በሲዳማ ክልል እና ወላይታ ዞን መካከል የተፈጠረው የ”ወሰን ይገባኛል” ውዝግብ የዜጎችን ሕይወት ቀጥፏል። መንግስት ለዚህ ውዝግብ አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ተጠይቋል።
በወላይታ ዞን፣ አበላ አባያ ወረዳ፣ “አባያ ክላስተር” በሚባል የእርሻ ልማት ላይ “ከሲዳማ ክልል መጡ” የተባሉ የልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት ባለፈው ሐሙስ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ጥቃት መፈጸማቸውን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪ ለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል። ነዋሪው አክለውም፣ በሲዳማ ክልል እና ወላይታ ዞን መካከል የተከሰተው የ”ወሰን ይገባኛል” ውዝግብ መፍትሔ አለመበጀቱ በአካባቢው ላይ ውጥረት እንዲፈጠር እና ለዜጎች ሕይወት መቀጠፍ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
የእርሻ ልማቱ በመንግስት ሲተዳደር ቆይቶ፣ ኋላ ላይ “አሚባራ” በተሰኘ ድርጅት በኪራይ ሲለማ እንደነበር ያወሱት ነዋሪው፣ እርሻው የነበረበትን ዕዳ በመክፈል የወላይታ ልማት ማሕበር ላለፉት አራት ዓመታት በባለቤትነት እንደያዘው አብራርተዋል። ነዋሪው አክለውም፤ “ለእርሻው ከብላቴ ውሃ የሚያስተላልፈው ትልቅ ቱቦ በመሰበሩ ሳቢያ ውሃው ፈስሶ እርሻውን አበላሽቶ ለሁለት ዓመታት ያህል ስራ ቆሞ ነበር። ዘንድሮ ግን የልማት ማሕበሩ የራሱን ባለሞያዎችና ትራክተር በመያዝ ዳግም ለማልማት ወደ እርሻው አመራ።” ይላሉ።
ይሁንና ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም. ትራክተር በመያዝ ወደ ስፍራው የተጓዙት ባለሞያዎች ላይ “ከሲዳማ ክልል መጡ” የተባሉ የልዩ ሃይል እና ሚሊሻ አባላት ጥቃት ማድረሳቸውን የተናገሩት ነዋሪው፤ “የጥቃቱ መነሻ ምክንያት የእርሻውን ስፍራ ወደ ሲዳማ ክልል ለማካለል ነው” በማለት ነው። የአበላ አበያ ወረዳ ጥቃት ወደ ተፈጸመበት ስፍራ የፖሊስ ሃይል ቢያሰማራም፣ ሁኔታም “ከአቅሙ በላይ” እንደሆነበት ነዋሪው ይገልጻሉ። ከተላከው የፖሊስ ሃይል ጋር አብረው በተጓዙት የወረዳው አመራሮች እና የወላይታ ልማት ማሕበር ስራ አስኪያጅ ላይ እነዚሁ የልዩ ሃይሎች ጥቃት እንዳደረሱ የሚናገሩት ነዋሪው፣ ነገር ግን ጉዳት ሳይደርስባቸው ከስፍራው መሸሻቸውን ይጠቅሳሉ። ሆኖም ግን ሁለት ወጣቶች ተገድለው፣ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ደግሞ ቆስለው ሆስፒታል መግባታቸውን አመልክተዋል።
ነዋሪው በ1994 ዓ.ም. ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደነበር ያወሱ ሲሆን፣ በጥቃቱም በርካታ መኖሪያ ቤቶች እንደተቃጠሉና በንጹሃን ዜጎች ላይ ግድያ መፈጸሙን ይገልጻሉ። “ያኔም ሆነ አሁን የሲዳማ እና ወላይታ አካባቢዎችን የሚለይ ግልጽ ወሰን አለመኖሩ የችግር መንስዔ ነው። ወሰኑን ለመለየት ባለመቻሉ ችግሩ ተባብሶ ቀጥሏል። በዚያ ላይ ጥቃት ፈጻሚዎች ላይ መንግስት ሕጋዊ እርምጃ እየወሰደ አይደለም።” ብለዋል፣ ነዋሪው።የአገር መከላከያ ሰራዊት ጥቃት ከደረሰ በኋላ ዘግይቶ ወደ አካባቢው መግባቱንና ለነዋሪዎቹ በቂ ጥበቃ እያደረገ አለመሆኑን ያስረዱት እኚሁ ነዋሪ፣ “በነዋሪዎች ላይ ድብደባና ወከባ እየፈጸመ ነው።” ሲሉ ስሞታቸውን አቅርበዋል።
“የአካባቢው ሕዝብ ለወላይታ ዞን አስተዳደር በተደጋጋሚ ቅሬታ አቅርቧል። ነገር ግን የሕዝቡ ቅሬታ ሰሚ አላገኘም።” ያሉት ነዋሪው፣ አካባቢው በውጥረት ውስጥ እንደሚገኝና ሕዝቡ የደህንነት ስጋት እንዳለበት አያይዘው አመልክተዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የአበላ አባያ ወረዳ እና የሲዳማ ክልል የመንግስት ሃላፊዎችን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።