጣም እወዳቸው ነበር፤ዛሬ ግን አስጠላኸኝ። የካድሬ ጽሑፍ አያምርብህም!” ስለው፣ተፈሪ ባልጠበቅሁት ሁኔታ የማያቋርጥና ሙዚቃ ያለው ሳቅ ሳቀ።...የሳቁ መርዘም እኔንም ወደ ማሳቅ መጣ። የንዴቴ ዕድሜ ሁሌም አጭር ነውና በዚያው ቋጨነው።
ከዚህ ቀጥሎ ተፈሪ መኮንን በአዲሱ ጋዜጣ፣በአዲስ አድማስ ብቅ አለ። ነቢይ መኮንን የአዲስ አድማስ አዘጋጅ ሆነ። ከተፈሪ ጋር ወዳጅነት ስለነበረን ጋዜጣዋን ገና በማለዳው ተዋውቄ ለሰዎች አስተዋዋቂ ሆንኩ። አሰፋ ጎሳዬ ነሸጥ አድርጎት በድንገት ሳይሆን ለዐመታት ከልቡ መክሮ፣ከወዳጆቹ ሀሳብ አንሸራሽሮና ጽሑፎች አጠራቅሞ የጀመረው ስለነበር፣ ነፍሴን አየር ላይ የሚያንጠለጥል ፍቅር አስያዘችኝ። አንዴ ብቻ ሳይሆን፤ደግሜ ደጋግሜ የማነብባት ጋዜጣ ሆነች። ቅዳሜ እስኪመጣ የነበረው ናፍቆት ሌላ ነው፤እስኪነጋም እንደዚያው ነበር። አቤት እሸት ለእሸት፣ ልቦች የተሻተቱበት ዘመን!?
እውነት ለመናገር ጋዜጣዋ በጭብጥ ብቻ ሳይሆን፣ በቅርጽም አዳዲስ ነገሮችን ይዛ መጥታ ነበር። በተለይ ሥነ ጽሑፍ ለምንወድደው “የግጥም ጥግ”ን የመሳሰሉና የአጫጭር ልብወለድ ገጾች ይዛ መምጣቷ ልዩ ስሜት ፈጠሩልን። የጥበብ አምድ ላይ የሚሠሩት ዳሰሳዎች ዐይኖቻችንን ገለጡልን። በግሌ ንባቡ የልጅነት ልምዴም ቢሆን የንባብ ምርጫዬን አሳመሩት ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። በዚያ ላይ ፖለቲካና ዐለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ዝንባሌ ላለን አልአዛር ኬ. የራሱን ቀለም ይዞ ሲሸነሽነው ትንግርት ነበር። ምን ያላየነው ጉድ ነበር?...
ከዚህ ቀደም የማናውቃቸው እንደ ሰለሞን ገብረእግዚአብሔር ያሉት፣ የኤኮኖሚና ፖለቲካ ፍልስፍናን ፈር አስይዘው ሲጋልቡት አብረናቸው መሮጥ ግድ ብሎን ነበር። አንዳንዴ ውይይትም ሙግትም ሲጨመርለት በብልጭታው ወጋገን ሕይወታችን ደምቃ እንደነበር አስታውሳለሁ። ሌላ ፕላኔት የተፈጠረልን ያህል ፈንድቀናል። ለጥቆም ገና ተማሪ እያለሁ የማውቀው ኀያሲ አብደላ እዝራ፣ በብርቅዬ ገለጻዎቹ ብቅ ብሎ ልቦለዶቻችንን ሲፈተፍት ቁርኝቴ ይበልጥ ጠበቀ። በሌላ በኩል፤ የቀድሞው ወዳጄ ተፈሪ መኮንን ሕፃን ልጅ የሚያባብል ያህል በሚመቸው ተረኩ፣ታላላቅ ሰዎችንና ሁነቶችን እያቀረበ በእሽሩሩ ዜማ አጅቦ ሲያጎርሰኝ እንደ ሕፃን ልጅ ጉንጭ ያወጣሁ ያህል ነፍሴ አማረባት። እናም አሰፋ ጎሳዬን በየዕለቱ መመረቅ ጀመርኩ። ይሄኔ የኔም የልቤ ምድጃ እየጋለች እንደነበር አስታወስኩ።
