ዕንቁራሪቶች፣ ጦጣዎች፣ አይጦችና የዱር አራዊቱ ንጉስ አንበሳ የሚኖሩበት ትልቅ ደን አለ፡፡ እንቁራሪቶቹ ከደኑ አጠገብ ካለው ኩሬ ውስጥ ነው የሚኖሩት፡፡ አንበሳ የሚጠይቃቸውን ሁሉንም በመታዘዝ ነው ሌሎቹ የሚኖሩት፡፡ አንድ ቀን እንቁራሪቶቹ፣ ጦጣዎቹና አይጦቹ አንድ ላይ መስክ ላይ በየበኩላቸው እየለቃቀሙ ሳለ፣ አዳኞች አንበሳውን ሲያሳድዱት ተመለከቱ፡፡ እንቁራሪቶቹ “ለጌታም ጌታ አለው! ሰው’ኮ የአንበሳ ጠላት ነው አይለቀውም፡፡ ከዚህ መዓት ለማምለጥ በሉ ወደ ኩሬያችን እንሂድ” አሉና ወደ ኩሬያቸው አመሩ፡፡ አይጦቹም፣ የደኑ ገዢ አንበሳ ነው ብለው ስለያሚስቡ፣ “ሰዎችና አንበሶች አጥፊና ጠፊ ናቸው፡፡ የዚህ አንበሳ ጣጣ ለእኛ እንዳይተርፈን በጊዜ ወደ ጎሬያችን ገብተን እንሸሸግ” አሉና ሄዱ፡፡ ጦጣዎቹ “ሰው አንበሳ ሲጠላ እንድ ጉድ ነው፡፡ በጊዜ ዛፋችን ላይ እንውጣ” ብለው በየዛፎቻቸው ላይ ተንጠላጥለው ወጡ፡፡
አዳኞቹ አንበሳውን ገድለው ቆዳውን ገፍፈው ወሰዱ፡፡ አዳኞቹ ከሄዱ በኋላ ዕንቁራሪቶቹ ጦጣዎቹና አይጦቹ እንደገና ተሰባስበው፤ ጦጣ ስለ ዛፍ ላይ ኑሮ፤ እንቁራሪት ስለ ኩሬ ኑሮ፣ አይጥ ስለ ከመሬት በታች ኑሮ አወጉና የአንበሳውን አሟሟት እያነሱ በየበኩላቸው የሚያስተዳድሩት ግዛት እንዳላቸው በመጥቀስ ወጋቸውን ሲሰልቁ ቆዩ፡፡
በነጋታው በኩሬ ውስጥ ያሉትን ነብሳት ሁሉ ለመብላት የሚፈልጉ አጥማጆች ሲመጡ ጦጣዎች ወደ ዛፋቸው፣ አይጦት ወደ ጉድጓዳቸው ሮጡ፡፡ እንቁራሪቶች ግን ሁሉም ከኩሬው ተለቃቅመው ተወሰዱ፡፡ ጦጣዎችና አይጦች እንደ ልማዳቸው በሦስተኛው ቀን ተገናኝተው እያወጉ “እንቁራሪቶቹን ምን አድርገዋቸው ይሆን?” እያሉ ተጠያየቁ፡፡ “ሰው እኮ ጨካኝ ነው፡፡ በልቶዋቸው ይሆናል” አሉ ጦጣዎቹ፡፡ “ምናልባት እሰኪበላቸው በእንክብካቤ ያኖራቸው ይሆናል” አሉ አይጦቹ፡፡
ይህንኑ እያወጉ፤ ሳሉ የአይጥ ወጥመድ የያዙ በርካታ ሰዎች መምጣታቸውን አዩ፡፡ ጦጣዎቹ ፈጥነው ወደዛፋቸው ወጡ፡፡ አይጦቹ ወደ ጉድጓዳቸው ሮጡ፡፡ ባለወጥመዶቹ አድፍጠው ወጥመዶቸውን በጥንቃቄ በየጉድጓዳቸው አፋፍና ውስጥ አኖሩባቸው፡፡
በነጋታው አይጦች የወጥመዶቹ ሲሳይ ሆኑ፡፡
ጦጣዎችን “አንበሳው ሰው ጠላቱ መሆኑን ረስቶ ጉልበቱን ተማምኖ በደን ውስጥ ሲጎማለል ተበላ፡፡ ዕንቁራሪቶቹም ማምለጫ በሌለው ኩሬ ውስጥ እንደተወሸቁ መውጫ ሳያበጁ ቀለጡ፡፡ እነዚህ አይጦችም ገብተው ከማይወጡበት ጉድጓድ ውስጥ ተቀርቅረው ብቅ ሲሉ በወጥመድ እየታነቁ ሲጥ አሉ፡፡ እኛ ግን ዛፍ ላይ ነንና ሰው ወደኛ ሲመጣ ወደታች በቀላሉ ስለሚታየን ከዛፍ እዛፍ እየዘለልን ደብዛችንን እናጠፋበታለን” ተባባሉ፡፡
