Saturday, 04 January 2025 00:00

“የደመና ሳቆች”ን ሳነብበው.....

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(1 Vote)

፨ በ”የደመና ሣቆች” የቦታ እና የጊዜ አሳሳሉ አንዳንድ ቦታ ግራ ያጋባል። የ‹ደጀኔ› ትረካ ምልሰት፣ ትዝታ ስለሚበዛው ከአኹንነቱ ጋር መገናኘቱን የሚያዛንቁ ተደጋጋሚ ትረካዎች አሉ። የሥርዓተ ነጥብ አገባብ እና (በተለይ ኹለቱ ? እና “ “) የንግግሮች አከፋፈል ላይ እነኚህም ከታሪኩ የሚያናጥቡ ናቸው። ባለፈው ሳምንትም የዘረዘርናቸው አኹንም የምንቀጥለው ኅፀፅ ፍለጋ ሳይኾን ከደረጀ ከዚህ በላይ ስለምንጠብቅ ነው። ወደ ዝርዝሩ ከማምራታችን በፊት ጥቃቅኖቹን አንድ ኹለት ልጥቀስ። ስለ ፋሪስ አባት ሲተርክልን መጀመሪያ ላይ ዐማርኛቸው የተስተካከለ ነበር። ቆይቶ ደግሞ ስለርሳቸው ሲተርክ የተንሻፈፈ አማርኛ ያወራሉ። ገጽ 66 - 67 ላይ በጠራ አማርኛ የሚያወሩት ሰውዬ፣ ገጽ 92- 93 ላይ ያንሻፍፋሉ። መልሶ ደግሞ ገጽ 126- 127 ላይ ሲያመጣቸው የተስተካከለ አማርኛ ያወራሉ። ሌላ ገጽ 161 ላይ ‹‹በላይ አዲስ አበባ ቀረ›› የሚል ደብዳቤ እናነብና ድንገት ሳይነገረን ‹ደጀኔ› ጋ ይከሰትና “ወሬ” ይነግረናል። (177- 179)
፨ በቀበሌ አዳራሽ ኪነታዊ ዝግጅት ተዘጋጅቶ ኹሉም ሰው እንዲሳተፍ ይነገራል። ‹ደጀኔ›ም ከጓደኞቹ ጋር ይሄዳል። መፈክር አለ። ይጨፈራል።
የወንድ ልጅ እናት ታጠቂ በገመድ፤
ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ። በመኻል በተንኮለኛው ጓደኛቸው ለገና ጊዜ የሚያፈነዱትን ሮኬት ያፈነዳል። ጥይት መስሏቸው ሰዎች ተተራመሱ። ተኝተውም ተቀምጠውም ሮጠውም ጸጥ ይላሉ፤ ኹሉም ፈርቷል። ‹ደጀኔ› ያስባል። ‹‹እኔ በልቤ አሰለፈችን አሰብኩ። በተተኮሰው ጥይት መድረክ ላይ ስለኾነች ልትመታ ትችላለች። ... ለእናትዋ አንድ ስለኾነች መጥተው መሞትዋን ሲያዩ አገር ይያዝ ሲሉ ታየኝ።››(81) .. አብዮት ጠባቂዎች መጥተው ሰላም መኾኑን ተናግረው ያረጋጋሉ። ኾታው ይቀጥላል። ድጋሚ መብራት ጠፋና ተኩስ ተከፈተ። ዋይታ በዋይታ ኾነ። ጩኸት ማጓራት ተሰማ። ሮጠው ወጡ። ‹ደጀኔ› ቤት እንደገባ እንዲህ ይላል፦ ‹‹ጥፋተኛ ስለነበርኩ ቃል አልወጣኝም። ዝም ብዬ ወደ መኝታዬ ገባኹ። እጄና እግሬ፣ በተለይ ጉልበቴ ይንቀጠቀጣል።[...] አንቀጠቀጠኝ፤ ብርድ ብርድ አለኝ።... ሲያስፈራ!››(83) ‹ጥፋተኛ ስለነበርኩ...