• ሃይማኖትና ዓለማዊ ኑሮ ይጣሉብናል? ከተጣሉብን ሁሌ እንደምናደርገው ወደ
ሃይማኖት እናደላለን። ምድራዊ ነገሮችን እናወግዛለን።
• ግን ያለ ምድራዊ ነገሮች ሃይማኖት ይኖራል?
• ምድራዊ ኑሮን ለማጥላላት የምንቸኩለውስ ምን ላይ ቆመን ነው?
•መሬት ሲንቀጠቀጥ፣ “ለካ ምድሪቱ ናት መተማመኛ ማደሪያችን” ያሰኛል።
የዓለማትን የሚያነቃንቁ ዋና ኃይላት ሁለት ናቸው ይባላል - ውጥረትና ጭነት።
“ክፉ ኃይላት” ይመስላሉ - ከስያሜያቸው። “ውጥረት” በሚል ስያሜ በጎ ነገር ማሰብ ያስቸግራል። “የጭነት ኃይል” ደግሞ፣ እንዲሁ ስያስቡት የሚያጨናንቅ ይመስላል።
“ውጥረት” ከታች በኩል ቁልቁል ወጥሮ ይይዛል፤ እየሳበ ይለጥጣል።
ጭነት ደግሞ ከላይ በኩል ተጭኖ የሥረኞቹን ይደፈጥጣል። የትኛው ይሻላል? እየጎተተ የሚበጥስ ኃይል? ወይስ እየገፋ የሚጨፈልቅ ኃይል?
እነዚሁ ናቸው ዋናዎቹ የዓለም ኃይላት። ይሄ እውነት ነው። ነገር ግን፣ አገላለጻችን ችግር አለው። “የዓለም ኃይላት ሁሉ፣ የጥፋት ኃይላት ናቸው” ለማለት የፈለግን ያስመስልብናል። እንዲያውም፣ ስለ ኑሮ ውጥረትና ስለ መንግሥት ጫና እየተናገርን ይሆን እንዴ ያስብላል። ግን አይደለም።
ለሁለቱም የዓለም ኃይላት “ጥሩ ስያሜ” ብናገኝላቸው፣ ወይም “በጎ ስሜት” በሚፈጥሩ ቃላት ልንገልጻቸው ብንችል፣ ይሄ ሁሉ ማስተባበያ ባላስፈለገ ነበር።
ሁሉንም ነገር ከፖለቲካ ጋር ስለምናያይዘው እንጂ፣ አነሳሴማ ስለ ሃይማኖት ስለ ዓለማዊ ኑሮ ለመናገር ነበር። ሃይማኖትና ዓለማዊ ኑሮ ምናገናኛቸው? ተቃራኒ አቅጣጫዎች ሆነው ነው የሚታዩን። እንደ ሰማይና ምድር ይራራቁብናል። ሃይማኖትንና ኑሮን ስናስብ እንደ ብርሃንና ጨለማ ይጣሉብናል። ሁልጊዜ ለሃይማኖት እናደላለን፤ በጭራሽ አናመነታም - ብዙዎቻችን። ካመነታንም፣ ምናልባት ገላጋይና አስታራቂ ለመሆን ነው። ኑሮንና ሃይማኖትን ማስታረቅ ከባድ ነው። ስንሞክርም ያን ያህል አይሳካልንም።
እና ምን ተሻለ?