የዛሬው ዋና አዘጋጅ ኢዮብ ካሣ ያኔ እንደኛው ተጋባዥ ጸሐፊ ነበረ። በዚያ ላይ በተለያዩ የብዕር ስሞች ያለውን ያካፍላል። አሁን ሳስታውሰው፣የሚያቀርባቸው የአጫጭር ልቦለዶች የትርጉም ሥራው፣ የተለያዩ ቴክኒኮችን አስተምሮናል ብዬ አምናለሁ። በሌላ በኩል፤ ሀገራዊና ባሕላዊ መልካችንን እንደ መስተዋት በማሳየት የሰለሞን አበበ ቸኮልን ያህል ያደነቅነው አልነበረም። በኋላ የአዲስ ዘመንን ቅርጽና ይዘት ቀይሮ የነበረው ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ፅጌ /ከእነ ቅንነቱ/ ከሀዋሳ ያስመጣው አብረሃም ረታ ዐለሙ፣በንባብ የበለጸጉ መጣጥፎቹን ሲጽፍ በግሌ ያመለከተኝ ነገር ነበር። ጥሩ አንባቢ ሀሳብ አያልቅበትም፤ውበት ብቻ ሳይሆን እውነትም በጽሑፍ ውስጥ ገዝፎ ምሰሶ መሆን አለበት።
የኔ ዘመን ሰልፈኞች ዓለማየሁ ገላጋይ፣እንዳለጌታ ከበደ፣በዕውቀቱ ሥዩም፣ተሾመ ገብረሥላሴና ሌሎቹም በውስጤ ያሰመሩት መስመር፣ያኖሩት ቀለም ዛሬም የተፋቀ አይመስለኝም። አዲስ አድማስ ካስተዋወቀችኝ ሰዎች ግዙፍ ሆኖ ቀርቶ ተንጠራርቼ የማየው፣ዓይቼ የማልጠግበው የሀገሬ ዋርካና የዘመኔ የሕግ ባለሟል ጋሽ አሰፋ ጫቦ አንዱ ነው። እንደ ሀገሬ ባንዲራ አጎንብሼ እንድወድደው፣ቀና ብዬ እንድቆም ያደረገኝም የአዲስ አድማሱ ገበታ ነው።
እንግዲህ ከዚህ አድማስ መለስ ብዬ ስለ ራሴ የጽሑፍ እርምጃ ባሰብኩ ቁጥር፣ ትዝታዬም ሆነ ወሬዬ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው። ዘመኔን ጠቅለል ሳደርግ፣ መላው ታሪኬ የእግዚአብሔር፤የሥነ ጽሑፍ ታሪኬ የአዲስ አድማስ ነው። ስለዚህም ይመስለኛል፣ብዙ ጊዜ ሬዲዮ ላይ፣አሊያም በቲቪ መስኮት ሥራዬን አስቤ ሳወራ፣ወይም እንዳወራ ስጠየቅ፣ ከአፌ ላይ አዲስ አድማስ የማይጠፋው፡፡
በርግጥም ቀስ በቀስ አዲስ አድማስ ላይ መጣጥፍ ማበርከት ስጀምር ማንበብ የሚገባኝን አካባቢ የተማርኩት፣ንባብን በማጣጣምና በመመዘን መለካት የለመድኩት፣ ከጋዜጣው ጋር ቁርኝቴ ሲጨምር ነው። በተለይ ከግጥም ጋር በፍቅር የወደቅሁት፣መመርመርም መፈተሽም ያሠኘኝና ሳላውቀው ራሴን በውስጡ ያገኘሁት እዚሁ ዐውድ ውስጥ ነበር። ልቦለዶችን መፈተን፣ቅርጻቸውን ማጤን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ የጀመርኩት ቢሆንም፣የተለያዩ ሰዎችን ትንተና በማየት ወደ ውስጥ መፈተሽን ደፍሬ የገባሁበት