ጥቂት ቀናት ሰነባብቶ ሰዎች ወደጫካው መጡ፡፡ ጦጣዎቹ ማንም አይነካን ብለው ዛፋቸው ላይ እንዳሉ ቆዩ፡፡
የሰው ልጅ ጥፋት ሰለባ መሆናቸውን ያወቁት ግን ከዳር ዳር ደኑ በእሳት መያያዙን ያዩ ጊዜ ነበር፡፡ ዛፍ ላይ ያሉት እዚያው እንደተንጠለጠሉ ተቃጠሉ፤ የወረዱትም በሰው እጅ አለቁ፡፡ የሚገርመው ግን አዳኞቹ ሰዎች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በጠላቶቻቸው ተቃጥሎ ዶግ-አመድ ሆኖ አገኙት፡፡
* * *
ዓለም የአጥፊና ጠፊ መድረክ ናት፡፡ ነግ በኔ ብሎ ገና በጠዋት ያልተጠናቀቀ ዕጣ-ፈንታው እንደቀዳሚዎቹ ሟቾች ነው፡፡ የፋሲካው በግ፣ በገናው በግ እንደሳቀ መሞቱ ከዓመት ዓመት የምናየው ሀቅ ነው፡፡ እኔ የራሴን ታሪክ እሰራለሁኝ እንጂ ሌሎች እኔን መሰሎች በታሪክ ውስጥ ምን ጽዋ ደረሳቸው? ብሎ አለመጠየቅ፣ ምላሹን ካገኙም የእኔንስ ክፉ-ዕጣ እንዴት እመክተዋለሁ? ብሎ አለማውጠንጠን የዓለምንም የሀገራችንንም የፖለቲካ ድርጅቶች ቡድኖች፣ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ታሪካዊ ዕጣ-ፈንታ ሳይታለም የተፈታ እንዲሆን ካደረገው ውሉ አድሯል፡፡ ነግ-በኔ አለማለት ክፉ እርግማን ነው፡፡
ለማርቲን ኒየሞይለር መታሰቢያ የተደረገው ጽሁፍ ይሄንኑ ይነግረናል፡፡ ማርቲን ኒየሞይለር (1892-1984) የፕሮቴስታንት ክርስቲያን የነበረ ጀርመናዊ ቄስ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ውስጥ ናዚዎችን በመቃወም ከባድ ዘመቻ በማካሄዱ እ.ኤ.አ ከ1938 እስከ 1945 ዓ.ም ለ8 ዓመታት ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ አስገብተው ሲያሰቃዩት ከርሞ ኋላ ተፈትቶ ከ1961 እስከ 1968 ዓ.ም ለሰባት ዓመታት የአለም አብያተ-ክርስቲያናት መማክርት ፕሬዚዳንት ሆኖ የመራ ጠንካራ ሰው ነበር፡፡ ለሱ መታሰቢያ የተደረገው ፅሁፍ እነሆ፡-
በጀርመን ናዚዎች መጥተው በመጀመሪያ ያጠቁት ኮሙኒስቶቹን ነበር፡፡ የኮሙኒስቶቹን በር እያንኳኩ ለጨፈጭፏቸው እያየሁ እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም ኮሙኒስት አልነበርኩም፡፡
ቀጥለው አይሁዶቹን ወረዱባቸው፡፡ የአይሁዶቹን በር ሲያንኳኩም እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ አይሁድ አይደለሁም፡፡