ገለልተኛ መሆን አንፈልግም - አብዛኞቻችን።
እናም እንደ ሁልጊዜው ለሃይማኖት እንወግናለን። “ዓለማዊ ኑሮ”፣ “ምድራዊ ሕይወት” ብለን ከተናገርን፣… ለማጣጣል ወይም ለማውገዝ ነው።
ሕይወትን አጣጥለን ወይም አጥላልተን ምን እንደምናገኝ ባይታወቅም፣ ከሕይወት የተለየ ሌላ የተሻለ አማራጭ ባይኖርም… “በሃይማኖት ከመጣብን” ግን አንምረውም። ውግዘትና እርግማን እናሸክመዋለን።
ግን ደግሞ፣ “ለዓለማዊው ሕይወት” እና “ለሰው ኑሮ” ተቆርቋሪነታችንን ለተመልካች ለማሳየት፣ በዚህም መንገድ “ሃይማኖተኛ” መሆናችንን ለተመልካች ለማስመስከር መሞከራችንም አልቀረም። ቀሽምነት ነው። ነገር ግን፣ ሕይወትን በግላጭና በአደባባይ ከማውገዝ ይልቅ፣ ለሕይወት ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት መሞከር ይሻላል።
መስለን ለመታየት የውሸት የጀመርነው “የተቆርቋሪነት ምልክት”… ምናልባት ከእውነተኛ የተቆርቋሪነት መልእክት ጋር የምንፋጠጥበትን ዕድል ሊፈጥርልን ይችል ይሆናል። ከምር ከሕይወት ጋር እውነተኛ የልብ ወዳጅነት በውስጣችን እንዲያቆጠቁጥ የሚያነሣሣ እርሾ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። ሕይወትን በደፈናውና በጭፍን ካጥላላን ግን… የመመለሻ ዕድል የምናገኝ አይመስልም። ብናገኝ እንኳ፣ እንደ መጥፎ ፈተና ልንቆጥረው እንችላለን። ፈጥነን ልናጠፋው እንጥራለን። ከእንዲህ ዓይነት በሽታ ይሰውረን!
“ምድራዊ ሕይወት”… ብለን ከማጥላላት ያድነን።
የራሳችንን ሕይወት ማናናቅ ብቻ ሳይሆን፣ ምድርን ማጥላላታችንስ ምን ይባላል? ጥንታውያኑ የሃይማኖት መሥራቾች፣ የምድር ሰማይ፣ የባሕር የከዋክብት አድናቂዎች ነበሩ። “የፈጣሪ ድንቅ ሥራዎች” ብለው ምድርና ሰማይን ያከብሩ እንደነበር በሃይማኖታዊ ትረካዎች ውስጥ ተጽፏል። ከጊዜ በኋላ ነው፣ “ምድራዊ” ወይም “ዓለማዊ” የሚሉ ማናናቂያ አባባሎች የመጡት። ጊዜውን በትክክል “እቅጩን” ለመናገር ይከብዳል።
ቢሆንም ግን፣ የሃይማኖት ትረካዎች በጥንቱ ዘመን በምድራዊ ነገሮች ላይ የከረረ ጥላቻ አልነበራቸውም።
ከአዳም እስከ ኖኅ፣ ከአብርሃም እስከ ሙሴ፣ እስከ ዳዊትና ሰለሞን ድረስ… ሃይማኖታዊው ትረካ በአመዛኙ ሲታይ፣ ዓለማዊ ነገሮችን የሚያከብር እንጂ የሚያራክስ አልነበረም። ምድራዊ ፍጥረቶችን የሚያደንቅ እንጂ የሚያናንቅ አልነበረም - የጥንታዊው የሃይማኖት ትረካ።
ደግሞስ ምድራዊ ኑሮን፣ ዓለማዊ ፍጥረትን አጥላልተን የት እንደርሳለን? ምን እናመጣለን? ይልቅስ ምድርን ያከበሩ ናቸው ብዙ ቦታ የደረሱት - ሲፈልጉ ውቅያኖስ መቅዘፍና መጥለቅ፣ ሲፈልጉ አየር ላይ መብረርና ወደ ኅዋ መምጠቅ የቻሉት “ዓለማዊውን ፍጥረት” ያከበሩ፣ ምድራዊ እውነታን ያጠኑ ሰዎች ናቸው።
ሌላው ሌላው ቢቀር፣ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ለምድር ያለን ክብር መጨመር ነበረበት።
የመሬት መንቀጥቀጥ ከአዋሽ እስከ አዲስ አበባ ድረስ ከሳምንት ሳምንት የቤት ግድግዳዎችንና ሕንጻዎች ሲያንገጫግጭ ሰምታችኋል። አንዳንዴም በየቀኑ ከእግራችን ሥር “ይነቀንቀን” ይዟል።
መሬት ሲንቀጠቀጥ፣ “ምድራዊ ነገር”! ብለን እንናቀው?
ይልቅስ በተቃራኒው፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ከምድር ጋር ለመታረቅ ሊገፋፋን ይገባል። መሬት ሲርድ፣ ወለሉ ሲወዛወዝ ወዴት ይኬዳል?