› ያለው አሰለፈች አንድ ነገር ትኾናለች ብሎ አስቦ ተኩስ ስለተከፈተ ነው? በልጅነት ልቡ ስላሟረተባትና ስለሞተች? ይህ ሳይመለስልን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ ያመራል። እዚያ አሰለፈች እንዳልሞተች ይነገረዋል፤ ኢሕአፓ ኾና ኮበለለች እንጂ። ግን ስለሞቱ ሰዎች ሲነገር ብስጭት ይላል። ብስጭቱ የመጣው በዚች ዕድሜው ሰው ሲሞት ስላየ ወይ ወሬውን ጓደኛው ከርሱ ቀድሞ ስለሰማ አልያም ከጎኑ ኾኖ አይዞህ የሚለው አባት ስለሌለው ሊኾን ይችላል። አሰለፈች የሞተች መስሎ መሰማቱ ነፍሱን ሰቀቀን ውስጥ ከቷት ነበር፤ ‹‹ለካስ አብሮ ማደግ፣ በጥልና በድብድብም ቢኾን ፍቅር ነው።››(85) እስኪል። (ይህ አባባሉ በዛች ትንሽ ዕድሜ የምትባል ባይኾንም..) ነገር ግን እንዳልሞተች ጓደኛው ሲነግረው በቅጽበት ‹ቀለል አለኝ› ይላል። ‹የምርህን ነው?!› ሳይለው ‹ኡፍፍ...› ብሎ የግልግል ትንፋሽ ይተነፍሳል፤ ያስማለው ራሱ ‹ቀለል አለኝ› ካለ በኋላ ነው። እንደዚያ ብስጩ ያደረገው፣ ነፍሱን ሰቅዞ ከያዛት ጭንቀት በአንዴው መገላገል የሚቻል ግን አልነበረም።
፨ ታሪኩ ላይ መካተት ያልነበረባቸው መስሎ የተሰማኝ አንዳንድ አረፍተ ነገሮች አሉ። ‹‹አብዮት ልጇን ትበላለች!›› ተብሎ ግርግር በነበረበት ወቅት፤ አስተማሪዎቻቸው ታፍሰው፣ ትምሕርት ሳይማሩ ቤት እንደተመለሱ፤ የጓደኛቸው አባት የአብዮት ጥበቃ ኾነው ‹‹የታለ ትልቁ ልጅ?›› ብለው ሃገር ይያዝልኝ ይላሉ። ‹ደጀኔ›ም ይህንን ያያል። እየኾነ ስላለው ነገር ከመጨነቅ ይልቅም ስለሌላኛው ታላቅ ወንድሙ ያስባል። ‹‹ታላቅ ወንድሜ አስማማው የለም። ምናልባት ቢይ እየተጫወተ ሊኾን ይችላል።››(71) ይላል። ነገር ግን አስማማው በአብዮቱ ሊወሰድ የማይችል፣ ገና ልጅ መኾኑን ቀድመን አንብበናል።
‹‹ይሄኛውስ?›› አለች ወደ አስማማው ዞራ
‹‹ይሄ እንኳን ልጅ ነው፤ ምንም አይኾንም።››(66)
ድጋሚም ስለ አስማማው ያነሳል።
‹‹አስማማው የት ቀረ?›› አሉ።
‹‹እኔ እንጃ!››
‹በዚህ ክፉ ጊዜ መንቀዥቀዥ ጥሩ አይደለም፤ ዐርፋችኹ ቤት ቁጭ በሉ! ቀኑ ከፍቷል።››(73)... እንደዚህ ደጋግሞ ሲያነሳሳው የኾነ ነገር ይፈጠር ይኾን? ብሎ አንባቢው ይጠብቃል። ኾኖም ስለ አስማማው ጉዳይ ይረሳል። ሌላ ምዕራፍ ይጀምራል።
፨ ‹ደጀኔ› እንደ በዓሉ ግርማ ገጸ-ባሕርያት በኹለት ሴቶች ፍቅር ወዲህ እና ወዲያ እየተናጠ የሚመርጠው ጠፍቶት ይመናቀራል፤ “ኹለት ፍቅር ያመናቅር” እንዲሉ። በጊዜው የነበሩ ተማሪዎች ተወስደው የቀድሞው የአየር ኃይል ማሠልጠኛ ተወስደው ውትድርና ሲሰለጥኑ ትልክለት በነበረው ደብዳቤ እና ስንት መንገድ አቆራርጣ የመጣች ሌላ እንስት መኻል ማንን መምረጥ እንዳለበት ተስኖት ነፍሱን ሲያንገላታ ቆይቶ መጽሐፉም በዚያው ያልቃል። ለኹለቱም አፍቃሪዎች እኩል ጉልበት ተሰጥቷቸው እሱን ማመናተላቸው ታሪኩን ሳቢ ያደርገዋል። የ‹ደጀኔ› ልብም ከኹለት ጣፋጭ ኩኪሶች አንዱን ማንሳት ከብዶት ምናልባትም ኹለቱንም ትቶ የጓደኛቸውን ‹ታደሰ› ኢየሱስን ብቻ እንደሚመርጥ ከታሪኩ አካሄድ እንረዳለን።