ከዚያ ወደ ሰራተኛ ማህበራቱ ዞሩ፡፡ የሰራተኞቹን በር ሲያንኳኩም እኔ ጭጭ አልኩ፡፡ ምክንያቱም የሰራተኛ ማህበሩ አባል ስላልነበርኩ አይመለከተኝም፡፡
ቀጥለው ካቶሊኮቹ ይፈጁ ጀመር፡፡ የካቶሊኮቹንም በር ሲያንኳኩ አሁንም እኔ ዝም አልኩ፡፡ ምክንያቱም እኔ ፕሮቴስታንት ስለሆንኩ አይመለከተኝም፡፡
በመጨረሻ የእኔን በር አንኳኩ፡፡ በዚያን ሰዓት ግን ተነስቶ ሊናገር የሚችል ምንም ሰው አልተረፈም ነበር፡፡
(ለማርቲን ኒየሞይለር [ፍሬድሪሽ ጁስታቭ ኤሚል]መታሰቢያ የተፃፈ- 1949)
የፈለገው መንግስት ይመቸኛል ባለው መንገድ ያሻውን ሀገር ሲረግጥ ያሻውን መሳሪያ ሲጠቀም፣ በእኔስ ላይ ፊቱን ያዞረ እለት ምን ይውጠኛል? የእኔስ በር የተንኳኳ እለት ማን አብሮኝ ይቆማል? ብሎ አለመጠየቅ ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ዛሬ በየቻናሉ በቀጥታ ሥርጭት በቴሌቪዥን የምናየው ጦርነት እንደተዋጣለት የሲኒማ አሊያም የቴያትር ዝግጅት የውሸት እልቂት እስኪመስል ድረስ ያስገርማል፡፡ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆንም አይቀር፡፡ የጋዜጠኞቹም ድምጽት “ጦርነቱ ሊጀመር ነው አብረን እንከታተል” እንደማለት ሆኗል- የሰው ልጅ ሞት ምፀት! እንደትላንት ወዲያ “ኢምፔሪያዝም ውርደት ቀለቡ ነው”… የሚባልበት የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አልፎ፤ እፎይ ብሎ አለም ለመተንፈስ አለመቻሉ ከመደገም የማይቀሩ ብዙ የታሪክ ስላች መኖራቸውን ያስገነዝበናል፡፡ እግረ-መንገዱንም ሀያላን መቼም በቃኝ እንደማያውቁ ዳግም ያስታውሰናል፡፡ የወታደራዊ ኃይል ግሎባላይዜሽን የት እንደሚደርስም ይጠቁመን ይሆናል፡፡ “ወተት ሰርቆ ከመጠጣቱ ይልቅ አፍ አለመጥረጉ ያሳፍረዋል” እንዲሉ ትላልቁን የሃያላን ጥፋት ትቶ በእንጭፍጫፊ ላይ ማተኮር ሌላ ጥፋት እንደመፈፀም መሆኑን ሳያስገነዝበን አያልፍም፡፡ ትንሹን አምባገነን ትልቁ አምባገነን፣ ሚጢጢውን ጉልበተኛ ግዙፉ ጉልበተኛ ሊውጠው ይመኛል፡፡ ይንጠራራል፡፡ ይስፋፋል፡፡
እስከዚያ እንቅልፍ የለውም፡፡ ህዝቡና አገሩ ከመጤፍ አለመቆጠሩ ግን የየዘመኑ ትራጀዲ ነው፡፡ የዛሬም፡፡ ታዋቂው ገጣሚ መንግስቱ ለማ “ባንተ አልተጀመረም ያዳሜ ምኞት” “ከተጠቃውሚ ’መራቅ‘ አጥቂን ‘መጠጋት’ የሚለውን እንደመርህ የያዘው በርካታ መሆኑ ደግሞ መራር ትራጀዲ ያደርገዋል፡፡ “ጠባይ ያለው ልጅ ኑክሊየር ይሰጠዋል፡፡ ጠባይ የሌለው ልጅ የአሻንጉሊት ሽጉጡንም ይነጠቃል ዓይነት ሆኗል የሃያላኑ የአባትነት ባህሪ፡፡ [ወይም በግልባጩ ጠባይ ያለው ብልጥ ልጅ አየሩን ለበረራ ይፈቅዳል፡፡