“ለካ ምድር ቀልድ አይደለችም። ለካ… ምድር ናት መተማመኛችን!” ያስብላል።
“መተማመኛችን” ናት በእርግጥም። ነገር ግን፣ ለኛ አስባ፣ እንደምንተማመንባት ተገንዝባ፣ ርዕደቷን ታቆማለች፣ ላታንገጫግጨን ላታስጨንቀን ቃል ገብታ ትረጋጋለች ማለት አይደለም። ለነገሩ፣ እኛን ለማስፈራራትና ለማጥፋት አስባም አይደለም - ንዝረትን እንደ ማዕበል የምታመነጨው። ባላንጣችን አይደለችም።
ነገር ግን፣ መተማመኛችን ናት ከተባለችም፣ የምድርን እውነታ ማወቅ፣ የሕይወታችን ዋስትና ነው ለማለት ይህል ነው። የምድርን ተፈጥሮ በማወቅ፣ ራሳችንን ማረጋጋት፣ አስቀድመን መዘጋጀት፣ ከአደጋም መጠንቀቅ እንችላለን።
የውጥረትና የጭነት ኃይላትም፣ የምድራዊ እውነታ ዋና ገጽታ ናቸው ማለት ይቻላል። ተወጥሮ የሚበጠስና የሚቀደድ፣ ተሰንጥቆ የሚሰበር ይኖራል። በጭነት ተጨናንቆ የሚፈነዳ፣ ተጨፍልቆ የሚፈርስና የሚደቅ ይኖራል።
ግን የክፋት ኃይላት ናቸው ማለት አይደለም። የሻንጣ ማንጠልጠያ ለውጥረት እንዲመች ተዘጋጅቶ የተሰራ ነው። እግሮቻችን የሰውነታችንን ጭነት መሸከም ስለሚችሉ ነው ቆመን የምንራመደው። እንደ ቄጤማ ቢሆን አስቡት። መቆም ባልቻልን ነበር። ለመራመድም ጭነት ያስፈልጋል። ያለጭነት “ፍሪክሽን” ስለማይኖር። የፈሰሰ ቅባት ላይ እንደመራመድ ይሆናል። በዚያ ላይ ነፋስ ሲመጣ፣ ቀላል ሽውታ ቢሆንም እንኳ፣ ነካ ሲያደርገን ክንብል ነበር የምንለው።
የዓለም ኃይላት፣ “ክፉና በጎ” ብለን ከምንፈርጃቸው አይደሉም ለማለት ነው።
የተፈጥሮ እውነታ ወይም የተፈጥሮ ሕግ ናቸው ብንል ይሻላል።
ያንጠለጠልነው ሻንጣ፣ እጃችን ላይ “ውጥረት”ን ያሳድራል። ወደ ትከሻችን አንሥተን ከተሸከምነው ደግሞ፣ “ጭነት” ይሆናል - በትከሻችን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ እስከ እግራችን ይደርሳል - ጫናው።
በእርግጥ፣ በእጃችን ያንጠለጠልነው ሻንጣም፣ ውጥረቱ በእጃችን ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም። ትከሻ ላይ ጫና ያሳድራል፤ ጫናው የጀርባ አጥንት ላይም ያርፋል፤ እና ደግሞ እግራችን ላይ።
በዚህም አያበቃም። “የጭነት ኃይል” ከእግራችን ሥር፣ ተጽዕኖውን ያስተላልፋል። የቆምንበት ወለልና መሬት ላይ፣ አሸዋና ፍራሽ ላይ፣ ጭቃና አለት ላይ… እንደ ሁኔታው ጭነቱን ያሳርፋል። የቆምንበት ምድር ነው፣ የሁሉም ሸክምና ውጥረት የመጨረሻ ማሰሪያና ማረፊያ።
የድልድይ ዓይነቶችን ማስታወስ ትችላላችሁ። አብዛኞቹ ድልድዮች፣ በምሶሶዎች አናት ወይም በዓምዶች ትከሻ ላይ ያረፉ፣ ቁልቁል የሚደፈጥጡ ጭነቶች ናቸው። ምሶሶና ዓምዶች ደግሞ ምድር ላይ ያረፉ።
ከዚህ የተለየ የድልድይ ዓይነትም አለ። የአባይ ድልድይን ማየት ይቻላል። ከረዥም ምሶሶዎች ላይ የተንጠለጠለ ድልድይ ነው ማለት ይቻላል - በጥቅሉ። “ሰስፔንሽን” የተሰኘው የድልድይ ዓይነት፣ ግዙፍ ዓምዶች ይኖሩታል። ነገር ግን ዓምዶች ላይ ያረፈ አይደለም። ከዓምድ ላይ ታች የብረት ገመዶች ላይ የተንጠለጠለ ድልድይ ነው። ወደ ታች የተዘረጉ እጆች ላይ የተንጠለጠለ ጠረጴዛ ወይም ሻንጣ እንደማለት ነው።የድልድይ ዓይነቶች በጣም ቢለያዩም ግን፣ ተንጠልጣይም ሆነ ተሸካሚ የድልድይ ዓይነቶች ማደሪያቸው አንድ ነው። በዚህ፣ ዓይነታቸውም ምንም ሆነ ምን፣ አየር ላይ የተንሳፈፈ ድልድይና ዓምድ የለም። ዞሮ ዞሮ ማረፊያው ምድር ነው፤ የሚቆመው መሬት ላይ ነው። ጭነቱና ውጥረቱ፣ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ መሬት ይደርሳል።
ለነገሩ፣ ሁሉም ነገራችንስ ዞሮ ዞሮ መሬት ላይ የቆመ አይደል?
