“መጻሕፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ”
ጄምስ ፓተርሰን በዓለም ዝናው የናኘ እጅግ ታዋቂና ትጉህ አሜሪካዊ ደራሲ ነው። የ77 ዓመቱ ፓተርሰን እ.ኤ.አ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ 200 ገደማ ረዥም ልብ ወለዶችን ጽፎ ለህትመት ያበቃ ሲሆን፤ መፃህፍቱ በዓለም ዙሪያ ከ425 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሸጠውለታል። 1 ሚሊዮን ያህል ኤሌክትሮኒክስ መፃሕፍት (e-books) በመሸጥም የመጀመሪያው ደራሲ ነበር፡፡
ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በፎርብስ የከፍተኛ ተከፋይ ደራሲያን ሰንጠረዥን በመቆጣጠር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዘልቋል- በ95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ። አጠቃላይ ገቢው ደግሞ ከአሰርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ 700 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር፡፡
ሚሊየነሩ አሜሪካዊ ደራሲ ከተወዳጅ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ ባሻገር የመጻሕፍት ሻጮች አለኝታም ነው፡፡ የመፅሐፍ ኢንዱስትሪውን የጀርባ አጥንት በመደገፍ ይታወቃል - የግል የመፃሕፍት መደብሮችን።
በዚህ የፈረንጆች በዓል ሰሞን በመላው አሜሪካ በሚገኙ 600 የግል መፃህፍት መደብሮች ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች በአጠቃላይ የ300ሺ ዶላር የበዓል ቦነስ አበርክቷል - በነፍስ ወከፍ 500 ዶላር!
“መፃህፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ- አራት ነጥብ!” በማለት ለABC ኒውስ የተናገረው ደራሲው፤ “በዚህ የበዓል ወቅት ለእነሱም ሆነ ለትጋታቸው ዕውቅና መስጠት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።” ብሏል።
ለዓመት በዓል የገንዘብ ስጦታው የታጩት የ600 መፃሕፍት መደብር ሠራተኞች አንድም ራሳቸው ያመለከቱ አሊያም በመደብር ባለቤቶች፣ በደራሲያን ወይም በደንበኞች የተጠቆሙ ናቸው ተብሏል- በትጋትና ታታሪነታቸው።
“የሚስተር ፓተርሰንን የገንዘብ ልግስናና የልብ ቸርነት እናደንቃለን። ሁላችንም ሚስተር ፓተርሰን ለግል መፃሕፍት ሻጮች ለሚያደርጉት የማያቋርጥ ድጋፍ ምስጋናችን ወደርየለሽ ነው፡፡” ብለዋል፤ የአሜሪካ መፃህፍት ሻጮች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊሰን ሂል በመግለጫቸው፡፡
“መፃሕፍት ሻጮች በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚጫወቱትን ወደር-የለሽ ሚና መገንዘባቸውና መሸለማቸው ከምንም ነገር የላቀ ነው” ሲሉም አክለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚው።
ደራሲው ለመፃሕፍት ሻጮች የ500 ዶላር የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ላለፉት አስርት ዓመታት ሲያደርገው የቆየው የልግስና ተግባር ነው፡፡ ሥነ-ፅሁፍን በማሳደግና ንቁ ማህበረሰቦችን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ በማመን፣ የግል የመፃሕፍት መደብሮችንም ያለማቋረጥ በመደገፍ ይታወቃል፤ በአገረ አሜሪካ፡፡
በመጋቢት ወር ላይ ፓተርሰን ለመፃሕፍት ሻጮች የሚከፋፈል 600ሺ ዶላር እንደሚያበረክት የአሜሪካ መፃሕፍት ሻጮች ማህበር አስታውቆ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ2020 ደግሞ በመላው አሜሪካ ለሚገኙ የግል መፃሕፍት መደብሮች 500ሺ ዶላር ለግሷል- ሥራቸውን እንዲያሳድጉና እንዲነቃቁ።
“ዋይት ሐውስ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪንና ትላልቅ ቢዝነሶችን ከውድቀት መታደግ ያሳስበዋል - ያንን እረዳለሁ። እኔ ግን በመላ አገሪቱ ዋና ጎዳናዎች እምብርት ላይ የሚገኙ የግል የመፃሕፍት መደብሮች ህልውና ያሳስበኛል።” ብሏል ፓተርሰን በሰጠው መግለጫ።
“የምናሰባስበው ገንዘብ የመፃሕፍት መደብሮችን በጣም በምንፈልግበት በዚህ ወቅት ህያው እንደሚያደርጋቸው ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲልም አክሏል፤ ደራሲው።
ጄምስ ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ለአሜሪካ የግል የመፃሕፍት መደብሮች 1 ሚሊዮን ዶላር ለግሶ ነበር- ለእያንዳንዳቸው 15ሺ ዶላር የሚከፋፈል። ባለፉት ዓመታት ደራሲው ለመፃሕፍት መደብሮችና መጻሕፍት ሻጮች ብቻ ሳይሆን ለቤተመጻህፍት ባለሙያዎችና ለመምህራንም የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ቆይቷል።
የመፃሕፍት መደብሮችንና መፃሕፍት ሻጮችን በገንዘብ ከመደገፍና ከማገዝም በተጨማሪ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መፃሕፍትን ለት/ቤቶች ቤተ-መፃሕፍት ለግሷል። የህፃናት መፃሕፍትንም በመፃፍ የሚታወቀው ደራሲው፤ ህፃናት የንባብ ባህል እንዲያዳብሩም በትጋት ይሰራል። “ህፃናት በለጋ ዕድሜያቸው የማንበብ ልማድ ካላዳበሩ ለውጭው ዓለም ባዕድ ከመሆናቸውም ባሻገር በራስ መተማመን ይጎድላቸዋል፤ ስለዚህ የግድ ማንበብ አለባቸው፤ ይህን ማድረግ ደግሞ የኛ የወላጆች ሃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡” ይላል- ፓተርሰን።
ጄምስ ፓተርሰን የበኩር ስራውን ለንባብ ያበቃው እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም ሲሆን፤ ርዕሱም “The Thomas Berryman Number” ይሰኛል። ከሌሎች በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ መካከልም፡- Alex Cross, Michael Bennet, Women’s Murder Club እና Maximum Ride የተሰኙት ልብወለዶች ይጠቀሳሉ። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ልብወለዶቹም ወደ ፊልም ተቀይረውለታል፡፡