ጠባይ የሌለው ልጅ “በሳዳም የመጣ በእኔ መጣ” ይላል፡፡ ሁሉንም ጠባይ ይዞ የተፈጠረው ደግሞ “ሳዳምንና አሜሪካን ያየ በኑክሊየር አይጫወትም” እያለ ከዛም ነዳጅ እየገዛ፣ ለዚህም ማዕድኑን እየቸረ ይቀመጣል፡፡ ማለትም ያስኬዳል] ጉዳዩ ግን የእኔን በር እስለካላንኳኳ ድረስ “ለእኔን አገር አማን ነው” ብሎ ማሰብ መተው ይጠይቃል፡፡ ሃያላን አልጠግብ ማለታቸው የስር መሰረት ነውና፡፡
የሐያላኑን ተወት አርገን አገራችን ስንገነባም፣ ነግ-በኔ ቁልፍ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ሌላ አገር ሲጠቃ ምን ግዴ ማለት ሌላ ፓርቲ ሲገፋ ምን ቁቤ ማለት፣ ሌላ ሰው ሜዳ ሲወድቅ እንደፍጥርጥሩ ማለት ቀን የጨለመ እለት ክፉ ነገር ነው፡፡ ትላንት በራሳችን መጥነንና ለክተን ያሰፋነውን የድንጋጌና የመርህ መጎናፀፊያ ዛሬ ዳር እስከዳር አገሬውን ካላለበስነው ብለን የምንታገልበት ሁኔታ የኋሊት ጉዞ ይመስላል፡፡ “ትንሽ ስንቅ የያዘ አስቀድሞ ይፈታል” እንዲሉ፡፡ አገርን የሚያህል ሰፊ ባህር፣ የትንጧን ህልማችንን መፍቻ ለማድረግና አንዲቷን ቀጭን ኩታችንን ለልጁም ላዋቂውም አለብሰዋሁ ብሎ አይሆንም ሲባሉ ግትር ማለት ደግ አይደለም፡፡ ቢያንስ የዋህነት ሲበዛ በሰፊው ተወጥሮ መሰነጣጠቅ ነው ውጤቱ፡፡ ሌላ አስቸጋሪ አባዜ የካፒታሊዝምን ሠሪ-አካል፣ በሶሻሊስት ልብ አንቀሳቅሰዋለሁ እንደ ማለት ያለ በውዥንብር የተሞላ መንገድ ላይ የምንራመድ ከሆነ “አንድ በአንድ ተንጠባጥበን እስክንጠፋ የዓላማ ጽናት እናሳያን” ወይም በወትሮው አባባል “እስከመጨረሻው አንድ ሰው እንታገላለን”… “የአብዮቱ ባቡር ፈጣን ው” እየተባባልን በሀገር እየተሳለቅን እንዳንከርም ነግ በኔን ማስተዋ ይበጃል፡፡
“ከቆየን አንድ ዓመት፣ ከበላን የተከለከለ ሣር!” እንዳለችው ላም በድርጅዊ አሰራርና ወገናዊነት በዘመዳምነት፤ በእከክልኝ-ልከክልህ፣ በአራዳነት፣ በወደቀው ዛፍ ምሳር በማብዛት፣ በዕቁብም በዕቁባትም በመመነዛዘር ለጌዜው ሙስናን ቢያስፋፉ የሥር የመሰረት ብቅ በሚልበት ሰዓት ምነው አፉን በቆረጠው ምነው እግሬን በሰበረው፣ ማለትን አሊያም የተሰራንበት ንጥረ ነገር በምንም ዓይነት ካባ ብንሸፍነው የማታ ማታ ብቅ ማለቱ ከቶ አይቀርም፡፡ “በትንባሆ የተገዛ ጦር፣ እገበያ መሀል ቢወረውሩት፤ ጓያ ጫፍ ላይ ይቆማል” የሚለው የወላይታ ተረትም የሚነግረን ይሄንኑ ነው፡፡