በትክክል ታስቦበትና በጥንቃቄ ተሰልቶ ከተነደፈ፣ በሙያዊ ብቃት ከተገነባ… ምድሪቱ ሁሉንም ችላ ታኖራለች። ቤትና ሕንጻ፣ ድልድይና ግድብ… ሁሉንም ነገር። የውጥረትና የጭነት ኃይሎች በደንብ ተቀምረው ተቆጥረው፣ እንደየ ዐይነታቸውና እንደየ ልካቸው፣ በሚመጥናቸው መንገድ ከተገነቡ ችግር አይፈጠርም።
የሕንጻው ዓምዶችና ማገሮች፣ ወለሎችና ደረጃዎች፣ “ሊፍት” ወደ ታች የሚያወርዱና ወደ ላይ የሚጎትቱ የብረት ገመዶች… ሁሉም በቂ የውጥረትና የጭነት ኃይልን ወደ ምድር እንዲያስተላልፉ ሆነው የተሠሩ ናቸው።
ችግር የሚፈጠረው፣ የውጥረትና የጭነት ኃይል ከምድር ሥር ሲመጣ ነው። ይህም ቢሆን፣ ቀመርና ስሌት ውስጥ ይገባል። ደህና ሥረ መሰረትና ጠንካራ ግንድ ያለው ሰማይ ጠቀስ ዛፍ፣ በመሬት መንቀጥቀጥና በነፋስ ኃይል ተነቅሎ አይገነደስም። በቀላሉ አይሰበርም። ልክ እንደዚያው ጠንካራ ሥረ መሠረት ላይ የተገነባ አስተማማኝ የሕንጻ ቁመና፣ በቀላሉ አይበገርም።
ምድርን ይዞ ይጸናል - ለአፍታ ያህል ቢንገጫገጭም።
“ምድራዊ ሕይወት” እያልን የማጥላላትና የማጣጣል አመል ቢጠናወተንም እንኳ፣ መነሻችንና መንገዳችን፣ እህል ውኃችን፣ መጠለያ ማደሪያችን ይህችው ምድር ናት። ሥረ መሠረታችንም የሥራ ፍሬያችንም ከዚህችው ከምድር ነው።
ደስታና የሕይወት ጣዕም ካገኘንም፣ ከዚህችው ከምድር ነው። በፍቅርና በመከባበር መኖር ከቻልንም፣ በምድር ነው። በነጻነትና በሃላፊነት፣ በቅንነትና በፍትሕም መኖርም እንዲሁ።
መልካም የሥነ ምግባር መርሖች፣ የብቃትና የጽናት በጎ መንፈሶች ሁሉ የሚያስፈልጉን ለሌላ ዓለም አይደለም። የሐሳብ፣ የተግባርና የባሕርይ ቅድስና ከነ በረከቱ ትርጉም የሚኖራቸው በዚህችው ምድር ላይ ነው።
ሌላ ምድረ ገነት፣ ሌላ ሰማያዊ ዓለም፣ ሌላ ሕላዌ ሕይወት፣ ሌላ ዓይነት ማንነት ብንመኝ… ምንም ትርጉም የለውም ማለት አይደለም። በጣም ሰፊና ጥልቅ ትርጉም አለው። ትርጉሙ ግን፣ ለምድራዊው ሕይወት ነው።
የዕውቀትና የሙያ ልሕቀት፣ የብቃትና የባሕርይ ከፍታ፣ የተቃና የሥራ መንገድና ውጤት፣ ዕድገትና የኑሮ በረከት፣ የበለጸገና የሠለጠነ ዓለም፣ የፍቅር ደስታና የሕይወት ጣዕም… እነዚህን ሁሉ ማሰብ፣ መመኘትና ማለም በጣም ተገቢ፣ እጅግ ጠቃሚ ነው።