ይመስለኛል። ይህኛው አካባቢ በተለመደው እውነታዊነት ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሳይሆን፣ለሀገራችን አዲስ የሆኑ ሥራዎችን የሚጎነትል ስለነበር፣ ሽንቁር ለሚያይ ሰው መስኮት መግጠም የሚያስችል ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ባመነበት ነገር ወደ ኋላ የማያውቀውና ከማንም ጋር የቡድን ሰልፍ የማይይዘው ሰለሞን ገብረእግዚአብሔር፤  የግጥሞቻችንን ስልት፣የምሁራኑን የተምታታ ቀለም ቆጠራ ሳይቀር በተጨባጭ መረጃ ሲፈትን የታየው በሌላ ጆርናሎች ሳይሆን፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው። እኔም በራሴ ክፍተቶችን ሳይ ባለዕዳነት ተሠምቶኝ ሽንቁሩን ለመድፈን፣አብዝቼ የሥነ ግጥም መጻሕፍትን ከአሮጌ ተራ አሳድጄ መሸመት የጀመርኩት ጋዜጣዋ ውስጤን ኮርኩራ ካነሳሳችኝ በኋላ ነበር። ንባብ የሚያመጣውን ለውጥ የተገነዘብኩት የዛሬ ሰባት ዐመት አዲስ አድማስ ላይ የሠራሁትን ዳሰሳ ሳይና ክፍተቶቼ የሚቆጩና ቁመናዬ ያልጠና መሆኑን ስፈትሽ ነበር። በርግጥም ወፌ ቆመች ብዬ መራመድ የቻልኩት በዚህችው ብዙ ደራስያንን ጥበብ ፈትፍታ እያጎረሰች ባሳደገች ጋዜጣ ነው።
የእነ ሌሊሳን ያልተለመዱ ቅርጾች፣የእነ ዳዊት ጸጋዬን ወፈፌ ግጥሞች፣የእነ አንተነህ ይግዛውን የዜና ቅኝቶች፣የእነ ገዛኸኝ ጸ.ን ዳሰሳዎች ለአደባባይ ያበቃቸው ይህቺው አዲስ አድማስ ነች። የተባባሪ ፕሮፌሰር በቀለ ጣፋጭ መጣጥፎችንም ያነበብኩት ከዚህችው ጋዜጣ ነው። የመንፈሳዊና ፍልስፍናዊ የጦርነት ዐውድማስ ሆና አልነበር?...ዶ/ር ፍቃዱ አየለ፣ጤርጢዮስ፣ጌታሁን ሔራሞና ሌሎችንም አስተዋውቃናለች፡፡ እናም በተለያዩ የዕድገት አንጓዎች፣በተዥጎረጎሩ የሀገር ጉዞ ምዕራፎች፣በምጣኔ ሀብታዊ መንገዳገዶች ስታልፍ ያንን ሁሉ አስልታ፣መክራና ዘክራ ኀላፊነቷን ተወጥታለች። በዚያ ሂደት እነሆ አሁን የብር ኢዩቤልዩ ደጅ ላይ መድረሷ የሚያሳየን፣ ብስለትና ዕድሜ በንባብ ከታጀቡ፣ ከኪሳራ ነፃ መሆናቸውን ነው፡፡ ስለዚህ ጋዜጣችን እንደ ብዙዎቹ ፕሬሶች እቅፍ አበባችንን በመቃብሯ ሳይሆን፤በሕያው አጸድዋ ለማስቀመጥ በመታደላችን “ተመስገን” ባይና እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡
ለሚወድዱሽ ሁሉ ሰላም ይሁን!

Read 675 times Last modified on Saturday, 04 January 2025 22:02