፨ ሌላው የታሪኩ መጨረሻ ላይ የመንግሥቱ ኃይለማርያምን ከሃገር መኮብለል ተከትሎ የነበሩበት ማሠልጠኛ ሲተራመስ፤ ተማሪዎችም ከግቢ ወጥተው መሔጃ መውጫ ሲጠፋቸው፤ የወደቀው ወድቆ፣ የቻለው ተርፎ፤ መሣሪያቸውን ሸጠው ሲተርፉ ያለውን ታሪክ በኹለት ገጽ ብቻ ሸራርፎ ‹‹ብቻ እንደምንም ደረስን›› ዓይነት መጻፉ ደረጀን ያስወቅሳል። ሌላውን ታሪክ በጻፈበት ጉልበት እዚህ ቦታ ላይ ምን ያህል ግሩም ሊኾን እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ግን ‹‹አዋሳ ገባን›› ብሎ ታሪኩን በአጭሩ ይቀጨዋል።
፨ ዘመንን ማሳየት የልብወለድ አንዱ ግብ ነው። ደረጀ በዚህ መጽሐፉ ዘመኑን ነው ያሳየው። ፖለቲካውን፣ ማኅበረሰቡን፣ ሕዝቦቹን ነው ያሳየው። ደቡብ ኢትዮጵያ (በተለይም ተፈሪ ኬላ እና ወላይታ ሶዶ) በዚያን ዘመን ምን ይመስሉ እንደነበር እናያለን። ያለ ጎርኪ ሥራዎች የሩሲያ ታሪክ አይሟላም እንዲሉ ዘመኑን የሚያሳይ ልብወለድም ታሪካችንን ያሟላል። አብዮቱ ቤተሰብን እንዴት እንደበተነ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ መተማመኛ የኾነው ፈጣሪ ሲሻር ሰው እንዴት እዝነት እንዳጣ፣ የአለቃውን ትዕዛዝ እየጠበቀ እጁ ላይ ቦንብ የፈነዳበትን የ18 ዓመት ታዳጊ አይተው ተማሪዎች ሲሸበሩ አለቃው ግን ዝንብ የሞተ ያህል እንኳ ሳይቆጥረው ሲቀር፣ ልጆቹን ታለ እናት አሳድጎ እስኪደርሱለት እየጠበቀ ‹‹በሥም ሥህተት›› በሚል ተልካሻ ምክንያት እንደገደሉት ያሳየናል። በዚያን ጊዜ ተስፋ ጉም ኾኖ ነበር። ሀገር፣ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ፈጣሪ ኹሉም ላይ ተስፋ መቁረጥ።
‹‹በዚች ቀፋፊና ደኻ አገር ኾነህ አትበሳጭ››፣
‹‹ወይኔ ልጆቼን›› ሲል አንዱ ‹‹ኢትዮጵያን አምነህ ትወልዳለህ?›› የሚባልበት. . . . የደመና ሣቆች፤ ወዲያው የሚበን፣ ተጨባጭ ያልኾነ፣ ባዶ ተስፋ፣ የሩቅ ህልም፣ ዩኒቨርሲቲ መግባት፣ ማግባት፣ መውለድ፣ ማፍቀር መፈቀር፣ የተወለደን ማሣደግ፣ አስተምሮ መዳር . . . ኹሉም ድመት እንዳየ ወፍ ደንብረው የበረሩበት።
‹‹ሕይወት ትርጉም የላትም!›› አልኩ። ሲወልዱ እልል መባሉ፤ ሲያድጉ ተስፋ ማድረጉ ሞኝነት ነው። ማንም በተመኘው መንገድ ወደ ግቡ አይደርስም። የሰው ልጅ ጎዳና በእንቅፋት የተሞላ ነው። እናም ሰው መከራ ሲቀበል ለምን እልል ይባላል?........162
ይህ ነው የልብወለዱ ቋጠሮ። ይህንን ነው ደረጀ ሊያሳየን የፈለገው።
***
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በቴሌግራም አድራሻው፡- @NEBILADU ማግኘት ይቻላል፡፡

 

Read 72 times