ሕልማችንን ስናይ አድረን፣ በማግስቱ ጀምበር ሳትጠልቅ የጥበብና የራዕይ ተራራ ላይ እንደርሳለን ማለት አይደለም። የበረከትና የቅድስና ጫፍ ላይ ባንድ አፍታ እመር ብለን እንወጣለን ማለት አይደለም። የፍጽምና ማንነትንና ምድረ ገነትን ወዲያውኑ እናገኛለን ማለትም አይደለም።
እንዲያውም፣ ሕልማችንን ጠንቅቀንና አሟልተን ለማወቅም ብዙ ጥረትና ረዥም ጊዜ ይፈጃል። ቢሆንም ግን፣ ምድረ ገነትን፣ የማርና የወተት ፏፏቴዎችን መመኘት ፋይዳ አለው። የዕውቀትና የብቃት ምጥቀትን፣ ያማረና የተትረፈረፈ የሥራ ፍሬ በረከትን፣ የጀግንነትና የቅድስና ስብዕናነት፣ የዕድገት ጉዞና የከፍታ መንገድን እስከ ፍጽምና ድረስ መመኘት፣ እጅግ በስፋትና በርቀት ማለም አለብን።
ይህን ሁሉ ከነ ልሕቀቱና ከነ ልዕልናው ማሰብ ካልቻልን፣ ከልብ ካልወደድነውና ካላከበርነው… ከመኝታ የመነሣት ውስጣዊ ዓቅም እናጣለን።
ብንነሣም መንገዳችንን፣ አቅጣጫችንንና መድረሻችንን አናውቅም።
እያንዳንዷ ግንዛቤና ሐሳብ፣ ተግባርና ውጤት፣ እያንዳንዷ የብቃት እርምጃና የባሕርይ በጎ ለውጥ፣ ትርጉም የሚኖራት…
“የመሻሻል ለውጥ” ወይም “መልካም እርምጃ” መሆኗን ከነዋጋዋ መገንዘብ የምንችለው…
መልካምነትን የምናውቅና ልሕቀትን የምናከብር ከሆነ ብቻ ነው። የሰማየ ሰማያት ያህል የራቀው እጅግ ውድ የበረከትና የፍጽምና ራዕይ፣ እዚሁ ምድር ላይ ዕድሜ ልክ ከአጠገባችን የማይለይ፣ ዕለት በዕለት የሐሳብና የተግባር መመሪያችን ሊሆን መቻሉ ነው - ፋይዳው።
ኑሮና ባሕርያችንን የምንቀርጽበት፣ የማንነትና የሕይወት ጣዕም ሥረ መሠረትና ቋሚ ምሶሶ ነው - የልሕቀትና የፍጽምና ራዕይ።
የሰማያዊ ዓለምና የምድረ ገነት ምኞት፣ የዘላለማዊነትና የድኅረ-ሕይወት ራዕዮች ሁሉ፣… መነሻቸውና መድረሻቸው ምድራዊ መሆኑ ነው ፋይዳቸውና ክብራቸው። የምድራዊ ሕይወት ንብረት ናቸው። የምድራዊ ሕይወት ሽልማትም ናቸው።
እናም፣ ምድራዊ ሕይወትን ለማቃናት እንጂ ለማጣጣል መዋል የለባቸውም። የሰውን ዓለማዊ ኑሮ በበጎ ከፍ ለማድረግ እንጂ የሰው ኑሮ ላይ ለመቀለድና ለማጉደፍ ማገልገል የለባቸውም።
ደግሞስ፣ ከሰው ሕይወት ወዲያ ምን አለ? ከምድራዊ እውነታ ውጭስ ምን መተማመኛ አለ?
