አሚጎስ የገንዘብ ቁጠባና ብድር የህብረት ሥራ ማህበር፣ በ2016 በጀት ዓመት 145 ሚሊዮን ብር ባጠቃላይ ማትረፉንና ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡ የማህበሩ አባላት የትርፍ ክፍፍል ድርሻ 53 በመቶ ነው ተብሏል፡፡
አሚጎስ ይህን ያስታወቀው ባለፈው ቅዳሜ ታሕሳስ 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ 11ኛ የባለአክስዮኖች ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚህ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻፀም ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በበጀት ዓመቱ ማህበሩ 145 ሚ ብር ማትረፉንና ከ101 ሚ. ብር በላይ የተጣራ ትርፍ ማግኘቱ ተነግሯል፡፡ የማህበሩ ጠቅላላ ሃብቱም 3 ቢሊዮን ብር ደርሷል ተብሏል፡፡
ተደራሽነትንና የአባላት የአገልግሎት አሰጣጥ እርካታን ለመጨመር አሚጎስ የቅርንጫፍ ቢሮዎችን በማብዛት፣ለአባላት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት እንዲቻል ጥናቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል። ማህበሩ፣ በተለያዩ ሀገራት እያደረጋቸው ያሉ የልምድ ልውውጦችና የስራ እንቅስቃሴዎችን በተመለከተም ገለፃ ተደርጓል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ አሚጎስ የ12ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በተለያዩ ኹነቶች ባለፈው ቅዳሜ ያከበረ ሲሆን፤ ለስኬታማ የማህበሩ አባላት የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷል፡፡ በኢንተር ላግዠሪ ሆቴል በተከበረው የማህበሩ የ12ኛ ዓመት የምስረታ ክብረ በዓል ላይ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ፣ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አብዲ ሙሃድ እንዲሁም የአዲስ አበባ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ልዕልት ግደይ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ክብረ በዓል ላይ የሕብረት ስራ ማህበሩን በትጋት ሲያገለግሉ ለቆዩት የአሚጎስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍፁም አብርሃ፣ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ሽጉጤ ሽልማት አበርክተውላቸዋል፡፡ በተመሳሳይ፣ በአግባቡ በመቆጠብና በመበደር ለሌሎች የማህበሩ አባላት አርአያ የሆኑ ስኬታማ አባላትም የዋንጫ ሽልማትና ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡
የዛሬ 12 ዓመት በሦስት ዓይን ገላጭ መሥራቾች ተጠንስሶ ዛሬ ወደ 10ሺ የሚጠጉ አባላትን ያፈራው አሚጎስ የህብረት ሥራ ማህበር፤ከ120 በላይ ሰራተኞችን ይዞ በተለያዩ የክልል ከተሞች ቅርንጫፎቹን በማብዛት ተደራሽነቱን እያሰፋ ይገኛል ተብሏል፡፡
Published in
ዜና