ላለመውደቅም፣ ለመነሣትም - ምድርን አጥብቀህ ያዝ።
ምድርን የምንተማመንባት፣ ቆመን ለመራመድ፣ ወደ ከፍታ ለመገሥገሥ ብቻ አይደለም።
በውድቀት ጊዜ፣ መውደቂያችን ናት። ቀድመን ለመዘጋጀት፣ ውድቀት በመጣ ጊዜም ደህና ቦታ የመምረጥ ዕድል የምትሰጠን፣ ይህችው ምድራችን ናት። በሕይወት የመትረፍ ዕድል ካገኘን፣ ከሌላ ዓለም ሳይሆን ከምድር ነው።ወድቀን እንዳንቀርና እንደገና ለመነሣትና በእግራችን ለመቆም፣ ምርኩዛችንና አለኝታችን ናት - ምድር።
እንዲህ ሲባል ግን፣ “ብንወድቅ ችግር የለውም፤ ምድር ትኑርልን እንጂ መነሣት እንችላለን” ለማለት አይደለም።
ገደልና ባሕር ውስጥ ገብቶ ሕይወት ማጣት አለ። አለት ላይ ተሰብሮ መቅረት አለ። ማጥ ውስጥ መዘፈቅና ንብረት ማጣት ይኖራል።
ሲነሡና ሲያነክሱም ካሰቡበት ሳይደርሱ ያድራሉ። በዘፈቀደ ሲወድቁና ሲነሡ ዕድሜ ያባክናሉ።
ከወደቁ ግን እዚያው ከመቅረት ይልቅ፣ እንደ ምንም መነሣት ይሻላል።
ወድቆ ከመነሣት ደግሞ፣ ከመነሻው አለመውደቅ ይሻላል።
ከወደቁ ደግሞ ቶሎ መነሣትና ደጋግመው እንዳይወድቁ መጠንቀቅ ይሻላል።
ላለመውደቅ ምን ዘዴ አለ? መቼም ከምድር ማምለጥ አይደለም ዘዴው።
እንግዲህ መሬት እንዳትወድቅ፣ መሬትን ያዝ።
መሬት መያዝ ማለት ግን አፈር ልሰህ፣ አፈር ላይ ተኛ ማለት አይደለም። እንዳትወድቅ ከፈለግክ አለመነቃነቅ! ከፍ ከፍ ለማለት አለመሞከር!... እንዲህ ዓይነት ምክር እንኳን ለሰው፣ ለግዑዝ ነገሮችም አይሆንም።
መሬት ይዘህ ሰማይ ጠቀስ መሆን ትችላለህ።
መሬት ይዘህ አገር ማቋረጥ ወደ ተራራው አናት መድረስ ትችላለህ።
ለነገሩ ባሕሩም አየሩም የምድር ንብረት ናቸው። ምድርን እስከያዝክ ድረስ፣ ከአድማስ እስከ አድማስ መብረር፣ ባሕርና ውቅያኖስን እየቀዘፍክ አህጉራትን ማዳረስ ትችላለህ።
ምድርን አጥብቀህ ያዝ ማለት፣ እግርህና ሐሳብህ ወንዝ እንዳይሻገር፣ ከመንደር እንዳይወጣ ማለት ነው? አይደለም።
መሬትን ያዝ ማለት፣ “ዓይንህና ምናብህ ከምድር ወደ ኅዋ እንዳያይ፣ ወደ ሩቅ ዓለማትና ወደ ከዋክብት እንዳያማትር” ማለት ነው? አይደለም።
እንዲያውም፣ ምድርን ይዘህ ነው ኅዋ ላይ በዙሪያዋ መሽከርከር የምትችለው። በዚያው ጠፍተህ የማትቀረው፣ የምድር ስበትን ስለያዝክ ነው። ለነገሩ ወደ ሌሎች ዓለማት ከደረስክም፣ ሌላ መተማመኛ አይኖርህም - የነዚሁ ዓለማት የምድር ስበትና የምትቆምበት መሬት ነው መተማመኛህ።
ምንም ሆነ ምን፣ የትም ቢሆን፣ በእውን ያለ ዓለም፣ በነፍስ ያለ ሕይወት፣ በውን ያለ አእምሮ፣… እነዚህን ማጣጣልና ማጥላላት… አንድም አላዋቂነት፣ አልያም ሽንፈት፣ አንድም ራስን የማታለል ስንፍና ወይም ሌሎችን የማነሳሳት ክፋትና ምቀኝነት ከመሆን አያልፍም።